>

ጆ ከ ሩ . . . . ተ ፋ ጧ ል ! ! ! አሰፋ ሃይሉ

ጆ ከ ሩ . . . . ተ ፋ ጧ ል ! ! !

አሰፋ ሃይሉ
ጆከሩ …አንዴ ፖለቲከኞችን የሚያወያይ በሳል ፖለቲከኛ፣ የሀገሪቱን ፖለቲካዊ መፍትሄ ጥናት አቅራቢ፣  አንዴ ኡለማዎችን አስታራቂ ኡስታዝ፣ አንዴ ሃዋርያ ሰባኪ ፓስተር፣ አንዴ ጳጳሳትን አደራዳሪ መሪጌታ፣ አንዴ ከለማ ጋር ጢባጢቦ ኳስ ተጫዋች፣ ሌላ ጊዜ እንደ ክርስቶስ እስረኞችን አስፈቺ፣ አንዴ አስታራቂ፣ ሌላ ጊዜ ስናይፐር አስተኳሽ፣ አንዴ ኦሮምኛ፣ ሌላ ጊዜ አረብኛ፣ ሌላ ጊዜ ትግርኛ፣ ሌላ ጊዜ እብራይስጥኛ ተናጋሪ፡፡ ሐውልቶች ገንቢና አስገንቢ፡፡ በባላደራ ላይ ዛቻና ማስፈራሪያ ደርዳሪ፣ ኦነግን አባባይና የጥፋቱም አስተባባይ…
 
* “ሕልም እልም”! “ሕልም እልም”! “ሕልም እልም”!
ግልፅነት ማንን ገደለ? ሳይሆን… ግልፅነትን ማን ገደለ??!! ብዬ መጀመር ፈለግኩ፡፡ ግልፅነት የዘመናዊነት መገለጫ ነው፡፡ ግልፅነት በሰዎች መካከል አስፈላጊ ንጥረ ነገር ነው፡፡ ግን ደግሞ ‹‹ክሎዝድ ሶሳየቲስ›› (ዝግ ማኅበረሰቦች) ተብለን የተፈረጅነው እኛ ደግሞ አለን፡፡ ምስጥ ነን እያልኩ አይደለም፡፡ ግልፅ ነን ግን አንልም – ማንም አይለንም፡፡ ግን አንዳንዴኮ ግልፅነት በኛ መካከል ባህል ያልሆነበት ምክንያት የኖርንበትና ያሳደገን የቀረፀን ህዝባችን ዝም ማለትን፣ ችሎ ማደርን ስለወደደ ብቻ አይመስለኝም፡፡ አይደለም፡፡ ይሄ በማኅበረሰብ አጥኚዎች ጥናቶችም የተረጋገጠ ጉዳይ ነው፡፡
ሀበሾች ግልፅነትን የማናዘወትረው፣ የውስጣችንን በግልፅ መናገር፣ በፖለቲካም በግልፅ የምናስበውን አውጥተን መቃወምን ለዘመናት እንደ ዓይነተኛ ባህርይ ያልተላበስነው ግልፅነትን ጠልተን አይደለም፡፡ በግልፅ የመናገርን መዘዙን ፈርተን ነው፡፡ መከራችንን ዋጥ አድርገናት የምንኖረው ግልፅነት የሚያስከትለውን ዱላ ህዝባችን ከዘመናት ልምዱ ስለሚያውቅ ነው፡፡ ዝምታ – በተግባር ሲፈተን – ከመሞት መሰንበቻ ሆኖ ስለተገኘ ነው፡፡
