>
5:13 pm - Sunday April 19, 2116

ፋሺስቶችን በቤታቸው ያዋረደው ጀግና – ዘርዓይ ደረስ!! (አንተነህ ቸሬ)

ፋሺስቶችን በቤታቸው ያዋረደው ጀግና – ዘርዓይ ደረስ!!

 

አንተነህ ቸሬ
ኢትዮጵያ በፋሺስት ኢጣሊያ በተወረረችበት ወቅት ለሉዓላዊነቷ ታግለው አኩሪ የጀግንነት ገድል ካስመዘገቡት አርበኞች መካከል አብዛኞቹ ድል ያስመዘገቡት እዚሁ ኢትዮጵያ ምድር ላይ ቢሆንም የፋሺስቱን የቤኒቶ ሙሶሎኒን መንግሥት እዚያው አገሩ፣ ኢጣሊያ ላይ ውርደትን ያከናነቡ ጀግኖችም ነበሩ። ይህን ደማቅ ታሪክ ከፈፀሙት መካከል ደግሞ አንዱ ዘርዓይ ደረስ ነው።
ዘርዓይ ደረስ በ1908 ዓ.ም ኤርትራ ውስጥ አዲ ሓይስ በተባለ ስፍራ ተወለደ። ያደገው ደግሞ እዚያው ኤርትራ ውስጥ ሓዘጋ በተባለ ቦታ ነው። ርዕሰ ደብር እቁበ እንድርያስ በተባሉ የሃይማኖት አባት አማካኝነት የቤተ ክህነት ትምህርት ተምሯል። ርዕሰ ደብር እቁበ እንድርያስ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች እየተዘዋወሩ ስለ ኢትዮጵያ ታሪክና ትምህርት የተማሩና ያስተማሩ ሰው ስለነበሩ ዘርዓይም የትምህርታቸውን በረከት የመቋደስ እድል አግኝቷል።
ከቤተ ክህነት ትምህርት በኋላ ዘርዓይ አስመራ ከተማ ውስጥ በሚገኝና በሳልሳዊ ኢማኑኤል ስም በተሰየመ ትምህርት ቤት ገብቶ ዘመናዊ ትምህርት ተምሯል። ከዚያም መምህር ሆና ማስተማር ጀመረ። ይሁን እንጂ ዘርዓይ ለተማሪዎቹ ስለኢትዮጵያ ደጋግሞ መናገሩና መከራከሩ ለጣሊያኖቹ ምቾት የሚሰጥ ስላልነበር ከስራው ተባረረ። እርሱ ግን ‹‹ገብረሚካዜላውያን›› የሚባል ማኅበር አቋቁሞ ኢትዮጵያ በጠላት እጅ ስለወደቀች ሁሉም ሰው በጸሎትም በመንፈስም ከኢትዮጵያዊያን ጎን እንዲቆም መቀስቀስ ጀመረ። የኢትዮጵያን መወረር ተቃውሞ በጋዜጣ ላይ ገለፀ።
ከአንድ የኤርትራ ገዢ ዘንድ ቀርቦ ሲጠየቅ አማርኛ፣ ትግርኛ፣ ጣሊያንኛና አረብኛ መናገር እንደሚችልና ኦሮሚኛ፣ ሶማሊኛና አገውኛ የሚያስጠናው ቢያገኝ መማር እንደሚፈልግ ተናገረ። አገረ ገዢውም እንዲህ ዓይነቱን ሰው አስመራ ውስጥ ከማስቀመጥ ወደ ኢጣሊያ ቢልከው የተሻለ እንደሆነ በማመኑ በመስከረም 1929 ዓ.ም ወደ ሮም ተላከ። በዚያም አንድ የቅኝ ግዛት አገር ዜጋ ሊያገኘው የሚገባውን ከፍተኛ ደረጃ ተሰጥቶት የአስተርጓሚነት ስራውን ጀመረ። ይሁን እንጂ ያ ሁሉ ስጋዊ ምቾቱ ለኢትዮጵያ ነፃነት ከመታገል ሊያግደው አልቻለም።
