>
8:04 am - Tuesday December 6, 2022

የአምባላጌ ውጊያ ወደ አድዋ ዉጊያ ጥርጊያ መንገድ!!! [በክቡር መተኪያ ሃይለሚካኤል]

የአምባላጌ ውጊያ ወደ አድዋ ዉጊያ ጥርጊያ መንገድ!!!

[በክቡር መተኪያ ሃይለሚካኤል]
~
ጥቁር ህዝቦች የአውሮፓን ውጊያ ለመጀመሪያ ግዜ በተደራጀ መልኩ በከባድ ውጊያ ያሸነፉበት እየተባለ በስፋት የሚነገርለት የአድዋ ድል የካቲት 23 ቀን 1888 ከመካሄዱ ከጥቂት ወራት ቀደም ብሎ አንዲት አምባላጌ በተሰኘች ቦታ ላይ ከባድ ውጊያ ተደርጎ ነበር::አምባ አላጌ በስተሰሜን ኢትዮጵያ የምትገኝ በዛሬዋ ደቡባዊ ትግራይ ክልል ያለች ተራራማ ስፍራ ነች::
 “በኢትዮጵያና በሻእቢያ ወታደሮች ውጊያ ግዜ የናቅፋ ተራራ ተፈጥሯዊ ምሽግ ሆኖ አገልግሏል” ተብሎ እንደተነገረው ሁሉ ሽቅብ ሲመለከቱት አንገትን የሚቆለምመው የአላጌው አምባን ተፈጥሯዊ ምሽግነቱን(በወታደራዊ አገላለጽ ደግሞ ስትራቴጂክ ጠቀሜታው ወይም ገዢ መሬትነቱን) አይቶና ገምግሞ ነበር ወራሪው የጠላት ሰራዊት በጦር ሰፈርነትና በተጠናከረ ምሽግነት የመረጠው::
የአምባላጌ ውጊያ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በታህሳስ 7 ቀን 1888 ዓ.ም ነበር የተካሄደው::በኢትዮጵያ በኩል የውጊያው መሪ የአጼ ምኒልክ የስጋ ዘመድ (የእህትና ወንድም ልጆች ናቸው) የቀዳማዊ ሃይለስላሴ ወላጅ አባት ራሰ መኮንን የጦሩ መሪ:የልጅ እያሱ አባት ራስ ሚካኤል: የትግራይና ወሎ ገዥና የአጼ ዮሃንስ ልጅ ራስ መንገሻ :ፊት አውራሪ ገበየሁ እንዲሁም፣ የእቴጌ ጣይቱ ወንድም ራስ ወሌ ብጡል ራሳቸው ጦራቸውን እየመሩ የተሳተፉበት ከባድ ውጊያ ነበር::
በጣልያን በኩል ጦርነቱን የሚመራውና ተራራማውን የአምባላጌ ምሽግን ደጀን አድርጎ የተቀመጠው ሻለቃ ፔድሮ ቶዞሊ (በአንዳንድ ጸሃፍት አባባል ማጆር ቶዞሊ)ነበር::በነገራችን ላይ ጦርነቱ ከመጀመሩ አስቀድሞ የጦሩ አዛዥ ራስ መኮንን ለሻለቃ ፔድሮ ቶዞሊ የጦርነት አይበጀንም ደብዳቤ ጽፈው እንደነበር አንዳንድ ታሪክ ጸሃፍት ይናገራሉ::ራስ መኮንን ቀደም ሲል ለሻለቃ ቶዞሊ የበላይ አዛዥ ለነበረው ለጀነራል ኦሬስቴ ባራቴሪ የጻፉት የሰላም ጥሪ ደብዳቤ ምላሽ እንዳላገኘ በመጥቀስ ነበር ደብዳቤያቸው የሚጀምረው::
