>

የኦነግ ፕሮግራም አቀንቃኞች ወሎን በሚመለከት የሚያስተጋቡት የፈጠራ ትርክታቸው ሲፈተሽ! [ክፍል ፩ - አቻምየለህ ታምሩ]

የኦነግ ፕሮግራም አቀንቃኞች ወሎን በሚመለከት የሚያስተጋቡት የፈጠራ ትርክታቸው ሲፈተሽ!

ክፍል ፩
አቻምየለህ ታምሩ
ፋሽስት ወያኔ ታላቋን የትግራይ ሪፑብሊክ ሊሰመሠርት ጫካ የወረደው ጥንታዊ የሆኑትን አማራ እና የአፋር ርሥቶችን በወረራ በመያዝ እንደሆነ መናገሩ ለቀባሪ እንደማርዳት ይቆጠራል። ልክ እንደ ወራሪው ፋሽስት ወያኔ ሁሉ ኦነግ የሚባለው የፋሽስት ወያኔ የርዕዮተ ዓለም ወንድምም ከተመሰረተባቸው የወረራ ትርክቶች መካከል አንዱ የአማራ  ጥንታዊ ርስቶች የሆኑትን ጠቅላይ ግዛቶች «ኦሮምያ» በሚል ዮዋን ክራምፍ የሚባለው አውሮፓዊ የቅኝ ገዢ ሜሲዮን በምናብ ወደ ፈጠራት የተስፋይቱ «አፍሪካዊት ጀርመን» ግዛት በማካተት ከአንጎት እስከ ኬንያ ድንበር የተዘረጋች አዲስ አገር መፍጠር ነው። የዚህ የኦነግ የወረራ ትርክት በተደጋጋሚ ከሚጎበኛቸው የአማራ  ጥንተ ርስቶች መካከል ጥንታዊው የቤተ አማራ  አውራጃ ወይንም ከኦሮሞ መስፋፋት በኋላ ወሎ ተብሎ የተሰየመው ሰፊ የአማራ  ግዛት ነው። በዚህ ጽሑጽ የኦነግ ፕሮግራም አቀንቃኞች ጥንታዊውን የቤተ አማራ  አውራጃ ወይንም ከኦሮሞ መስፋፋት በኋላ ወሎ ተብሎ ስሙ ስለተለወጠው የአማራ  ርሥት ለመውረር እየተመሰረቱበት ያለውን የውሸት ትርክት እያነሳን እውነታው ከታሪክ አኳያ ምን እንደሚመስል ለማቅረብ እንሞክራለን።
የዚህ ጽሑፍ የታሪኩ ምንጮቻችን Herbert Weld Blundell እ.ኤ.አ. በ1922 ዓ.ም. «The Royal chronicle of Ethiopia, 1769-1840» በሚል ያሳተሙ የዘመነ መሳፍን ዘመን የኢትዮጵያን ነገሥታትን ዜና መዋዕል የያዘ መጽሐፍ፣ተክለ ጻድቅ መኩሪያ በ፲፱፻፶፩ ዓ.ም. «የኢትዮጵያ ታሪክ፡ ከዐፄ ልብነ ድንግል እስከ ዐፄ ቴዎድሮስ» ያሳተሙት የታሪክ መጽሐፍ፤በጎበዜ ጣፈጠ ተጽሞ በ1996 ዓ.ም. የታተመው አባ ጤና እያሱ መጽሐፍ፤ አባ ባሕርይ የጻፉት «ዜናሁ ለጋላ» የሚለው የአስራ ስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሰነድ፤ አለቃ አጽመ ጊዮርጊስ በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ያዘጋጁት «የኦሮሞ ታሪክ» መጽሐፍ፤ አቶ ይልማ ደሬሳ በ1959 ዓ.ም ጽፈት ያሳተሙት «የኢትዮጵያ ታሪክ በ16ኛ መቶ ክፍለ ዘመን» ድርሳን፤ ፕሮፌሰር መሐመድ ሐሰን እ.ኤ.አ. በ2015 ዓ.ም. ያሳተሙት «The Oromo and the Christian Kingdom of Ethiopia: 1300-1700» የሚለው መጽሐፍ፤ሌተናት ኮሎኔል ጌታቸው መኮንን ሐሰን የጻፉት «ወሎ – “ያገር ድባብ”» መጽሐፍ፤ ዶክተር ሑሴን አሕመድ «Islam in Nineteenth-Century Wallo, Ethiopia: Revival, Reform and Reaction» በሚል ያሳተሙት የታሪክ መጽሐፍ፤ Juxon Barton እ.ኤ.አ. በSeptember 1924 ያሳተሙ «The Origins of the Galla and Somali Tribes» አርቲክልና የትውልድ ሐረግን በሚመለት ደግሞ ባብዛኛው ያቀረብሁት በሪሁን ከበደ በ1993 ዓ.ም. ካሳተሙት «የዐፄ ኃይለሥላሴ ታሪክ» መጽሐፍ በቀጥታ በመውሰድ ነው።