ሰኔ ሰባት ቀን 1930 ዓ.ም የኢጣሊያ መንግሥት በዶጋሊ ጦርነት ለሞቱት ጣሊያናውያን የተሰናዳ የመታሰቢያ መርሃ ግብር በሮም ከተማ በአንድ የመንግሥት አደባባይ ላይ አዘጋጅቶ ነበር። [ጥር 18 ቀን 1879 ዓ.ም የራስ አሉላ (አባ ነጋ) ጦር የኢትዮጵያን ድንበር ጥሰው የመጡትን ጣሊያኖችን ዶጋሊ በተባለ ቦታ ላይ ገጥሞ የጣሊያን ጦር አሰቃቂ ሽንፈት ገጥሞታል] … ዘርዓይ በዕለቱ ፒያሳ ዲ ፒአሞንቲ በተባለው አደባባይ እንዲገኝ የተደረገው የኢትዮጵያን የጦርና ሌሎች ዕቃዎች ይዞ ለማላገጫነት እንዲቆም ነበር። ዘርዓይ ከያዛቸው እቃዎች መካከል አንዱ ራስ አሉላ ዶጋሊ ላይ ጀብዱ የሰሩበትና በፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ ወቅት ከኢትዮጵያ ተዘርፎ የተወሰደው ጎራዴ ነበር። ዘርዓይም እቃዎቹን ይዞ እንዲሄድ ከመታዘዙ በቀር ለመሳለቂያነት መቆም እንዳለበት አልተነገረውም ነበር።
ዘርዓይ ፒያሳ ዲ ፒአሞንቲ አደባባይ ሲደርስ እንግዳ ነገር ተመለከተ። ቀደም ሲል አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ተተክሎ የነበረው የይሁዳ አንበሳ ሐውልት ሮም አደባባይ ላይ ተተክሎ አየው። ከሐውልቱ ላይ ሁለት ግልገሎች የምታጠባ የተኩላ ምስል ተቀምጦበታል። በአንበሳው መስቀል ላይ ደግሞ የኢጣሊያ ባንዲራ ተሰቅሏል። የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ መሬት ላይ ተጥሏል። በዙሪያው ተጽፈው ከሚታዩና የኢትዮጵያንና የሕዝቦቿን ክብር ከሚነኩ መፈክሮች መካከል አንዱ ‹‹ … የይሁዳ አንበሳን ልጆችሽ እንደፍየል ጭራውን ጠምዝዘው አምጥተው ከእግርሽ ስር ያሰግዱታል …›› የሚል ነበር። በአደባባዩ የተሰበሰበው ሕዝብም እየሳቀና እየጮኸ አንበሳው ላይ ምራቁን በመትፋት ያፌዝና ይሳለቅ ነበር።
ዘርዓይ ደረስ ሁኔታውን በመገረምና በመናደድ ስሜት ሲመለከት ማርሻል ማሪዮ ኢሶን የተባለ የዘበኞች አለቃ ወደ ዘርዓይ ቀርቦ ድርጊቱን መመልከት እንደማይችል ነገረው። በተጨማሪም ማርሻል ኢሶን የዘርዓይን መናደድ ስለተመለከተ ዘርዓይን ከአካባቢው ሊያባርረው ሞከረ። ዘርዓይ ‹‹እናንተ የምታዩትን እኔ የማላይበት ምን ምክንያት አለ?!›› ብሎ ጠየቀው። የዘበኞቹ አለቃም የዘርዓይን ጥያቄ እንደድፍረት በመቁጠር ‹‹ … ከእንግዲህ አንበሳ የለም! ለተኩላዋ ልትሰግድና ልታመልካት ይገባሃል!›› አለው። ዘርዓይ ግን ‹‹አይደረግም!