>

“ዳኛቸው ወርቁና መጽሐፎቹ” (በሣህለሥላሴ ብርሃነማርያም )

“ዳኛቸው ወርቁና መጽሐፎቹ”

በሣህለሥላሴ ብርሃነማርያም
ማንኛውንም መጽሐፍ ገዝቼም ሆነ ተውሼ ከማንበቤ በፊት ማን እንደጻፈው፣ በኋላው አጎበር ምን እንደተጻፈ፣ መግቢያ ወይም መቅድም ካለው እዚያ ውስጥ ምን እንደተባለ፣ ማውጫ ካለውም በዚያ የሠፈረውን ገረፍ ገረፍ አድርጌ እመለከታለሁ።
ይህንን የማደርገው መጽሐፉን ከአጎበር እስከ አጎበር ማንበብ ከመጀመሬ በፊት “መነበብ የሚገባው መጽሐፍ ነው ወይንስ አይደለም?” የሚል ግምት ለመውሰድ ያህል ነው። አብዛኛውን ጊዜም ግምት ወስጄ በማነባቸው መጻሕፍት ከሞላ ጐደል እደሰታለሁ፤ የአእምሮ ብርሃን የሚሰጡ፣ ስለ ሕይወት ብዙ ነገር የሚያስተምሩ፣ የሚያዝናኑና የሚያስደስቱ ናቸው።
ከእነዚህ መጻሕፍት አንዳንዶቹን ብጠቅስ እወዳለሁ።
የሐዲስ ዓለማየሁ “ፍቅር እስከ መቃብር” (1958)፣ የዳኛቸው ወርቁ “አደፍርስ” (1962)፣ የአፈወርቅ ገብረየሱስ “ልብወለድ ታሪክ [ጦቢያ]” (1900) እና “ዳግማዊ አጤ ምኒልክ” (1901)፣ የገብረሕይወት ባይከዳኝ “መንግሥትና የሕዝብ አስተዳደር” (1916)፣ የአሰፋ ገብረማርያም “እንደወጣች ቀረች” (1946) … እና ሌሎችም።
ከላይ የጠቃቀስኳቸውን የአገራችን ደራስያን የማውቃቸው በጽሑፎቻቸው አማካኝነት እንጂ በግንባር አይደለም። በግንባር ላያቸው ፍላጎት ቢኖረኝ ኖሮ እንኳ ባልተቻለኝም ነበር፤ እነሱ የኖሩበትና እኔ የምኖርበት ዘመን በጣም የተራራቁ በመሆናቸው።
ዳኛቸው ወርቁ ግን የዕድሜ አቻዬ በመሆኑና ሁለታችንም የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በመሆናችን እሱ በሕይወት በነበረበት ዘመን ብዙ ጊዜ የመገናኘትና የመጨዋወት ዕድል አጋጥሞናል።
የማልረሳው የመጀመሪያው ግንኙነታችንን ነበር።
ከብዙ ዓመታት በፊት አንድ ቀን፣ የቀድሞው ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ባልደረባዬና ወዳጄ የሆነውን ሰው ለመጠየቅ ወደ ማስታወቂያ ሚኒስቴር እሄዳለሁ። ያ ወዳጄ በዚያን ሰዓት ከዳኛቸው ወርቁ ጋር ነበር፤ በቢሮው ውስጥ።
“እገሌ”፣ “እገሌ” ብሎ አስተዋወቀንና የ“አደፍርስ” ደራሲ መሆኑን ገለጸልኝ። “አደፍርስ” ስለሚባል መጽሐፍ ከዚያን ቀን በፊት ሰምቼ አላውቅም።
 ከታተመ አንድ አመት እንኳ የሞላው አይመስለኝም።
“በዚህ ርዕስ የሚታወቅ መጽሐፍ ካለ ምነው መጽሐፍ መሸጫ መደብር ውስጥ አይቼው አላውቅም?” ስል ጠየቅሁት ዳኛቸውን።