በሀገራችን የመጣ ሀገረ ገዥ ሁሉ ጉልበቱን የሚፈትሸው በሚናገረው ላይ ነው፡፡ ያኛው ሄደ፣ ይሄኛው መጣ፣ ሁሉም እየተፈራረቀ ግልፅ ግልፁን እየፈጀ፣ መከራውን እያበላ፣ እየገረፈ፣ እየሰቀለ፣ ለመናገር ከተፈጥሯዊ የላንግዊጅ ሲስተምስ ጋር ሀሳቡን በነፃነት እንዲያስብና እንዲገልፅ የተፈጠረውን ሰውን ያህል ታላቅ ፍጥረት – የኛ ሀገር ተረኛ ገዢ እየተፈራረቀ ያለልክ አሸማቅቆት ቀረ፡፡ ስናውቅ በግልፅ አውጥተን እንዳንናገር ተሸማቅቀን ቀረን፡፡ እና የኅቡዕነታችን ምንጩ የግል ወይም የወል ባህርይ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን – የአገዛዞቻችን ዓይነተኛ የአፋኝነት ባህርይ ያመጣው ነው፡፡
ይህን ርዕስ ያመጣብኝ ነገር ምንድነው? በትናንትናው ዕለት በአዲስ አበባ (ይቅርታ በፊንፊኔ!) “የሴቶች እህቶቻችንን መታገት በመቃወም ሠላማዊ ሰልፍ ልንወጣ ስለሆነ እወቁት” የሚል ደብዳቤ ይዛ የተረኞቹ ቢሮ የሄደች አንዲት ቪዲዮዋ በመለዮ ለባሽ ወጠምሾች እየተመራች ወደ ተሽከርካሪ ስትወሰድ በውጭ ሚዲያ የተለቀቀ “መዓዛ” የተባለች አንዲት ልበሙሉ ኢትዮጵያዊት ወገናችንን አይቼ ነው፡፡ ተረኛው መሪያችን እና የከንቲባችን ጋሻጃግሬ ልጅቱን እጅግ በቁጣ ካመነጫጨቃት በኋላ የፌዴራል ፖሊስ ደውሎ እንደጠራና እየገፈታተሩ ይዘዋት እንደሄዱ ነው የተዘገበው፡፡ ይህ ምን ማለት ነው? አፋኝነት መንግሥታዊ መርህ ሆኗል ማለት ነው፡፡ አሸባሪዎችን አስታግሶ ሥርዓት ማስፈን ያቃተው መንግሥት – ዝምታን ማስፈን ታላቅ ስኬቱ አድርጎ ቆጥሯል ማለት ነው፡፡
የምር ግን፡፡ አሁን በኛ ሀገር — ሀገርን በሥርዓት የመምራቱን፣ የዜጎችን ሰብዓዊና የዜግነት መብቶች የማስከበሩን፣ የሰውንና ንብረቱን ደህንነት ዋስትና የማስጠበቁን… ዋናውን የመሪነት ተግባራቱን ትቶ — ወጧ እንዳማረላት ወይዘሮ — እዚህም እዚያም እጎረቤት ሀገር፣ ሩቅ ሀገር፣ ቅርብ ሀገር እያንጦለጦለ የሚያንቀዠቅዠውን መሪያችንን (የአብዮትን) ነገረሥራ ዝም ብዬ ሳስተውል — ከግርምት ልበለው ከሰቀቀን ብዛት – ምን ብዬ ስም እንደማወጣለት ሁሉ ግራ ይገባኛል፡፡
እንደቀልድ ሳስበው ግን በቃ — ለቅፅበት አንድ ስም ሽው አለብኝ፡፡ ትክክለኛ ስም፡፡ ጆከር!! ትክክለኛ ጆከር፡፡ እዚጋ እዛጋ – ሞቅ አርጊው – በቃ – ቁርጥ ጆከር!! (እነዚያ ወያኔዎች ለካ ወደው አይደለም “መሽረፈት” (“ማራገቢያ”) እያሉ ሲጠሩት የሰነበቱት?! የእነሱን ትቼ – ለምን በራሴ በማውቀው ቃል – ጆከሩ – ብዬ አልጠራውም?! እንደሥራውማ ሲያንሰው ነዋ – ጭርጭር ብለን ቀረን እኮ! እግዜርን!?)
