>

አስገራሚው የሼህ ሁሴን ጅብሪል እና የእምዬ ወዳጅነት...!!! (በከድር ታጁ) 

አስገራሚው የሼህ ሁሴን ጅብሪል እና የእምዬ ወዳጅነት…!!!

 

በከድር ታጁ 
ሼህ ሁሴን ጅብሪልና አጤ ምኒልክ – አድዋ!
(አላማጣን አልፈህ፣ ማይጨው ትዘምታለህ
“ነጭ” አስመራ መጥቶ፣ “አድዋ” ትገጥማለህ
አድዋን እንዳያልፉ፣ በጣም ትዋጋለህ
ጦርህ ግን ያልቃሉ፣ “ድል!” ግን ታደረጋለህ፥)›
××××××
.
የሁለቱ ወዳጅነት ከማንም አይገጥምም፡፡ ተቃርቦታቸው ስንዝር አይገኘውም፡፡ ሼህ ሁሴን ጅብሪል መነጠፍ መጎንበስ ያለመውደዳቸውን ያክል፣ አጤ ምኒልክ ወደ-እርሳቸው ረመድ ማለቱ አልጠናቸውም፡፡ ትውውቃቸው ዕድሜን የራቀ፣ ወዳጅነታቸውም ከአጤ ቴወድሮስ ጀምሮ የጠበቀ ነበር፡፡ ግንኙነታቸው ግን በድርበቡ የተከረከመ ነው፡፡ ‘የጁ’ ከሙሉካን ቤት ያደገውን፣ በኋላም በ’እመት ወርቂት’ እገዛ ከግዞት ያመለጠውን፣ ቀጥሎም መስፍኖ፣ ዘውድ ጭኖና ነግሶ፣ ከዚያም ንጉሰ-ነገሥት ሆኖ የተዘባነነውን አጤ ምኒልክን – አራት ዓይናው ሼህ ሁሴን ጅብሪል አንቀርቅበው ያውቁታል፡፡ የማይደፈረውን የአጤ ቴወድሮስን ደጀ-ፊት፣ የማይገረሰስ ይመስል የነበረውን የአጤ ዮሐንስን ንግሠት፣ እናም የሌሎችን መሣፍንት ሹም-ሽረት፣ ዕድሜ-ልካቸውን ሲያወርዱና ሲጥሉ፣ ሲያነሱና ሲሰቅሉ የባጁትን ሼህ ሁሴንን – አጤ ምኒልክም አበጥረው ለይተዋል፡፡
.
ጊዜው ከአሁኑ የማይወዳደር፣ ዘመኑም ሌላ ነበር፡፡ ሹሙ፣ ወደ ሊቃውንት ደጅ ይዘምታል፡፡ የልቡ እስኪፈርጥለት ድረስ፣ ወገቡን ሰንጎ ጉድ-ጉድ ይላል፡፡ ጉዳይ ለማስፈፀም ላይ-ታች የማለት ያክል፡፡ የፈጣሪ ምድራዊ-ሹሞችን፣ በረ-ስሙዓንን ይውጃል፡፡ በዚያ ጊዜ ሼህ ሁሴን፣ እንደ ዋርካ ዙሪያቸውን በአደግዳጊ ተከምክመዋል፡፡ ሊቅና ደቂቅ፣ ፍቅና ምሩቅ፣ ሹምና አሽከር፣ አለቃና ምንዝር፣ ሙስሊምና ክርስቲያን በሙሉ አክቦ ቀንቷቸዋል፡፡ ከሼህ ሁሴን ቅሩቦች መካከል፣ አጤ ምኒልክ አንዱ ሊሆኑ ችለዋል፡፡ “ከየጁ ጀምሮ ነው ትውውቃቸው” እየተባለ ይነገራል፡፡ በአንድ ወቅት ሼህ ሁሴን፣ ‹የአጤ ዮሐንስን ምስቅል ውድቀት› ተናገሩ፡፡ ጉዱ ወገኖችን፣ በሀሳብ ከበሮ ደስታ አስቋጠሩ፡፡ መንበሩን ለመጨበጥ የተቃረቡትን ተስፋ አበሰሩ፡፡ አጤ ምኒልክ ይሄን ሰሙ፡፡ ሀገር በጃቸው ገብታ፣ ዘንፍታ ከሆነ ረግታ፣ ጠፍታ ከሆነ ለምታ የምትሄድበትን ቁና እያውጠነጠኑ በሀሳብ ተሲያት ኳተኑ፡፡ ይሄን ተሸክመው ወደ ሼህ ሁሴን ደጅ ጠኑ፡፡ የሚላስ-የሚቀመስ፣ የሚረገጥ የሚለበስ እየሰነቁ ዚያራቸውን አዘወተሩ፡፡
.
