>
5:14 pm - Tuesday May 17, 2022

የአስዋን ግድብ የግብጽን ሕይወት እንዳላሠጋው የኢትዮጵያው ግድብም የግብጽን ሕይወት አያሠጋም !!! (ፕ/ሮ ጌታቸው ኃይሌ)  

የአስዋን ግድብ የግብጽን ሕይወት እንዳላሠጋው የኢትዮጵያው ግድብም የግብጽን ሕይወት አያሠጋም !!!

ፕ/ሮ ጌታቸው ኃይሌ  
በዓባይ ወንዝ የመጠቀም ጕዳይ በግብጽና በኢትዮጵያ ማህል አለመስማማትን አስከትሏል። ስለጉዳዩ ብዙ ተጽፏል። ከዚህ በታች ያለው ተጨማሪ ቢሆን አይጎዳም።
ግብጽ የኢትዮጵያ ስጦታ እንደሆነች የታሪክ ጸሐፊው ሄሮዶቱስ በተዘዋዋሪ አነጋገር፥ “Egypt is the gift of the Nile” ብሎ ነግሮናል። ግብጽ የወሰደችው እርምጃ ግን ምስጋና ቢስ የሚያደርጋትን ነው። የምትሰጠው ምክንያት ተቀባይነት የለውም። ምናልባትም ያጣላ ይሆናል። የአስዋን ግድብ መፍረስ የሚያህል አደጋ እያንዣበበባት በጦር ታስፈራራለች። ግድቡ ለድርቅ ዘመን ውሓ እንዲከትላትም ሐሳብ አቅርባለች። ኢትዮጵያ ግድቡን ለመሥራት ያን ያህል ወጪና ጊዜ የሠዋችው የግብጽን ችግር ለማስወገድ አይደለም። ድርቅ ከጥንት ዘመን ጀምሮ የነበረ ነው። በዘመነ ፈርዖን ዮሴፍ ለግብጽ መፍትሔ እንደፈጠረ አሁንም ፈጣሪ እዚያው መፈለግ ይኖራታል። ለምሳሌ ለክፉ ቀን የሚያገለግል ግድብ ልትሠራ ትችላለች።
የኢትዮጵያን ግድብ ግብጽ ላይ ሊያስከትል ይችላል የተባለውን ጥፋት አስቲ ከግብጹ የአስዋን ላዕላይ ግድብ (Aswan High Dam, al-sadd al‘ali) ጋር እናነጻጽረው። የግብጽን ሕይወት በተመለከተ የግብጽ የአስዋን ግድብና የኢትዮጵያው ግድብ ተጽዕኖ መቶ በመቶ ተመሳሳይ ናቸው። የግብጽ የአስዋን ግድብ የግብጽን ሕይወት እንዳላሠጋው የኢትዮጵያው ግድብም የግብጽን ሕይወት አያሠጋም። የአስዋን ግድብ ያላመጣውን የትኛውን አደጋ ነው የኢትዮጵያው ግድብ የሚያመጣው? አንድ ከሆኑ የኢትዮጵያው ግድብ ግብጽን ለምን ያሠጋል? እንደ እውነቱ ከሆነ፥ የኢትዮጵያው ግድን የአስዋን ግድብ ካመጠው አደጋ አንዳቸውንም አያመጣም። የአስዋን ግድብ ኑብያን ግማሽ በግማሽ አስጥሟታል። ለማዳን ዓለም ባይተባበር ኖሮ ብዙ ቅርስ ይወድም ነበር።
የግብጽን ሕይወት ግን አልጎዳም። ስለዚህ ግብጽ ከኢትዮጵያ ጋር ስትነጋገር፥ የአስዋንን ግድብ ስትገነባ እንዴት የግብጽን ሕይወት አንዳይጎዳ አድርጋ እንደገነባችው ዘዴውን ማካፈል ነው። የኢትዮጵያ መንግሥትም፥ ለግብጽ መንገር ያለበት ዓባይ ላይ አንድ ብቻ ሳይሆን ብዙ ግድቦች መሥራት እንደሚቻል ግብጽ አስዋን ላይ የሠራችው ግድብ መመስከሩን ነው።
ግብጽ እንዲከበሩ ከምትጠቅሳቸው ውሎች አንዱ “በግንቦት በ፯ ቀን በ ፲፰፻፺፬ ዓመተ ምሕረት ባዲስ አበባ” የተጻፈው ውል ነው። (“Done at ADIS ABABA, the 15th day of May, 1902.”) የዚህ ውል ሦስተኛው ክፍል፥ እንደ ውጫሌው ውል ኢትዮጵያን የሚነክስበት ጥርስ የለውም። ልእንግሊዝኛው፥ “His Majesty the Emperor MENEKEK II, King of Kings of Ethiopia, engages himself towards the Government of His Britannic Majesty not to construct or allow to be constructed any work across the Blue Nile, Lake Tsana or the Sobat, which would arrest the flow of their waters