በሰሜን ምስራቅ ኢትዮጵያ የሚገኘውና ከ1842 ዓ.ም. በፊት የነበረውን የቀድሞ ስሙን ቤተ አማራ ን ለውጦ ወሎ በመባል የሚጠራው የአማራ  ጥንተ ርሥት ወሎ የሚለውን ስያሜ ያገኘው 17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኦሮሞ መስፋፋትን ተከትሎ በአከባቢዉ በሰፈረው በወሎ ኦሮሞ ነገድ መጠሪያ ነው። ወሎ በዘር አማራ  ወይም ቤተ ዐምራ ከመሆኑም በተጨማሪ የሰው ጥንተ ዘር የሆነችው የሉሲ አጽመ ርስት ከተገኘበት ምድር በአስርት ኪሎሜትሮች ርቀት ላይ ውልደቱን ያደረገው የአማራ  የዘር ግንድ መነሻም ጭምር ነው። ወሎ ወይንም ጥንታዊው ቤተ አማራ  በቀድሞ ካርታዎች ላይ እንደሚታየው አሸንጌ ሐይቅ ፣ በደቡብ ጃማ ወንዝ ፣ በምእራብ አባይና በምስራቅ ሐረር ያዋስኑታል። ከዚህ በተጨማሪ የወሎ ወሰን ፋሽስት ወያኔ ወደ ስልጣን እስከመጣበት ዘመን ድረስ እስከ አሰብ ድረስ ይሰፋ ነበር።
የኦነግ ፕሮግራም አቀንቃኞች ጥንታዊውን ቤተ አማራ ፣ ከኦሮሞ መስፋፋት በኋላ ደግሞ ወሎ ተብሎ የተሰየመውን የአማራ  ታሪካዊ ግዛት ጀርመናዊው ዮዋን ክራምፍ ከፈጠረላቸው ኦሮምያ የሚባለው ምዕናባዊ አገር አካል ለማድረግ የሚነሱት በዘመነ መሳፍንት ዘመን ከሰማኒያ ዓመታት በላይ ኢትዮጵያን ገዙ የሚሏቸውን የየጁ መሳፍንትን የዘር ታሪክ ባፍ ጢሙ ደፍቶ በማቅረብ ነው። ከወሎ መሳፍንቶች መካከል ኦነጋውያን በብዛት ሲጠቅሷቸው ከሚሰሙት የታሪክ ሰዎቻችን መካከል ዕቴጌ ጠሐይቱና ንጉሥ ሚካኤል ናቸው። ኦነጋውያን በተለይም ንጉሥ ሚካኤልን ኢትዮጵያዊነታቸውን እየጠሉ ወሎን ከሚገዙት ኦሮሞዎች መካከል አድርገው ከፍ አድርገው የሚያነሷቸው ንጉሡን ኦሮሞ አድርገው ወሎን ዮዋን ክራምፍ በፈጠረላቸው የምናብ አገር ለመውረር እንጂ የትውልድ ሐረጋቸውን በሚገባ ዘርዝረው ኦሮሞ ስለመሆናቸው አንዳችም ማስረጃ አቅርበው አያውቁም።
በርግጥ የየጁንና የመሳንፍቶቿን ታሪክ አዛብተው የሚያቀርቡት ታሪክ አዋቂ ነን የሚሉ ደጋሚዎች ኦነጋውያን የመጀመሪያዎቹ ባይሆኑም ይህንን ተንጋዶ የተፈጠረ የውሸት ታሪክ ግን የፖለቲካ አሽከር በማድረግ የሰው ርስት ወረው አገር ለመመስረትና እንደደቡቡ የኢትዮጵያ ክፍል ሁሉ የአማራ ን ርስት ለመንጠቅ ከወያኔ ቀጥለው ጦር የሰበቁ፣ሰይፍ የመዘዙና ዛሬም ለወረራ እየተዘጋጁ ያሉት ግን ቀዳሚዎች እነሱ ናቸው።