መቼም ‘ዓይኒቱ’ የሼህ ሁሴን ኳስ ነበረች፡፡ በዘመኑ ከእርሳቸው ሽሽግ፣ አንዲትም ጉዳይ የለች፡፡ ወደ ደጃቸው የዘወተሩትን አጤ ምኒልክንና ውጥናቸውን ለቅመው ያውቃሉ፡፡ እንዲህ እያሉ ተስፋ ልገሳ ጀመሩ፦
‹‹አርባ ጊዜ መጣህ የልብህ ይድረስ
ፊትም ዱአ አረገናል አንተ እንድትነግስ
ቀልብህ ደህና ቢሆን ብትወድ መጅሊስ
ስንቱ እስላም ወደደህ ሁሉን አለው ደስ፥
አንድ አመት ሲቀረው ምኒሊክ ሊነግስ
አላህ መተማ ላይ ይስላል መቀስ
እራስ የምትቆርጥ ያውም የንጉስ፥››
ዓይናማው ሼህ ሁሴን ለአጤ ምኒልክ እንዲሁ ብስራት እየሰደሩ፣ በሰፊው ተናገሩ፡፡ ያለፈውን፣ ተጨባጩንና የወደፊቱን አንድም ሳያስቀሩ እየዘረዘሩ አወሩ፡፡ አጤ ዮሐንስን ከነ-ምንነቱ እያነሱ በረበሩ – ከአጤ ምኒልክ ፊት፣ ከባለፈው ሊያስተምሩ፡፡ የአጤ ምኒልክ ዚያራ ቀጥሏል፡፡ የሼህ ሁሴን ንግሪያም ሥር ይዟል፡፡ ጊዜ ጊዜን ውጦ ሄዷል፡፡ ዓመት ዓመትን ሽሮ ነጉዷል፡፡
.
‹‹አራት ወር ሲቀረው ምኒሊክ ሊነግስ
በመተማ በኩል ትጨሳለች ጭስ
እጅግም አትበጀው ለአፄ ዮሀንስ
አላህ ሽቶበታል አንገቱን ሊቀምስ›› – እያሉ፣ ሼህ ሁሴንም ልፈፋቸውን አፋጠኑ፡፡ አጤ ዮሐንስ “ክተት” ብለው ወደ መተማ ሲያቀኑ፣ ሼህ ሁሴን የልባቸውን ትንታግ ለኩሰው ተናገሩ፦
‹‹ምኒሊክ ደስ አለው ምጡ ሊፈረጅ
ዮሀንስ ክፉ ነው የለውም ወዳጅ
መተማ ደጉ አገር ገላገለን እንጅ፥
አላህ ገላገለን በዟሂር መከራ
እንግዲህ ምኒሊክ አይዞህ እንዳትፈራ
ዮሀንስ ሊሄድ ነው ጦሩን እየመራ
ሞቱ ብላሽ ሆነ እንዲህ ሲንጠራራ›› – አሉ፡፡ እንዳሉትም መተማ ላይ ድርቡሽና አጤ ዮሐንስ ተገበያዩ፡፡ አጤ ምኒልክም ንጉሰ-ነገሥት ዘ ኢትዮጵያ ሆኑ፡፡ የሁለቱ ወዳጅነት ከንግሥና በኋላም ቀጠለ፡፡ ሼህ ሁሴን በክብር እየተጠሩ ከቤተ-መንግሥት የሚታደሙ ሆኑ፡፡
‹‹የሸዋ አረጋ እናት ሀለቴን ያውቃሉ
ሁሴን መጣ ሲባል ቡንዎን ያጥባሉ
ቄጤማ ጎዝጉዘው አድሩስ ያጤሳሉ
ደስ ደስ እያልዎት በጣም ይስቃሉ›› – ይላሉ፣ ቤተኛ እንደነበሩ ሲጠቁሙ፡፡ አጤ ምኒሊክ በበኩላቸው፣ መስተ-ጋብሩ ላይ የዋዛ አልነበሩም፡፡
.