ራስ መኮንን ለጦርነቱ ተዘጋጅተው እዛው አምባላጌ ድረስ መምጣታቸውን ሆኖም ግን ደም አፋሳሽ ውጊያዎችን እንደማይፈልጉና ጉዳያቸውን በሰላም መፍታት ቢችሉ ምርጫቸው እንደሆነ በጦማራቸው ላይ ካሳወቁ በኋላ ዝቅ ብለው “ካምፕህን ለቀህ ብታፈገፍግ ምክሬ ነው”ብለው ይጠቅሱና በጎ ምላሹን እንደሚጠብቁ ተስፋ እንዳላቸው አያይዘው ተናግረው ነበር::ሆኖም በያዘው ስትራቴጂክ ቦታና በዘመናዊ የጦር መሳሪያ የተማመነው ሻለቃ ፔድሮ ቶዜሊ የቋመጠበትን ጦርነት እየተቁነጠነጠ ይጠብቅ ጀመር::
ጸሃፍት በአምባላጌው ውጊያ 30000 የኢትዮጵያ ወታደሮች እንደተሰለፉ ይጠቅሳሉ::ይሄም እጅግ ሁዋላ ቀር የሆኑትን ቤልጂግ: አልቤንና ናስማሰር ጠመንጃ ያነገቡትን ብሎም ለጨበጣ ውጊያ ካልሆነ ለመስክ ውጊያ የማይሆኑትን ጦር ጋሻና ጎራዴ ይዘው የተሰለፉትን ወዶ ዘማቾች ያካትታል::በኢጣልያኖች በኩል ደግሞ በእጅጉ የሰለጠነ በበርካታ አውደ ውጊያዎች የተፈተነና እስከ አፍንጫው የታጠቀ እንዲሁም በዋናነት ገዥ መሬትን (አምባ) የተቆናጠጠ 2350 ወታደሮች ለውጊያ ተዘጋጅተዋል::
ጣልያኖች ስትራቴጂክ ጠቀሜታ ያላትን ኮረብታማዋን አምባላጌን ይዘው እየተጠባበቁ ሳለ ድንገት የፊታውራሪ ገበየሁ ጦር ያገጠጠውን ገደል በጥፍሩ እየቧጠጠ አንዱ ወታደር የሌላውን እጅ እየያዘና ጨለማውን በደጀንነት እየተጠቀመ ከነሻለቃ ቶዞሊ ምሽግ ግርጌ ደረሰ::የጦርነቱን መጀመር እየተቁነጠነጠ ሲጠባበቅ የነበረው የጣልያን ጦርም መትረየስና መድፉን ያንፈቀፍቀው ጀመር::ምድር ቁና ሆነች::የከባድ መሳሪያና የመትረየስ ተኩስ ተፈርቶ የነበረውን የአምባላጌን ውጊያ ማስጀመሪያ ፊሽካ ሆነ::
የተኩሱን ድምጽ የሰማው የነ ራስ ወሌ የነ ራስ መንገሻና የነ ራስ ሚካኤል ጦር ከፊት ከፊታውራሪ ገበየሁ ጋር ሲጠዛጠዝ የነበረውን የጣልያን ጦር ከኋላው በከበባ ገብተው መግቢያና መውጫ ማሳጣት ጀመሩ::ባልገመተው መልኩ የተጠለፈው የጣልያን ጦር የያዘው መትረየስና አውቶማቲክ ጠመንጃ እንደማያድነው ሲያውቅ ማፈግፈግ ጀመረ::ምንም እንኳ የወገን ጦር በዘመናዊ የነብስ ወከፍ መሳሪያ ያልተደራጀና በመደበኛ መልኩ ያልሰለጠነ የፋኖ ሰራዊት ቢሆንም የሞተው ሞቶ የወደቀው ወድቆ በመሸሽ ሊያመልጥ ካልቻለውና ጥይት ከጨረሰው የጣልያን ጦር ጋር በጨበጣ ውጊያ መከታተት ጀመረ::
ይሄኛው የውጊያ አይነትም ለኢትዮጵያዊያኑ ወታደሮች እጅግ የተመቸ የውጊያ አይነት ሆኖ ተገኘ::በዚህ ላይ የቀኙን ረድፍ ይዞ ሲዋጋ የነበረው የራስ አሉላና የራስ መንገሻ ጦር በዚህ ቀውጢ ሰአት የወገን ጦርን ለመርዳት በነብስ ደረሰ::