ጆከሩ አንዴ ወታደራዊ ተንታኝ ሆኖ ጄኔራሎችን ሰብስቦ የወታደራዊ ሳይንስ ያስተምራል፡፡ አንዴ ችግኝ ተካይ ኢንቫየሮመንታሊስት ይሆናል፡፡ አንዴ የከባድ መኪና ሹፌር፡፡ ሌላ ጊዜ የመሪዎች የግል አስጎብኚ ሹፌር፡፡ አንዴ የኖቤል የሠላም ሎሬት፡፡ አንዴ የአርቲስቶች የጥበብ መምህር፡፡ አንዴ የሶስት ማዕዘን የፊልም ስክሪፕት ፀሐፊና ዳይሬክተር፡፡ አንዴ የመጻሕፍት ደራሲ፡፡ አንዴ የመንግሥት ሀገራዊ ፖሊሲ ቀራፂ፡፡ አንዴ አጋዚዎችን ፑሽአፕ አሰሪ የኩዴታ አምካኝ፡፡ ሌላ ጊዜ በቴሌቪዥን የወታደራዊ ዩኒፎርም ለብሶ በድራማ የሰው እና የመፈንቅለ መንግሥት አምካኝ፡፡
ጆከሩ …አንዴ ፖለቲከኞችን የሚያወያይ በሳል ፖለቲከኛ፡፡ የሀገሪቱን ፖለቲካዊ መፍትሄ ጥናት አቅራቢ፡፡ አንዴ ኡለማዎችን አስታራቂ ኡስታዝ፡፡ አንዴ ሃዋርያ ሰባኪ ፓስተር፡፡ አንዴ ጳጳሳትን አደራዳሪ መሪጌታ፡፡ አንዴ ከለማ ጋር ጢባጢቦ ኳስ ተጫዋች፡፡ ሌላ ጊዜ እንደ ክርስቶስ እስረኞችን አስፈቺ፡፡ አንዴ አስታራቂ፡፡ ሌላ ጊዜ ስናይፐር አስተኳሽ፡፡ አንዴ ኦሮምኛ፣ ሌላ ጊዜ አረብኛ፣ ሌላ ጊዜ ትግርኛ፣ ሌላ ጊዜ እብራይስጥኛ ተናጋሪ፡፡ ሐውልቶች ገንቢና አስገንቢ፡፡ በባላደራ ላይ ዛቻና ማስፈራሪያ ደርዳሪ፡፡ (ከመንጌ ጋር ፎቶ ተነሺነትን ብቻ – ለጥቂት ኃይለማርያም ደሳለኝ ቀደመው!)፡፡
ጆ ከ ሩ . . . . ተ ፋ ጧ ል ! ! ! እና ግን… እንግዲህ – ይሄ – የጊዜያችን የዓለሙ ምርጥ ጆከር መሪያችን — ከትወናውና እዚህም እዚያም ጥልቅ ከሚለው ጆከራዊ ተግባሩ ባለፈ — ለዚህች ሀገር ሕዝብ ሠላምና ደህንነት ወይም ብልፅግና ያበረከተው የተጨበጠ መሬት ላይ የወረደ ፋይዳ ወይ ለውጥ ምንድነው? ነገሩ ሁሉ የሚያስቅም፣ የሚያሳቅቅም ነው፡፡ (“ወጣ ወጣና እንደ ሸምበቆ፣ ተንከባለለ እንደ ሙቀጫ!” ቢል ያዲሳባ ሰው ምን ይደንቃል?)
