>

ከቀውስ የሚያተርፍ ሥርአት? (ያሬድ ጥበቡ)

ከቀውስ የሚያተርፍ ሥርአት?

 

ያሬድ ጥበቡ
በታገቱት የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ አባይ ሚዲያ ጥሩ ዝግጅት አድርጓል አድምጡት። 50 በመቶ ሴት ሚኒስትሮች ባላት ኢትዮጵያ፣ ፕሬዚዳንቷ፣ የጠቅላይ ፍርድቤት ሰብሳቢዋ፣ የምርጫ ቦርድ ኮሚሽነሯ ሴቶች በተደረጉበት ሀገር ላይ፣ 17 ልጃገሮዶች ታፍነው አንድም ደፍሮ የሚናገር የለም። መንግስት ተብዬው ሀይልም እርስ በርሳቸው የሚጣረሱ መረጃዎች እየለቀቀ ደንታቢስነቱንና ጭካኔውን እያሳየ ይገኛል። ይህ ሁሉ አበሳ የሚደርስብን ለምን ይሆን ብዬ ራሴን ደጋግሜ ጠየቅኩ። ከዚህ ቀውስ አትራፊውስ ማነው ብዬ አእምሮዬን አስጨነቀኩ። ያገኘሁት አንድ የይሆናል መልስ ብቻ ነው። አውዳሚ ካፒታሊዝም የኢትዮጵያን በሮች እያንኳኳ መሆኑ።  በሀሳብ ተከራክሮና አሳምኖ መግባት ስላልደፈረ በጓሮ በር፣ በገበያ ግርግር ማንቁርታችንን ለመያዝ እየሠራ ነው።
ወደኋላ ተመልሼ የከተብኳቸውን የመፅሀፍት ማስታወሻዎች ማገላበጥ ጀመርኩ። ናኦሚ ክላይን ስለሻክ ዶክትሪን የፃፈችውን አገኘሁ። አውዳሚ ካፒታሊዝም ከቀውስ የማትረፍ ልምድ አለው። በቺሌ በ1970ዎቹ፣ በ1999 በዩጎዝላቪያ፣ በ2001 በአሜሪካ፣ በ2003 በኢራቅ፣ በ2004 በስሪላንካ ወዘተ አውዳሚ ካፒታሊዝም ከቀውስ የማትረፍ ተግባራት ላይ ተሰማርቶ የነዚህን ሀገር ህዝቦች ንብረት ወደ አነስተኛውና የዓለምአቀፍ ትስስር ያለው ባለሀብትና መንግስታዊ ሸሪኮቹ አስተላልፏል።
በቺሌ በ1970ዎች መጀመሪያ ላይ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠውን የሳልቫዶር አየንዴን መንግስት በጄኔራል ፒኖቼ በመገልበጥ ከፍተኛ አፈናና ፍጅት ካካሄደ በኋላ፣ ህዝቡ በፍርሀትና ተስፋ መቁረጥ በተዋጠበት ቅፅበት፣ የቺሌ ህዝብ በታሪኩ ያጠራቀማቸውን ሀብቶች ለግል ባለሀብቶችና ለዓለምአቀፍ ሽርካዎቻቸው እንዲተላለፉ በማድረግ፣ የሀገሩ ድሀ ከመንግስት ያገኝ የነበሩትን ማህበራዊ ጥቅሞችና ፕሮግራሞች በማውደም ቺሌን አመሳቀለ።
በ1999 ኔቶ በዩጎዝላቪያ ላይ ያወረደውን የሚሳይሎች ጥቃት ተከትሎ በደረሰው የህዝብ መደናገጥና ተስፋ መቁረጥ ማግስት በ50 ዓመታት የሶሻሊስት ልምድ የተሰባሰበውን የህዝብ ሀብት ለግል ባለሀብቶች ካዘዋወረ በኋላ፣ በየጓሮው በተነሱት የማንነት ጥያቄዎች ጭምብል ሀገሩን አፈረሰ።
በ2001 በአሜሪካ የመንትያ ሰማይ ጠቀስ ፎቆች በአልካይዳ መፍረስን ተከትሎ በተፈጠረው መደናገጥና ቀቢፀ ተስፋ መሀል የቡሽ አስተዳደር “በሽብር ላይ ጦርነት” ካወጀ በኋላ፣ ከጦርነት የሚጠቀምና የሚያተርፍ አዲስ የኢኮኖሚ መዋቅር ዘረጋ። የጦርነቱም አበጋዞች የግል ድርጅቶች እንዲሆኑ ተደረገ። እነዚህም የግል ድርጅቶች ለአንዲት ቆርቆሮ ኮካኮላ 8 ዶላር የአሜሪካንን መንግስት በማስከፈል የታክስ ከፋዩ ንብረት ወደነርሱ እንዲተላለፍ አደረጉ።
በጣም እንግዳ በሚመስል መንገድ ከመከላከያ ሚኒስትሩ ዶናልድ ራምስፌልድና ከምክትል ፕሬዚዳንቱ ጋር ቁርኝት ያላቸው ሀሊበርተንና ቤክተል የተሰኙ ካምፓኒዎች በተቋራጭነት ከለላ በቢሊዮኖች ዘረፉ። የመንግስት ሥራ በመሆን የሚታወቁ ተግባራት በሙሉ ለወታደሮች የጤና አገልግሎት ከማቅረብ ጀምሮ፣ እስረኞችን እስከመመርመር የግል ተቋራጮች (ኮንትራክተሮች) ሥራ ሆነ። ይህን ዓይነት መረን የለቀቀ ለውጥ ሲደረግ በሽብርተኝነት የደነገጠው የአሜሪካ ህዝብም ሆነ ምክርቤቱ አንዲትም ቃል አልተነፈሱም።