ከዚህ በኋላ የሆነውን ነገር በምርኮ ወደ አዲስ አበባ የተወሰዱ የጣልያን ወታደሮችና በአውደ ውጊያው ላይ የተሳተፉ አርበኞች እንዲሁም ታሪክ ጸሃፍት እንደነገሩን ነገር ቢኖር አንድ ሰአት ባልሞላ ግዜ ውስጥ ያ ከሰሜን እስከ ምስራቅ አፍሪካ ድረስ የቅኝ ግዛቱን ቀንበር በአፍሪካዊያን ወንድሞቻችን ላይ ጭኖ አስፈሪነትንና ስመ ገናናነትን አትርፎ የነበረው የጣልያን ጦር እንደ ሃሞት የመረረ እንደ ኮምጣጤ የጎመዘዘ የሽንፈቷን ጽዋ መጎንጨቱን ነው::
የጣልያን ወታደሮች ጥቂቶች ሸሽተው ሲያመልጡና ሲማረኩ አብዛኛዎቹ ተደመሰሱ::የቀሩትም እስከ 400 ሜትር ይደርሳል የሚባለው ገደል ውስጥ(የጦር መሪውን ሻለቃ ፔድሮ ቶዞሊን ጨምሮ)የአርበኞችን ጥይት ሲሸሹ ገብተው ሞቱ::
የቅድመ አድዋ ጦርነት በነበረው በዚህ በአምባላጌ ውጊያ ሌላው እጅግ የማይረሳው በጣልያን ገበርዲን ጨርቅና ሊሬ ተታለው ለጣልያን ያደሩ የነበሩ የሰሜን ባንዳዎች ጉዳይ ነበር::ይህ በክፉ የሚታወስ የወገንን ጦር በእጅጉ ያሳዘነ ጉዳይ ሆኖ ዛሬም ድረስ ይነገራል::በዚህ በአምባላጌው ውጊያም ላይ የግራና የቀኝ ክንፍ በመሆን የሻለቃ ፔድሮ ቶዞሊን ጦር አጅበው የነበሩት ሁለቱ ባንዳዎች “ሼህ ጧላ” እና “ራስ ስብሃት” ናቸው::እነዚህ ባንዳዎች በአውደ ውጊያ የተሳተፉ የመጀመሪያ ባንዳዎች አድርጎ ታሪክ መዝግቧቸዋል::ጣልያን ባንዶቹ የትግሪኛ ተናጋሪ ስለነበሩ “ሃገሬውን ያግባቡልኛል” ብሎ ተስፋ ጥሎ የነበረ ቢሆንም ከሽንፈት አላዳኑትም::እነዚህ የጣልያን ጦር መሪ የነበረው ቶለንቲን እንደ ጌታ ያዩ የነበሩ ባንዶች “ቶለንቲኒ ጌታዬ ሆይ”(ጎይታ ቶለንቲኒ)እያሉ ይሰግዱለት እንደነበር የተገኙ ሰነዶች አረጋግጠዋል::የነዚህን የሰሜን ባንዶች ዝክረ ነገር ዝነኛው ጋዜጠኛው ጳውሎስ ኞኞ በ “አጼ ምኒልክ” መጽሃፉ የሚከተለውን ብሎ ነበር::
“በፊታውራሪ ገበየሁ አበጋዝነት የሚመራው የኢትዮጵያ ሰራዊት አምባላጌ ደረሰ:: ከራስ መንገሻና ከራስ አሉላ ጋር ተጣልተው ለኢጣልያ ገብተው የነበሩት ራስ ስብሃት 350 ዘመናዊ ጠመንጃ ከኢጣልያ ተቀብለው ፋላጋ ኮረብታ ላይ እንዲሆኑ የአምባላጌው ጦር አዛዥ ቶዚሊ አዟቸው መሽገዋል::” በማለት ትረካውን ይጀምራል::ከዚያም… “በስተቀኝ በመቶ አለቃ ቮልፒቺሊ የሚመራው ጦር በሱጎን ደግሞ ቶጉራ ኮረብታ ላይ ከኢትዮጵያ ከድቶ ለኢጣልያ የገባው ሼህ ጧላ 350 ዘመናዊ ጦር ይዞ ለጣልያን ጦር ሊዋጋ መሽጓል”በማለት ያስታውሰናል::
