>
5:13 pm - Monday April 18, 6321

ምኒልክን አንተ ባታውቃቸው… ድፍን ዓለም ያውቃቸዋል!!! (አሰፋ ሃይሉ)

ምኒልክን አንተ ባታውቃቸው… ድፍን ዓለም ያውቃቸዋል!!!

አሰፋ ሃይሉ

        (አንዳንድ የስደት ሀገር ወጎች. . . !)

በካናዳ የምኖር ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡ እንዲህ ስልህ ግን ‹‹ዳያስፖራ›› ምናምን የምትለውን ዓይነት ሰው አልምሰልህ፡፡ ገና የፈነጠቅኩት ምራቅ አልደረቀም፡፡ የካናዳን ምድር ከረገጥኩ ዓመት ከመንፈቅ እንኳ አይሞላኝም፡፡ አካሌ ውቅያኖስን ከመሻገሩ በስተቀር… አሁንም ሁለመናዬ ኢትዮጵያ ላይ እንደተቸነከረ ነው፡፡ ሃሳቤና መንፈሴ የአዲሱን መኖሪያዬን ሠማይ አልለምድ ብለውኝ በኢትዮጵያ ሠማይ ላይ እንዳረበቡ ናቸው፡፡ ሌላ ቀርቶ በህልሜ እንኳ የአዲሱን ምድሬን ላመል ታህል የአዲሱን ምድሬን አይቼው አላውቅም፡፡ የማልመውም የምቃዠውም ከምድሯ ጋር በማይለቅ የዝምድና ክር የፈተለችኝን ያቺኑ የፈረደባትን እናት ሀገሬን ኢትዮጵያን ነው፡፡
እንዳየሁት ከሆነ – ብዙ እዚህ ሀገር ያገኘኋቸው ኢትዮጵያውያውያንም – የዘመናይቱን ሀገር ዘመናይነት የተላበሱ ዘመናዮች ሆነው ለመታየት መከራቸውን ከሚበሉት አንጀት የሚበላ ነገራቸው በስተቀር – ብዙዎቹ – ያው እንደኔው – በአካል ሌላ ምድር ላይ ተገኙ እንጂ – በሁለመናቸው እዚያችው ኢትዮጵያ ሀገራቸው ላይ ናቸው፡፡ የሚገርመኝ – ኤርትራውያኑ ራሱ የሚያወሩልህ – መቼ አዲሳባ ደርሰው እንደተመለሱ ነው፡፡ የኤርትራውያን ምግብ ቤቶች ሁሉ የኢትዮጵያን ምግቦችና ቅመማ ቅመሞች – ከሽሮ እስከ በርበሬና ጥቁር አዝሙድ፣ ከጤፍ እንጀራ እስከ ድርቆሽና የተነጠረ ቅቤ – አምጥተው ደንበኞቻቸው የሚመግቡ ናቸው፡፡ እንጀራቸው፣ በርበሬያቸው፣ ወሬያቸው፣ ሹሩባቸው፣ ቅዳሴያቸው፣ (እና ጥቂቶች ሌሎችም አዛናቸው)፣ የሁሉም ሀበሻ ልብ እዚያችው ኢትዮጵያ ላይ እንደተሰካ ቀርቷል፡፡
በየከተማው የኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ኦርቶዶክስ አማኞች ሰንበትን የሚያስቀድሱባቸው፣ ልጆቻቸውን ክርስትና የሚያስነሱባቸው፣ የነፍስ አባቶችን መንፈሳዊ አገልግሎት የሚያገኙባቸው ቢያንስ በየከተማው አንድ አንድ ቤተክርስትያኖችን አንፀዋል፡፡ እኛ በገዛ ሀገራችን ቤተክርስትያን አታንፁም ብሎ ምዕመናንን የሚገድል፣ ቤተክርስትያናትን የሚያቃጥል አፅራረ ቤተክርስትያን መንግሥት ሰጥቶን፣ እዚህ በሰው ሀገር በነፃነት ቤተክርስትያን እንደየአቅማቸው አንፀው አማኞች በነፃነት ከአምላካቸው