እንግዲህ ከወያኔ/ኢህአዴግ ሥርዓት አፋኝነት ተገላገልን ያለው የኢትዮጵያ ሕዝብ የመጣበት የአሸባሪዎችን የሴቶች እገታ ድርጊት በግልጽ አደባባይ ወጥቼ ላወግዝ አስቤያለሁ ያለችን ሴት እያዳፉ ወደ ዘብጥያ የሚያወርድ ክፉ ጆከር ነው!! የቡራዩውን የአሸባሪዎች ጭፍጨፋ ወጥቼ አወግዛለሁ ያሉ ወጣቶችን በትያትር ቤት ፊት ለፊት ስናይፐር አስተኩሶ የሚያስገድል እርኩስ ጆከር ነው የገጠመን እንግዲህ ከለውጡ በኋላ፡፡ ምኑ ነው የተለወጠው? ሰዉ ያው፡፡ ሥርዓቱ ያው፡፡ አፈናው ያው፡፡ ግድያው ያው፡፡ አንዱ በሟች ራዕይ የሚመራ ንጉሥ ሄዶ፣ ሌላ ሰባተኛው ትያትረኛ ጆከር ንጉሥ ስለመጣ ነው ለውጡ??!!  ለውጥ ግን ቆይ…. ምን ማለት ነው? ወዳፈጠጠ ጨፍኑ ላሞኛችሁ የሚደረግም ለውጥ… ይሄም ራሱን የቻለ ለውጥ እንደሆነ ያላወቅን… በጆከር ሿሿ የተሠራን ምንኛ ጅሎች ነበርን?!
በቅርቡ (ምን በቅርቡ… ድሮ ድሮ እንበለው እንጂ!) ድሮ ታጣፊ ክላሹን 27 ዓመት ሙሉ እንደወደረ አንድም ቀን ጥላውን ሳያምን የዛፍ ላይ እንቅልፍ ተኝቶ በግፊ ገለል ያለው ወያኔ/ኤህአዴግ — “አንድም ሁለትም ሆናችሁ ስሜን በከንቱ ብትጠሩ፣ እነሆ በመካከላችሁ እገኛለሁ” እስከማለት የደረሰ አቋሙን ያለ ምንም ምንተ እፍረት እያወጀና እየተገበረ የኖረበትን እና የኖርንበትን (መኖር ከተባለ) መቼም እንደቀልድ አሳልፈነዋል፡፡ ያም አፈና እያለም እንኳ ቢሆን ግን — ለህይወታቸው ሳይሳሱ — አንድም ሁለትም ብቻ ሳይሆን — አንድ ሺህም ሁለት ሺህም ሆነው የተቃውሞ ድምፃቸውን ለማሰማት አደባባይ የወጡ በርካታ “እምቢኝ ባይ” ጀግኖች አላጣችም መቼም ይህቺ ሀገር (ፈጣሪ ይመስገነውና)፡፡
ያኔ ብዙ የተቃዋሚ መሪዎችና ጋዜጠኞች አንድም ሁለትም እየሆኑ የሥርዓቱን ስም በከንቱ እየጠሩ ለእስርና ለመከራ ሲዳረጉ ብዙዎቻችን ከመቅሰፍቱ ለመዳን አይተን እንዳላየ፣ ሰምተን እንዳልሰማ ማለፋችንም — ታሪክ የማይረሳው አሳፋሪ የታሪካችን መንታ ገፅ ነው፡፡ ወይ በባህሪ ጉዳይ ካልተመካኘ በቀር ይህን የቅርብ ‹ጆሮ ዳባ ልበስ› ታሪካችንን ማንም ሊያስተባብለው የሚችል አይመስለኝም፡፡