›› አለ። ክርክሩ ከረረ። ማርሻል ኢሶን ‹‹ … ከእንግዲህ በኋላ አንበሳው የተኩላዋ አሽከር መሆኑን ልነግርህ እወዳለሁ … ያውም ንጽሕናውን ያሻሽል እንደሆነ … ›› አለ። ዘርዓይ በእልህ ተከራከረ። አንበሳው ጣሊያኖችን ከአንድም ሁለት ጊዜ ሰባብሮ ድራሻቸውን እንዳጠፋቸው አስረዳው። የዘበኞቹ አለቃ ‹‹ … ከአንበሳው ጀርባ ላይ ወጥታችሁ አሳዩት ቁርጡን ይወቀው!›› የሚል ትዕዛዝ ለወታደሮቹ ሰጠ። ሕዝቡ ጭምር አንበሳው ላይ ለመውጣት ተተረማመሰ።
ዘርዓይ ደረስ ስራውን የጀመረው በዚህ ሰዓት ነበር። በያዘው ጎራዴ ጣሊያኖችን መጨፍጨፍ ጀመረ።
‹‹ … ከእንግዲህ በኋላ አንበሳው የተኩላዋ አሽከር መሆኑን ማመን አለብህ … ተኩላዋን ልታመልካት ይገባሃል …›› ብሎ ያፌዘበትን ማርሻል ኢሶንን ለአንበሳው እንዲሰግድ አድርጎ እጅና እግሩን ክፉኛ አቆሰለው። የሌሎችንም ሬሳ በአንበሳው ስር ጎተተው። ይህን ሁሉ ካደረገ በኋላ እንኳ ለመሸሽ አልፈለገም።
ሮም ተሸበረች። ‹‹ኢትዮጵያ ሰብራ ገብታ የኢጣ ሊያን ሕዝብ ጨፈጨፈችው … ታጥቀህ ራስህን ተከላከል …›› ተብሎ ታወጀ። ሁሉም በያለበት ተኩስ ከፈተ። በዘርዓይ ጎራዴና በአደባባዩ ላይ በነበረው ትርምስ ምክንያት ከሞተው ሰው በተጨማሪ ‹‹ … ታጥቀህ ራስህን ተከላከል …›› ተብሎ በታወጀው አዋጅ ምክንያት ብዙ ሰው እርስ በእርሱ ተጋደለ። የኢጣሊያ መንግሥት ባለስልጣናት ድርጊቱ ውርደት ስለሆነባቸውና ነገሩን በምስጢር ስለያዙት ስንት ሰው እንደሞተ በውል አይታወቅም። አንዳንድ የታሪክ ጸሐፊዎች በዕለቱ በጥቂቱ የአምስት ሰዎች አስክሬን ከአደባባዩ ላይ መነሳቱን ሲጽፉ ሌሎች ደግሞ ቁጥሩን እስከ 18 ያደርሱታል። በትርምሱ ምክንያት ብዙ ሰዎች መቁሰላቸው የታሪክ ጸሐፊዎቹን አስማምቷል።
ዘርዓይ ጣሊያኖች ላይ እርምጃ መውሰድ የጀመረው ከረፋዱ አራት ሰዓት አካባቢ ነበር። ሽብሩ ግን እስከ 10 ሰዓት ተኩል ድረስ ቀጥሎ ነበር። ከቀኑ 10 ሰዓት ተኩል አካባቢ አገሪቱ ሰላም መሆኗንና ሽብሩ የተፈጠረው አንድ የአዕምሮ በሽተኛ ህመሙ ተነስቶበት እንደሆነ የሚገልፅ አዋጅ ተነገረ። የአዋጁ ቃል ይህ ብቻ አልነበረም። ‹‹ … ወደ ፒያሳ ሄዳችሁ እጁን ያዙ!›› የሚል ትዕዛዝም ነበረው። በዚህ ትዕዛዝ ምክንያት የከተማው ሕዝብ እንደገና ወደ አደባባዩ ወጣ።
