>
5:13 pm - Saturday April 19, 1169

ግብፅ በናይል ድርድር ላይ እየሄደችበት ያለው የተጠና ጉዞና መዳረሻው [ተስፋዬ ታፈሰ (ፕሮፌሰር)]

ግብፅ በናይል ድርድር ላይ እየሄደችበት ያለው የተጠና ጉዞና መዳረሻው

 

ተስፋዬ ታፈሰ (ፕሮፌሰር)

 

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የአፍሪካና ኦሪየንታል ጥናትና ምርምር ተቋም የጂኦፖሊቲክስና የአፍሪካ ጥናት ፕሮፌሰር

 

ባለፈው ፅሑፌ ግብፅ በናይል ድርድር ላይ እየሄደችበት ያለው በጥያቄ መልክ ያነሳህዋቸው ነጥቦች ላይ ተመሰርቼ አሁን እዚህ አዲስ አበባ ላይ ሦስቱ የናይል ተፋሰስ አገሮች (ግብፅ፣ ኢትዮጵያና ሱዳን) ከታህሣሥ 29 እስከ 30፣ 2012 ዓ.ም አራተኛውና የመጨረሻ የሚባለውን ስብሰባ አድርገው ካለምንም ስምምነት ከተበተኑበት መንፈስ ጋር በማያያዝ ሃሳቤን ለማጋራት በማሰብ ነው ይቺን አጭር ፅሑፍ ለመፃፍ የወሰንኩት፡፡

በኔ ግምት የግብፁ ፕሬዚደንት አልሲሲ የአሜሪካኑን ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕን ከኢትዮጵያ ጋር አማልዱኝ ባሉበት ጊዜ ፈጣኑ የሦስትዮሽ ውይይት በመጨረሻ ካለስምምነት እንደሚጠናቀቅ ያውቁ ነበር እንዲሆንም በደንብ ሰርተውበታል፡፡ የግብፆች አላማ ይህ መሆኑን ለማስረዳት ብዙ ሳንሄድ ባሁኑ ስብሰባ ያቀረቡትን ጥያቄ ማንሳቱ በቂ ይመስለኛል፡- ኢትዮጵያ የሕዳሴውን ግድብ የምትሞላበት ጊዜ ከ 12 – 21 ዓመታት መሆን አለበት ሲሉ ላለመስማማት የመጡ ብቻ ሳይሆን ንቀታቸው የደረሰበትንም ጠርዝ ወለል አድርጎ ያሳያል፣ አልያም ‘ጌታዋን የተማመነች በግ ላትዋን ከደጅ ታሳድራለች’ እንዲሉ የተማመኑበት ነገር ሊኖር ይችላል ብሎ መገመት ይቻላል፡፡ 

ያም ሆነ ይህ በአሜሪካኖች አማላጅነት ከጥቅምት ወር ጀምሮ ላለፉት አራት ወራት የተካሄዱት ድርድሮች ማጠቃለያቸውን የሚያገኙት በሚቀጥለው ሳምንት ዋሺንግተን ዲሲ በሚካሄደው የመጨረሻ ስብሰባ ነው፡፡ በዚሁ በአሜሪካ ሸምጋይነት በአዲስ መልክ በተቀረፀው የድርድር ውል መሰረት ሦስቱ የናይል ተፋሰስ አገሮች እስከ ጃንዋሪ 15፣ 2020 ድረስ ስምምነት ላይ መድረስ ካልቻሉ እ.አ.አ በ ማርች 2015 የተፈራረሙት ‘ዲክላሬሽን ኦፍ ፕሪንስፕልስ’ (Declaration of Principles) ዉስጥ የተካተተው አንቀፅ 10 ስራ ላይ ይውላል ይላል፡፡ አንቀፅ 10 የሚለው፡- “If the parties involved do not succeed in solving the dispute through talks or negotiations, they can ask for mediation or refer the matter to their heads of states or prime ministers”. ይህ በአማርኛ ሲተረጎም፡- “የተፋሰሱ አገሮች ስምምነት ላይ መድረስ ካልቻሉ አሸማጋይ መጠየቅ ይችላሉ ወይንም ጉዳዩን በርዕሰ ብሔሮቻቸው ወይንም በጠቅላይ ሚኒስትሮቻቸው እንዲታይላቸው ይመራሉ” ነው የሚለው፤