‹‹ሕዝቤ የጠንቅ-ዋይ ጅራት ሆነ›› በሚል ተነሳሽነት፣ ጉዳዩን ለማከም ከ60 በላይ ባህታዊያንንና ቃልቻዎችን አሰሩ፡፡ ትላልቁን ሁላ በጥርጣሬ አጎሩ፡፡ መላ ነበራቸው፡፡ የሚያስሩበት ዘዴም አላቸው፡፡ ‹ሆዴን ነፍቶ አምሞኛል፡ በሽታና መድሀኒቴን ንገሩኝ?› ብለው አልጋ ላይ ተኝተው ነበር፣ የሚታሰረውን ሁሉ ያሳሰሩ፡፡ ሼህ ሁሴንም የዚህ ፈተና አንዱ ሰለባ ነበሩ፡፡
‹‹ምኒሊክ ክፉ ነው በስንቱ ፈተነኝ
እንደአለፉት ጠንቋይ በእሳት ሊያቃጥለኝ›› – ይላሉ ክስተቱን ሲዘክሩ፡፡ የዓይናቸውን ነገረ-ወጊነት፣ እዚህ ላይ አፈነጠቁትና ግን፣ እጅግ “ጉድ” ተሰኙ፡፡
‹‹በራስህ ገብቼ በሆድህ ብወጣ
ከትረንጎ በቀር ሌላ ምንም ታጣ
ይህ ያልሆነ እንደሆን እኔ በጉድ ልውጣ
ሆድህን የሚገልጥ ሽማግሌ ይምጣ
ይህንን ጉድ ሳላይ ከቤትም አልወጣ
በሽታም ከሆነ እኔው በጉድ ልውጣ
ማንን ታሞኛለህ እኔ አልወድም ላግጣ
እኔ እሳት አልገባም ነግረንሃል ቁርጣ፥›› – ብለው ደነፉ፡፡ ‹አጤ ምኒልክ አምሟቸው ሳይሆን፣ ከሆዳቸው ላይ ትርንጎ ደብቀው የጫኑ› መሆናቸውን ከመኳንንታኑ ፊት ለፈፉ፡፡ አጤ ምኒልክ ፈተናቸውን አጠፉ፡፡ ከተኙበት ተነስተው፣ ጠብ-እርግፍ እያሉ ለሼህ ሁሴን ተንፏፉ፡፡ ላይ ታች እያሉ በከበሬታ ተነጠፉ፡፡
.
ከዚህ ዕለት ጀምሮ፣ አጤ ምኒልክ ፍቅራቸው እጥፍ ድርብ ሆነ፡፡ ከበሬታቸው ጨመረ፡፡ አመኔታቸው ከፍ አለ፡፡ ወዲህም ልባቸው፣ ለሼህ ሁሴን ቃል ውስጠ-ላዩን ሰጠ፡፡ ልቦናቸው በፈተናና በምርመራ ደርጅቷልና፣ ከሼህ ሁሴን የሚወጣውን ንግርት ሁሉ ያለጥርጥር ኖላዊ-ተቀባይ ሆነ፡፡ አጤ ምኒልክ “እንዲህ ልክና-መልክ ነስተው” ከሚያምኗቸው፣ ቃላቸውን ያለ-ሣንክ ከሚቀበሏቸው፣ ከታላቁ ሼህ ሁሴን ጅብሪል በኩል ነበር – የአደዋ ክስተት፣ ጦርነትና ድል አድራጊነት ቀድሞ የተነገራቸው፡፡ ትንቢቱ – ለሥጋ ትጥቅ፣ ለመንፈስ ስንቅ ይታጠቁበት ዘንድም ጉልበትና ብርታት መቋጠሪያ ሆኖ አገለገላቸው፡፡
‹‹ስራቸው ባለጌ አህያ እሚበሉ
ባህር ወዲያ ማዶ ክፉ ሰዎች አሉ
ሐበሻን ለመውረር ሀሳብ ያስባሉ፥
አላማጣን አልፈህ ማይጨው ትዘምታለህ
“ነጭ” አስመራ መጥቶ “አድዋ” ትገጥማለህ
አድዋን እንዳያልፉ በጣም ትዋጋለህ
ጦርህ ግን ያልቃሉ፣ “ድል” ግን ታደረጋለህ፥›› – በማለት ብዙውን ጉዳይ፣ ሼህ ሁሴን እንዲህ ሳያመሳጥሩ ከተቱ፡፡ የንጉሱንና የሐበሻውያኑን ዘማችነት፣ የአታካቹን ጦርነት ሁነት፣ እንደ-ዘበት ሰንዝረው ወተወቱ፡፡ ዘመነ-አዝማናት የሚሻገረውን የአድዋ-ድል፣ ቀድመው አበሰሩ፡፡
.