በዘመነ መሳፍንት ዘመን ለሰማኒያ አመታት ኢትዮጵያን እንደገዙ ታሪክ የሚያወሳቸው የየጁዎች ምድር የጁ ጥንት የክርስቲያን አማራ  አውራጃ እንደነበርና በአቡኑ ዕርግማን ምክንያት የጁ ተብሎ ከመጠራቱ በፊት ስሙ ገነቴ እየተባለ ይጠራ እንደነበርና በዚህም ቦታ ሰባት ጳጳሳት ጉርባጆ ማርያም እንደተቀበሩ የጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ግሸን ደብረ ከርቤ መቀመጡንና ሌሎችንም ታሪኮች ያያዘውና በግሸን ደብረ ከርቤ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የሚገኘው ጥንታዊው መጽሐፍ «መጽሐፈ ጤፉት» ያትታል። ከግራኝ አሕመድ ወረራ በፊት ከፍ ሲል ስፋቱንና የሚያዋስኑትን ቦታዎች ያቀረብነው ጥንታዊው ቤተ አማራ  ወሎ ተብሎ የመሰየሙ የአውራጃው መጠሪያ ብቻ ሳይሆን ስሩ የነበሩት እንደ አንጎትና ላኮመል የመሳሰሉ ጥንታዊ የወረዳ ስሞች ጭምር ናቸው። ከኦሮሞ መስፋፋት በፊት አትራኖስ ማርያም በሚል ይታወቅ የነበረው አካባቢ ዛሬ ለጎጎራ ተብሎ ተለውጧል። ጥንት ክላሜንቶ ይባል የነበረው ምድር ከኦሮሞ መስፋፋት በኋላ ለጋንቦ ተብሏል። ጥንት መካነ ሥላሴ ተብሎ ይታወቅ የነበረው ዛሬ ወረኢሉ ተብሏል።
የየጁ ስርዎ መንግሥት ትውልዶች የዘር ሀረግ የሚሳበው ከኦሮሞም ከግራኝም ወረራ በፊት ከነበረ አራት የአማራ  እናቶች አንድ የመናዊ አግብተው ከሚፈጥሯቸው የአማራ  ልጆች ነው። እዚህ የመናዊ ሰው ሸሕ ዑመር ይባላሉ። ቀደም ሲል እንዳልነው ሸሕ ዑመር የተባሉት የየመን ተወላጅ ወደ የጁ የመጡት ኦሮሞዎች ወደ ደቡብ፣ ሰሜን፣ ምስራውና ምዕራብ ኢትዮጵያ ሳይስፋፉና ግራኝም ወሎን ሳይወር ነበር። ሸሕ ዑመር ወደ የጁ እንደገቡ የአገቧቸው አራት ሚስቶችን ናቸው። አራቱም የሸሕ ዑመር ሚስቶች የዐምራ ሙስሊሞች ናቸው።
ከነዚህ ከአራቱ አማራ  ሚስቶቻቸው ሸሕ ዑመር ብዙ ልጆች ስለወለዱና ስለተበራከቱ፣ ብዙ መሬት አስፋፍተው ጎረቤቶቻቸውን እየገፉና እየገዙ ስለያዙ የሸሁ ልጆች ወረሩን፣ ቦታውን ሁሉ አስፋፍተው ያዙብን በማለት «የወራሪው የሸሁ ልጆች» አሏቸው። ከእነዚህ የአማራ  እናቶች የተወለዱት የሸሕ ዑመር ዘሮች ከጊዜ ብዛት ወረሸኮች ወይንም ወረሴኮች ተባሉ። ከነዚህ ከአራቱ የሸሕ ዑመር ሚስቶች መካከል አንዷ የየጁ ባላባቷ ወይዘሮ ራጅያ ይባላሉ። ሸሕ ዑመር ከወይዘሮ ራጅያ ወሌ የሚባል ልጅ ይወልዳሉ። ወሌ ደግሞ አብዩ የሚባል ልጅ ይወልዳል። አብዩም ልጅ ይወልድና ልጁን ወሌ ሲል ስም ያወጣለታል። የታሪክ ጸሐፍቶች የወይዘሮ ራጅያን ልጅ ወሌን ከአብዩ ልጅ ወሌ ለመለየት የወይዘሮ ራጅያን ልጅ ወሌን ቀዳማዊ ወሌ ሲሉት የአብዩን ልጅ ወሌን ዳግማዊ ወይንም ሁለተኛው ወሌ ይሉታል። ሁለተኛው ወሌ አማራ  ሚስት አግብተው አባ ገትዬን ወልደዋል። አባ ገትዬም ሴሩ ጓንጉልን ወልደዋል።
