>
8:18 am - Saturday November 26, 2022

እንደ አበጀ በለው...!!!  (እንዳለጌታ ከበደ)           

እንደ አበጀ በለው…!!!

  (እንዳለጌታ ከበደ) 
በኢትዮጵያ የሥነ-ጽሑፍ  ታሪክ ውስጥ የሀዲስ አለማየሁ (ከአ.አ. ዩኒቨርስቲ የክብር ዶክትሬት ያገኙ) ተወዳጅ  ድርሰት የሆነው፣ ‹ፍቅር እስከ መቃብር› በይዘትም በቅርጽም በብዙ መንገድ ሲተነተን የቆየና የሚቆይ ልቦለድ ነው፡፡
እንደሚታወቀው ‹ፍቅር እስከ መቃብር›፣ እስከ መቃብር ስለዘለቀ ፍቅር ነው የሚተርከው፡፡ ልቦለዱ ውስጥ ብዙ የፍቅር ዓይነት አለ፡፡ እነዚህ የፍቅር ዓይነቶች ደግሞ አቀንቃኞች አሉዋቸው – ደቀ- መዛሙርት፡፡ እንደ እኔ እምነት ደራሲው ‹ፍቅር እስከ መቃብር› ያሉት የበዛብህንና የሰብለን ፍቅር እስከ መጨረሻ ድረስ እንደ ዘለቀ ለማሳየት ብቻ አይመስለኝም፡፡ ቦጋለ መብራቱ ከውድነሽ በጣሙ ጋር፣ ጉዱ ካሳ ከእንቆዝዮን ጋር፣ ፊታውራሪ መሸሻ ከወይዘሮ ጥሩ ዓይነት ጋር ያላቸው ፍቅር እስከ መቃብር ዘልቋል፡፡ ከጾታዊ ፍቅር ውጪም፣ ጉዱ ካሳ ለአቋሙ/ ለእውነቱ/ለነጻነቱ እስከ መቃብር ድረስ ሞቷል፡፡ ፊታውራሪ መሸሻም ለሥርዓቱ ያላቸው ፍቅር እስከ መቃብር ድረስ ሸኝቷቸዋል፡፡ ሌላም ሌላ…
ያም ሆኖ፣ ልቦለዱን ያነበቡ – ብዙዎች ማለት ይቻላል – በዓዕምሮአቸው ተቀርጾ የሚቀረው የበዛብህና የሰብለ ወንጌል ትራጀዲ የፍቅር ትረካ እንጂ የአበጀ በለው ጀብዱ አይመስለኝም፡፡
በሁለቱ መካከል ደግሞ ሰፊ የሆነ የባህርይ ልዩነት አለ፡፡ ውሏቸውም ኑሮቸውም ለየቅል ነው፡፡ በዛብህ ይበልጥ የሚታዘንለትና ሊረዱት የሚፈልጉት ዓይነት ሰው ነው፡፡ ‹የሥዕለት ልጅ› ተብሎ በመሰሎቹ የተሰደበ፣ ወላጆቹ ሕይወቱን ያጨለሙበት የሚመስለው፣ የወላጆቹ መሞት ከታሰረበት የሥዕለት ልጅነት ነጻ የመውጣት ስሜት የፈጠረበት ሰው ነው፡፡ ያፈቀራት ሰብለወንጌልም ‹አጥንቷ የከበረ› ነውና የፊታውራሪ ልጅነቷ ዕዳ የሆነባት፣ እንደ መሰሎቿ ሌሎች ሲኖሩ የመመልከት ዕጣ ፈንታ የገጠማት የሚታዘንላት ምስኪን አፍቃሪ-ተፈቃሪ ናት፡፡ አበጀ ግን የተለየ ሰው ነው፡፡ ‹አበጀህ!› የሚያስብሉ ጀብዱዎችን የፈጸመና የተበዳይ ጠበቃ ነው፡፡ የበለው ልጅ ነው፡፡ በለው ካለ በለው ነው፡፡ አገር የሚዘፍንለት ሰው ነው፡፡ እሱ በዞረበት አደባባይ ፍትሕ ዕርቃንዋን ስትሄድ ካየ አልባሽዋ እሱ ነው፡፡
ባላገርም፣ (ገጽ 235) እንዲህም ብሎ አሞካሽቶታል፡፡     
       
‹አየ! ምን፡ ያደርጋል፡ በከንቱ፡ መመኘት፡ የማይገኝ፡ ነገር፡-
ባይሆንማ፡ ኖሮ፡ ሹመት፡ እንደ፡ ቂጥኝ፡ የሚወረስ፡ ከዘር፡-
ቅን፡ ፍርድ፡ ለመስጠት፡ ሕዝብ፡ ለማስተዳደር
የያንዳንዱን፡ ደሃ፡ መብት፡ ለማስከበር፡ ለዚህ፡ ለተጠቃ፡ ለተበደለ፡ አገር፡-
መድኃኒት፡ እንዲሆን፡ እሱን፡ መሾም፡ ነበር፡›
ፍቅር እስከ መቃብር›፡- ትንቢታዊ ልቦለድ?
