>
5:13 pm - Monday April 19, 6680

በእጅ አዙር የ1929ኙና የ1959ን ስምምነቶች መቀበል……!!! (ውብሸት ሙላት)

በእጅ አዙር የ1929ኙና የ1959ን ስምምነቶች መቀበል……!!!

         ውብሸት ሙላት
የሕዳሴውን ግድብ የውሃ አሞላልና አለቃቅ በተመለከተ ግብጽና ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር በድርድር ላይ ናቸው፡፡ ድርድሩ እየተደረገ የነበረው ደግሞ በዓለም ባንክና በአሜሪካ ፊት ነው፡፡ በታዛቢነትም ይሁን በአደራዳሪነት ብቻ ግልጽ ባልሆነ አቋም ተሳትፈዋል፡፡
ስለ ዓባይ ውሃ የዓለም ባንክ ሁልጊዜም ቢሆን ከግብጽ ባለነሰ ሊባል በሚችል መልኩ ወገንተኛ እንደሆነ አገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ጉዳይ ነው፡፡ አሜሪካም ብትሆን ግብጽ ከፍ ያለ ጆኦ-ፖለቲካዊ ጥቅምና ፋይዳ ስላላት ከኢትዮጵያ ይልቅ ለእሷ ማዘንበሏ አይቀሬ መሆኑ ቀድሞም የታወቀ ቢሆንም ዘግየት ብሎ ፕሬዚዳንት ትራምፕ የዕብሪትና የንቀት “ትእዛዝ” እስከመስጠት ደርሷል፡፡
ኢትዮጵያ እ.አ.አ. በ2015 ስለ ግድቡ ካርቱም ላይ ከተስማሙት ባፈነገጠ አካሄድ ግብጽ ብቻዋን አደራዳሪ መርጣ እንወያይ ስትል ኢትዮጵያም ምንም ሳታቅማማም የካርቱሙን ስምምነትም በመዘንጋት አሜን ብላ ተቀብላለች፡፡ ዋናው ስህተት የተፈጸመው እዚህ ላይ ነው፡፡ ግብጽ በቀደደችልን ቦይ ፈሰስን፡፡ ከዚያም አጣብቂኝ ውስጥ ገባን፡፡ ለዚያውም ያለምንም ፋታ በሳምንታት ልዩነት እየተመላለሱ፣ ለጥናትም ሆነ ለማሰላሰልና ለመምከር ጊዜ ሳያገኙ ድርድሩን ቀጠለ፡፡ ምንም እንኳን ያለቀ ስምምነት ባይኖርም በረቂቅ ደረጃ እንዳሉ የተነገሩ መረጃዎች አሉ፡፡ በእርግጥ ዘግይቶም ቢሆን፣ዋሽንግተን ላይ በሚደረገው ድርድር ኢትዮጵያ መሳተፍ እንደምታቆም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ ይፋ አድርገዋል፡፡
ድርድሩ ዋሽንግተን ላይ ይቀጥልም አይቀጥለም የሕዳሴው ግድብን የውሃ አሞላልና አለቃቀቅ በሚመለከት የቀረበው ረቂቅ ሐሳብ አሁን ባሉበት ደረጃ የተወሰኑ ነጥቦችን በመውሰድ ሊያስከትሉ የሚችሉትን አንድምታ እንቃኛለን፡፡ ከእነዚህ መረጃዎች በጥቅሉና በግርድፉ መረዳት የሚቻለው ኢትዮጵያ  የዓባይን ውሃ “ርትዓዊና ሚዛናዊ መርህ”ን (Equitable and Reasonable Utilization Principle) ከመከተል ይልቅ “ዓቢይ (ጉልህ) ጉዳት ያለማድረስ መርህ”ን (No Significant Harm Principle) ወደ መቀበል እየተንደረደረች ይመስላል፡፡ በአንድ በኩል የሕዳሴው ግድብ ውሃ የሚሞላበትን ወቅት፣ በሌላ በኩል ደግሞ የዓየር ንብረትን መሠረት ያደረገ የውሃ አሞላልና አለቃቅን የሙጥኝ ተብሏል፡፡
