>

ግልጽ ደብዳቤ ለክቡር ጠ/ሚ/ አብይ አህመድ - ጉዳዩ:- ብቸኛው የህሊና እስረኛ ጋዜጠኛ ፍቃዱ ማህተመ ወርቅ እንዲፈታ ስለመጠየቅ

ግልጽ ደብዳቤ ለክቡር ጠ/ሚ/ አብይ አህመድ 

ፅናት ለኢትዮጲያ የሀገር ወዳዶች ማህበር
ጉዳዩ :- ብቸኛው የህሊና እስረኛ ጋዜጠኛ ፍቃዱ ማህተመ ወርቅ እንዲፈታ ስለመጠየቅ
 
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር
ፅናት ለኢትዮጲያ የሀገር ወዳዶች ማህበር ላለፉት 5 አመታት በሀገራችን ዴሞክራሲያዊ ለውጥ እንዲመጣ ከለውጡም በኋላ ሽግግሩ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ከፍተኛ ትግል እያደረገ የሚገኝ፣ በመላው አለም የሚገኙ በርካታ ሀገር ወዳድ ኢትዮጲያዊያን የሚገኙበት ማህበር ነው። በነዚሁ አመታት ውስጥ ፅናት ካከናወናቸው አበይት ተግባራት መሀል ሀሳባቸውን በሰላማዊ መንገድ በመግለፃቸው ብቻ በእስርና በስደት መከራ እና እንግልት ሲደርስባቸው ለነበሩ የፖለቲካ እና የፕሬስ ማህበረሰቡ አባላት ፍትህ እንዲያገኙ መወትወት ነበር።
 
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር
በትናንትናው እለት እርሰዎ ባቀረቡት ሀሳብ መሰረት ጠቅላይ አቃቤ ህግ  ምህዳሩን ለማስፋት በሚል 63 እስረኞችን በምህረት እንዲፈቱ መወሰኑን ሰምተናል። የፅናት አባላትም ይህንን በጎ እርምጃ በደስታ የተቀበልነው ሲሆን ተመሳሳይ እርምጃዎችንም የምናበረታታ መሆኑን ለመግለፅ እንወዳለን።
ይሁን እንጂ ሲጀመርም መታሰር ያልነበረትን ከሆነም በዚህ ምህረት መካተት የነበረበትን ጋዜጠኛ ፍቃዱ ማህተመ ወርቅን ስናስብ ስሜታችን ክፉኛ ተጎድቷል። ጋዜጠኛ ፍቃዱ የግዮን መፅሄት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ነበር። ሀሳብን የመግለፅ ነፃነት አደጋ ላይ በነበረበት በዚያ የጨለማ ዘመን ጋዜጠኛ ፍቃዱ የሀሰት ክስ ተመስርቶበት ጉዳዩ በፍርድ ችሎት መታዬት ጀመረ። ጊዜው 2008 ዓ/ም ነበር ከ40 በላይ ጋዜጠኞች በስደት ሀገራቸውን ጥለው የሸሹበት እና ሌሎችም ለአካልና ለመንፈስ ሰቆቃ የተዳረጉበት።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር 
ለውጡ ይዟቸው ከመጣቸው ትሩፋቶች አበይቱ በ10000 ዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካና የህሊና እስረኞች እንዲፈቱ መደረጉ ነው። በጣም የሚያሳዝነው ግን ይህ ከሆነ ከበርካታ ወራት በኋላ ጋዜጠኛ ፍቃዱ ማህተመ ወርቅ ከለውጡ በፊት ሲንከባለል በመጣ ክስ የ7 አመታት እስራት ተፈርዶበት ዘብጢያ ከወረደ እነሆ ወራትን አስቆጥሯል። በለውጡ አከርካሪያቸው የተሰበረው የጨለማው ዘመን ቅሪቶች ፍትህን ይበይኑበት ዘንድ የተሰየሙበት ወንበር ላይ ሆነው በዚህ ሰው ላይ የብቀላ በትራቸውን አሳርፈውበታል።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር 
ጋዜጠኛ ፍቃዱ በአሁን ሰአት በኢትዮጲያ ውስጥ በእስር ላይ የሚገኝ ብቸኛ ጋዜጠኛ ነው። በበርካታ አስከፊ ወንጀሎች ላይ ዋና ተዋናይ የነበሩ ሰዎች ባልተጠየቁበትና በምህረት ተለቀው፣ እንዲሁም በስልጣን እርከን ላይ ጭምር በሚገኙባት ሀገር የዚህ ንፁህ ሰው በእስር ላይ መገኘት እጅግ አሳዛኝ እና ለሀገራችንም ሆነ ለለውጡ ሂደት መጥፎ ገፅታ ነው ብለን እናምናለን። በተለይም እርሰዎ በባእዳን ሀገራት የሚገኙ ኢትዮጲያውያንን ሳይቀር አስፈትተው ይዘዋቸው ሲመለሱ ባይኖቻችን የተመለከትን ሰዎች የወንድማችን በደል ለእርሰዎ  ባለመገለጡ እንጂ በዝምታ ያልፉታል ብለን ከቶውንም  ማሰብ አልተቻለንም። ስለሆነም ጋዜጠኛ ፍቃዱ ነፃነቱን ይቀዳጅ ዘንድ ክቡርነትዎ አስፈላጊውን መመሪያ እንዲሰጡ በታላቅ አክብሮት እንጠይቃለን።
ፈጣሪ ኢትዮጲያን አብዝቶ ይባርክ!
ፅናት ለኢትዮጲያ የሀገር ወዳዶች ማህበር
Filed in: Amharic