ጋር የሚገናኙበትን ዕድል ስታይ – በልብህ የሆነ ቁጭት ጠቅ ያደርግሃል፡፡ ጉልበትን የሚያንጠፈጥፉ ከባባድ የፋብሪካ ሥራዎችን እየሠሩ – ከጧት እስከ ማታ ሲደክሙ እየዋሉ – ድካምና ያገሩ ልማድ ሳይበግራቸው አጿማትን ቀጥ ብለው የሚያከፍሉ በርካታ ፅኑ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ቤተሰቦችን በአድናቆት ታዝቤያለሁ፡፡
(ቆይ ግን … የገንዘብ ነፃነትን ለማግኘትም፣ የፖለቲካ ነጻነትን ለማግኘትም፣ የሐይማኖት ነፃነትን ለማግኘትም፣ የገዛ እግዜርህን ለመገናኘትም… የግድ የገዛ ሀገርህን ጥለህ መሰደድ ሊኖርብህ ነው ማለት ነው የዘንድሮ ነገር? ምናባታችን ብናደርግ ይሻለን ይሆን? ወቸ ጉድ!! ምን ዘመን ላይ ነው የደረስነው ግን?! እያልክ ትብሰከሰካለህ – የአዲሳባዎቹን ሰማዕታት የእነ ሚኪንና ሚሊዮንን አሳዛኝ ህልፈተ-ሕይወት እያሰብክ)!
በምኖርባት ከተማ ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የመጡ ስደተኛ ዜጎች እንደልብ ያሉባት ነች፡፡ ዋነኞቹ የሀገሩ ባለቤቶች ቀይ ህንዶች (ሲዩክስ፣ ኑናቩት፣ ኔቲቭስ፣ ኢንዲጅነሶች፣ ወዘተ እያሉ የሚጠሯቸው) በመልክ ትለያቸዋለህ፡፡ የሆነ የቻይናዊና የሀረር ሴቶቹን አዮዎች (ቆቱዎች) የሚመስል መልክ አላቸው፡፡ የሀገሩ ዜጎች ካናዳውያን መስለውህ ጠጋ ብለህ ስታዋራቸው ሩስኪ በሚመስል የተሰባበረ ቋንቋ የሚያናግሩህ በተለይ ከፖላንድ፣ ከሮማኒያ፣ ከቼክ፣ ከሃንጋሪ፣ ከቡልጋሪያ፣ ከመሳሰሉት የምስራቅ አውሮፓ ሀገሮች የመጡ ነዋሪዎች ታገኛለህ፡፡ እነዚህን ካናዳውያኑ ‹‹ኢንቪዚብል ማይኖሪቲስ›› ነው የሚሏቸው፡፡ ምክንያቱም ከውጭ ስታያቸው ነባር ካናዳውያኑን ራሳቸውን ይመስሉሃል፣ ጠጋ ስትላቸው ብቻ ነው ከሌላ ስፍራ የመጡ ‹ላገሩ ባዳ ለሰዉ እንግዳ› መሆናቸውን የምታውቃቸው፡፡ የማይታዩ አናሳዎች!
እንደኔ ያለው ሰውስ? እንደኔ ያለው ደግሞ ከሩቅ ይታያል፡፡ ቪዚብል ማይኖሪቲ ነው፡፡ የሚታይ፣ የማይሸሸግ፣ የማይታበል አናሳ!! ሀሀሀ!! ‹ሀበሻ ጠይምነቱን፣ ነብር ዥንጉርጉርነቱን አይተውም› ሆነና ነገሩ – እኛን ከሩቅ ያየን ሰው ሁሉ ይለየናል፡፡ ደግነቱ እኛም አናፍርም፡፡ ኩሩ ነው ኢትዮጵያዊ፡፡ እና ኤርትራዊ፡፡ ቆዳህ ቢነጣም፣ ቢጠቁርም፤ ፀጉርህ ቢሳሳም ቢከረድድም፤ አፍንጫህ ቢሞረድም ቢደፈጠጥም፤ አይንህ ቢጎላም ቢጠብም፤ ብትረዝምም ብታጥርም፤ ማይም ብትሆንም ምሁር፣ ሀብታም ብትሆንም መናጢ… ኢትዮጵያዊ አይደለህ? ኤርትራዊ አይደለህ? በቃ ጥቁር ነህ፡፡ አይ አም ኧ ፕራውድ አፍሪካን – ትላቸዋለህ!! ዘራፍ ያገሬ ጎበዝ!!