“ቀደም ብሎ እንኳ ከመጽሐፍ መሸጫ መደብር ይገኝ ነበር፤ አሁን ግን እኔ ዘንድ እንጂ ሌላ ቦታ አታገኘውም” አለኝ።
ሦስታችንም የመጻሕፍት አፍቃሪያን ስለነበርን ስለሥነጽሑፍና በጊዜው ታትመው ይወጡ ስለነበሩት መጻሕፍት ስንጨዋወት ቆየንና በመጨረሻም ዳኛቸውና እኔ ወዳጃችንን ተሰናብተን ወጣን።
“መጽሐፍህን ልገዛው እፈልግ ነበር። ነገር ግን እንዴት ነው የማገኘው?” አልኩት።
“ማግኘት እንኳ ታገኘዋለህ። ነገር ግን ዋጋው እንደቀድሞው አይደለም” አለኝ።
“ስንት ነው?” አልኩት።
“መጀመሪያ በአምስት ብር ነበር የሚሸጠው። ነገር ግን አልሄድ ስላለ አስር ብር አደረግሁት። አሁንም እንደገና አልሄድ አለ። ስለዚህ መሸጫ ዋጋውን አስራ አምስት ብር አድርጌዋለሁ” አለኝ።
ይህንን ስሰማ ሳቅ ወጥሮ ያዘኝ። ነገር ግን ከዚያ በፊት የማልተዋወቀውን ዳኛቸውን እንዳላስቀይመው በመፍራት ሳቄን ታግዬ አስቀረሁትና፣
“ለማንኛውም አንድ ኮፒ እፈልጋለሁ” አልኩት።
“እንግዲያውስ ተከተለኝ” ብሎኝ መኪናው ውስጥ ገባ። እኔም በያዝኩት መኪና ተከተልኩት።
በፒያሳ አድርገን አራት ኪሎ ስንደርስ ወደታች ተጠምዘን ወደ ምኒልክ ግቢ አቅጣጫ አመራን። እዚያ ሳንደርስ ከፓርላማ ወደ እሪ በከንቱ የሚያመራውን መንገድ አቋርጠን ትንሽ ከሄድን በኋላ ወደ ቀኝ ታጥፈን በጠባብ ኮረኮንች መንገድ ተጓዝን። ከዚያም በኋላ ከመኪናችን ወርደን በእግራችን ወደ መኖርያ ቤቱ አመራን።
ከጽሕፈት ቤቱ ስንገባ ከወለሉ እስከ ጣራው ድረስ በብዙ ረድፍ የተደረደሩ የመጻሕፍት ክምር ይታያል። ሄድ ብሎ ከአንዱ እሽግ አንድ ኮፒ መዞ አወጣና “ይኸውልህ” አለኝ። ተቀብዬው፣ ሂሳቡንም ከፍዬ ተሰናብቼው ወጣሁ።
ዳኛቸው ወርቁ ልዩ ባህሪ ያለው ሰው መሆኑን ያን ቀን ነው የተረዳሁት።
ከዚያም በኋላ ብዙ ጊዜ ተገናኝተናል፤ ተቀራርበናልም። እኔ እንደማውቀው በጣም ሰዓት አክባሪ ሰው ነበር። አንድ ቀን እቢሮው ተቃጠርንና ከዚያ ስሄድ እሱ ከቢሮው ወጥቶ ወደ መኪናው ሲያመራ አየሁና፤
“ዳኛቸው! ዳኛቸው!” ብዬ ተጣራሁና፤ “ምነው? እረሳህ እንዴ? ቀጠሮ ነበረንኮ!” አልኩት።
“ቀጠሮውንማ አፍርሰህብኝ ወደ ሌላ ጉዳዬ መሄዴ ነበር” አለኝ፤ መለስ ብሎ።
እጅግ በጣም ተገርሜ ሰዓቴን ብመለከት ያሳለፍኩት ጊዜ ሦስት ደቂቃ ብቻ ነበር!
ዳኛቸውን ከሌሎች ሰዎች ለየት የሚያደርገው ሰዓት አክባሪነቱ ብቻ አልነበረም። እኔ እንደማውቀው እውነተኛ ሰው ሆኖ ተጠራጣሪም ነበር –
 “ሰውን ውደደው እንጂ አትመነው” እንደሚባለው አይነት!
