>
6:48 pm - Wednesday June 7, 2023

የገሩ ሰው ስንብት...!!! (አባይ ነህ ካሴ)

የገሩ ሰው ስንብት…!!!

አባይ ነህ ካሴ
ጋሽ ውብሸት ወርቅዓለማሁ መታመሙን ሳልሰማ ማረፉን ትናንት ማታ ባለሁበት ሀገር አቆጣጠር ለእኩለ ሌሊት አንድ ሠዓት ሲቀረው ሰማሁ፡፡ አንዳች ነገር የወደቀብኝ ያኽል ደነገጥሁ፡፡ ባለፈው በጠና ታምሞ እግዚአብሔር አትርፎት ነበር፡፡ ዓመት ቢኾነው ነው፡፡ ያኔ ተፈርቶ ሳለ ተርፎ አሁን አሸለበ፡፡ መንገዳችን ሁሉ እንደዚህ ግራ የገባው ነው፡፡ ሔደ ሲሉት መምጣት አለ ሲሉት መሔድ ፡፡ ነፍሱን በአፀደ ገነት በቅዱሳን እቅፍ ያሳርፍልን!
እኔና ጋሽ ውብሸት ወደ ሃያ ዓመት የሚጠጋ ወዳጅነት አለን፡፡ አጋፔ የሚባል በቅዱስ ሚካኤል ስም የተመሠረተ የጽዋ ማኅበር ካላቸው ታላላቅ ሰዎች አንዱ ነው፡፡ ለረዥም ጊዜ የማኅበሩ ሙሴም እንደነበረ ዐውቃለሁ፡፡ በቀሲስ ጌታቸው ደጀኔ እና በጋሽ ሰለሞን ታደሰ አማካኝነት ከዚህ ማኅበር ጋር በቅርበት ኾነን ብዙ መንፈሳዊ ሥራዎችን ሠርተናል፡፡ ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ የዚህ ማኅበር አባል ነበሩ፡፡ ፈቃዳቸውን አላገኘሁም እና ስም ልጠራ አልቻልሁም እንጅ ሌሎች ታላላቅ ሰዎች የዚህ ጽዋ ማኅበር አባላት ናቸው፡፡
እንደ አንዳንድ ዘመነኞች ቀን አሳልፈው ሳይኾን በዕለቱ ዝክራቸውን በሥርዓቱ ይዘክራሉ፡፡ ሰፊ የጸሎት እና የትምህርተ ወንጌል መርሐ ግብር አላቸው፡፡ ታላላቆቹ ወንጌል ሲነገር በታናሽነት (በአትሕቶ ርእስ) ይቀመጣሉ፡፡ ጊዜ ሰጥተው ይማራሉ፡፡ ጥያቄ ካላቸው ይጠይቃሉ፣ ይሞግታሉ፡፡ ከወንድሜ ከዲያቆን ዳንኤል ክብረት ጋር እየተፈራረቅን የቻልነውን አድርገናል፡፡ ይናፍቁናል እንንናፍቃቸዋለን፡፡ ኋላ ደግሞ ቃለ እግዚአብሔር ከአፋቸው ሲወጣ የሚገመጥ አካል ያለው የሚመስለው ሊቀ ማዕምራን ደጉዓለም ካሣ የማኅበሩም አባል ኾነው እያስተማሯቸው አሉ፡፡ እርግጥ አሁን ሊቀ ማዕምራን በጡረታ ምክንያት ከአዲስ አበባ ራቅ ብለዋል፡፡
ከጋሽ ውብሸት ጋር በጣም በቅርበት ለማገልገል የቻልሁበትን አጋጣሚ ላስታውስ፡፡ ጊዜው ከ፲፮ ዓመታት በፊት ፲፱፻፺፬ ዓ.ም. ነው፡፡ ማኅበረ ቅዱሳንን ለ፪ተኛ ጊዜ በዋና ጸሐፊነት እንዳገለግል ግድ የተባልሁበት ጊዜ ነበረ፡፡ ማኅበሩ አዲስ ዓይነት የአሠራር መዋቅር ዘርግቶ በከፍተኛ ትጋት አገልግሎቱን የሚያቀላጥፍበት የመጀመሪያው ዓመት በመኾኑ ሁሉም ተፍ ተፍ ሲል ላየው ይገርማል፡፡ ንቦች እንጅ ሰዎች አይመስሉም፡፡ ሁሉም ለተልዕኮው ዕረፍት የለውም፡፡