በነገራችን ላይ እዚህ ሀገር በተለያዩ አገልግሎት መስጫ ተቋማትም ሆነ በተለያዩ ድርጅቶች መጠይቆችን ወይም የተዘጋጁ ፎርሞችን ስትሞላ… የየትኛው የካናዳ ነዋሪ ዘር ምድብተኛ እንደሆንክ ትጠየቃለህ፡፡ በዘሮቹ ውስጥ ከሌለ ‹‹ከእነዚህ ውጭ ነው›› የሚል አማራጭም ይሰጥሀል፡፡ ግን ከጥያቄው ሥር ሁልጊዜ እንደዚህ የሚል ፅሑፍ ታገኛለህ፡- ‹‹ይህን ጥያቄ ለመመለስ ካልፈለግክ አለመሙላት ይሄን ጥያቄ መዝለል ትችላለህ፣ ባዶውን መተው ትችላለህ›› የሚሉ ማሳሰቢያዎችን፡፡
አንዴ ከማላውቀው ከኮስታሪካ ከመጣ ስደተኛ ጋር ጎን ለጎን ፎርም እየሞላን እዚህ የዘር ጥያቄ ላይ ሲደርስ በጣም ተናዶ… ወደኔ ዞር አለና፡- ‹‹ይሄንን አትሙላው! ምናባታቸው ሊያደርግላቸው ነው! አላውቀውም በላቸው! አትሙላው! እነዚህ ዘረኞች!›› ብሎ በንዴት እየተንተከተከ ይሄ ስደተኛን ማሸማቀቂያ መሆኑን አስረዳኝ፡፡
እኔ ደግሞ ቅድም ብዬሀለሁ፡፡ ‹‹አይ አም ብላክ፣ በት አይ አም ካምሊ›› (‹‹ጥቁር ነኝ፣ ግን የተዋብኩ ነኝ!››) እንዳለችው ንግስተ ሳባ የእስራኤል ቆነጃጅትን – እኔም ‹‹አይ አም ኧ ፕራውድ ብላክ አፍሪካን !›› ከአፍሪካም ኩርት ያልኩ ሀበሻ ነኝ!›› የምል ጥቁር ነኝ! እና አንገቴን በአዎንታ በመነቅነቅ ‹‹ሊፕ ሰርቪስ›› በግንባሬ ሰጥቼው – ጥ ቁ ሬ ን – በጅነና አጥቁሬ እብስ!! (ኮስታሪካ – ስለምክርህና ንዴትህ ግን – ሳላደንቅህ አላልፍም – ወኔህን ሳየው – ከሀበሻ ወኔ ጋር አንድ ይመስለኛል – እያልክ በልብህ!)