(የባህሪ ጉዳይ ማለቴ … አንዳንዱን ሰው ብታፈርጠውም የሆዱን ነገር ባፉ አውጥቶ አይነግርህም፡፡ የአንዳንዱ ሆድ ደግሞ ሲፈጥረው እንስፍስፍ ነው — በሆዱ ቅቤ የማያድር ለፍላፊ፡፡ ያ ለፍላፊ ነው የሚማገደው፡፡ ጥይት ሳያጮኹ፣ ድምፅም ሳያሰሙ ወያኔ/ኢህአዴግን አስብተው ያረዱ የሰው ተንከሲሶች ደግሞ አሉልህ አሁን በቤተመንግሥትና በዙሪያው፡፡)
ብቻ ግን — ቀን እስኪወጣ በዝምታ መገዛትና ግልፁን በጊዜ ተናግሮ የመሸበት መታጎር — የህሊና ሰብዕና ጉዳይ ሳይሆን የሰው ባህርይ ጉዳይ ነውም ከተባለ — ግልፅነትን፣ ግልፅ ሰውነትንማ የመሠለ ታላቅ ባህርይ ከወዴት ሊገኝ? በዚህ ሕልም እንኳ ዝም ተብሎ ለተገኘ ሰው በማይነገርበት በኛ የዝም ባህል መካከል — ግልፅ ሰው ሲገኝማ እልልልልል ነው እንጂ፡፡ ተገኝቶ ነው?፡፡ ግልፅ ሰው —ለራሱ አይበረክት ይሆናል እንጂ — ለሰሚውማ አንደበቱ ነው፡፡ አንጀትህን ቅቤ ያጠጣልሀል፡፡ እሰይ፡፡ ምን ላድርግህ? ትለዋለህ፡፡
ካለፉት ሃያ ምናምን ዓመታት ወዲህ — ብዙዎቹ የኛ የሕዝብ ጀግኖች — በኒሻንና በማዕረግ የተንቆጠቆጡት የቤተመንግሥት ጀግኖች ሳይሆኑ — ፖለቲካችንን የሰብዓዊ ድርቅ በመታባቸው ክፉ ወራት — አንጀታችንን በአንደበታቸው ያረጠቡ፣ ሆዳችንን በንግግራቸው ቅቤ ያጠጡ – ግልፅ ወጥተው እውነትን ለወገኖቻቸው ያሳዩ – ግን የፈረደባቸው – ግልፅ ሰዎች ናቸው ብንል ምንም ማጋነን የለውም፡፡
በነገራችን ላይ – በጣም የሚገርመኝ ፓራዶክስ (አያዎ) ነገር ምንድነው? አንዳንዴ የምታደንቀውን ግልፅነት – ከማታደንቀው ቦታ እና ከማታደንቀው አንደበትም ልትሰማው መቻልህም ነው፡፡ በቅርቡ ካጋጠሙኝ የዚህን መሰል ግልፅ ሰዎች የማልረሳውን ምሳሌ ልጥቀስ፡፡ የማልረሳው ምሳሌዬ “ኦቦ ዳዑድ ኢብሳ” ነው፡፡
ባለፈው ጥቅምት ወር ላይ ይመስለኛል፡፡ ዋልታ ይጠይቀዋል ስለ ኦነግ ትጥቅ መፍታት ጉዳይ፡፡ ዳዑድ ኢብሳ ጋር ምንም ድብቅብቅ አልታየም፡፡ ገረመኝ፡፡ በቀጥታ ለጠያቂው እቅጩን ቁጭ ሲያደርግለት፡፡ ያ ግልፅነቱ – አንጀቴን እንዴት ቅቤ ጥጥት እንዳደረገው!? እንዲህ ነበር ያለው፡-
“ኦነግ ወደ ሀገር ቤት የገባው ከኢትዮጵያ
መንግሥት ጋር ትጥቁን ፈትቶ በሠላማዊ
መንገድ ለመታገል ነው ተብሎ የሚነገረው
መሠረተ ቢስ ወሬ ነው፣ እኛ ትጥቅ እንድ
ንፈታ የተስማማንበት ስምምነት የለም፣
የታጠቀው አካል ትጥቅ ይዞ እያለ እኛ
ትጥቅ የምንፈታበት ምክንያት አይኖርም፣
ትጥቅ ፈቺም አስፈቺም የለም፣ ማነው
ፈቺ? ማነው አስፈቺ?”