በዚያ የተቀባ የአገልግሎት ጊዜ ማኅበሩ ካቀዳቸው ዕቅዶች መካከል ታላቅ ዐውደ ርዕይ ማዘጋጀት ይገኝበታል፡፡ ይህ ዐውደ ርዕይ ከዚያ በፊት በአዲስ አበባ መዘጋጃ ቤት ተካሒዶ ከነበረው በዓይነቱም፣ በስፋቱም፣ በጥልቀቱም እጅግ የተለየ እና ከፍ ያለ እንዲኾን ታስቧል፡፡ ግን ከተያዘለት ዕቅድ ሦስት ወራት እስኪቀሩት አሳማኝ ሥራ አልተሠራም፡፡ በዚህ መካከል የማኅበሩ ሥራ አስፈጻሚ ሒደቱን ሲገመግም ከፍተኛ ክርክር በመካከላችን ኾነ፡፡ ገሚሱ የቀረን ጊዜ አጭር ስለኾነ ከምንዋረድ ቢቀርብን እና ዕቅዱን ከወዲሁ ብንሠርዘው ሲል ገሚሱ ደግሞ የለም መከፈል ያለበት መሥዋዕትነት ተከፍሎ መካሔድ አለበት አለ፡፡ በቀላሉ ሊቋጭ ስላልቻለ በይደር ታለፈ እና በአስቸኳይ ስብሰባ ራሱን ችሎ ለብቻው ጉዳዩ እንዲታይ ተወሠነ፡፡
ለማሰላሰልም ጊዜ ስለሚሰጥ እንደዚህ ያለው አካሔድ ብዙ ይጠቅማል፡፡ በተያዘው ቀጠሮ አቋሙን አለዝቦ ይመጣል የተባለው ብሶበት፣ አቋሙን ያነሣል የተባለው ይበልጡኑ አጠናክሮት መጣ፡፡ ሌሊት ሙሉ ታድሮበት እንደገና በቀን ቀጠለ፡፡ በማኅበሩ አሠራር ረዥም የስብሰባ ጊዜ ከፈጁብን አጀንዳዎች አንዱ ሳይኾን አይቀርም፡፡  አንድም የሰለቸ ግን አልነበረም፡፡ ሁሉም ትኩስ ሁሉም አዲስ ኃይል እና አዕምሮ እንደነበረው አስታውሳለሁ፡፡ በመጨረሻም በአንድ ጉዳይ ሥራ አመራሩን ማሳመን ከተቻለ ይካሔድ ወደሚለው ሁሉም አዘነበለ፡፡ እርሱም ዋና ጸሐፊው ሥራዬ ብሎ ካልያዘው እና ከመደበኛው የዋና ጸሐፊ ተግባር በከፊል ካልቀነሠ ፈጽሞ ሊሳካ እንደማይችል እና የዐውደ ርዕዩን ዐቢይ ኮሚቴ እርሱ እንዲመራው ተደርጎ የሚል አቋምም ላይ ተደርሷል፡፡ በዋና ጸሐፊው ጊዜአዊ የሥራ ድልድል ላይ ደግሞ ሥራ አመራሩ ማመን ይጠበቅበታል፡፡
ይህ አጀንዳ በአስቸኳይ የሥራ አመራር ጉባኤ እንዲታይ ከሰብሳቢው ከዲያቆን ሙሉጌታ ኃይለማርያም እና ከጸሐፊው ዶ/ር ወራሽ ጌታነህ ጋር ከስምምነት ተደረሰ፡፡ ሥራ አመራሩም ጉዳዩን እንደ ሥራ አስፈጻሚው ሁሉ በኹለት በተከፈለ መንገድ ተመለከተው፡፡ ከረዥም ውይይት በኋላ የሥራ አስፈጻሚው አሳብ ተቀባይነት አግኝቶ ባለችው አጭር ጊዜ ውስጥ ዐውደ ርዕዩ ለስኬት የሚበቃበት የተቀላጠፈ አሠራር እንዲዘረጋ እና ከዋና ጸሐፊው የተወሠኑት ኃላፊነቶች ወደ ምክትል ዋና ጸሐፊው ወደ ዲያቆን ዜና ብርሃኑ እና ወደ ተወሠኑ የሥራ አስፈጻሚ አባላት ድልድል ተደርጎ የተቻለው ሁሉ እንዲደረግ ተወሠነ፡፡