ከመጀመሪያው ወሌ ጀምሮ እስከ አባ ገትዬ ድረስ ያሉት የአማራ ይቱ የወይዘሮ ራጅያ ዘሮች ሁሉ ያገቧቸው ባሎችና ሚስቶች በሃይማኖት እስላም ይሁኑ እንጂ በዘር ሁሉም አማራ ዎች ናቸው። የሁለተኛው ወሌ የመጀመሪያ ልጅ የሆነው የአባ ገትዬ ልጅ የሆነው አባ ሴሩ ጓንጉል የታወቁትን የላስታና የሰለዋን ባላባት የራስ ፋሪስን ልጅ ወይዘሮ ገለቡን አግብተው መጀመሪያ ወይዘሮ ከፈይን፣ ቀጥለው ትልቁን ራስ አሊን፣ ሰልሰው ራስ አሊጋዝን ወልደዋል። እንደ ወይዘሮ ራጅያ ሁሉ የላስታና የሰለዋን ባላባት የራስ ፋሪስን ልጅ የሆኑት ወይዘሮ ገለቡም በአባታቸውም በናታቸውም የተጣሩ አማራ  ናቸው። አባ ሴሩ ጓንጉል በዘመነ መሳፍንት ዘመን ኢትዮጵያን ከ፲፯፻፸፯ ዓ.ም. እስከ ፲፯፻፹፩ ዓ.ም. የገዙት የትልቁ ራስ ዓሊና ኢትዮጵያን ከ፲፯፻፹፩ ዓ.ም. እስከ ፲፯፻፹፮ ዓ.ም. የገዙት የአሊጋዝ አባት መሆናቸውን ልብ ይሏል።
አባ ሴሩ ጓንጉል መልከ መልካምና ጀግና ፈረስ ጋላቢ፣ ጋሻ መካች፣ ጦር ሰባቂና ወርዋሪ ስለነበሩ፣ ይህን የሚያውቀው ሕዝቡ በርሳቸው ዙሪያ አሴረላቸው አለላቸው። አሴረላቸው ማለት ሕዝቡ አበረላቸው፣ ተባበራቸው ማለት ነው። ስለዚህም ሕዝቡ ስለተባበረላቸው «አባ ሴሩ» የሚል ቅጽል የማሞገሻ ስም በሕዝብ ዘንድ ተሰጥቷቸዋል። የአባሴሩ ጓንጉል ልጅ ወይዘሮ ከፈይ አቶ መርሶ በሬንቶን አግብተው ትልቁን ራስ ጉግሣን ወልደዋል። የመርሶ በረንቶ ልጅ ራስ ጉግሳ በዘመነ መሳፍንት ዘመን ኢትዮጵያን ከ፲፯፻፺፪ ዓ.ም. እስከ ፲፰፻፲፰ ዓ.ም. ለሀያ ሰባት ዓመታት ያህል የገዙ ሲሆን ልጆቻቸው የሆኑት ራስ ይማም ከ፲፰፻፲፰ ዓ.ም. እስከ ፲፰፻፳ ዓ.ም. ድረስ፤ ራስ ማርዬ ከ ፲፰፻፳ ዓ.ም. እስከ ፲፰፻፳፫ ዓ.ም. ድረስና ራስ ዶሪ ለሶስት ወር ያህል ኢትዮጵያን ገዝተዋል። እንደ ወይዘሮ ራጅያና ወይዘሮ ገለቡ ሁሉ የአባ ሴሩ ጓንጉልና የመርሶ በረንቶ ልጆች ሁሉ ዘራቸው አማራ  ናቸው።
በዘመነ መሳፍንት ዘመን ኢትዮጵያን ከ፲፯፻፺፪ ዓ.ም. እስከ ፲፰፻፲፰ ዓ.ም. ለሀያ ሰባት ዓመታት ያህል የገዙ የነ ራስ ይማም፣ የነ ራስ ማርዬና የነራስ ዶሪ አባት ራስ ጉግሳ ጎንደር ሆነው አገር በሚገዙበት ወቅት የጎንደሯን ባላባት ወይዘሮ ማሪቱን አግብተው ወይዘሬ ሂሩትን፣ ወይዘሮ ተክሌንና ወይዘሮ አስቴርን ይወልዳሉ። ወይዘሮ ሂሩትም የስሜንና ወልቃይት ገዢ የነበሩትን የራስ ገብሬን ልጅ ደጃዝማች ኃይሉን አግብተው ደጃች መርሶን፣ ደጃች ብጡልንና ወይዘሮ የውብዳርን ይወልዳሉ። ደጃች ብጡልም በበኩላቸው የጎጃም ደብረ መዊዕ ባላባት ልጅ የሆነችውን ወይዘሮ የውብዳርን አግብተው ዕቴጌ ጠሐይቱን ይወልዳሉ። ከወይዘሮ ራጅያ አንስቶ እስከ ደጃች ብጡልና ወይዘሮ የውብዳር ድረስ ያሉት የዕቴጌ ጠሐይቱ ዘሮች በሙሉ ዐማሮች ናቸው። የስሜኑና የወልቃይቱ ገዢ የነበሩት ራስ ገብሬ በዐፄ ሱኒስንዮ ዘመነ መንግሥት ወልቃይትን ይገዙ የነበሩትና ዐፄ ሱሲንዮን ሃይማኖታቸው በመቀየራቸው የተነሳ «ፋሲል ይንገስ፤ ሃይማኖት ይመለስ» ተብሎ ሕዝባዊ አመጽ ሲነሳ ዐፄ ፋሲለደስ ከስልጣን ወርደው ልጃቸው ፋሲለደስ እንዲነግሥ የመሪነቱን ድርሻ የተጫወቱት የደጃዝማች ዮልዮስ አራተኛ ትውልድ ናቸው።
የዕቴጌ ጠሐይቱ የትውልድ ሐረግ ከላይ የቀረበውን የሚመስል ከሆነ ዕቴጌዋ ከኦሮሞ የሚወለዱት ከየት ላይ ነው? እናታቸው የጎጃም አማራ  ናቸው። በአባታቸው በኩል ከአያት እስከ ቅድመ አያት ብሎም እስከ ምንጅላት ድረስ ዐማሮች ናቸው። የራስ ገብሬ አባት ደጃች ወልደ ሩፋኤል የስሜን ሰው ናቸው። እሳቸውም የስሜኗን ባላባት ልጅ ወይዘሮ ማሪቱን አግብተው ነው ራስ ገብሬን የወለዱት። ከፍ ሲል እንዳየነው ራስ ገብሬ ደግሞ የስሜኗን ባላባት ወይዘሮ ሳሕሊቱን አግብተው ነው ደጃች ኃይሉን የወለዱት። ደጃች ኃይል ደግሞ በበኩላቸው ወይዘሮ ሂሩትን አግብተው ነው የዕቴጌ ጠሐይትይን አባት ደጃች ብጡልን የወለዱት። የዕቴጌ ጠሐይቱ ስም በራሱ ታሪካዊ አመጣጥ አለው።
ቀደም ሲል እንደጠቀስነው ዐፄ ሱሲንዮስ ካቶሊክ ሲሆኑ ከስልጣናቸው ለማውረድና ልጃቸውን ፋሲልን ለማንገስ የአንሰባውን ድርሻ የተጫወተው የዕቴጌ ጠሐይቱ የምንጅላት ቅድመ አያት ደጃዝማች ዮልዮስ ናቸው። በግሪክ ቋንቋ ዮልዮስ ማለት ፀሐይ ማለት ነው። ይህ ማለት የዕቴጌ ጠሐይቱ የምንጅላት ቅድመ አያት የደጃዝማች ዮልዮስ ስም ወደ አማርኛ የወንድ ስም ሲመለስ ፀሐዩ የሚል ይሆናል ማለት ነው። ይህ ስም ወደ የአማርኛ የሴት ስም ሲሆን ደግሞ ጠሐይቱ ይሆናል ማለት። በኢትዮጵያ ታሪክ ወላጅ የቀድሞ አያት ቅድመ አያቶቹ ስም እንዳይጠፋ የአያት ቅድመ አያቶቹን ስም የልጆቹ ስም አድርጎ ያወጣዋል። የዕቴጌ ጠሐይቱ አባት ደጃዝማች ብጡልም የምንጅላት ቅድመ አያታቸውን ስም የታላቁን አርበኛ የዮልስዮስ ስም ወደ አማርኛ በመመለስ ለልጃቸው ጠሐይቱ ሲሉ ያወጡላት የጀግናው የጦር መሪ የቅድመ አያታቸው ምንጅላት የደጃዝማች ዮልዮስ ስም እንዳይረሳና እንዳይጠፋ ነው።
ስለዚህ ዕቴጌ ጠሐይቱ ብጡል ከኦሮሞ ትውልድ አላቸው ተብሎ በኦነጋውያን የጁን የኦሮሞ ለማድረግ የተፈጠረው ትርክት ነጭ ውሸት ነው። ኦነጋውያን እቴጌ ጠሐይቱን ኦሮሞ የሚያደርጉት የአባ ሴሩ ጓንጉልን ልጅን በዘመነ መሳፍንት ዘመን ኢትዮጵያን ከ፲፯፻፸፯ ዓ.ም. እስከ ፲፯፻፹፩ ዓ.ም. የገዙትን ትልቁ ራስ ዓሊን ኦሮሞ በማድረግ ነው።
ኦነጋውያን ኦሮሞ ከደቡብ ተነስቶ ወደ ሰሜን ተስፋፍቶ ነባሩን ሕዝብ እየገደለ፣ ማንነቱን እየለወጠና እያፈናቀለ የያዘውን ምድር ሁሉ የኦሮሞ አድርገው ትርክት ፈጥረዋል። እንዲሁም ኦሮሞ ወደ ወሎ ከገባ ጊዜ ጀምሮ በአማራ  ሳይንት፣ በዋድላ፣ በደላንታ፣ በላስታና በሰቆጣ ያለውን ሕዝብ ብቻ አማራ ና አገው አድርገው ጥንት የአማራ  ሕዝብ ስም አውጥቶላቸው የነበሩትን ግዛቶች ኦሮሞ ወደ ቦታው ከገባ በኋላ በቀየራቸው ስሞች እየጠሩ፤ ለምሳሌ እንደ ለጎጎራ፣ ለጋንቦ፣ ወረኢሉ፣ ወረሂመና ሌሎች ተመሳሳይ ስሞችን እያነሱ ግዛቶቹን የኦሮሞ አድርገው ያቀርቧቸዋል።
የውጭ አገር ታሪክ ጸሐፊዎች ጭምር ከየጁ፣ ከለጎጎራ፣ ከለጋንቦ፣ ከወረኢሉ፣ ከወረሂመና ሌሎች ተመሳሳይ ስሞች ካሏቸው አካባቢዎች መጥቶ ጎንደርን ወይንም ጎጃም ቢያስተዳድር ሰዎቹን ኦሮሞ አድርጎ የመመልከት የተሳሳተ ትርክት ፈጥረዋል። በዚህ መልክ እውነትና ታሪክ እያዛቡ ነው የአማራ ውን ቁጥር ከኦሮሞ ቁጥር ያንሳል እያሉ የፈጠራ መቶኛ አሃዝ ሲፈበርኩ የኖሩት። ኦነጋውያንም ኦሮሞ አብላጫ ወይንም majority ነው፤ ከአማራ ው በቁጥር ይበልጣል እያሉ የሚጽፉት የውጭ ጸሐፍቶች ጭምር ኦሮሞ ያልሆኑ ጎሳዎችን ጭምር ኦሮሞ አድርገው ስለቆጠሩላቸው ነው። ከዚህ በስተቀር በመላው ኢትዮጵያ ተሰራጭቶ የሚገኘውን አማራ ን ዛሬም ቢሆን በትክክል የሚቆጥረው ቢገኝ ከኦሮሞው ቁጥር የአማራ ው ቁጥር እንደሚበልጥ የሚጠረጠር አይደለም።