‹ተራራውን ለማንቀሳቀስ ምኞት ሳይሆን፣ ተፈላጊው ዕምነት ነው›፡፡ ንጉሰ-ነገሥቱ፣ ለወራት የጦርነት ዝግጅት ሲያደርጉ፣ በድል-አድራጊነት ወኔ የታፈጉ፣ በምሉዕ ዕምነት ለአጥቂነት የተረጋጉ እንደነበሩ መዋዕለ-ህይወታቸው ይጠቁማል፡፡ ከዚህ የድል አድራጊነት የዕምነት ፋና ጀርባ፣ ባለ-ራዕዩ ሼህ ሁሴን ነበሩ፡፡ ‹ሰዎች አንድ ነገር ሊደርስባቸው እንደሆነ ሲተነብዩ፣ አሉታዊ ሀሳቦች ውስጠ-ህሊናቸው ላይ ስለሚንፀባረቁ፣ የመሆን ዕድሉ ሰፊ ነው› ይላሉ፣ ሀሳባውያን፡፡
.
ሼህ ሁሴን፣ የአድዋውን አዝማች በአዎንታዊ የአቸናፊነት መንፈስ አበልፅጎ በመሙላት ረገድም፣ ተቀዳሚ አይረሴ ይሆናሉ፡፡ የእርሳቸውና መሰል የዚያ-ጊዜ ኢትዮጵያውያን ንቁጥ ሚናዊ ድማሬ – የአድዋ ድል ፅንሰተ-ፍሬን ቀድሞ ቋጥሯል፡፡ የአመራሩ ብልፁግ ችሎታ ግን፣ ሁሉንም ትልም “ዝንታለማዊ” ወደሆነ ታሪክ እንዲሻገር አብቅቷል፡፡ “COLLAPSE: How Societies Choose to Fail or Succeed” በተሰኘ መጽሀፍ፣ በማህበራዊና ፖለቲካዊ ሥርዓቶች ውድቀትና ስኬት ላይ፣ ሰፊ ጥናት ያደረገው ‘ጃሬድ ዲያመንድ’ – የአመራር ችግር፣ የውድቀቶች ሁሉ ቁልፍ ምክንያት መሆኑን ያትታል፡፡ እናም፣ ወደ አድዋ ሲተምሙ – ‘ጋን በጠጠር እንደሚደገፍ’ በአስረጅነት እየተንገታገቱ፣ ‘ድር ቢያብር  አንበሳ ያስር’ን እየተረቱ፣ ከ’አንድ ብርቱ ሁለት መድኃኒቱ’ን አውስተው እየወተወቱ የዘመቱ፣ በዚያ አግባብም ድል ያስመቱ አመራሮች አበርክቶም፣ አድዋ ላይ ለተገኘው ስኬት መራሔ ተጠቃሽ ይሆናል፡፡ ዞረም-ቀረም፣ ከ124 ዓመታት በፊት፣ በአያቶች ህብርና ክቡር፣ እንዲሁም ንቡር መሰዋዕት የተገኘው የሁሉም-ድል – ትውልዳን ከሀሳብ ድኑዛዜ ሲነቁበት የኖረ፣ እኛም እንድንስፈነጠርበት የተሰመረ፣ ወደፊተኞችም እንዲመጥቁበት ሆኖ የተነበረ “አይሻሬ-ክስተት” ነው!!!
.
ዋቢዎች
– BRIAN JAMES፣ “Invisible Actors፡ The Oromo And The Creation Of Modern Ethiopia(1855-1913)”
– አፈወርቅ ገብረ-እየሱስ፣ “ዳግማዊ አጤ ምኒልክ(ሮማ፣ 1901)”
– ቦጋለ ተፈሪ፣ “ትንቢተ ሼህ ሑሴን ጅብሪል(1985)”
– ሷልህ ሙሀመድ፣ “ትንቢተ ሼህ ሁሴን ጅብሪል(2004)
– ዘመነ-ታሪክ
– ወንድሙ አሳምነው፣ “የአመራር ስነ-ልቦና(2007)”
– ጦቢያ መጽሔት ቁ-9 1995
– ሌሎች ልዩ ልዩ
Filed in: Amharic