በዚህ ውሣኔ መሠረት ሳይውል ሳያድር የዐውደ ርዕዩ ዐቢይ ኮሚቴ በአስቸኳይ ተሰብስቦ የዕቅድ ክለሳ በማድረግ በታላላቅ ገዳማት አገልግሎቱ በጸሎት እንዲታሰብ የሚገባውን በማድረግ ሥራውን ማከናወን ጀመረ፡፡ በዚህ ጊዜ ነበር አማካሪ ቦርድ ያስፈልገናል ብለን የወሠንነው፡፡ ለአማካሪነት ያጨናቸው ጉምቱ ጉምቱ የኾኑ ታላላቅ ሰዎችን ነበረ፡፡ ከእነዚህም መካከል እነ አቶ ሽመልስ አዱኛ፣ ጋሽ ውብሸት ወርቅ ዓለማሁ፣ አትሌት አሰፋ መዝገቡ፣ ጋሽ ማሩ (ማሩ ብረታ ብረት)፣ እኅታችን ወይንእሸት . . . ይገኙበታል፡፡
ዘወትር ማክሰኞ ምሽት በማኅበሩ ጽ/ቤት የምናካሒደው የአማካሪዎች ቦርድ ጉባኤ ሁል ጊዜ ሙሉ አልፎ አልፎም በሚጋበዙ እንግዳዎች ምክንያት ከአፍ እስከገደፉ ጢም ብሎ ይሞላ ነበር፡፡ በጽሕፈት ቤታችን ዙሪያ ገባ የመኪና ዓይነት ይደረደራል፡፡ ሠርግ ያለ ይመስላል፡፡ እስከማስታውሰው አንዳቸውም ቀርተው አያውቁም፡፡ በአዲስ ጉልበት በአዲስ መንፈስ በልዩ ፍቅር ወደ ጉባኤያችን ይመጣሉ ከአንጀት ጠብ የሚል ምክራቸውን በየአቅጣጫው እየለገሱን ልባችንን አንጠልጥለውት ይሔዳሉ፡፡
ጋሽ ውብሸትን እና አቶ ሽመልስ አዱኛን ቀድሞ የሚደርስ ግን አልነበረም፡፡ ጥቁሯን ማርቸዲሱን ይዞ ከተፍ ይላል፡፡ ከፍተኛ ግምት ለሚሰጠው ጉዳይ ካልኾነ በጥቁሯ ማርቸዲሱን ይዞ መሔድ ደስ አይለውም፡፡ ወደ ማኅበረ ቅዱሳን ሲመጣ ግን አንድም ቀን ያለ እርሷ መጥቶ አያውቅም፡፡ ከገርነቱ ብዛት እንደ ልጅ ይታዘዛል፡፡ በኢትዮጵያ እና በተዋሕዶ በእርሱ ዘንድ ቀልድ የለም፡፡
የዐውደ ርዕዩ ዝግጅት እንደ ዳመራ እሳት ተቀጣጠለ፡፡ አብዛኛው አዲስ አበባ ያለው የማኅበሩ አባል ቀን ቀን መደበኛ ሥራውን ሲሠራ እየዋለ ማታ ማታ ቤቱ የማኅበረ ቅዱሳን ጽ/ቤት ኾነ፡፡ እንቅልፍን የተሰናበተው ኃይል የዋዛ አልነበረም፡፡ ቀኑ እየቀረበ ሲሔድ ከዋናው ማዕከል ጽ/ቤት አልፎ  የአዲስ አበባ ማዕከልን አጨናነቀው፡፡ በእነዚያ ሰፋፊ ግቢዎች ቦታ እናጣለን ብለን አንድ ቀን አስበን አናውቅም ነበረ፡፡ ግን ግድ ኾነ፡፡ ስለዚህ በቅድስት ማርያም አካባቢ ቤታቸውን ተከራይተው የሚኖሩ የማኅበሩ አባላት ቤቶቻቸውን ወደ ጊዜአዊ ጽ/ቤትነት መቀየር ተገደዱ፡፡