የቺካጎ ዩኒቨርሲቲ ታዋቂ የሶሲዮሊጂ ምሁር ፕሮፌሰር የሆኑት ዶናልድ ሌቪን የአሜሪካን መንግሥት ጥናት ጠቅሰው «Greater Ethiopia» በሚል እ.ኤ.አ. በ1974 ዓ.ም. ባሳተሙት መጽሐፋቸው ከገጽ 37 እስከ 38 ባለው የኢትዮጵያ ነገዶችን ብዛትና የሚኖሩበትን መልክአ ምድር አስመልክተው ባቀረቡት ጥናታቸው እንዳስቀመጡት የአማራ  ሕዝብ ቁጥር አስር ሚሊዮን በላይ እንደሚገመት አውስተው የኦሮሞ ሕዝብ ቁጥር ደግሞ ሰባት ሚሊዮን አካባቢ እንደሚገመት አስቀምጠዋል። የፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን መጽሐፍ ከታተመ ከአስር ዓመታት በኋላ እ.ኤ.አ. በ1983 ዓ.ም. በእንግሊዝ መንግሥት አዘጋጅነት «Britannica World Data Annual» በሚል የታተመው የ186 አገሮችን የማኅበራዊ፣ ኢኮሚሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ሥነ ሕዝባዊ መረጃዎችን የያዘ ጥናት የኢትዮጵያን ማኅበራዊ፣ ኢኮሚሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ሥነ ሕዝባዊ መረጃዎች ባቀረበበት ገጽ 607 ላይ እንዳስቀመጠው የአማራ  ሕዝብ ከጠቅላላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛት 38% እንደሚሆን ጠቅሶ የኦሮሞን ሕዝብ ብዛት ደግሞ ከጠቅላላው የኢትዮጵያ ውስጥ 35% እንደሆነ አስቀምጧል።
እርግጥ ነው ተማርን የሚሉ ጸሐፍቶች ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ሕዝብም ጭምር ርስ በርሱ ያን ያህል ስለማይተዋወቅ አንዱ ሌላውን ከስረ መሰረቱ የሚያውቅበት እድሉ የተመናመነ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ደህና አድርጎ መተዋወቅ የቻለው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የሕግ መመርያና የሕግ መወሰኛ ምክር ቤቶች አቋቁመው በአንድ አዳራሽ እንዲሰበሰብ እድል ከፈጠሩ ወዲህ ነው። ይህ ድልድይ ተዘርግቶ የተራራቀው ተቀራርቦ የተለያየው ተገናኝቶ መነጋገር ሲጀምር የኢትዮጵያ ሕዝብ ደህና አድርጎ እንዲተዋወቅ ከመደረጉ በፊት ከደቡቡ ክፍልም ሆነ ከየጁ ማንም ሰው ወደ ጎንደርና ጎጃም ቢሄድ የውጭ ጸሐፍትና ደቀ መዝሙሮቻቸው ጭምር ኦሮሞ ነው ብሎ የመገመት የተሳሳተ ልምድ ነበር።
