>

የትኛው ነው አማርኛ? "መድኀኔ ዓለም" ወይስ "ፈይሳ አዱኛ"?!? (አቻምየለህ ታምሩ)

የትኛው ነው አማርኛ? “መድኀኔ ዓለም” ወይስ “ፈይሳ አዱኛ”?!?

 

አቻምየለህ ታምሩ
በግዕዝ መቀደሱ የኦሮሞን ሕዝብ ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለየ መልኩ ተጎጂ ሊያደርገው አይችልም።  አማራው፣ ትግሬው፣ አገዉ፣ ጉራጌው፣ ዎላይታው፣ ጋሞው፣ ሐድያው፣ ቅማንቱ፣ ወዘተ የሚቀድሰው በግዕዝ ነው። ተራው ምዕመን አማራውም ሆነ ትግሬው እንዲሁም ሌላው የግዕዝ ቋንቋ ተናጋሪ አይደለም። ሆኖም ግን በግዕዝ ስለተቀደሰ  የጥንቱን ሥርዓት ላፍርስ፤ በቋንቋዬ አልተቀደሰም ብሎ እንደ ቄስ በላይ በቤተክርስቲያን ላይ አልተነሳም…!
የጃዋር መሐመድ የመንፈስ ልጅ የሆኑት ቄስ በላይ መኮንን የሚመሩት «የኦሮምያ ቤተ ክህነት» የሚባለው የፖለቲካ ቡድን ከሰሞኑ  ወደ ሰሜን አሜሪካ «ታቦት» ይዞ እንደተጓዘና የታቦቱን ስምም «ፈይሳ አዱኛ» የሚል «የኦሮምኛ» ስም እንዳወጣለት የተወሰኑ የቡድኑ አባላት ከሰሞኑ ከጃዋር  መሐመድ ቴሌቭዥን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ነግረውናል። የኦሮምኛ ስም አወጣንለት ያሉትን የታቦቱን ስም ምንነት ሲያብራሩም «ፈይሳ አዱኛ  የሚለው የታቦቱ የኦሮምኛ ስም የአማርኛው መድኀኔ ዓለም  ነው» ብለዋል።
ከጅምሩ ጀምሮ የነ ቄስ በላይ ችግር ቋንቋ አልነበረም። ከ121 ዓ.ም. በፊት መጽሐፍ ቅዱስ ወደ አማርኛ  ሳይተረጎም  በኢትዮጵያ ፊደል ወደ ኦሮምኛ እንዲተረጎም ያደረጉት ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ናቸው። በየትኛውም የኢትዮጵያ አካባቢ ቅዳሴ የሚካሄደው በግዕዝ ነው። ይህ የተደረገው  በዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ወይም በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን አይደለም። ይህ የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ  ከገባ ጀምሮ የኖረ ሥርዓት ነው። ዛሬ ወለጋ ከሆነው እስከ ባሌ ድረስ፤ አልፎም እስከ ዘይላ ድረስ ያለው ሕዝብ  የኦሮሞ የገዢ መደብ ኢትዮጵያን ከመውረሩ  ከአምስት መቶ ዓመታት  በፊት ጀምሮ  በኢትዮጵያ ፊደል የሚጽፍ፣ በግዕዝ የሚቀድስና  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ  ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተከታይ ነበር።
ከዚህ በፊት ባቀረብሁት አንድ ጽሑፍ Sanaag የሚባለው «የሶማሌ ክልል» ውስጥ የሚገኘው ትልቅ  ጎሳ  ጥንት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ተከታይ እንደነበረና  ወደ እስልምና ከመቀየራቸው በፊት ያመልኩበት የነበረን የቤተ ክርስቲያን ፍርስራሽ እንዳሳዩት ሪቻርድ በርተንን ጠቅሼ ጽፌ ነበር።  ከዛሬው ኢትዮጵያ አልፎ ሶማሊያ ውስጥ  ስለነበሩ የጥንት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች የአርኪዮሎጂ ማስረጃዎችን ማንበብ የሚሻ ቢኖር Ben I. Aram እ.ኤ.አ. በ2003 ዓ.ም. Africa Journal of Evangelical Theology ላይ “Somalia’s Judeo-Christian Heritage: A Preliminary Survey” በሚል ያሳተመውን ጥናት ይመልከት።