into the Nile except in agreement with His Britannic Majesty’s Government and the Government of the Soudan.” ሲል፥ አማርኛው የሚለው እንዲህ ነው፤ “ጃንሆይ፡ ዳግማዊ፡ ምኒልክ፡ ንጉሠ፡ ነገሥት፡ ዘኢትዮጵያ፡ ከጥቁር፡ ዓባይና፡ ከባሕረ፡ ፃና፡ ከሶባት፡ ወንዝ፡ ወደነጭ፡ ዓባይ፡ የሚወርደውን፡ ውሀ፡ ከእንግሊዝ፡ መንግሥት፡ ጋራ፡ አስቀድሞ፡ ሳይስማሙ፡ ወንዝ፡ ተዳር፡ እዳር፡ የሚደፍን፡ ሥራ፡ እንዳይሰሩ። ወይም፡ ወንዝ፡ የሚያፍን፡ ሥራ፡ ለማሠራት፡ ለማንም፡ ፈቃድ፡ እንዳይሰጡ፡ በዚህ፡ ውል፡ አድርገዋል።”
እኛ የምናቀው አማርኛውን ስለሆነ፥  ውሉ ኃይል ሊኖረው የሚችለው፥ አማርኛው እንደሚለው፥ ድርድሩ  በኢትዮጵያና በእንግሊዝ መንግሥት ሲሆን ነው። ውሉ ሱዳንንና ግብጽን የሚያስገባቸው በር የለበትም። ከእንግሊዝ መንግሥትም ጋር ቢሆን፥ “ሳይስማሙ” ይላል እንጂ እንግሊዝ ላለመስማማት መብት አላት አይልም። “ካልተስማሙ” አይልም። ያም ሆነ ይህ፥ እንግሊዝ አሁን በአካባቢው ድራሿ የለም። ውሉም አብሯት ድራሹ ጠፍቷል። አፄ ምኒልክም ይኸን ውል የተዋዋሉት፥ ኢትዮጵያ ዓባይን ለመገደብ አቅም እስኪኖራት እንግሊዝ እዚህ እንደማትቆይ ስላወቁ ነው። ለምሳሌ፥ ኢትዮጵያ ለብሪታንያና ለሱዳን መንግሥት አንድ የንግድ ቦታ ስታውስ፥ ስለተውሶው  በአራተኛው አንቀጽ የተጻፈው ውል ፥ ውሉ የሚጸናው፥ “የእንግሊዝ መንግሥት  ሱዳንን እስኪለቅ ድረስ” ነው ይላል። አንቀጹ እንግሊዝ አካባቢውን  የምትለቅበት ጊዜ እንደሚመጣ ማወቃችንን ይመሰክራል።
ዓባይን “ጥቁር፡ ዓባይ” ያሉት የእንግሊዝኛውን “Blue Nile” ተርጕመው ነው። “ሰማያዊ ዓባይ” ያላሉት በኦሮምኛ “ቢሻን ጉራቻ” የሚል ስላለን ነው።
ዓባይ የሚያልፍባቸውን ሀገሮች ሊያስተሳስር ሲገባው እያቃቃራቸው ነው። ግብጽ ኢትዮጵያን ከማስፈራራት ደርሳለች። የኢትዮጵያ አየር ኀይል የዛሬ ኀይሉ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የነበረው እንዳልሆነ ብትገምት ነው እንጂ፥ ከገጸ ምድር ሊያጠፋት የሚችለውን የአስዋንን ግድብ ታቅፋ እንዲህ ያለ ሞኝነት አታሰማም ነበር።
ሁለቱን ሀገሮች የሚያጣላው ጉዳይ ባልተነሣበት በአሁኑ ጊዜ የሚጣሉት በማያጣላ ጉዳይ ላይ ነው። ሊያጣላ የሚችለው ኢትዮጵያ ውሐውን ለመስኖ የምትፈልግበት ጊዜ ሲመጣ ነው። እንዳነበብኩት ከሆነ ግን፥ አሁን ያልተግባቡት ኢትዮጵያ ግድቡን ለመሙላት በሚያስፈልጋት ጊዜ ላይ ነው። ግብጽ የምትለው ግድቡ ጊዜ ፈጅቶ ቀስ እያለ ቢሞላ፥ እስኪሞላ ድረስ ወደ ግብጽ የሚወርደው ውሐ መቀነሱ ግብጽን አይጐዳትም ነው። ኢትዮጵያ የምትለው የግድቡን መሙላት ካዘገየነው በማዘግያው ዘመን የማገኘው ጥቅም ይቀርብኛል ነው።
ይጠቅሙ የሚመስሉኝን ሁለት መፍትሔዎች ላቅርብ፤ አንደኛ፥ ግብጽ ለመቶ ዓመት የሚበቃት ውሐ ከመሬት በታች እንዳላት ይነገራል። ግድቡ እስኪሞላ ድረስ ትጠቀምበት። ከኢትዮጵያ ጋር በመነታረክና አስታራቂ በመፈልግ የምታጠፋውን ጊዜ ቁፋሮ ላይ ታውለው።
ተቀባይነት ሊኖረው የሚችለው ሁለተኛው መፍትሔ ነው፤ ግድቡን ለመሙላት የሚፈጀው ጊዜ ሊራዘም ይችላል። ከተራዘመ፥ መራዘም ምክንያት ኢትዮጵያ የምታጣውን ገቢ ግብጽ ትክፈል። የሚረዷት ሀብታም ወዳጅ የዐረብ አገሮች ረዳት አሏት። ለማስታረቅ የሚጋበዙትም ታላላቅ አገሮች ቢጠየቁ ሊረዱ ይችላሉ።
Filed in: Amharic