ዘርዓይ ደረስ ሰውነቱ እንደነብር ተቆጣ። በተኩላዋ ሐውልት ላይ ቆሞ በመናገር ሕዝቡን ዝም አሰኘው። ‹‹ … በየቤታችሁ እየዞርኩ ብዙ ሰው አርድ ነበር። ግን እኔን አስሮ የያዘኝና እዚህ ሲያኮራምተኝ የዋለው የአንበሳው ፍቅር ነው። ደግሞም አሟሟቴ ከአንበሳው ስር እንዲሆንልኝ ፈልጌ ነው። ወንድ ይምጣና ይማርከኝ …›› ብሎ ተናገረ። ከተኩላዋ ላይ ወርዶ አንበሳውን እየዳሰሰ ቆመ።
አውቶማቲክ መሳሪያ የያዙ ወታደሮች በሞተር ሳይክል፣ ከሁለት አቅጣጫ በመምጣት ዘርዓይን ተኩሰው መቱት። ጎራዴውን መዘዘና እንደገና ወደ ሕዝቡ ገሰገሰ። ከተማዋ በተኩሱና በሽሽቱ ምክንያት እንደገና ተረበሸች። ዘርዓይ ቢወድቅም ሊቀርበው የደፈረ ሰው አልነበረም። ጎራዴውን ይዞ ከወደቀበት ተነሳ። መሬት ላይ ወድቆ የነበረውን የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በማንሳት በደሙ ለውሶ አንበሳው ላይ ሰቀለው። ተኩላዋ ላይ የነበረውን የኢጣሊያ ባንዲራ የተሰበሰበው ሕዝብ እያየው አወረደው፤ቀዳዶ ከመሬት ጣለውና ረገጠው። አንበሳውን እየሳመ ያነጋግረው ነበር። ዘርዓይ ይህን ሁሉ ሲያደርግ ሊያስቆመው የሞከረ ሰው አልነበረም። አሁን ግን ወታደሮቹ ደግመው ተኮሱበት … ዘርዓይም ወደቀ … ግን አልሞተም ነበር።
ዘርዓይ ይህን ሁሉ ሰርቶ፤በስድስት ጥይት ተመትቶ መትረፉ ጣሊያኖችን አበሳጫቸው፤አስደነገጣቸውም። በወቅቱ በሮም ከተማ ውስጥ ከነበሩት ሐኪም ቤቶች ሁሉ የተሻለ ወደሚባለው የሕክምና ተቋም (ቀዳማዊ ኡምቤርቶ ፖሊክሊኒክ) አስገቡትና ሕክምና ተደርጎለት አገገመ። ሐምሌ 15 ቀን 1930 ዓ.ም ቤኒቶ ሙሶሎኒ በዘርዓይ ጥቃት የቆሰሉትን ለመጠየቅ ሐኪም ቤት ሲደርስ ማርሻል ማሪዮ ኢሶን ሞቶ እየተገነዘ ነበር። ለኢሶን ያመጣለትን ኒሻን አስቀምጦ በከፍተኛ ቁጣ ዘርዓይ ወደተኛበት ክፍል ገባ። አገግሞ ስላገኘው የበለጠ ተናደደ። ‹‹ … አንተ ነህ ሮምን የደፈርካት?›› ብሎ ጠየቀው። ሙሶሎኒም ዘርዓይ በሚገባ ታክሞ እንዲድን ለሐኪሞቹ አደራውን ሰጠ። ዘርዓይን በሞት መቅጣት የኢጣሊያን ስም በማይረባ ነገር በመላው ዓለም መበተን መሆኑን ገልፆ፤በዳነ ጊዜ በቃልም በጽሑፍም ይቅርታ እንዲጠይቅ፣ የአዕምሮ ሕመምተኛ መሆኑን የሚገልፅ ማስረጃ እንዲዘጋጅና ዘርዓይም ሕመምተኛ መሆኑን እንዲያምን እንዲደረግ ትዕዛዝ ሰጠ።