የዚህ “በሽብር ላይ ጦርነት” አዋጅ ገፈት ቀማሾችም ኢራቅና አፍሃኒስተን ሆኑ። በጥቅምት 2006 ከሶስት ሺህ ሰባት መቶ በላይ ኢራቃውያን ሲሞቱ፣ ሀሊበርተን ግን 20 ቢሊዮን ዶላር አተረፈ። በ2003 የአሜሪካ መንግስት 3512 ኮንትራቶችን ሰጥቶ ነበር፣ የኢራቅ ጦርነትን በጀመረ በ22 ወራት ውስጥ ግን በነሀሴ 2006 የተሰጡት ኮንትራቶች ብዛት ወደ 115 ሺህ አሻቀበ። ለሀገር ደህንነት የሚደረገውም ወጪ በ2006 ዓም በቤተሰብ ሲሰላ 545 ዶላር በዓመት ደረሰ። አሁን የአሜሪካንን ጦር መመገብ፣ ማከም፣ ማዝናናትና መጠበቅ የግል ተቋራጮች ሥራ በመሆኑ፣ ከቀውስ የሚያተርፉ ካምፓኒዎች ቁጥር የትዬለሌ ነው።
ኢትዮጵያችን ተመሳሳይ ቀውስ ውስጥ ልትገባና ሠላም አስከባሪ ሆነው የሚመጡላት ጦሮችና ከቀውስ አትራፊ የግል ኩባንያዎች አለመኖራቸውን ርግጠኞች ነን? የኢትዮጵያ መንግስት ከማን ጋር ነው የቆመው? ሴት ልጆቻችን ታግተው የመንግስታችን ግዴለሽነትና የውሸት መረጃዎች  ፍብረካን ምን አመጣው? ሀገሪቱ ወደሙሉ ቀውስ እንድትገባ እየተሠራ ነውን?  እኛ ተናጠልና ትንንሽ የሚመስሉ ቀውሶች ላይ ልቦናችን ተመሳቅሎ ሳለ በአባይ ግድባችንና በኢኮኖሚያችን ላይ የሚደረጉት ደባዎች ምንድን ናቸው? የመከላከያ ሚኒስትሩ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጣሉ ብለን ወሬ ስናሳድድ፣ የሚኒስቴሮች ምክርቤት በህዝብ ሀብት ላይ ያሳለፋቸው ውሳኔዎች ምንድን ናቸው? እኛ በሴት ተማሪዎቻችን እገታ ላይ ተጨንቀን ሳለ በአባይ ላይ የሚደራደረው መንግስታችን  በማን ይሁንታ ነው? የኢኮኖሚውን አቅጣጫ ለመቀየርም ሆነ በአባይ ላይ ለመደራደር በመጀመሪያ በህዝብ ፍላጎት የተመረጠ መንግስት አያስፈልገንምን? ተቃዋሚ ነን የሚሉት ፓርቲዎችስ አገር በጠራራ ፀሀይ ወደ ቀውስ ሲገፋ ዝምታቸው ከወንጀል ትብብር ያነሰ ነውን?
30ሺህ የማይሞሉ አደሬዎችን እወክላለሁ የሚል የክልል መንግስት በተዋህዶ ክርስትያን ታቦትና ቀሳውስት ላይ አስለቃሽ መርዝና ጥይት ሲተኩስ ዝም ብሎ የሚያይ ጠቅላይ ሚኒስትር ከቀውስ ለማትረፍ እየሠራ አይደለም ብሎ አፍን ሞልቶ መከራከር ይቻላል? የዓለምአቀፍ ሚዲያውም በናይጄሪያ ወጣት ሴቶች እገታ ላይ ያን ሁሉ የሚዲያ ሽፋን እንዳልስጠ ሁሉ በኢትዮጵያውያኑ ላይ መጨከኑ፣ ወይ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በተሰጣቸው ቃል መተማመኛ አግኝተዋል፣ አለበለዚያም ኢትዮጵያን ወደቀውሱ ጥግ ለመግፋት የሚረዳ አንድ ክንዋኔ ስለሆነ ለመፃኢው አውዳሚ ካፒታሊዝም አስፈላጊ ግብአት ነው ተብሎ ከአርኪቴክቶቻቸው ተነግሯቸዋል።
እነዚህ ትናንሽ ቀውሶች እየተበራከቱና እየጨመሩ ሲመጡ፣ አንድ ነጥብ ላይ እንዳንንበረከክ እፈራለሁ። ፈርተን ግን እጃችንን አጥፈን መቀመጥ የለብንም። ኢትዮጵያን ያህል ሀገር በአንድ ሰው ትከሻና በአንድ ሰው መልካም ምግባር ላይ ተማምነን መተው ከስንፍናና ፍርሀትም ያለፈ ወንጀል ነው። ሽግግር ላይ ነን። ያሻግረናል ተብሎ የታመነበት አሰኳል ተፈርክሶ፣ የሀገራችን እጣ በአንድ ሰው መዳፍ ውስጥ ወድቋል። እንዴት በሥራ የሚረዱት ጎበዞች ጨምረንለት፣ በሽግግሩ ወቅት የሚሠሩትንም ተግባራት ወስነን፣ ሽግግሩን የተረጋጋና ዘላቂ መፍትሄ የሚያመጣ እናድርገው ብሎ አንድ ህዝብ ሳይወያይ እንዲሁ በፍርሀት ወደ አውዳሚ ካፒታሊዝም እቅፍ ውስጥ ይወድቃል? መጥኔ!
Filed in: Amharic