ለምሳሌ በንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ዘመነ መንግሥት ንጉሥ የሆኑትና በዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ደግሞ ራስ የነበሩት ራስ ወልደ ጊዮርጊስ ራስ ተብለው የራስ ወርቅ አስረው የባለቤታቸው የትውልድ ጠቅላይ ግዛት ወደ ነበረው ጎንደር አስተዳዳሪ በመሆን ተሹመው በሐምሌ ወር 1902 ዓ.ም. ሲሄዱ አስከትለውት የሄዱት የኩሉ፣ የኮንታና የከፋን ጦር ነበር። ሆኖም ግን ጸሐፍቱና ሕዝቡ እንኳን የዚያን ሰዓት አሁንም ድረስ የራስ ወልደ ጊዮርጊስን ጦር የኦሮሞ ጦር ነበር ብለው የሚያምኑና የሚጽፉ በርካቶች ናቸው። እንደዚህም ሁሉ ኦሮሞ ተስፋፈቶ ወደ ሰባት ቤት ወሎ ከገባና በፊት አንጎት፣ ላኮ መልዛ፣ ወዘተ… እየተባለ ይጠራ የነበረውን አገር የወሎ ልጆች የጥንት ስሙን ለውጠው በአባታቸው ስም ወሎ ብለው ስለጠሩት ከዚህ የአማራ  ግዛት ወደ ሌላው የኢትዮጵያ ክፍል ለምሳሌ ጎጃምና ጎንደር ሄዶ ቢያስተዳደር ኦሮሞ እንደሆነ ተደርጎ ሲተረክ ኖሯል። በዚህ ሰሜን ምስራቃሚ የአገራችን ጠቅላይ ግዛት በመስፋፋት የሄዱ የወሎ ኦሮሞ ጎሳዎች እንዳሉ ባይካድም ከአማራ ው ቁጥር አኳያ ግን የእነሱ ድርሻ እንኳን ኗሪውን በሙሉ ኦሮሞ ሊያስደርግና ግዛቱንም ኦሮምያ ተብላ ለተፈጠረችው የኦነጋውያን የተስፋ ምድር አካል ሊያደርግ የሚችል ቁጥር ሊኖር ወሎ ውስጥ የሚኖረው የኦሮሞ ቁጥር ከአማራ ው አኳያ ሲሰላ መቶኛው ከአስር አንድ አይበልጥም።
ከዚህ በተጨማሪ አንዳንድ የኢትዮጵያን ማኅበረሰባዊ ስሪት የማያውቁ የውጭ አገርና የአገር ውስጥ ጸሐፊዎች ጭምር በጥንታዊው ቤተ አማራ ና በአሁኑ የወሎ ክፍል የሚኖረው ከዘጠና በመቶ በላይ የሚሆነው ሕዝብ ማንነታቸው አማራ  ሆኖ ሳለ የእስልምና ሃይማኖት ስለሚከተሉ ብቻ ዘራቸውን አማራ  አድርገው አይቆጥሩትም ነበር። እነዚህ ጥልቀት ያለው ጥናት ሳያካሂዱ የተሳሳተ ትርክት በመፍጠር አንዳንድ ቦታ ሳይቀር ሕዝብን ጭርም ሲያሳስቱ የኖሩ ጸሐፍት አማራ  ከተባለ ክርስቲያን እንጅ የእስላም አማራ  ያለ ስላማይመስላቸው አማራ  የሚለውን የነገድ መጠሪያ የእስልምናና የክርስትና መለያ አድርገው የነገድ መታወቂያነቱን በተሳሳተ አኳኋን በማቅረብ ብዙ ጉዳት ፈጥረዋል። ለዚህም ነበር ከትልቁ ወሌ ጀምሮ እስከ ትልቁ ራስ ዓሊን ድረስ የነበሩትን ወረሴኮች በሃይማኖት እስላም ስለነበሩ አማራ ዎች እንዳልሆኑ ተቆጥሮ ኦሮሞዎች ተደርገው ይታዩ የነበረው።
እዚህ ላይ አቶ በሪሁን ከበደ «የዐፄ ኃይለ ሥላሴ ታሪክ» በሚል ባሳተሙት መጽሐፍ ውስጥ የወረሴኮች የነ ራስ ዓሊ ትውልድ ስለነበሩት ስለ ዋግስዩም አድማሱ ወሰን የጻፉትን ማውሳቱ ጠቃሚ ነው። ታሪኩ የተከሰተው ዋግስዩም አድማሱ ወሰን በ1937 ዓ.