ፕሮፌሰር ፋውስቶ ኮንስታንቲኒ የተባለው ሐኪም የሙሶሎኒን ትዕዛዝ ለማስፈፀም ላይ ታች አለ። ለብዙ ቀናት አግባብቶ አንድ ወረቀት እንዲፈርም አቀረበለት። ደብዳቤው ስለተደረገለት ሕክምና አመስግኖ ‹‹ … በ500 ወታደሮች አደባባይ ላይ በድንገት ታምሜ በሰዎች ሕይወት ላይ ስላደረስኩት በደል … ይቅርታ እጠይቃለሁ። በስድስት ጥይቶች የተመታው ሰውነቴና አንጎሌም ድኖ በቅርብ ቀን ለመውጣት ሀኪሙ ተስፋ ሰጥቶኛል …›› የሚሉ ሃሳቦችን ያካተተ ነበር። ዘርዓይ ደብዳቤውን ከሐኪሙ ነጥቆ በመቀዳደድ ፊቱ ላይ በተነበት። ቀደም ሲል በዚሁ ጉዳይ ላይ በተደረገ ክርክር ዘርዓይ ‹‹ … በእናንተ አፍ እውነት የሚነገረው መቼ ይሆን?›› ብሎ በድፍረት የጠየቀው ፕሮፈሰር ኮንስታንቲኒ የሐፍረት ማቅ ለብሶ ወጣ፤ድጋሚ ወደ ዘርዓይ አልተመለሰም።
ፕሮፌሰር ኮንስታንቲኒ በድጋሚ እርሱ በአካል ወደ ዘርዓይ ባይመለስም ጥረቱን ግን አላቋረጠም ነበር። ሁለት ኢትዮጵያዊያንን (አንድ ስማቸው ያልተጠቀሰ ደጃዝማችና አንድ መነኩሴ) ላከበት። ሁለቱ ሰዎች የዘርዓይን አቋም ለማስለወጥ ብዙ ደከሙ። የኢጣሊያን መንግሥት ኃያልነትና የእርሱን ወጣትነት እያገናዘቡ ብዙ አባበሉት። እርሱ ግን ሀሳቡን መለወጥ አልፈለገም። ወደ ደጃዝማቹም ዞሮ ‹‹ … እንደርስዎ ያለ ሰው የማንም ጭነት ማጓጓዣ መሆን አልነበረበትም …›› አላቸው። በተጨማሪም ‹‹ … ለእነርሱ ክብርና ለእነርሱ ወረራና መስፋፋት ከቶ የእናንተ አጠንጣኝነት ምንድን ነው? ሲል ጠየቃቸው። ደጃዝማቹ ግን መልስ አልነበራቸውም። ዘርዓይ ቀጥሎም ‹‹ … እንስሶች እንኳ ጌታቸውን ይወዳሉ። እናንተ ግን ቅሌታችሁን ተሸክማችሁ ትዞራላችሁ!›› ብሏቸው ወደ መነኩሴው ዞረ። ‹‹ … የእግዚአብሔር እንደራሴ መስለው በጥቁር ጨርቅ ትምነሸነሻላችሁ … የሰውን የእኩልነት ኑሮ ለማጥፋት ከላይ ተልካችሁ የመጣችሁ መቅሰፍቶች ናችሁ … ቅስናዎን ይተውት! ተራ መሐይም መስለው እንደሌሎች ባንዳዎች ቢያገለግሉ ይሻላል … ከአጠገቤ ውጡ!›› ብሎ አባረራቸው። ዘርዓይ አቋሙን እንደማይቀይር ስለታወቀ በድጋሚ እንዲህ ዓይነት ጥያቄ አልቀረበለትም።
ስለሆነም ጉዳዩ ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት ቀረበ። መደበኛው ፍርድ ቤት ወደ ጦር ፍርድ ቤት መራው። የጦር ፍርድ ቤቱ ዳኞች በጭካኔያቸው የታወቁ ሦስት ኮሎኔሎች ነበሩ። ሕዝቡ ተሰብስቦ የፍርድ ሂደቱ ተጀመረ። ዓቃቤ ሕጉ ዘርዓይ 11 ወንጀሎችን እንደፈጸመ በመጥቀስ በቤንዚን ተቃጥሎ እንዲሞት ወይም እጁ ታስሮ በሰረገላ እየተጎተተ በከተማው እየዞረ ለከተማው ሕዝብ እንዲታይ ለቅኝ ግዛት አገራት ዜጎች የተደነገጉ ሕጎችን በመጥቀስ አመለከተ። ሌላ ሕግ ስለሌለ እንጂ እነዚህ ሕግጋትም ለዘርዓይ ወንጀል በቂ ናቸው ብሎ እንደማያምንም ዓቃቤ ሕጉ ገለጸ። የክሱ ፍሬ ነገር አቀራረብም ‹‹ ከሙሶሊኒ የተፈቀደ የይለፍ ፊርማ ይዞ ወታደሮችን በማዘናጋት ጎራዴ ይዞ አደባባይ ገብቷል … የኢጣሊያን ታሪክ አደፍርሷል … የኢጣሊያን ባንዲራ አውርዶ ከመርገጡም ባሻገር የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በደሙ ቀብቶ ሰቅሏል … የኢጣሊያ ፋሺስት መንግሥት ይውደም በማለት በኢጣሊያ መንግሥት ላይ ጥላቻ አሳይቷል … ኢጣሊያ ተደፍራለች … አንድ ማርሻልና ብዙ ወታደሮች ተገድለዋል … ከተማ ተረብሿል … ከፍተኛ ረብሻ በመነሳቱ ብዙ ሰው ለሞትና ለአካል ጉዳት ተዳርጓል …›› የሚል ነበር።
ሰብሳቢ ዳኛው ሌሎቹን ዳኞች ሳያማክር የራሱን ሃሳብ ሰነዘረ። ‹‹ … ኢጣሊያ አንዳች ጉዳት አልደረሰባትም … ›› ብሎ ሲናገር ሕዝቡ ተንጫጫ። ዳኛው ግን ጫጫታውንና ፉጨቱን ከምንም ሳይቆጥር ‹‹ … አንድን እብድ የምንቀጣበት አንቀፅ በዚያው በአእምሮ ሕመምተኞች ቦታ ተቀላቅሎ እንዲኖር ብቻ ነው›› በማለት ፍርዱን ደመደመ። ሌሎቹ ዳኞች ግን ሳይስማሙ ቀሩ። ‹‹እኛ እብድ መሆኑን አናምንም፤በተጠቀሰው አንቀፅ ይፈረድበትና አሟሟቱን እንመልከት›› አሉ። ዓቃቤ ሕጉ በሁለቱ ዳኞች ሃሳብ ተበረታቶ ‹‹እርሱን ‹እብድ ነው› የሚል ሰው ራሱ ያበደ ነው›› አለ። የሕዝቡ ጭብጨባ አስተጋባ።
ዳኞቹ መጀመሪያ ማድረግ የሚገባቸውን ስራ ማከናወን ጀመሩ። ዘርዓይ ቃሉን እንዲሰጥ ተፈቀደለት። ጣሊያንኛ በሚገባ ማወቁ ጉዳዩን እንደልቡ ለማስረዳት ጠቀመው። ‹‹ … ምን እንድል ነው የምትሹት? እብድ ነኝ እንድል ነው ወይንስ ጤነኛ?›› ብሎ ዳኞቹን ጠየቃቸው። መልስ የለም። ወደ ዓቃቤ ሕጉ ዞሮ ‹‹አንተ እንደምትለውና እንደምታወራው መሆኑን ላረጋግጥልህ እወዳለሁ። በእውነቱ የእኔ ዶክተር አንተ ብቻ ነህ›› አለው። ዘርዓይ ሐኪሙ ከሙሶሎኒ ተሻርኮ እብድ ነው ማለቱን፤ሰብሳቢ ዳኛውም ይህንኑ ማስተጋባቱን አጋለጠ። ሙሶሎኒ ሮምን ጥቁር ታሪክ አልብሷት እንደሚሄድም ተነበየ።
የተሰበሰበው ሕዝብ ‹‹ … ይገደል! ይሰቀል! ይቃጠል!›› እያለ ጮኸ። እርሱ ግን በድፍረት ንግግሩን ቀጠለ። ብዙ ከወቀሳቸው በኋላ ‹‹ … እኔ ሙሉ ጤነኛ ነኝ!›› አላቸው። ከእነርሱ በቀር ምንም በሽታ እንደሌለው ነገራቸው። ‹‹ … ያገርን መውደድ ቋንቋ ካወቃችሁ አገራችንን እንድንጠላ፣ እርስ በእርሳችን እንድንጣላ ለምን ታስገድዱናላችሁ?