>

በኤርትራ የምድር ውስጥ እስር ቤት ያሉ ዜጎቻችንስ ....??? (ደስ ኢትኦፕ)

በኤርትራ የምድር ውስጥ እስር ቤት ያሉ ዜጎቻችንስ ….???

 

ደስ ኢትኦፕ
ጠ/ሚንስትር አብይ በጎረቤትና በመካከለኛው ምስራቅ አገራት በተለያየ ምክንያት በእስር ላይ የሚገኙና የጉዞ ሰነድ የሌላቸው ዜጎችን እያስፈቱ ለገራቸው እንዲበቁ አድርገዋል ። ይህም እርምጃቸው ብዙ አሶድሷቸዋል ። ለወደፊቱም የዜጎችን መብት በዲፕሎማሲም ሆነ በሌላ አስገዳጅ ሁኔታ የማስከበር መሪያዊ ግዴታቸው እንደሚቀጥል ይታመናል ።
.
ከዚህ ጋር ተያይዞ ከኤርትራ ጋር የነበረው ወዳጅነትም በማስቀጠል የሄዱበት ርቀት ብዙ ነው ። ከዚህ በመነሳት ከኤርትራው ፕሬዚዳንት ጋር ያላቸውና የፈጠሩት  ወዳጅነትም ከየትኛውም ሌሎች አገራት ጋር ሲነፃፀር  የላቀ ሆኗል ። መቼም የኤርትራው ፕሬዚዳንት ከነመለስም ጋር የነበራቸው ወንድማማችነት ከጠ/ሚንስትር አብይም በላይ እንደነበር እናውቃለን ። ስውር አጀንዳና ጥቅም ወዳጅነታቸውን ወደ እንጦርጦስ አወረደው እንጂ ። የዛሬው የኢሳያስ ወዳጅነት ከጀርባው የተደበቀ የጥቅም ፍላጎት ከሌለበት በስተቀር ማንም ኢትዮጵያዊ ያለፈውን ረስቶ በግንኙነቱ አንፃራዊ ደስታ አግኝቷል ።
.
ከላይ እንደተገለፀው ጠ/ሚንስትር አብይ በባእዳን እጅ ያሉ ዜጋ አስረኞችን በማስፈታት ያስመዘገቡት ስኬት ፍፀም ወዳጃቸው በሆኑት ኢሳያስ ላይ ማሳየት አለመቻላቸው ለምን ይሆን ? እንደሚታወቀው በኤርትራ በረሃዎችና ተራራዎች ውስጥ በተሰሩ የምድር ውስጥ ዋሻዎች የታሰሩ በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ወንድሞቻችን አሉ ። እነዚህ የምድር ሲኦል የሚግፋቸው ዜጎቻችን ለ30 እና ከዚያም በላይ ለሆኑ አመታት በነዚህ ዋሻዎቻ ታስረዋል ። ብዙዎቹ በይሕወት ባይኖሩም የተወሰኑት አሁንም እንዳሉ ይገመታል ። በተለይም አብዛኛዎቹ የቀድሞ ሰራዊት ምርኮኞችና በ1983 ሻቢያና ወያኔ አገሪቷን ሲቆጣጠሩ በጠላትነት የተፈረጁ  ከመላው ኢትዮጵያ እየታፈኑ ወደ ኤርትራ የተጓዙ ዜጎች ናቸው ።
.
አቶ ኢሳያስ በእውነትም በጥልቅ ስሜት የኢትዮጵያ ወዳጅነታቸውን ካረጋገጡ …የወዳጃቸው የኢትዮጵያን ዜጎች መፍታትና ለገራቸው መሬት እንዲበቁ መፍቀድ ይኖርባቸዋል ። ጠ/ሚንስትር አብይ በተመረጡበት ወቅት ባደረጉት ንግግር  እንኳንም በሕይወት ያሉ ዜጎች ቀርቶ በሊቢያ የባሕር ዳርቻ በአይሲስ የተቀሉ የ30 ኢትዮጵያውያን አፅም በአገራቸው አፈር እንዲያርፍ አመጣለሁ ብለውን ነበር ። አሁን ከመኖር በታች ያሉና  የኤርትራ የበረሃ ዋሻዎች የሸሸጋቸው ዜጎች አሉንና ፤ …. ለጠ/ሚንስትራችንም  ከኢሳያስ በላይ ወዳጅ የላቸውምና ፤ ይህንን ሐሳብ ለወዳቸው/ወንድማቸው ኢሳያስ በድፍረት በማቅረብ ዜጎቻችንን ከዚያ ሲኦል ማውጣት ይኖርባቸዋል ።
.
እነዚህን ዜጎች ማስፈታት ከሞት ወደ ሕይወት አለያም ከሲኦል ወደ ገነት የማውጣት ያህል ነው ። ሁለቱም ወዳጆች ይህን ታሪክ መስራት አለባቸው ። አቶ ኢሳያስም እውነተኛ  የኢትዮጵያ  ወዳጅነታቸውን የሚያረጋግጡት አንደኛው እድል በዚህ ነው ። ካለበለዚያ ወዳጅነቱ ለሌላ የተደበቀ አጀንዳና ጥቅም እንጂ የልብ አለመሆኑን ያሳያል ።
Filed in: Amharic