የሆነ ሆኖ ወደ መጻሕፍት እናምራ።
“አደፍርስ” በርካታ ምሁራንን በሰፊው ያነታረከ መጽሐፍ ስለሆነ እኔም ተጨማሪ ንትርክ ውስጥ ለመግባት ፈቃደኛ አይደለሁም። ስለምንነቱ ጥቂት ሳልል ግን ለማለፍ አይቻለኝም።
“አደፍርስ” በሌሎች ልብ ወለዶች የምናየው ዓይነት አንድ ወጥ የሆነና የጐለበተ ፈጠራ ታሪክ የለውም።
በዚህ ፈንታ ቁርጥራጭ ትርኢቶች ነው የሚታዩበት።
ትረካውን ይፋትንና ጥሙጋን ከጣርማ በር ተራራ ላይ ሆነው ሲመለከቱት ምን እንደሚመስል የሙዚቃ ቃና ባለው ቋንቋ ይጀምራል፤
“ቁንዲ አንገቷን አስግጋ ቃፊርነት የቆመች መስላለች። የዓዋዲና የጀውሃ ጅረቶች ደረታቸውን ለፀሐይ ሰጥተው ይምቦገቦጋሉ። ሰማይና ምድር የተገናኘበት፣ ሕይወት ያሸለበችበት የሚመስለውን በስተግርጌ የሚታይ ሜዳ አቧራ ረግቶበታል … የይፋትና ጥሙጋ አውራጃን ጣርማበር ተራራ ላይ ሆኖ ሲመለከቱት እግዚአብሔር ዓለምን ሠርቶ ሲያበቃ የተረፈውን ትርክምክም ያጐረበት እቃ ቤቱ ይመስላል – ሸለቆው፣ ጉባው፣ ተራራው፣ ገመገሙ፣ ጭጋጉ፣ አቧራው ሕይወትን አፍኗት ተኝታለች – ያቺ በሌላው አገር የምትጣደፈው፣ የምትፍለቀለቀው፣ የምትምቦለቦለው ሕይወት እዚህ እፎይ ብላለች – በርጋታ፣ በዝግታ ታምማለች፤ በተገማሸረ መስክ ውስጥ እንደሚብሰከሰክ ውሃ …” (ገጽ ፭)
ገጠሩን በተዋበ ቋንቋ ከገለጸልን በኋላ ወ/ሮ አሰጋሽ የተባሉ የገጠር እመቤት ከጢሰኛቸው ጋር ቲያትር መሰል የንግግር ልውውጥ ሲያደርጉ ያሳየናል። ጢሰኛው የዘንጋዳ ዘር አጥቶ ሊበደር ወደ እመቤቱ ዘንድ መጥቶ ይለምናል። ወ/ሮ አሰጋሽ በተባ አንደበት የጢሰኛቸውን ሞራል አንኮታኩተው ከሰበሩት በኋላ ዘጠኝ ቁና ዘንጋዳ ሰጥተውት በመኸር ወራት አስራ አምስት ቁና እንዲመልስ ይነግሩታል።
የ”አደፍርስ” ጀርባ ሥዕል (በታዬ ወልደ መድኅን)
አራጣው በጣም የበዛ መሆኑ በተሰበረ ድምፅ ይገልጽላቸውና እንዲራሩለት ይማጸናቸዋል። ወ/ሮ አሰጋሽ ግን በአራጣው ከተስማማ ዘጠኙን ቁና እንዲወስድ፣ አራጣው በዛ ካለም እንዲተወው ርህራሄ በሌለው አንደበት ቁርጥ አድርገው ይነግሩታል።
ሌላ ምርጫ ስለሌለው እመቤቱ ለሚሰጡት ዘጠኝ ቁና ዘንጋዳ አስራ አምስት ቁና እንዲመልስ ይስማማል። ወ/ሮ አሰጋሽም ይህንን ገፈፋ ውለታ እንደዋሉለት በመቁጠር በመሬታቸው ላይ የበቀለውን የድርቆሽ ሳር (ሰማንያ ሸክም ይሆናል) አጭዶ፣ ተሸክሞ አምጥቶ ከደጃቸው እንዲከምረው ይነግሩታል። እሱም ትእዛዛቸውን ለመፈጸም የቃል ውል ከገባ በኋላ ዘንጋዳው ተሰፍሮለት አህያውን እየነዳ ከግቢያቸው ይወጣል።
በዚህ ክፍል ያለው ድንቅ ትርኢት በመድረክ ላይ የሚታይ ትርኢት እንጂ ሌላም አይመስል።
ታሪኩ በዚሁ ይቀጥላል ብለን ስንጠባበቅ ሳለን የመድረኩ መጋረጃ ተዘግቶ ይከፈትና ሌሎች ባህርዮች ሲጨዋወቱ እናያለን።
ምሽት ይሆንና “የፌንጣ ሲርሲርታ፣ የዝንብ ዝዝታ፣ የንቦች እምምታ” እንሰማለን። ጨረቃ ትወጣለች። የወ/ሮ አሰጋሽ አገልጋይ የሆነውን የወርዶፋ ዋሽንት ሙዚቃ እናዳምጣለን።
በዚህ መልክ የመድረኩ መጋረጃ ተዘግቶ እንደገና እየተከፈተ እስከ መጨረሻው ድረስ የተለያየ ትርኢት እናያለን።
ከዚህ ቀደም እንዳልኩት መጽሐፉ ከልብ ወለድነት ይልቅ ወደ ድራማነት የተጠጋ ነው … አንዳንዴ አስቸጋሪ ቢሆንም በውብ ቋንቋ የተደረሰ ድራማ።
[ሣህለሥላሴ ብርሃነማርያም
[ምንጭ] – “ ሹክታ ”]
Filed in: Amharic