ከዚህ በተጨማሪ ሶማሌው ዶክተር ዐሊ አብዲራህማን ኸርሲ እ.ኤ.አ. በ1977 ዓ.ም. በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ “The Arab Factor in Somali History: The Origins and Development of Arab Enterprise and Cultural Influences in the Somali Peninsula” በሚል ባቀረበው የሦስተኛ ዲግሪ ማሟያ ጥናቱ፣ የ10ኛ እና የ11ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የዐረብ ተጓዦች የመዘገቧቸውን የታሪክ ማስረጃዎች በመጥቀስ ገጽ 117 ላይ፡- “Tenth and eleventh century Arab sources all describe Zaila as an Abyssinian Christian city which traded peacefully with the Yamani (sic) ports across the Red Sea.” በሚል ካቀረበው የዛሬው ምዕራብ ሶማሊያ የክርስቲያን ምድር እንደነበር መገንዘብ ይቻላል። እነዚህ  ሁሉ ይጽፉ የነበሩት በኢትዮጵያ ፊደል፤ ይቀድሱ የነበሩት ደግሞ በግዕዝ ነበር።
በግዕዝ መቀደሱ የኦሮሞን ሕዝብ ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለየ መልኩ ተጎጂ ሊያደርገው አይችልም።  አማራው፣ ትግሬው፣ አገዉ፣ ጉራጌው፣ ዎላይታው፣ ጋሞው፣ ሐድያው፣ ቅማንቱ፣ ወዘተ የሚቀድሰው በግዕዝ ነው። ተራው ምዕመን አማራውም ሆነ ትግሬው እንዲሁም ሌላው የግዕዝ ቋንቋ ተናጋሪ አይደለም። ሆኖም ግን በግዕዝ ስለተቀደሰ  የጥንቱን ሥርዓት ላፍርስ፤ በቋንቋዬ አልተቀደሰም ብሎ እንደቄስ በላይ በቤተክርስቲያን ላይ አልተነሳም።
ለዚህም ነው የነ ቄስ በላይ ቡድን «ፈይሳ አዱኛ በአማርኛ መድኀኔ ዓለም  ማለት ነው» በሚል  እያደረጉት ያለው ፖለቲካ የቡድኑ አላማ የኦነጋውያንን ፖለቲካ ማራመድ እንጂ ሃይማኖት ባለጉዳይ አይደለም የምንለው። ኦነጋውያን አጥንታቸው ድረስ የሚጠሉት ከከብት ጥበቃ አውጥቶ ሀርቫርድና የዬል እንዲማሩ በር የከፈተላቸውን አማርኛን ነው። የነቄስ በላይ ፉክክርም ከአማርኛ ጋር ነው። አንድ ቃል አማርኛ ባይሆን እንኳ አማርኛ ነው ብሎ ይነሱበታል።  መድኀኔ ዓለምን አማርኛ ያደረጉት ለፉክክር ስለሚጠቅማቸው እንጂ ግዕዝ መሆኑ ጠፍቷቸው አይደለም። «ፈይሳ አዱኛ» የሚል አዲስ መጠሪያ ያወጡለትን ታቦት ከተለያየ ነገድ የሚወለዱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኞች ለሺህ ዘመናት የመድኀኔ ዓለምን ስም እየጠሩ ከፈጣሬያቸው ጋር ሲገናኙ ኖረዋል። የነ ቄስ በላይ  ፖለቲካ ግን አማርኛ የሚመስላቸውን ነገር ሁሉ ካልቀየርን ሞተን እንገኛለን የሚል የኦነጋውያን እሳቤ  የወለደው የጥላቻ ፖለቲካ  ስለሆነ ከአማርኛ ጋር በማፎካከር ሃይማኖትን ወደ ጥላቻ ፖለቲካ ለወጡት። ሥርዓት መፍጠር እውቀት ስለሚጠይቅና ችሎታው ስለሌላቸው ፖለቲካ አድርገው የያዙት አማርኛ ያልሆነውን አማርኛ ነው እያሉ በመቀናቀን  በመሰላቸው መንገድ መተርጎምን ነው።
