>

"ማጆር ቶዚሊ ሞተ፣ አንጊራ ሞተ፣ ማንፍሬዲኒ ሞተ፣ ሁሉንም አበሾቹ ፈጇቸው!" (ከጦርነቱ የተረፈ ወታደር) 

“ማጆር ቶዚሊ ሞተ፣ አንጊራ ሞተ፣ ማንፍሬዲኒ ሞተ፣ ሁሉንም አበሾቹ ፈጇቸው!”

ከጦርነቱ የተረፈ ወታደር 
በስንታየሁ ሀይሉ
* . . .የተተከለው ድንኳን ሲታይ ከብዛቱ የተነሣ አፍሪቃ አውሮጳን ለመጠራረግ የተነሣች ይመስላል፡፡ የጦርነቱ ዕለት ኢትዮጵያውያኑ ደማቅ ቀለም ያለው ካባ ለብሰው፣ የነብርና ያንበሳ ቆዳ ለብሰው አዝማሪዎቹ እየዘፈኑ፣ ቄሶች፣ ልጆች፣ ሴቶች ሳይቀሩ ፀሐይዋ ፈንጠቅ ስትል በተራራው ላይ በታዩ ጊዜ የኢጣሊያን ጦር አሸበሩት፡፡›› ቀጠለናም ፡ “ኢትዮጵያውያን ባበደ መንፈሥ ተዋግተው የአውሮጳን ቅኝ ገዢዎች አሸነፉ”…
የእንግሊዝ ጋዜጦች በአድዋ ድል ማግስት የዓለም ታሪክ ተገለበጠ ታላቅ የትውልድ ኃይል በአፍሪቃ ተቀሰቀሰ … ብለው ፃፉ፡፡ በኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ፡- ዘመናዊት ኢትዮጵያን የፈጠረ የተባሉት ዳግማዊ ዓፄ ምኒሊክ በሌሉበት (እርሳቸው በአካል ባልተገኙበት የነፃነት ተጋድሎ መሪዎች ጉባኤ) የአፍሪቃና የመላው ዓለም ጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተጋድሎ መሪ ተደርገው ተመረጡ፡፡ ጦርነቱ ከመደረጉ በፊት እ.ኤ.አ በ1880ዎቹ መጀመሪያ ጀርመን አገር በርሊን ከተማ ላይ በተደረገው የአውሮጳ ቅኝ ገዢ (ኮሎኒያሊስት) መንግስታት ሥልጣናትና ልሂቃን የጦር ጄኔራሎችና ሊቃውንት ስብሰባ ላይ ጥቁር ትልቅ ትል ነው ቅንቡርስ ነው እንጂ ነፍስ ያለው ሰው አይደለም ብለው የነበሩ አፈሩ፤ እውነትና ፍትህ ኢትዮጵያና አፍሪቃ ከበሩ፡፡ ከሲግመንድ ፍሮይድ የሳይኮ አናላይሲስ ጥናትና ምርምር በፊት፡- ጥቁር ህዝብ ትልቅ ትል ላይሆን ነፍስ ያለው ሰው ከሰውም ሰው ጀግና መሆኑን በተጨባጭ ያስመሰከረ የኢትዮጵያ ገበሬ ሠራዊት ነው፡፡
*
ታሪክ ጸሃፊው በርክሌይ እንዲህ ብሎ እማኝነቱን ከተበ፡ ‹‹. . .የተተከለው ድንኳን ሲታይ ከብዛቱ የተነሣ አፍሪቃ አውሮጳን ለመጠራረግ የተነሣች ይመስላል፡፡ የጦርነቱ ዕለት ኢትዮጵያውያኑ ደማቅ ቀለም ያለው ካባ ለብሰው፣ የነብርና ያንበሳ ቆዳ ለብሰው አዝማሪዎቹ እየዘፈኑ፣ ቄሶች፣ ልጆች፣ ሴቶች ሳይቀሩ ፀሐይዋ ፈንጠቅ ስትል በተራራው ላይ በታዩ ጊዜ የኢጣሊያን ጦር አሸበሩት፡፡›› ቀጠለናም ፡ “ኢትዮጵያውያን ባበደ መንፈሥ ተዋግተው የአውሮጳን ቅኝ ገዢዎች አሸነፉ”…በማለት ፅፏል፡፡