ብሎ እቅጩን ተናግሮ የመሸበት እርርርፍ፡፡ በኢትዮጵያዬ ዓይን የመጣው – የተነከረበት የኦነግ ነፃ አውጪነት አዚሙ እጅጉን ቢያንገፈግፈኝም – በዚያ ግልፅ አነጋገሩ ግን – ዳዑድ ኢብሳን – ሁሌም በአድናቆት ሳስታውሰው የምኖር ይመስለኛል፡፡ አንደኛ ነገር — እነ ጆከሩ የኢትዮጵያን ሕዝብ ሰመመን የወጉበትን የውሸት ፕሮፓጋንዳ ዶጋ አመድ ነበር ያደረገባቸው፡፡ ሁለተኛ ነገር ደግሞ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በሀገራችን “መንግሥት” ተብሎ ሊጠራ የሚችል አካል እንደሌለ ነበር በግላጭ አስረግጦ የተናገረው፡፡
አባባሉ እኮ ግልፅ ነው — ትጥቅ የሚያስፈታ በትክክል “መንግሥት” የሚባል አካል ካለ — እስቲ ህወኀትንም ባለችበት ሄዶ ትጥቋን ያስፈታ፡፡ እስቲ ብአዴንን ሄዶ ትጥቁን ያስፈታ፡፡ እስቲ ኦህዴድን ትጥቅ ያስፈታ፡፡ በትክክል በዚህች ሀገር በተግባር የመንግሥትነት ኃይልና ሥልጣን ያለው መንግሥት አለ ከተባለ — ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲ ነኝ ባይ ትጥቅ ያስፈታ፡፡ ሌላውን ትጥቅ የሚያስፈታ መንግሥት ካለ — እኛም ትጥቅ የማንፈታበት ምክንያት የለም ነው ዕቅጭ መልሱ፡፡ የውሸት አባቱን (ጆከሩን) እና ጭፍሮቹን ሁሉ— ፀጥ ያደረገ ግልፅ ቃል ነበር፡፡ (እውይ! እውይ! ውይ! ውይ!! አይ አነጋገር!!! “ለካ ኦነግ ቅኔም ይዘርፋል?” ብዬ ነበር የኦቦ ዳዑድ ኢብሳን መልስ ስሰማ በአግራሞት ተውጬ!!) ግልፅ ሰውስ አይጥፋ አቦ!!
መቼም ህልም አይከለከል አይደል?፡፡ ህልም ማየት አዎ፡፡ መናገርማ ሳይከለከል አይቀርም፡፡ አሁን አደባባይ አንድም ሁለትም ሆነህ ወጥተህ “I have a dream…” ብትል – እነሆ ጆከሩና አጃከሮቹ ወገብ ዛላህን ሊሉ በመካከልህ ይገኛሉ፡፡ ማን ፈቀደልህ? ህልምህን መናገር ለአንተ አልተፈቀደም፡፡ ለማንኛውም ሕልም አይቻለሁ፡፡ ቅዠት ይሁን ህልም አላወቅኩም፡፡ ህልም መሰለኝ፡፡ ይኸው ልናገረው ነው፡፡
ግን ቆይ እንጂ፡፡ የምን መቸኮል ነው?! ጀበናው ከነመግላሊቱ፣ ስኒው ከነረከቦቱ፣ ሰንደሉ ከነመሰኪያው ይደርደር፡፡ ብረትምጣዱ ይምጣ፡፡ ቡናው ይታጠብ፡፡ ሣሩ ይጎዝጎዝ፡፡ ዕጣኑ፣ ሉባንጃው፣ ከርቤው፣ አደሱ፣ ጭሱ ይጫጫስ፡፡ መቁያው፣ ሙቀጫው በቦታው ይረፍ፡፡ ፈንዲሻው ይንዷዷ፡፡ ለምቀኛውም፣ ላድባሩም፣ ላውጋሩም ረጨት ረጨት ይደረግ፡፡ እና የነፍስ አባት ይጠሩ፡፡ አሁን ነው በግልፅ መናገር፡፡ (እንዲያው ግን ብቻ — የሕልሜ ነገር በጨዋታ ቢያዝ፡፡)
