>

የአድዋ ነገር - አፈ ንጉሥ ነሲቡ (ታምሩ ተመስገን)

የአድዋ ነገር – አፈ ንጉሥ ነሲቡ

 

ታምሩ ተመስገን
ወሩ የአድዋ ወር እንደመሆኑ መጠን ጀብዱን ስንዘክር እግረ መንገ’ዳችንን ስለዚያ ዘመን አኗኗር ጥቂት እያልን እንለፍ
….. አፈ ንጉሥ ነሲቡ መስቀሎ (አፈ ንጉሥ ነሲቡ አባተ ምትኩ ቦርጃ) በዳግማዊ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት እጅግ የታፈሩና የተከበሩ ዳኛ ነበሩ፡፡ በአፈ ንጉሥነትም ስልጣን ከ1874 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 1900 ዓ.ም ድረስ 26 ዓመት የቆዩ ናቸው፡፡ በፍርዳቸው ጨካኝና ጠንካራ ስለሆኑ ማንም ሰው በተከሰሰ ጊዜ “እባክህ በነሲቡ ፊት አታቁመኝ” እያለ ከባላጋራው ጋር ይታረቅ ነበር፡፡
.
….. አፈ ንጉሥ ነሲቡ በዳኝነት ስራቸው የተመሰገኑ ሲሆኑ ጉቦ ተቀባይ ናቸው ይባላሉ፡፡ በጉቦ ነገር ከሚተረክባቸውም ውስጥ አንዱን እፅፋለሁ፡፡
በርስት ነገር በርሳቸው ችሎት የሚከራከሩ ሁለት ሰዎች ነበሩ፡፡ አንዱ ቀደም ብሎ ገብቶ የብር ጎቦ ሰጠና ጉዳዩን አመልክቶ ወጣ፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ቀጥሎ ገብቶ በቅሎ ሰጠና ጉዳዩን ተናግሮ ወጣ፡፡ ከዚህ በኋላ ሁለቱም በእርሳቸው ችሎት ቀርበው ከተከራከሩ በኋላ ባለበቅሎው ረታ የብር ጉቦ የሰጠው ተረታ፡፡ በዚህ ጊዜ ያ የተረታው ሰው “ምነዋ ጌታየ ብር ብየ መጥቼ ነግሬዎት አልነበር ወይ” ብሎ የጉቦውን ነገር አሳሰባቸው፡፡ እርሳቸውም ነፍላሌ “አንተ ብር ብለህ ብትመጣ እርሱ መጭ ብሎ ቀደመሃ” ብለው መለሱለት ይባላል፡፡ ይሁን እንጂ ምንም እንኳ ጉቦ ቢበሉም እውነተኛ ፍርድ አያዛቡም ነበር የሚል ታሪክ አላቸው፡፡
.
…. አሁን የምፅፈው አፈ ንጉሥ ነሲቡ በአታላዮችና በሌቦች ላይ ሰርተውት የነበረውን የቅጣት ዓይነት ለመግለጽ ነው፡፡ በዚያ ዘመን በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ አታላዮችና ሌቦች በርክተው ሕዝቡን አስቸገሩ፡፡ ሌባው ተይዞ ሲቀርብ አፈ ንጉስ ነሲቡ በጅራፍ እየገረፉ ይቀጡት ነበር፡፡ ነገር ግን ሌባው ከተገረፈና ከተቀጣ በኋላ እንደገና መስረቁን የማይተው ሆነ፡፡ ስለዚህ አፈ ንጉሥ ነሲቡ ለዳግማዊ ምኒልክ ነግረው አስፈቀዱና ደጋጋሚ የሆነ ሌባ በግምባሩ ላይ አግድም በጋለ ብረት እንዲተኮስና ባለ ምልክት እንዲሆን አደረጉ፡፡ ሐሳባቸውም ሌላው ሰው ምልክቱን አይቶ ሌባ መሆኑን እንዲያውቅና እንዲጠነቀቅ በማለት ነበር፡፡ ሌባው ግን በዚህ አልታገሰም፡፡ የተተኮሰው ግምባሩን እንዳይታይበት ሻሽ እየጠመጠመ ይሄድ ጀመር፡፡ ስርቆቱንና አታላይነቱንም ስለ ቀጠለ እንደገና እየተያዘ ይቀርብላቸው ጀመር፡፡
አፈ ንጉሥ ነሲቡም ይህን በተረዱ ጊዜ ተኮሱ የፊደል “ፐ” ዓይነት እንዲሆን አዘዙ፡፡ ይኸውም ግምባሩን ወደ አግድምና አፍንጫውን ወደ ቁልቁል እንዲተኮስ ማለት ነው፡፡
.
…. በዚያ ዘመን ዳግማዊ ምኒልክ ሌብነትን ለማጥፋት የሚረዳ ስለ መሰላቸው በሌባ ላይ አንድ ደንብ አውጥተው  ነበር፡፡ እርሱም የባርነት ግዴታ በሌባ ላይ እንዲጸና ያወጡት ደንብ ነው፡፡ የደንቡ ቃል እነሆ ከዚህ ቀጥሎ ያለው ነው፡፡
ሞዓ አንበሳ ዘእመነገደ ይሁዳ
ዳግማዊ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጲያ
የሌባ ነገር የተቀጣህልኝ መስሎኝ ከዚህ ቀደም እጅህንም እግርህንም ቆረጥሁ በዥራፍም ገረፍኩ ግንባርህን ተኮስኩ፡፡ አንተ ግን መስረቅህን የማትተው ሆንክ፡፡ ስትሰርቅ የተገኘህ ሌባ ባርያ ሁነህ ትገዛለህ ሌብነትህን ተወኝ፡፡ እንግዲህ ግን በከተማም በባላገርም ሲሰርቅ ባርያም ሲፈነግል ያገኘኸውን ሰው እጁን ይዘህ አምጣልኝ፡፡ ግንባሩን እየተኮኩ  እስከ ልጅ ልጅህ ባርያ አድርገህ እንድትገዛው መርቄ እሰጥሃለሁና እያሰርህ ታሰራዋለህ ::
.
የሐያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ የዘመን ታሪክ ትዝታየ ካየሁትና ከሰማሁት 1896-1922 መርስዔ ኀዘን  ወልደ ቂርቆስ
Filed in: Amharic