እነ ቄስ በላይ ፈይሳ አዱኛ የሚል የታቦት ስም ያወጡት መድኀኔ ዓለም  አማርኛ  ነው ብለው አማርኛ ላለመጠቀም ነው። ሆኖም ግን መድኀኔ ዓለም  ግዕዝ እንጂ አማርኛ አይደለም። የመድኀኔ ዓለም ትርጉም – ሥጋውን ቈርሶ ፡ ደሙን አፍስሶ ፡ ዓለምን ያዳነ ፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ፡ የእግዜር ልጅ ፡ የነፍስ መድኅን ማለት ነው። እነ ቄስ በላይ ግን መድኀኔ ዓለምን አማርኛ አድርገው ፖለቲካቸው ከአማርኛ ጋር መቀናቀን ስለሆነ የኦሮምኛ ትርጉም ያሉትን አወጡ። ገራሚው ነገር ከአማርኛ ለመሸሽ ሲሉ ያወጡት «ፈይሳ አዱኛ» የሚለው ስም ውስጥ ያለው አዱኛ የሚለው ቃል አማርኛ እንጂ ኦሮምኛ  አለመሆኑን አለማወቃቸው ነው። የግዕዙ ሊቅ አለቃ ደስታ ተክለ ወልድ እንደጻፉት  የአዱኛ  የሚለው የአማርኛ ቃል ትርጉም  ዐለም፣ ተድላ ፣ደስታ  ወይም ሀብት ማለት ነው።
እነ ቄስ በላይ ግን ጠባቸው ከአማርኛ ጋር ስለሆነ ወደ ኦሮምኛ ተረጎምን ብለው መድኀኔ ዓለም  የሚለውን የግዕዝ ስም  አማርኛ አድርገው አዱኛ ወደሚል የማይገጥም የአማርኛ ቃል ተረጎሙት። ለመቶ ዓመታት የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታይ ሆኖ የኖረው ኦሮሞ መድኀኔ ዓለም  ማን እንደሆነ ያውቃል።  ፈይሳ አዱኛ ሲባል ግን መድኀኔ ዓለም  የሚለው  ታቦት ወደ አእምሮው ሊመጣ  እንደማይችል  በእርግጠኛነት መናገር ይቻላል። አንዱ ነገ ተነስቶ መድኀኔ ዓለም  ግዕዝ ስለሆነ ወደ አማርኛ ልተርጉም ብሎ መድኀኔ ዓለምን  «የነፍስ መድኅን» ብሎ ቢተረጉምና ታቦት ቢያስቀርጽ  የነፍስ መድኅን የሚለው አዲስ ታቦት  ሲጠራ መድኀኔ ዓለም ወደ ውስጤ ሊመጣ አይችልም። ፈይሳ አዱኛም እንደዚያው ነው።
መድኀኔ ዓለም  የሚለውን የግዕዝ ስም ባይኖር ኖሮ «ፈይሳ አዱኛ» ያሉት ሊኖር አይችልም። መድኀኔ ዓለም  የሚለውን የግዕዝ ስም የተሰራው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ሲሰራ ነው። ሥርዓት ሲሰራ የተሰጠ ስም አይተረጎምም፤ አይለወጥም። የእስልምና ሥርዓት የተሰጣው መሐመድ በሚለው ስም ዙሪያ  ነው።  የክርስትና ሥርዓት የተሰራው እየሱስ በሚለው ስም ዙሪያ  ነው። መሐመድ አረብኛ፤ እየሱስ ኢብራይስጥ ስለሆነ ተብሎ  ክርስትናና እስልምና ስንቀበል  የአማርኛ ወይም የኦሮምኛ ትርጉም  ይውጣላቸውም አልተባለም።  ከወጣላቸው ደግሞ የእስልምናው መሐመድና  ከክርስትናው እየሱስ መሆናቸው ያከትማል። መድኀኔ ዓለምም እንደዚያ ነው።  መድኀኔ ዓለም  በአማርኛ ተተርጉሞ «የነፍስ መድኅን» የሚል ታቦት ሲቀረጽለት፤ በኦሮምኛ ተተረጎመ ተብሎ «ፈይሳ አዱኛ»  ከሆነ መድኀኔ ዓለም  መሆኑ ያበቃል። መድኀኔ ዓለም  ምን ማለት እንደሆነ ማስረዳት ይቻል ይሆናል፤ ሥርዓቱ የተሰራበትን መድኀኔ ዓለምን  እንደነ ቄስ በላይ መተርጎምና ሌላ ስም መስጠት ግን የመሐመድንና የክርስቶስ ስም እንደመተርጎም አይነት በጥላቻ የመናወዝ ድንዛዜ ነው።
Filed in: Amharic