>

የዓድዋ ጦርነት -  ታላላቆቹ የውጊያ አውዶች !!! (ጳውሎስ ኞኞ )

የዓድዋ ጦርነት –  ታላላቆቹ የውጊያ አውዶች !!!
ጳውሎስ ኞኞ 
ሀይማኖት ተፈራ
፪) የመቀሌ ውጊያ 
የመቀሌው ምሽግ ዙሪያውን በድንጋይ ካብ በጥብቅ የተሠራ በቀላሉ የማይደፈር ምሽግ ነበር። ግን ደግሞ አንድ ጉድለትም ነበረው ይኸውም በአካባቢው የሚገኘው ምንጭ ከምሽጉ ውጪ ነበር የሚገኘው።
ኢጣልያኖች በበርሜል ቀድተው ያስቀመጡት ውሃ ቢኖርም ብዙም የሚያወላዳ አልሆነም። እቴጌይቱም ይሄን ያውቁ ስለነበር ለአዛዥ ዘአማኑኤል “ሂድና ከሊቀ መኳስ አባተ ምንጩን ለመያዝ ትችል እንደሆነ ተመካከር” ብለው አዘዙዋቸው። እርሳቸውም ወደ ሊቀ መኳስ አባተ ሄደው ቢነጋገሩ “የምንጩ ስፍራ ጥልቅና ለኢጣልያኖች ምሽግ የቀረበ ነው። በምንጩና  በምሽጋቸው መካከል በግምት አንድመቶ ሃምሳ ክንድ የሚሆን ርቀት ቢኖር ነው። ቢሆንም መተላለፊያውን በመድፍ ሳስጠብቅ ቆይቼ ሌሊት ሲሆን ወታደር ልኬ ምንጩን አስይዛለሁ” በማለት መለሱ እቴጌይቱም በዚህ ደስተኛ ሆኑ።
“ሂዱና የምንጩን ውሃ ተቆጣጠሩ ከምሽግ ገብተን እንዋጋለን ያላችሁ እንደሆነ ግን መንገዱ ጠባብ  ስለሆነና እናንተም ብዛት ስላላችሁ ከኢጣልያ መድፍና መሳሪያ በላይ እርስ በርሳችሁ ተረጋግጣችሁ ታልቃላችሁ” በማለት ምንጩን እንዲይዙ ላኳቸው።
ጣልያኖች ኢትዮጵያውያኑ በምንም አይነት ምንጩን የመያዝ ሃሳብ ይኖራቸዋል ብለው አላሰቡም ነበር።
መያዙን ሲያውቁ መድፎቻቸውን ጎትተው መጥተው ተኩስ ከፈቱባቸው ሆኖም ግን ኢትዮጵያውያኑ ጠንክረው ስለተዋጉ ኢጣልያኖች ወደ ምሽጋቸው መመለሳቸው ግድ ሆነ። ሊቀመኳስ አባተም ለአስር  ቀናት ሳይንቀሳቀሱ ውሃውን በመድፍ እየጠበቁ ታላቅ ጀግንነትን ፈፅመዋል። ጣልያኖች ጥር ዘጠኝ ለአስር አጥቢያ ሌሊት በሰባት ተኩል፣ በስምንት ተኩል፣ በአስር ሠዓት ከሩብና አስራአንድ ሠዓት ላይ እየወጡ በመዋጋት ምንጩን ሊያስለቅቁ ቢሞክሩም የሚቻላቸው አልሆነም። ውሃ ጥሙ እየባሠባቸው ሲሄድ ግን ጥር ፳፩ ቀን ለቀው ለመውጣት ተገደዋል።
፫) ታላቁ የዓድዋ ውጊያ
የባሻህ አውአሎምን “ሠንበት ስለሆነ አብዛኛው ወታደር አክሱም ፂዮንን ሊሳለም ይሄዳል” የሚል መረጃ ያመኑት ጣልያኖች በአራት ታላላቅ የጦር አዝማቾች እየተመሩ ኢትዮጵያውያኑን ድል አድርገው የአውሮፓውያንን የበላይነት ለማረጋገጥ እንዲሁም የአምባላጌና የመቀሌ ቂማቸውን ለመወጣት ከጦር ሠፈራቸው ቢወጡም ባልጠበቁት መልኩ ከባድና መራራ የሆነ ሽንፈትን አስተናግደዋል። ይሄም ድል በዓለም ጥቁሮች ሁሉ ዘንድ በደማቅ ቀለም ተፅፎ ሲዘከር ይኖራል።
የውጫሌው ስምምነትና እቴጌ ጣይቱ!!!
የእቴጌ ጣይቱ የአድዋ ገድል የሚጀምረው ለአድዋ ጦርነት መነሻ ከሆነው #ከውጫሌ ስምምነት ነው፡፡
ኮንት አንቶኔሊ የውጫሌ ውል እርሱ እንደፈለገው እንደማይሆን እና 17ኛዋ አንቀፅ እንደተሰረዘ በሰማ ጊዜ እቴጌ ጣይቱ እና አጤ ምኒልክ በተቀመጡበት እልፍኝ ገብቶ የ 17 ተኛዉ ክፍል ተሰርዞአል ተብሎ ተፃፈ በማለት አጤ ሚኒልክን ይጠይቃል አጤ ሚኒልክ ም ሁለታችን አንተና እኔ ተነጋግረን አንተ ወደህና ፈቅደህ የተፃፈ ቃል ነዉ ሌላ አልታከለበትም ባስተርጐሚህ የተናገርከዉ ነዉ አሉት። ከዛ ኮንት አንቶኔሊ እንዳልተሳካለት አዉቆ የዉሉን ወረቀት በጫጨቀዉና ጦርነቱ እንደማይቀር ተናግሮ ከልፍኝ እየወጣ እያለ “#እቴጌ_ጣይቱ ከት ብለዉ በመሳቅ የዛሬ ሳምንት አድርገዉ በዚህ የሚደነግጥ የለም ሂድ የፎከርክበትን አድርግ እኛም የመጣዉን እናነሳዋለን እግሩን ለጠጠር ደረቱን ለጦር ሰጥቶ አገሩን የማያድን ሰዉ ከዚህ የሌለ አይምሰልህ የገዛ ደሙን ገብሮ ለገዛ አገሩ መሞት ጌጥ ነዉ እንጅ ሞት አይደለም አሁንም ሂድ አይምሽብህ የፎከርክበትን በፈቀደህ ጊዜ አድርገዉ እኛም ከዚሁ እንቆይሀለን››
“ያንተ ፍላጐት ኢትዮጵያ በሌላ መንግስት ፊት የኢጣሊያ ጥገኛ መሆኗን ለማሳወቅ ነው። ነገር ግን ይህን የመሰለው የምኞት ሃሳብ አይሞከርም!! እኔ ራሴ ሴት ነኝ። ጦርነት አልፈልግም። ነገር ግን ይህን ውል ብሎ ከመቀበል ጦርነትን እመርጣለሁ!” በማለት ፈፅሞ በኢትዮጵያ ሉአላዊነት እንደማይደራደሩ መናገራቸውን
ጳውሎስ ኞኞ አጤ ምኒልክ በሚለው መፅሃፍ አስፍረዋል፡፡
Filed in: Amharic