በነገራችን ላይ እዚህ ለኢትዮጵያውያንና ለኤርትራውያን ያሉት የኦርቶዶክስ ቤተክርስትያኖች ብቻ አይደሉም፡፡ የፕሮቴስታንት ‹‹የዎተርሉ-ዌሊንግተን›› አጥቢያ ቤተክርስትያኖችም አሉ! ደናግላን አማኞቹ ፀጉራቸውን ስስ ላስቲክ ወይም የፀጉር መከለያ የሚሸፋፈኑት… ዓለምን የናቁና በውስን አኗኗር ተቆጥበው የሚኖሩት ሜኖናይቶች የሚባሉት ‹‹አባ-ዓለም-ለምኔዎች›› ም አሉ፡፡ እንዲያውም አንድ የእነርሱ የሜኖናይትስ እምነት ተከታይ የሆነ ከኢትዮጵያ ከወጣ 38 ዓመቱ የሆነ የዩኒቨርሲቲ ሪሰርቸር የሆነ የጋራሙለታ ሰውም አግኝቼያለሁ፡፡ ስለኢትዮጵያ – የኦርቶዶክስ መነኩሴ ስለሆኑት ወላጅ እናቱ – ስለሐረር ሰው ደግነት አንስቶ አይጠግብም፡፡ እጅግ ጨዋና ትሁት – እና ስለሀገራችን የድሮዎቹ መልካም ነገሮች ሁሉ ተመርጠው ከዕይታው ያልጠፉ ‹‹አባ-ዓለም-ለምኔ››!!
እስላሞችም አሉ፡፡ እዚህ ካናዳውያኑ ዘንድ ቁጥራቸው የበዛ የፓኪስታን፣ የሕንድ፣ እና የተለያዩ አረብ ሀገራት ተወላጆች በብዛት እንዳሉም አትዘንጋ፡፡ እና እስላሞች መኖር ብቻ ሳይሆን – በየከተማውም ከአላሃቸው ጋር የሚገናኙበት፣ ሶላት የሚያደርጉበት፣ አዛናቸውን የሚያደርሱበት… የራሳቸው መስጊድ አላቸው፡፡ ፂማቸውን በነፃነት አንዠርግገውት ነው የሚሄዱት፡፡ አንዳንዶቹ ሙስሊሞች በጀለቢያ ብቻ ነው የሚንቀሳቀሱት፡፡ ሲዩክስ ህንዶችና የተወሰኑ ፓኪስታኖች ደግሞ አሉልህ – ወንዶቹ ራሳቸው ላይ እንደቄስ (ከቄስም የበለጠ ከፍታ ያለው) ጥምጣም እንደጉድ ጠምጥመው ነው የሚንቀሳቀሱት፡፡ ማንም ዞር ብሎ የሚናገራቸው የለም፡፡ የእምነት ነጻነት አለሃ፡፡
እንዲያውም ይግረመኝ ሲል ደግሞ – አንዱ እጅግ መልካም የሆነ እዚህ ከ20 ዓመት በላይ የኖረ ኢትዮጵያዊ ሙስሊም አለልህ፡፡ በአጋጣሚ ሆኖ የተዋወቅኩት የአጎቴ ጓደኛ ሆኖ ስለተገኘ ነው፡፡ እርሱ ቅልጥ ያለ አፋር ነው፡፡ ትውልዱ ከእነ ሃምፍሬይ አሊ ሚራህ ቤተሰብ የሚመዘዝ አፋር፡፡ የባለቤቱ ደግሞ ወሎዬ ነች፡፡ የራያ ወሎዬ፡፡ ሁለት ልጆች አሉት፡፡ ወንድና ሴት፡፡ እሳት የላሱ የኮሌጅና የሀይስኩል ተማሪዎች፡፡ መልካም ሙስሊሞች፡፡