*
የድሉ ወሬ እንደደረስው በእንግሊዝ መናገሻ በሆነችው በለንደን ከተማ የሚታተመው ዘታይምስ ጋዜጣ ይኸንን በማያወዛግብ ሁኔታ ጥርት አድርጎ እንዲህ ሲል አስቀምጦታል፡
“ኢጣልያኖች በጀብድነትም ሆነ በጦር ስልት ከሌሎቹ አውሮጳውያን አያንሱም። ድሉ የመላ [ጥቊር] አፍሪቃ ድል መሆኑ አይካድም። ይኸም አስተያየት ወደፊት እያየለ ሄዶ በግልጽ የሚታይ ነው። ወሬው በነፋስ ክንፍ በረኻውን አቋርጦ እየበረረ በመጓዝ በነዚህ አገሮች ከጫፍ እስከጫፍ ተዛምቶ ሲያበቃ፣ አፍሪቃውያን አውሮጳውያንን ማሸነፋቸው አይቀርም የሚለውን ስሜት አነቃቅቷል። ነገሩ አስጊ በመሆኑ በኢጣልያኖች መሸነፍ መደሰት [ለነጮች] ተገቢ አይደለም። ሽንፈቱ የሁላችንና የሌሎችም ጭምር ሽንፈት ነው። ዛሬ ቅኝ ገዢ የሆነችውና ከዚያም ባሻገር የነገይቱ አውሮጳ ሽንፈት ነው።”
*
ካፒቴን ሞልቴዶ በጻፈው ደግሞ ‹‹. . . ከአራተኛው ባታሊዮን አንድ የሸሸ የኢጣሊያ ወታደር ወደ ካምፓችን ሲሮጥ መጣ፡፡ ካለሁበት በራፍ ላይ ሲደርስም ወደቀ፡፡ የእኛ ጦር ደጀን ነበር፡፡ በአረብኛ ቋንቋም ነገሩ ምንድን ነው? ምን ሆንክ? አልኩት፡፡ አለቁ፣ ሞቱ አለኝ፡፡ የወታደሩ ጠርቡሽ (ባርኔጣው) ካጠገቡ ወድቋል፡፡ ጠርቡሹን አቧራና ላብ በክሎታል፡፡ ኮቱ የመድፈኞች ኮት መሆኑን ባውቅም ምልክት ያለበት የኮቱ እጅጌ ተገንጥሎ ስለሌለ ከየትኛው መድፈኛ ክፍል እንደሆነ ላውቅ አልቻልኩም፡፡ በዚያ ክንዱ ላይም ክፉኛ ስለቆሰለ ደሙ በብዛት ይወርዳል፡፡ ዙርያውን ከብበን በጥያቄ አጣደፍነው፡፡ አንጌራ፣ ማንፍሬዲኒ፣ ቶዜሊ፣ አስካላ እያለ ይቃዣል፡፡
‹‹ምንድነው የምትለው! አልኩት
‹‹ሰላም መቶ አለቃ፡፡ አበሾች ደርሰዋል እዚህ ናቸው፡፡ የአራተኛው ወታደር ሁሉ አለቀ፡፡ ሁሉም ሞቱ፡፡ ማጆር ቶዚሊ ሞተ፡፡ አንጊራ ሞተ፡፡ ማንፍሬዲኒ ሞተ፡፡ ሁሉም፣ ሁሉም ሞቱ አለኝ፡፡
‹‹ንገረን እንዴት ሞቱ? አልኩት፡፡
‹‹ዛሬ ጧት፡፡ አበሾቹ ብዙ ነበሩ፡፡ ግማሹ ያህል ሞተ፡፡ ሌሎቹ ግን መጡብን፡፡ መድፍ ይተኮሳል፡፡ ጥይት ይተኮሳል፡፡ አበሾቹ ግን መጡብን፡፡ ኦህ ስንትና ስንት መሰሉህ፡፡
‹‹በማን ውስጥ ነበርክ? አልኩት፡፡
‹‹ማንፍሬዲኒ ውስጥ፡፡
‹‹አይተሃል እሱን?
‹‹አዎን አይቼዋለሁ፣ ሞቷል፡፡
‹‹አስካላንስ አይተኸዋል?
‹‹አዎን አይቼዋለሁ፣ ሞቷል (አስካላ ግን ቆስሎ ተማርኳል) ሁሉንም አይቻለሁ፡፡ ሁሉም ሞተዋል፡፡ ታመልጡ እንደሆነ እናንተም አምልጡ፡፡ አበሾቹ ከኋላዬ ናቸው፡፡ ጥፉ አለን››
Filed in: Amharic