>
5:18 pm - Wednesday June 16, 6849

አረጋሽና ሞንጆርኖ! (አርአያ ተስፋማርያም)

አረጋሽና ሞንጆርኖ!

አርአያ ተስፋማርያም
ኢህአዴግ እንዲፈርስ እቅድ የነደፉት መለስ ዜናዊ ናቸው። ዶ/ር አብይ ስም ካልቀየሩ በቀር ያንን ነው ተግባራዊ ያደረጉት!!!
አረጋሽ አዳነ የመጀመሪያዋ ሴት ታጋይ ናት! ሞንጆርኖም ታጋይ፣ ከአባይ ፀሀዬ አንድ ልጅ በረሃ የወለደች የስብሃት ነጋ ስጋ ዘመድ ናት። በ1993 ዓ.ም ህወሀት ለሁለት ተከፈለ። አረጋሽ የመለስ ዜናዊን ቡድን በሃሳብ ተቃውመው ወጡ። አረጋሽን ጨምሮ ቤሳ ቤስቲን በሌላቸው በነገብሩ አስራት፣ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ (ነፍሰ ሄር) ወዘተ የመለስን ሃሳብ በመቃወማቸው አንድ መፅሀፍ ሊወጣው የሚችል የግፍ ግፍ ተፈፀመባቸው! አረጋሽ በ96 ዓ.ም በውጭ ድርጅት ስራ ተወዳድረው ሰኞ ይጀምሩ ተብለው ሲሄዱ “ይቅርታ ከበላይ አካል ተደውሎ እንዳትቀጥሯት ተብለናል” ተብለው ተመለሱ።
 የማነ ኪዳኔ (ጃማይካ) በውጭ ጉዳይ ሚ/ር ሃላፊ ነበሩ። “ከነገብሩ ጋር ለምን ትገናኛለህ” ተብለው በመለስ ዜናዊ ትእዛዝ፣ በስዩም መስፍን ደብዳቤ አስፈራሚነት ከድርጅቱና ከሃላፊነት ተባረሩ።
ስዬ አብርሃ ከዘጠኝ ወንድሞቻቸው ጋር እስር ቤት ተወረወሩ። መብራት ተቆርጦ ልጆቻቸው በጨለማ ሁለት አመት ኖሩ፣ በመጨረሻ ከመንግስት ቤት ተባረሩ።
ይህ ሁሉ ግፍ በሃሳብ መለየት ያመጣው መዘዝ ነው! ዛሬ እነሞንጆርኖ በዶ/ር አብይ ከስልጣን ተነሱ ሲባል አቧራ ሲነሳ እያየን ነው። ኢህአዴግ እንዲፈርስ እቅድ የነደፉት መለስ ዜናዊ ናቸው። ዶ/ር አብይ ስም ካልቀየሩ በቀር ያንን ነው ተግባራዊ ያደረጉት። መለስ ቢተገብሩት የህወሀት ሹሞች ሊቃወሙ ቀርቶ ትንፍሽ አይሉም ነበር! አዲሱን ውህደት አንደግፍም፣ አባል አንሆንም ብለው ከወጡ ስልጣን ላይ ሊቆዩ አይገባም! እርምጃው እንዳውም በጣም ዘግይቷል! ከመንግስት ወጪ የሚደረገው የጥበቃና መሰል ወጪ ባስቸኳይ ሊቆም ይገባል! እነአረጋሽ በሃሳብ ስለተለዩ ብቻ ያ ሁሉ ግፍ ሲፈፀም ስታጨበጭቡ የነበራችሁ ካድሬዎች ዛሬ ድርጅቱን አንፈልግም ብለው ለወጡ ለነሞንጆርኖ ስታላዝኑ ማየት አስቂኝም፣ አሳፋሪም ነው! በዶ/ር አብይ የሚመራው ፓርቲ የወሰደውን እርምጃ እደግፋለሁ!!
Filed in: Amharic