›› ብሎ ጠየቃቸው። አሁንም መልስ የለም። በእርሱ ላይ ለመፍረድ ብዙ ሺ ሕዝብ መሰብሰቡን አሳይቶ ፋሺስቶች ግን በአገሩ ሚሊዮኖችን ሲጨፈጭፉ ዳኛ እንደሌለባቸው ገለጸ። ‹‹ግን የኢትዮጵያውያን አጥንትና ደም ዋጋ ሲኖረው የእናንተ ስም እየገማ ትኖራላችሁ!›› አላቸው። በመጨረሻም ‹‹የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በክብር ትኑር! ንጉሥ ተፈሪ በድል አድራጊነት ይኑር! የይሁዳ አንበሳ ምንጊዜም ድል ከሱ ይሁን!›› ብሎ ንግግሩን አበቃ። ሕዝቡ እጅግ በጣም ጮኸ፤ችሎቱ ተተረማመሰ፤ዳኞቹ የሚሰማቸው በማጣታቸው ተበሳጩ። ለዘርዓይ ስሜቱን የሚገልጽበት፤ንቀቱንና ድፍረቱን የሚያሳይበት እድል በመስጠታቸው ተፀፀቱ። ዓቃቤ ሕጉ ‹‹ሮማ ማልቀስና ማዘን የሚገባት ዛሬ ነው!›› አለ። ሰብሳቢ ዳኛው ተሸነፈ፤በቤንዚን ተቃጥሎ እንዲሞት ሁሉም ዳኞች ተስማሙ።
ችሎቱ በዚህ ሁኔታ ላይ ሳለ ሁለት የፖሊስ መኮንኖች ወደ ችሎቱ ዘለቁ። አንዱ ፖሊስ ወታደራዊ ሰላምታ ከሰጠ በኋላ አንዲት ፖስታ ለሰብሳቢ ዳኛው ሰጠ። ሰብሳቢ ዳኛው ደብዳቤው ላይ የሙሶሎኒን ፊርማ ሲመለከት ደነገጠ። ሙሶሎኒ በደብዳቤው ለአንድ ‹‹እብድ›› ዋጋ በመስጠት ሲጨቃጨቁ እንደዋሉ መስማቱን ገልፆ ‹‹ … በአርባ ሚሊዮን ደንቆሮ መካከል ተፈጥሬ እናንተን ጠዋት ማታ ማስተማሩ ሰለቸኝ …›› የሚል ከባድ ወቀሳ በማቅረብ ‹‹ … ለእብድ የተደነገገ ሕግ ስለሌለኝ ወደ አዕምሮ በሽተኞች ሐኪም ቤት ሄዶ እንዲቀመጥ ይሁን … በእብደቱ እንጂ ሮምንና ሕዝቧን እንዳልደፈረ እንዲታወቅ›› የሚል ትዕዛዝ አስቀምጦ ነበር። በተጨማሪም ደብዳቤው ማንኛውም ሰው ዘርዓይ ደረስ ስለፈጸመው ነገር ቢያነሳ በገመዱ እንደሚገባ ያስጠነቅቅ ነበር። ፋሺስቶችን በራሳቸው ምድር ላይ ያሸማቀቃቸው ዘርዓይ ደረስም ወደ እስራት ኑሮው ተሸጋገረ።
የፋሺስት አስተዳደር ከተወገደ በኋላ ዘርዓይን ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት የተደረገው ጥረት ሳይሰምር እስራት ላይ እንደነበር በ1937 ዓ.ም አርፏል። አስከሬኑ ወደ ኤርትራ መጥቶ ሐዘጋ ማርያም ቤተ ክርስቲያን እንዲያርፍ ተደርጓል። አንጋፋው ባለቅኔ ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድኅንን ጨምሮ ሌሎች ደራሲያን ለዘርዓይ ደረስ መታሰቢያ የሚሆኑ የኪነ ጥበብ ስራዎችን ሰርተዋል።
አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 11/2012
Filed in: Amharic