ቤታቸው ስትሄድ በየማዕዘኑ የምታገኘው የኢትዮጵያችንን አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ባንዲራ ነው፡፡ የአፋሩ መሪ አሊሚራህ – በጃንሆይ ዘመን ኢጣልያ ስትወርረን – ‹‹እንኳን እኛ ግመሎቻችን የኢትዮጵያን ባንዲራ ከሩቅ አይተው ያውቁታል›› ብለው ለኢትዮጵያችን በክብር የቆሙት ትዝ አለኝ፡፡ ያው እዚህም የኢትዮጵያን ባንዲራ ልጆቹና በቤቱ የመጣ ሁሉ ከርቀት እንዲለየው በየግድግዳው ማዕዘን የሰቀለ የአፋር እስላም አለ!!! ይህን ስታይ ልብህን ደስስ ይለዋል፡፡
እንግዲህ እኔ ከተሰደድኩ በዓመቴ ሀገሬ በውስጤ ብትሆን አይግረምህ፡፡ ገና የሚጥሚጣ ቃሪያ ጣዕሙ ከምላሴ ላይ ሳይጠፋ ሀገሬ ከውስጤ እንድትጠፋ እንዴት ትጠብቃለህ? ይኸው ግን አለልህ እንደዚህ ከሀገሩ ከወጣ ሃያ ምናምን ዓመት እንዳስቆጠረው አፋር – እርሱ ከእነ ቤተሰቡ ኢትዮጵያ ውስጡ ናት! በሆዱ ውስጥ አለች! በማጀቱ ውስጥ አለች! በሁለመናው ውስጥ ኢትዮጵያ አለች! ይህ ሰው በቅርብ አደጋ ደርሶበት ለመጎብኘት ከዘመድ ወዳጅ ጋር ወደ ቤቱ ዳግመኛ ሄድኩ፡፡
ይግረምህ ሲለኝ – በፍሪጁ አናት ላይ አንዲት በመሰኪያ ዘንግ ላይ የተሰቀለች ትንሽዬ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ባንዲራ ጨምሯል – አምስተኛውን ባንዲራ ማየቴ ነው፡፡ እና ከዚህች አምስተኛዋ ባንዲራ ጎን ምን ጉብ አድርጎ ቢጠብቀን ጥሩ ነው?? — የአብይ አህመድ አሊን ፎቶግራፍ!!! ኡዉዉዉዉይይ!! አሁን ገና … አፋር ጉድ ሠራኝ!! የት ሂጄ ልሽሸው ግን ይሄን ሠላቢ ሰውዬ?! በየት በኩል አድርጎ እሰው ማጀት ውስጥ ገባ?! ብዬ በሆዴ መገረሜ አልቀረም፡፡ ‹‹ለመንገደኛ ሰው.. አይሰጡም ስንቁን፣ እየበላ ይሂድ.. አንጀት አንጀቱን…››፡፡
(ይኸው ሰውየው የሰው አንጀት እየበላ.. ውቅያኖስ ተሻግሮ.. በሰው ቤት ፍሪጅ አናት ላይ ጉብ ብሎ እንዳለ አለ፡፡ በበኩሌ በጋ እስኪመጣልኝ እየተጠባበቅኩ በቤቴ ካኖርኩት ከእነ አሳምነው ፅጌ መታሰቢያዬ – ከሰውየው አድናቂዎች ተርታ ራሴን ባሰናበትም፣ በአፋሩ ወገናችን ቤት ባየሁት ነገር መገረሜ ግን አልቀረም! እንግዲህ ይሁናቸው አንድዬ…!! የሚያምኑበት አምላክ፣ መጨረሻውን ጥሩ ያድርግለት – ብዬ በፅሞና ተሰናበትኩ!)