ም. የስሜን አውራጃ ገዢ ሆነው ተሹመው ወደ ጎንደር በሄዱበት ወቅት ነው። ቀደሚ ሲል ባቀረብናቸው የተሳሳቱ ጸሐፍት ገፊነት በተፈጠረው የተሳሳተ እሳቤ የተነሳ አንዳንድ ሰዎች ዋግስዩም አድማሱ ወሰን ኦሮሞ አድርጎ ይቆጥራቸው ነበር። ይህንን ወሬ ሲናፈስ የሰሙት ዋግስዩም አድማሱ ወሰን ከእለታት አንድ ቀን በሰጡት መልስ «እኛ ከኦሮሞ ብንወለድ ደስ ይለናል እንጂ አይከፋንም፤ ነገር ግን እኛ የምንወለደው ከወረሴኮች እንጂ ከኦሮሞ አይደለንም። አንዳንድ ሰዎች ግን ከምን እንዳገኙት አይታወቅም ኦሮሞ ናችሁ እያሉ ሲናገሩ እንሰማለን፤ እኛም ኦሮሞ አይደለንም ብለን በአዋጅ እንዲነገር ለማድረግ አንችልም» ሲሉ መናገራቸውን አቶ በሪሁን ከበደ አውስተዋል። ታዳሚው ሕዝብም በበኩሉ «እኛም ኦሮሞ ቢሆኑም ደስ ይለናልም እንጂ አይከፋንም፤ ማንም ቢያስተዳድረን በጥሩ ሁኔታ እስካስተዳደረ ድረስ የነገዱ ማንነቱ ለኛ ዋና የምንሰጠው ቁም ነገር አይደለም» ብሎ እንደመለሰ አክለው አቶ በሪሁን ጽፈዋል።
ወረሴኮችን ኦሮሞ አድርገው በመጻፍ ለኦነጋውያን ትርክት ግብዓት የሆኑት አማራ  የሆኑትን ወሬሴኮች ኦሮሞ አድርገው የሚቆጥሩ ጸሐፍት ብቻ ሳይሆኑ ወረሼክ በሚል በጽሑፍ የተገኘውን ቃል ኦሮሞ ብለው የሚቀይሩ የታሪክ ባለሞያዎችም ጭምር ናቸው። ለዚህ እንደ አንድ ምሳሌ ተደርገው የሚቀርቡት እውቁ የታሪክ ጸሐፊ ተክለ ጻዲቅ መኩሪያ ናቸው። ተክለ ጻዲቅ መኩሪያ በደጃዝማች እሸቴ ኃይሉና በግራዝማች ወልደ ገብርኤል አቀነባባሪነት ከጨጨሆ በታች ከመተማ በላይ ያለው ሕዝብ ተሰብስቦ ፍፄሜ መንግሥት ተክለ ጊዮርጊስ ከዙፋናቸው እንዲወርዱና ታላቁ ራስ ዓሊ የመንግሥቱ እንደራሴ እንዲሆኑ በተወሰነ ጊዜ ፍጻሜ መንግሥት ተክለ ጊዮርጊስ ለዘውዱ ጠባቂዎች የተናገሩት «በደም ጥልቀት፣ በሥጋ ልደት የማልለያችሁን እኔን ወንድማችሁን አውርዳችሁ «የሼህ ዑመር ልጅ» መንግሥታችሁን አሳልፋችሁ ትሰጣላችሁን?» ብለው የተናገሩትን ታሪክ «የኢትዮጵያ ታሪክ፡ ከዐፄ ልብነ ድንግል እስከ ዐፄ ቴዎድሮስ» በሚል ጽፈው በትንሳኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት በ፲፱፻፶፩ ዓ.ም. ባሳተሙት የታሪክ መጽሐፍ ገጽ 292 ላይ እንደጻፉት ፍጻሜ መንግሥት ተክለ ጊዮርጊስ «እኔን አውርዳችሁ ለኦሮሞ አሳልፋችሁ ትሰጣላችሁን?» አላሉም።
የፍጻሜ መንግሥት ዐፄ ተክለ ጊዮርጊስን ዜና መዋዕል ጸሐፊ የነበሩት አለቃ ገብሩ የጻፉትን ታሪክ ለተመለከተ የንጉሡ ጸሐፌ ትዕዛዝ የጻፉት ንጉሡ «በደም ጥልቀት፣ በሥጋ ልደት የማልለያችሁን እኔን ወንድማችሁን አውርዳችሁ «ለሼህ ዑመር ልጅ» መንግሥታችሁን አሳልፋችሁ ትሰጣላችሁን?» እንዳሉ እንጂ ተክለ ጻዲቅ መኩሪያ በስህተት «የኢትዮጵያ ታሪክ፡ ከዐፄ ልብነ ድንግል እስከ ዐፄ ቴዎድሮስ» በሚለው የታሪክ መጽሐፋቸው እንደጻፉት «እኔን አውርዳችሁ ለኦሮሞ አሳልፋችሁ ትሰጣላችሁን?» የሚል አይደለም! እንግዲህ! እነ ኦነጋውያን ወሎን ዮዋን ክራምፍ «ኦሮሞያ» ሲል የፈጠረው የተስፋ ምድራቸው አካል ለማድረግ ወሎ የኦሮሞ ነው እነራስ ዓሊም ኦሮሞ ናቸው የሚሉን የጁዎችና ወረሴኮችን ኦሮሞ የማድረግ አባዜ የወለደውን የተሳሳተ ትርክት ተንተርሰው የሰው አገር ለመውረር እንጂ ከላይ ተዘርዝሮ በተገለጠው ሁኔታ እንደቀረበው ወሎም የኦሮሞ አይደለም ራስ ዓሊም ሆነ ወረሴኮች የኦሮሞ ትውልድም ሆነ ጎሳ የላቸው።
Filed in: Amharic