በሚቀጥለው ሳምንት በዋሺንግተን ዲሲ ከተማ ከሚካሄደው ስብሰባ ምን መጠበቅ ይቻላል የሚለው የሁሉም ሰው ጥያቄ የሚሆን ይመስለኛል፡፡ ግብፅ የሕዳሴው ግድብ የሙሊት ጊዜ ከ 12 እስከ 21 ዓመታት የሚደርስ መሆን አለበት ብላ ያቀረበችውን አዲስ ሃሳብ የኢትዮጲያ ተደራዳሪዎች/ልዑካን፣ የውጭጉዳይ ሚኒሰትራችንም ሆኑ ጠቅላይ ሚኒሰትራችን ይስማሙበታል ብዬ ለሰከንድም ማስብ ይከብደኛል ቢያንስ በሦስት መሰረታዊ ምክንያቶች፡- (ሀ) መጠነ ሰፊ የኢትዮጲያ አንጡራ ኃብት የተከሰከሰበት ግድብ ሉዓላዊነታችንን በሚፈታተን መንገድ በሌሎች ኃይሎች ይሁንታ ስር መውደቅን ስለሚያመጣ (ለ) በግብፅ ዕቅድ መስረት ሙሊቱ ከተካሄደ የሕዳሴው ግድብ ለረዥም ዓመታት ስራውን ከዓቅም በታች ስለሚያከናውን ተርባይኖቹ፣ ማሺነሪዎቹ፣ ብረታብረቶቹ ባጠቃላይ መሠረተ ልማቱ ባለመንቀሳቀስ ለሚመጣ ዝገት (corrosion) እንዲሁም በግልጋሎት ማነስ ለሚመጣ ብልሽት (wear out) ስለሚጋለጥ (ሐ) የውኃ አሞላሉ በከፍተኛ ሁኔታ መዘግየት፣ ግብፅ በድርቅ ወቅት ይህን ያህል ልቀቁ፣ ኢትዮጵያ ከግድቡ ቢያንስ 40 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር በዓመት ውኃ መልቀቅ አለባት ወዘተ ከምትላቸው አስገዳጅ ሃሳቦች ጋር ሲደመር የሕዳሴው ግድብ በ13 ተርባይኖች ታግዞ 6400 ሜጋዋት ኃይል ያመነጫል ብሎ ለማስብ ስለሚከብድ፡፡

አንዳንድ ፀሐፊዎች የሚሉትና እኔም ይሆናል ብዬ የምገምተው ግብፅ፣ የአሜሪካ ገንዘብ ሚኒስቴር (Treasury Secretary) እና የዓለም ባንክ በሚቀጥለው ሳምንት ስብሰባ የቢዝነስ ፕሮፖዛል (Business Proposal) ይዘው ይቀርባሉ የሚል ነው፡፡ ይኸውም ግብፅ ያቀረበችው አዲሱ የውኃ ሙሊት የጊዜ ሰሌዳ (ከ12 እስከ 21 ዓመታት) ተግባራዊ እንዲሆን ኢትዮጵያ ልታጣ የምትችለውን በዓመት ከ 1 እስከ 1.5 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ለመካስ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይህ ምን ሊሆን እንደሚችል ለማሳየት ትንሽ ስሌት ማስላት ይቻላል፤ ኢትዮጵያ ከ4 እስከ 5 ዓመታት ባለው ጊዜ ውስጥ ግድቡን እሞላዋለሁ የሚል ዕቅድዋን ለግብፅ አዲሱ ፕላን አስገዝታ ከ12 እስከ 21 ዓመታት ካደረገች የሕዳሴውን ግድብ ውኃ አሞላል ከ4 እሰከ 5 ጊዜ እጥፍ ያራዝመዋል፡፡ ኢትዮጵያ ያቀረበችውን የውኃ ሙሊት ስሌዳ መነሻ አድርገን የግብፅ አዲሱ የሙሊት ፕላን ተግባራዊ ቢደርግ ከ 8 እሰከ 16 ዓመታት ጊዜ የሚዘገየውን የውኃ ማከማቸት ለማካካስ በዓመት በ 1.25 ቢሊዮን ዶላር አባዝተው ከ 10 አስከ 20 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ በጊዜ በተገደበ ተከታታይ ክፍያ (በ installment መልክ) ለመስጠት ሊዘጋጁ ይችላሉ፡፡ 

እንደኔ ከላይ በተዘረዘረው ሃሳብና ስልት መስማማት ማለት እስካሁን አገራችን ስትከተለው ከነበረው መርህ መራቅ ብቻ ሳይሆን የሕዳሴውን ግድብ ፍፃሜ በጉጉት ለሚጠብቀው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ የኤልክትሪክ ኃይል ከኢትዮጵያ በተመጣጣኝ ዋጋ እናገኛለን ብለው በተስፋ ሲጠባበቁ ለነበሩ የጎረቤት አገሮች እንዲሁም የናይልን ዉኃ አጠቃቀም ሚዛናዊና ፍትኃዊ ለማድረግ ሌት ተቀን ለለፉት የተፋሰሱ አገሮችና ግለሰቦች አንገት የሚያስደፋ ውሳኔ ወይንም እርምጃ ይሆናል፡፡ እንደኔ ሃሳብ ግብፅ ተስማማች አልተስማማች፣ የአሜሪካው ትሬዠሪ ሴክሬታሪ እና የዓለም ባንክ እራሳቸው ወይንም በግብፅ በኩል የገንዘብ ካሳ አቀረቡ አላቀርቡ ኢትዮጵያ ባወጣችው የግድቡ ውኃ ማከማቻ ሙሊት ሰሌዳ መሰረት ተንቀሳቅሳ በዕቅድዋ መሰረት ውኃ ማከማቸቱን በመጪው ክረምት (2012 ዓ.ም) በመጀመር ከሦስት ወራት በኋላ በታህሣሥ ወር 2013 ዓ.ም ከአሥራሦስቱ የህዳሴው ግድብ የኃይል ማመንጫ ተርባይኖች ሁለቱ ኃይል ማምረት እንዲጀምሩ ማድረግ አለባት ነው የምለው፡፡  

ለፀሐፊው አስተያየት ለመስጠት ወይንም ጥያቄ ለማቅረብ ይህንን ኢሜይል አድራሻ መጠቀም ይችላሉ፡- tesfayeidr@yahoo.com

Filed in: Amharic