እንዲህ እንዲህ እያለ በዐቢይ ጾም ለደብረ ዘይት ዐሥር ቀን ሲቀረው ለአንድ ሳምንት ብቻ መስቀል አደባባይ በሚገኘው የአዲስ አበባ የዐውደ ርዕይ ማዕከል ዐውደ ርዕዩን ለማሳየት ቀጠሮ ይዘናል፡፡ ቅድሚያ ክፍያውንም በሙሉ ከፍለናል፡፡ ወዲህም ከዐውደ ርዕዩ ጎን ለጎን ታላቅ የዐውደ ጥናት መድረክ በአፍሪካ አንድነት አዳራሽ ተዘጋጅቷል፡፡ የአፍሪካ አንድነት ጽ/ቤት ለዚህ መድረክ ከፍተኛ የኾነ ገንዘብ እንደሚያስከፍል ዐውቀናል፡፡ ተመኑን ስንሰማ ከአዲስ አበባ ኤግዚብሽን በላይ ይጠይቃል፡፡  ነገር ግን ጉዳዩን በጥብዐት ጀመርነው፡፡ የኢትዮጵያን ባለውለታነት ጠቅሰን አጀንዳችንም የመላው አፍሪካ ስለኾነ በነፃ ሊፈቅድልን ይገባል ብለን በደብዳቤም በግምባርም ጠየቅን፡፡ እግዚአብሔር ይስጣቸውና ሻይ፣ ቡና፣ ቁርስ እና መክሰስ ራሳቸው ችለው ለአምስት ቀን በነፃ ፈቀዱልን፡፡ በዚህ ሁሉ መንገድ ስንሔድ እነ ጋሽ ውብሸት አብረውን ናቸው፡፡
የዐውደ ርዕዩ መክፈቻ ቀን እየደረሰ ነው፡፡ ልባችን ተራራ ነውና ፓትርያርኩ አቡነ ጳውሎስ እና የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ መርቀው እንዲከፍቱት አስበናል፡፡ ወንድማችን ገዛኸኝ የዐይንእሸት እና እነዚህ አማካሪዎቻችንን ይዘን ገፋንበት፡፡ መንገዶች ሁሉ ክፍት ነበሩ፡፡ የእነርሱን መገኘት ስናረጋግጥ አዲስ አበባ ውስጥ መቀመጫ ያላቸውን ሀገራት ኤምባሲዎች አምባሳደሮችም በክብር እንግድነት እንዲገኙ በፓትርያርኩ ደብዳቤ ጥሪ እንዲተላለፍ አደረግን፡፡
ጋሽ ውብሸት ድንገት ሮጥ ብሎ በቀን መጥቶ እንዴት ናችሁ? ጉዳዩ ቁም ነገር ነውና ጠንክሩ ብሎን ይሔዳል፡፡ ሞትም ይሙት እንዳለው ባለቅኔው ደራሲ ከማኅበሩ አባላት በተጨማሪ ብዙ የሰንበት ት/ቤት አባላት ከጎናችን እኛን ኾነው እኛን መስለው ተሰለፉ፡፡
ቀኑም ደረሰ፤ እንቅልፍ ማጣት ያጠወልጋቸው ይኾን ብለን የፈራናቸው እኅቶቻችን እና ወንድሞቻችን እንደ ንሥር አሞራ እየታደሱ ከብርታት ወደ ብርታት እንጅ ድካምን ማን አስቦት፡፡ እነ የወርቅ ውኃ ቀለሙ ማኅበራችንን አምስት ሳንቲም አናስወጣም ብለው በየቀኑ ለአንድ ሺህ ሰው የሚኾን ቁርስ፣ ምሳ እና እራት ወገባቸውን ታጥቀው በእሳት እየተጠበሱ ግን እየዘመሩ ያደረጉት ሁሉ በእግዚአብሔር እንጅ በሰው የሚቻል አይደለም፡፡ ሁሉን እንዳመሉ አባብለው እያበሉና እያጠጡ ያደረጉት ነገር ከዐይኔ ብሌን ልብ ውስጥ ሁልጊዜ ውን ውን ይላል፡፡ እሳቱ እሳት አደረጋቸው እንጅ አልነካቸውም፡፡ እናንተን የመሳሰሉ እኅቶች ፈጣሪ ባይሰጠን ኖሮ ምን እንኾን ነበር?