አይበለውና — (አይበለውና ብዬ ብጀምረው ይሻላል) — እንዲያው አይበለውና — የሆነ — በሀገሪቱ ሕግና ሥርዓት ለማስፈን፣ የነዋሪዎችን ደኅንነት ከአሸባሪዎች ጥቃትና ለመታደግ የቆረጠ — ኮስተር ያለ ጊዜያዊ ባለአደራ የሚሊቴሪ ጥምር ኮሚቴ — ድንገት ጆከሩን (ከእነ ሆድ-አደር ተከታዮቹ) በቁጥጥር ሥር ቢያውል — እና ከቤተ መንግሥት በቀጥታ — ወደ ተዘጋጀላቸው አስተማማኝ ጊዜያዊ የማቆያ ቤት ቢዶላቸው — እና “ለሀገሪቱና ለሕዝቡ ደህንነት ስል ለጊዜው ሀገርን የማስተዳደሩን ከባድ ኃላፊነት ተረክቤያለሁ!” ብሎ — በኢትዮጵያ ሬዲዮ የጠዋቱ ሰበር ዜና ላይ ቢያውጅ — እውን ይሄንንም ድርጊት — ሌሎች ሀገሮች መሰል ድርጊት ሲፈፀም እንደምንለው — አሁን በእኛም ሀገር — አፋችንን ሞልተን “መፈንቅለ-መንግሥት” (“ሥዒረ-መንግሥት”) ተፈፀመ — ብለን ልንጠራው — እና ልናወግዘው ነው? (እያልኩ ለሥዒረ…. እንትኑ… የሚመጥን ስያሜ ለማውጣት ስጨነቅ ከእንቅልፌ ነቃሁ፡፡)
I don’t know ሃሳቤን (ማለቴ ሕልሜን) በትክክል መግለፅ ችዬ እንደሆነ! ግን የህልሜ ሀሳቡ አስደንግጦኛል፡፡ በየምሥራቹ፡፡ እውነት ግን (አልኩ ከነቃሁ በኋላም) እውነት ግን… ከባዱን የዜጎቹን ደኅንነት የመጠበቁን መንግሥታዊ ሥራውን ለመሥራት ፍቃደኛ ያልሆነ፣ እና በትክክል እንደ ቃሉ ትርጉም በተግባር “መንግሥት” ተብሎ ሊጠራና ሊታመን የሚበቃ ኃላፊነት የሚሰማው ሀገር አስተዳዳሪ አካል በሌለበት ሀገር ላይ… በምን አፍ ነው “መፈንቅለ-መንግሥት” ተካሄደ ተብሎ የሚነገረው??? ለመፈናቀልም እኮ በቅድሚያ በትክክል “መንግሥት” ሆኖ መገኘት ሳይጠይቅ አይቀርም ብዬ እኮ ነው???!!! ታዲያ ዳዑድ ኢብሳስ ከዚህ የተለየ ምን አለ? (መቼም ግልፅ ግልፁንም አይደል የምናወራው?! እንዲህ ነው እንጂ!!)
እና ግን መጀመሪያ ወዳነሳሁት ሃሳብ ልመለስና — እንዲያው ግን እውነት — ግልፅ ግልፁን እንነጋገር ከተባለ — እውነት ግን — ባገራችን — እውነት መንግሥት አለ? እውነት ግን — ነገ ከነገ ወዲያ ከቤተመንግሥት መቀመጫው ቢፈናቀል — የምሩን “መፈንቅለ መንግሥት ተፈፀመበት!” ሊባል የሚበቃ መንግሥት በትክክል አለን ወይ??? /በነገራችን ላይ መፈንቅለ መንግሥቱ ከሰሞኑ በሕልሜ የመጣብኝ ትዕይንት ነው — “ሕልም እልም” በሉኝ! “ሕልም እልም”! “ሕልም እልም”! “ሕልም እልም”!
ፈጣሪ የሚበጀንን ያምጣልን አቦ!    
Filed in: Amharic