በዚህ ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ተከላካይ አርበኞች መሞታቸውም እሙን ነው::በተለይ በዚህ በሞቱ ኢትዮጵያዊያን አርበኞች የቀብር ስነስረአት ላይ ሃዘኑና ቁጭቱ ከፍ ብሎ በነበረበት ግዜ ላይ የጦሩ መሪ ራስ መኮንን አብዝቶ ማዘን እጅግ ተገቢ እንዳልሆነና እንዲያውም ሊጽናኑ እንደሚገባ ጠቅሰው ለሃገርና ለንጉስ መሞት ክብር መሆኑን አበክረው በመግለጽ ለንጉሰ ነገስቱ እጅግ ጥልቅ ፍቅር የነበራቸውን ወታደሮች ሲያጽናኑ እንዳመሹ የጦር ሜዳ ውሏቸውን ከትበው የነበሩ አርበኞች ይናገራሉ::
በዚህ ውጊያ ላይ ታላቅ ጀብድ የፈጸሙት ፊት አውራሪ ገበየሁ ከጦርነቱ በፊት ተናግረውት የነበረው ነገር እጅግ አስገራሚና ወኔ ቀስቃሽ ንግግር ምን ያክል ለሃገራቸው ነብሳቸውን ለመገበር ደማቸውን ለማፍሰስ አጥንታቸውንም ለመከስከስ ተዘጋጅተው እንደነበርና ለዚያም ደስተኛ እንደነበሩ ጥሩ ማሳያ ነው::ፊት አውራሪ ገበየሁ በጦርነቱ ለሃገራቸው ከሞቱ ደስተኛ እንደሚሆኑ: ጥይቱ ግንባራቸውን ወይም ደረታቸውን ከመታ በጀግንነት ሲዋጉ ስለመሞታቸው ማረጋገጫ እንደሆነና በክብር እንዲቀብሯቸው እንደሚፈልጉ ገልጸው ሲሸሹ ጥይት ጀርባቸውን መትቶ ከገደላቸው ግን ስጋቸውን ለአሞራ እንዲሰጥላቸው ተናዘው እንደነበር ይነገራል::
ስለ ገበየሁ ጀግንነት በአንድ ወቅት የጠላት ጦር ቤተ ክርስትያንን እንደ ምሽግ ተጠቅሞ ከነ ቦት ጫማው መቅደስ ውስጥ ዘው ብሎ ስለመግባቱ የሃገሬው ሰው
የአድዋ ሥላሴን ጠላት አረከሰው
ገበየሁ በሞቴ ግባና ቀድሰው፤
በማለት እባክህ ናና ጠላትን ከቤተ ክርስትያናችን አባርልን ሲል ምኞቱን በስነ ቃል ተማጽኖውን አሰምቷል::
የዚህ ጦርነት ውጤትን በገደምዳሜ ስንመለከት የኢትዮጵያዊያንን ጀግንነት እጅግ በሳል የሆነ የጦር ስልት ነዳፊነት በሃገር ጉዳይ አንድነትን ሲያሳይ በጣልያን በኩል ደግሞ ፍትሃዊ ጦርነት ያለማድረጉን ጠቁሞት ከማለፍ ባሻገር የወቅቱን የጣልያን ጠቅላይ ሚኒስቴር ክሪስፒ ተጨማሪ በርካታ ሚሊየን ሊሬዎችን በተጨማሪነት በምስራቅ አፍርካ ለሰፈረው ጦር ድጎማ ማድረግ እንደሚገባው ጠቁሞት አልፏል::
ክብር በደምና በአጥንታቸው ሃገራችንን ምሶሶና ማገር በመሆን በነጻነት ላኖሩን ለጀግኖች አባቶቻችን ይሁን!!
Filed in: Amharic