በነገራችን ላይ እዚህ ሀገር ካሉ ኢትዮጵያውያን ላይ ያላየሁት አንድ ነገር ንባብን ባህል አለማድረጋቸውን ነው፡፡ ለነገሩ ቀን ከሌት እየለፉ፣ የቤተሰብ ኃላፊነት ተሸክመው፣ ከስንት ቻሌንጅ ጋር እየተጋፈጡ በሚኖሩበት የስደት ምድር ላይ – መጽሐፍ በየት በኩል ይታያቸዋል? መጽሐፍ ቅዱሱን ካነበቡ በቂያቸው ነው፡፡ በውክቢያ ዓለም ውስጥ ማን አላነበባችሁም ብሎ ይፈርድባቸዋል? እዚህ ያለውን ብዙውን ከንባብ የነጻ ኢትዮጵያዊ (እና ኤርትራዊ) ስመለከት… ከጥቂት ዓመታት በፊት ኢትዮጵያዊው አርቲስት በቀለ መኮንን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሚገኘው የገብረክርስቶስ ደስታ የጥበብ ማዕከል ውስጥ ስለኢትዮጵያውያን የጥበብ አረዳድ ያቀረበው አንድ የጥናት ፕሬዘንቴይሽንን ያስታውሰኛል፡፡ ‹‹እኛ ኢትዮጵያውያን ቪዥዋል ነን!›› ነበረ ያለው፡፡
እንደ እርሱ ድንቅ ትንታኔ የሺኅ ዓመታት የስነፅሑፍ ታሪክ እያለንም – ከጥቂት ልሂቃንና ካህናት በቀር – አብዛኛው ሕዝባችን ከጽሑፍ ይልቅ የሚመርጠው – ሥዕልን ነው፡፡ ትዕይንትን ነው፡፡ ለዚህ ነው ብዙዎቹ ቤተመቅደሶቻችን ግድግዳዎችና ጣሪያዎች ሁሉ በቀለማት ባሸበረቁ የቅዱሳን ታሪኮችና ገድሎች ሥዕሎች ተሞልተው የምናገኛቸው፡፡ ለዚህ ነው በብዙው ሰው አዕምሮ ውስጥ ቅዱሳን ከፅሑፍ ተመዝዘው ሳይሆን – በአካል በአምሳል ከጥበብ መስታወት ተመዝዘው ህያው ሆነው በጉልህ የሚመላለሱት… ያለው ትዝ ይለኝ ጀምሯል፡፡
አርቲስት በቀለ መኮንን ያለው እውነቱን ሊሆን ይችላል፡፡ ግን ሕዝባችን የሥዕል እንጂ የጽሑፍ አፍቃሪ ካልሆነ – ለምን ከያንዳንዱ ጥንታዊ ያገራችን ሥዕሎች ግርጌ በሌላ ዓለም በማይገኝ አኳኋን  – ለምን ከየሥዕላቱ ሥር የሥዕላቱን ማንነት እና ምንነት በጽሑፍ የመግለጽ (የጽሑፍ ካፕሽን) ባህል ባገራችን ሊዘወተር ቻለ? እንዴ በቀለ?!! ምናልባት ሳናውቀው… እኛ ኢትዮጵያውያን ብዙሃን.. የጽሑፍም ሰዎች ነን እንዴ?!! (ወንድሜ! ካናዳ ካናዳ ስንገኝ እኛ ኢትዮጵያውያን ብዙሃን… ቪዥዋል ሶሳየቲዎች ነን፣ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ስንገኝ ደግሞ.. ምናልባት… ምናልባት… ኦዲዮ-ቪዥዋል ወ ካፕሽን ሶሳየቲዎች! Lol!)፡፡ የፈለገውን ይሁን! ይምጣብኝ ሀበሻ!!! አቦ!!!
ከጥቂት ወራት በፊት ነው፡፡ አንድ ቀን፡፡ ከምኖርበትን ከተማ የህዝብ ቤተ መጻሕፍት አንዱን እንኳ ሳላየው ብቀመጥ.. የእውነት የሀገሬ የጥበብ አድባሮች በዕርግማናቸው አይምሩኝም ብዬ… ድንገት ታክሲ ጠርቼ ወደ አንዱ ፐብሊክ ላይብረሪ አዘገምኩ፡፡ እንደዚያን ቀን ተደስቼ አላውቅም፡፡ ያገኘሁት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጀት (ዩኔስኮ) ያሳተመውን ባለ 865 ገጽ ”General History of Africa – Africa under Colonial Domination 1880-1935” የሚል ዳጎስ ያለ የአፍሪካ ጠቅላላ ታሪክ የተከተበበትን ብርቅዬ መጽሐፍ ነበረ፡፡ ከኢትዮጵያና ከላይቤርያ በስተቀር – የአፍሪካውያን ሁሉ አንድ በአንድ እንዴት በቅኝ ግዛት ሥር እንደወደቁ በዝርዝር ያሰፍራል፡፡ ምንጮቹ እጅግ የዳጎሱ ናቸው፡፡ የነጮችን የቅኝ ግዛት ወረራ ለመከቱት ለነፃዎቹ ጥቁር አፍሪካ የነጻነት ፀሐዮች – ለኢትዮጵያና ለላይቤሪያ – አንድ ራሱን የቻለ ምዕራፍ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ብዙ ማጣቀሻዎችን የተሞሉ፡፡
ያስደመመኝ ደግሞ የኛው ብርቅዬ ሀገር ወዳድ የፕ/ር ሪቻርድ ፓንክረስት ለዚያን የኢትዮጵያን ነገር ለሚመለከተው የዩኔስኮ ፕሮጀክት የተቻላቸው አዋጥተው ማለፋቸውን አለፍ አለፍ እያሉ የፕሮፌሰሩን ስም ይዘው ብቅ ከሚሉ ፉትኖቶች ማየት ይቻላል፡፡ እርሳቸው ሞተዋል፡፡ ሥራቸውን ግን ይሄው ውቅያኖስን ተሻግሮ የከፈተው ሁሉ የዓለም ሕዝብ እንዲያነበው ክፍት ሆኖ በጥበብ ሰበካ በክብር ተቀምጧል፡፡ ስም ከመቃብር በላይ ይኖራል የማለት ትርጉም ከዚህ በላይ ከወደየት ሊገኝ?!! ከየትም!! ክብር – በተለይ የሀገር ክብር – ከብር እንደሚበልጥ የሚያሳዩን ምሁራን አይጥፉ! የሚያሳዩን መሪዎች አይጥፉ!!
በዚህ የዩኔስኮ መጽሐፍ የነጻይቱ ኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት የእምዬ ምኒልክ ፎቶ አንድ ገጽን ሞልቶ በክብር ተቀምጧል፡፡ የላይቤሪያው የነፃነት ሐዋርያ አቻቸው የፕሬዚደንት አርተር በርክሌይ ፎቶም ከእርሳቸው አለፍ ብሎ ተቀምጧል፡፡ እኚህ የነጻነት ሐዋርያት የክፉ ቀን መጽናኛ ናቸው!! የኩራታችን ምንጭ ናቸው!! ሀገራቸውን ያከበሩ፣ እና ያስከበሩን ክቡራን፡፡  አንተ ምኒልክን ባታውቃቸው… የፈለግክበት ሂድ… ድፍን ዓለም ያውቃቸዋል!!! እንግዲህ ምን ትሆን?!! ‹‹አይ አም ኧ ፕራውድ ብላክ አፍሪካን!››
(በነገራችን ላይ… ይህን መጽሐፍ ከቤተመጻሕፍቱ ገጠመኜ በኋላ እንዴት ብዬ አፈላልጌ እንዳገኘሁት ዝርዝሩ ለራሴ ተከድኖ ይብሰልልኝ፣ ነገር ግን በውስጡ ስለያዛቸው የሚያኮሩ የኢትዮጵያ እና የላይቤሪያ የነፃነት አንጸባራቂ ገድሎች ግን በቅርብ ቀን የተወሰነ ነገር ለማስፈር እመለሳለሁና – በምኒልክ ዘዬ – ጉልበት ያለህ በጉልበትህ፣ ጉልበት የሌለህ በጠሎትህ – ያን ለመታደም ከትተህ ቆየኝ – ኋላ ትጣላኛለህ!! – ለማለት ዳዳኝ!!)
‹‹…Today, you who are strong, give me of your strength, and you who are weak, help me by prayer››
        (- Emperor Menelik II of Ethiopia)
(Quoted in Harold G. Marcus, The Life and Times of Menelik II: Ethiopia 1844-1913, 1975, p. 160, Oxford Clarenden Press)
“ምኒልክ ማለፉን ለምትጠይቁኝ፤
ጥንትም አላለፈ ዛሬም አይገኝ።”
   (-ቀኝ ጌታ ዮፍታሄ ንጉሤ)
 
እናት ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!
Filed in: Amharic