‹ፍቅር እስከ መቃብር› ልቦለድ ለንባብ በበቃ በስምንተኛው ዓመት የጉዱ ካሳ ሕልም ዕውን ሆኗል፡፡ ጉዱ ካሳ ሲሞግተውና ሲያንኳስሰው የቆየው ሥርዓት ፈርሷል፡፡ ካቡ ተንዷል፡፡ ይሄ በብዙዎቻችን ዘንድ የሚታወቅ ሀቅ ነው፡፡ የሚታወቅ የማይመስለኝ አበረ አዳሙ፣ ‹የፍቅር እስከ መቃብሩ አበጀ በለው ከእውነተኛ ታሪክ አንጻር ሲቃኝ› በሚለው መጣጥፉ የገለጸውን እውነት ነው፡፡ መጣጥፉ እንደ ሚለው ‹ፍቅር እስከ መቃብር› ታትሞ ወጣ በሁለተኛው ዓመት (በ1960 ዓ.ም) አበጀ በለውን የመሰለ ሰው በጎጃም/ በብቸና ተነሳ፡፡ በአምላኩ አባግዮን የሚባል፡፡ በአምላኩ አባ ግዮን የሽፍትነት ስሙ እንጂ መጠርያ ስሙ በአምላኩ አየለ ነው፡፡ በአምላኩ እንደ አበጀ በለው ለሽፍትነት/ ለአማጺነት/ ለነጻ አውጪነት ልቦናው ያዘነበለው አንድ ደሃ ባላገር በቅሎው በአንድ ‹የዘመኑ ሰው› ተዘርፎ፣ በቅሎው በሹሙ  መዘረፉ ሳይበቃ በዘራፊው ሲገደል በማየቱ ነው፡፡ በአምላኩ፣ አበረ እንደሚለው፣ ‹አዋጅ ያስለወጠ አርሶ አደር› ነው፡፡ አዋጅ የማስለወጡ ታሪክም እንዲህ ነው፡፡ ታሪክ ድርጊቱን ‹የጎጃም አርሶ አደሮች አመጽ› ብሎ ይጠቅሰዋል፡፡ ከበአምላኩ ውጪ አመጹ ጅምርም ጭርስም አይኖረውም፡፡
በአምላኩ ነው፣ በእያንዳንዱ የጎጃም አርሶ አደር ላይ ተጨማሪ የብር ከሃምሳ ግብር ሲጣልበት፣ ‹ጎበዝ! ዛሬ ብር ከሃምሳ ተጨማሪ ሲጣልብን ዝም ካልንና ክፈሉ የተባልነውን ከከፈልን ከርሞ መቶ ሃምሳ ይሆንብናል፤ይደረግብናል፤ተጠቅተናል፤ ተደፍረናልና ተነስ!› ብሎ ሕዝቡን አሳምኖ ለአመጽ ያነሳሳው፡፡ ሆኖለታልም፡፡ በአምላኩ ልክ እንደ አበጀ በለው የፊውዳሉ ሥርዓት መሪ ተዋንያን መጣብን ብለው የሚሸሹት ዓይነት ሞገደኛ የለውጥ ሎሌ ነው፡፡ ፍርሃታቸው አለምክንያት አልተወለደም፡፡ ዐይተዋል፡፡ የቢቸና ገዥ የሆኑት ፊታውራሪ ደምስ አላምረው፣ ለፍልሚያ ተቃጥረው፣ ነገሩ እንዳይሆን እንዳይሆን ሲሆን፣ በአምላኩ አባግዮን ‹እጁን ይዠ ባቄላ ያላስፈጨሁት እንደሆነ ወንድ አይደለሁም› ብለው መዛታቸውን ሰምተው፣ ሕይወታቸውን ለማትረፍ እሳቸውና መሰሎቻቸው ቤተክርስቲያን ገብተው ልብሰ ተክህኖ ለብሰው፣ ታቦት ከመቃጠል ለማትረፍ እንደ ሚቻኮል ሰው ‹ድራማ ሠርተው› ነፍሳቸውን ማትረፋቸውን ሰምተዋል፡፡ በአምላኩ አባ ግዮን አበጀ በለውን ሆኖ የተገኘው በአጋጣሚ ነው ወይስ…. ያጠያይቃል፡፡
….