ከብሔራዊ ቤተ መጸሕፍት ወመዘክር ለመንካት የሚያስፈሩ መዛግብት በእምነት ተሰጡን፡፡ ታላላቅ ገዳማት ቅርሶቻቸውን ያለምንም ማመንታት አስረከቡን፡፡ የማዕከሉ ጥበቃዎች በውጭ እኛ በውስጥ ኾነን እዚያው አዳራሽ ውስጥ ማደሩን ተያያዝነው፡፡ በቀጠሮ መሠረት የዐውደ ርዕይ (ኤግዚብሽን) ማዕከሉ በዝግጅቶች ተሞላ፡፡ ሁሉም ተሰድሮ ስፍራ ስፍራውን ያዘ፡፡ ልክ መኾኑም በአማካሪ ቦርዱ እና በዐቢይ ኮሚቴው እንዲሁም በተለያዩ ተቺዎች ተረጋገጠ፡፡ በእርግጥ ከዋናው ዐውደ ርዕይ በፊት በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ አዳራሽ ያደረግነው ሠርቶ ማሣያ ዐውደ ርዕይ ብዙ ነገሮችን ለማስተካከል ዕድል ሰጥቶን አቃሎልናል፡፡
እናም ለመጀመሪያ ጊዜ ቤተ ክህነቱ እና ቤተ መንግሥቱ ከዘመናት መራራቅ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀራረቡበት መድረክ የዐውደ ርዕዩ መክፈቻ ዕለት ኾነ፡፡ የአሜሪካውን ጨምሮ የ፳፪ ሀገራት አምባሳደሮች ተገኙ፡፡ በርካታ ዲፕሎማቶችም ነበሩበት፡፡ ጸሎተ ኪዳን ደርሶ ወንጌል ተነብቦ ዐውደ ርዕዩ በታላቅ ድምቀት ተከፈተ፡፡ የቀረውን ሌላ ጊዜ ካስፈለገ እናወጋዋለን፡፡ ጋሽ ውብሸት ያኔ እንግዶቻችንን በሰላም ከሸኘን በኋላ አንተ አሽከር አለኝ “በዐይኖቹ የሞሉትን እንባዎች እየፈነጠቀ ዛሬ ብሞት አይቆጨኝም . . . ክብሬን ዐይቻለሁና” ብሎኝ ነበር፡፡ ግን እንደ ሕዝቅያስ ፲፭ ለእርሱ ቀሪ ፲፮ ዓመታት ነበሩት፤ እነርሱን ሲፈጽም ሔደ፡፡ እንዲህ ያለኝ በዐቢይ ጾም ውስጥ ነበረ፤ ገሩ ሰው የሔደውም በዐቢይ ጦም ኾነ፡፡ ነፍስ ይማር ጋሼ!
[ በነገራችን Exhibition ለሚለው ቃል ትክክለኛ አቻ ትርጉም የተሰጠው የዚያን ጊዜ ነበር። ዐውደ ርዕይ የሚለው ቃል የተፈጠረው እና ዛሬ ሁሉም የለመደው ቃል ያኔ ነው የተፈጠረው። ]
Filed in: Amharic