በዛብህን ሳይሆን አበጀ በለውን ስለመሆን
….
በዚህ ዘመን በዛብህ ስለደረሰበት መገፋትና መከፋት በማሰብ ብቻ ዘመናችንን የምንፈጅ ሳንሆን፣ እንደ አበጀ በለው የነጻ አውጪነት መንፈስ ሊኖረን ይገባል ብዬ አምናለሁ፡፡
አብዛኛው የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ታሪክ የአልቃሽና የአስለቃሽ ትረካ ይመስላል፡፡ (በዛብሆች በዝተናል) ዜማውም ዜማው የታዘለበት ግጥምም ተመሳሳይ ነው፡፡ ‹እኔ ነኝ በአንደኝነት የተጨቆንኩት፤ እኔ ነኝ ከማንም በላይ የተገፋሁት› ዓይነት ዲስኩሮች፣ የምሬት ማመልከቻዎች እዚህም እዚያም፣ ተበታትነውና ተለጣጥፈው ይነበባሉ፡፡
መጨቆን ሜዳሊያ የሚያሸልም ይመስል የአብዛኛው ብሔር ትኩረት እዚህ ላይ ሆኗል፡፡ ‹አልጨቆንኩም፤ አልተጨቆንኩም› የሚል ማኅበረሰብ/ ብሔር የምናገኘው መቼ ነው?
መቸም ሆነ መቸ፣ የትምም ሆነ የት አበጀ በለው፣ በአምላኩ አባ ግዮንን ሆኖ እንዲመጣ መጠበቅና መናፈቅ የለብንም፡፡ በዚህ ዘመን አበጀ በለውን መፈለግ ሳይሆን አበጀ በለውን መሆን፣ አበጀ በለውን እልባችን ውስጥ መውለድ ነው የሚያስፈልገው፡፡
ሀዲስ አለማየሁ፣ ‹መልእክት ለወዳጆቼ› በተሰኘ የግጥም መጽሐፋቸው ‹የተኩላ ሞት› ብለው የጻፏት ግጥም እስካሁን ስለው የቆየሁትን፣ ወይም ለማለት የፈለግሁትን ብቻ ሳይሆን በየመጽሐፎቻቸው ሲሉ የቆዩትን በአጭሩ ትልልኛለች፡፡ በከፊል እንዲህ ትነበባበለች፡፡
‹‹ሰውና ሰይጣናት ባንድ አብረው ዶልተው
ህግን ከመንገዱ ካስወጡት ገፋፍተው፤
ይህን ሁሉ እያየህ ሳይጨንቅህ ሳትባባ
ልብህ ልብ ገዝቶ ግራ ስትጋባ፤
መሆኑን አስበህ ይኸ የደረሰ
ስርአት ባጣ ዘመን በደፈራረሰ
ሳትርቅ ታሳዛባ ከያዝከው አላማ
ሳትጮህ ሳታቃስት ድምጽ ሳታሰማ
ፍትህ ርትዕ ተጓድሎ በግፍ መበደለኽን
አውቀህ ስታምንበት ስታገኘው ልኩን
ጦሩን ነክሰኽ ሙት የቆሰልኽበትን፡፡
Filed in: Amharic