በረቂቅነት የቀረበው ስምምነት፣ ከወቅት አንጻር ግድቡ የሚሞላው በክረምት እንዲሆን፣ እንዲሁም የሚሞላበትን የጊዜ ርዝማኔ ማራዘምን ይጠይቃል፡፡ ከዓየር ንብረት ለውጥ አንጻር ደግሞ በኢትዮጵያ ድርቅ በሚከሠትበት ጊዜ የዓባይ ውሃ ስለሚቀንስ በግድቡ ከሚገባው የውሃ መጠን ምን ያህል መልቀቅ እንዳለባት የስምምነቱ አካል እንዲሆን ተፈልጓል፡፡ በዚህም መሠረት በኢትዮጵያ ድርቅ ተከስቶ ወደ ሱዳንና ግብጽ የሚያልፈው ውሃ ስለሚቀንስ ወደግድቡ ከሚገባውም ቀድሞ በግድቡ ከተከማቸውም መልቀቅን ግዴታ የሚደርግ ድንጋጌ የስምምነቱ አካል እንዲሆን ተፈልጓል፡፡
ድርቅን ብያኔ ለመስጠት የተሞከረው፣ ወደ ግድቡ የሚገባው ዓመታዊ የውሃ መጠን 37 ቢሊዮን ኩዩቢክ ሜትር (ቢኪሜ) ሲደርስ እንደሆነ፣ ከባድ ድርቅ ደግሞ አሁንም ወደ ግድቡ የሚገባው ውሃ 31 ቢኪሜ ሲሆን እንደሆነ ተገልጿል፡፡ የድርቁ ወቅት ከተራዘመም እንዲሁ ተጨማሪ ግዴታን በኢትዮጵያ መጣል ሌላው ዳርዳርታ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ወደ ግድቡ የሚገባውን 37 ቢኪሜ ውሃ ምንም ሳታስቀር ከማሳለፍ ጀምሮ ድርቁ ከቀጠለ በግድቡ ካከማቸችው 40 ቢኪሜ እንድትለቅም የስምምነቱ አካል እንዲሆን ተፈልጓል፡፡
አሁን ባለው መደበኛ የውሃ ፍሰት መጠን ወደግድቡ የሚገባው አማካይ የውሃ መጠን 49.5 ቢኪሜ ሆኖ ሳለ ከዚህ መጠን ላይ የድርቅ ማሳያ መስፈርቱ 37 ቢኪሜ እንዲሆን ነው በአቦሰጥ የተመረጠው፡፡ 12 ቢኪሜ ገደማ የሚሆን ውሃ በሙቀት መጨመር፣የመስኖ ፕሮጀክቶችን ጥቅም ላይ በማዋል ሊቀንስ ይችላል፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ከግምት ሳይገቡ 37 ቢኪሜ ውሃን እንደ የድርቅ መለኪያ አድርጎ ወደ ግድቡ የሚገባውን ውሃ ምንም ሳታስቀር እንዲታሳልፍ መስማማት በታችኛው ተፋሰስ አገራት ላይ ዓበይት/ጉልህ ድርሻ አለማድረስ ብቻ ሳይሆን “የራሷ አሮባት ሰው ታማስል ዓይነት” መርህን  መሆኑ ነው፡፡
በ1997 ዓ.ም. በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ የጸደቀው “ከመጓጓዣ በስተቀር ዓለምአቀፍ የውሃ ተጋሪዎች ስምምነት”ም (The Convention on the Law of Non-Navigational Uses of International Watercourses) በአንቀጽ ስድስት ላይ ርትዓዊና ሚዛናዊ መርህ ተጨባጭ ለማድረግ አመላካቾችን በማስቀመጥ አገራት ዓለም አቀፍ የውሃ ተፋሰስን በግዛታቸው ውስጥ እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው፤ እንዲሁም ሲጠቀሙም፣ሲያለሙትም ሆነ ጥበቃ ሲያደርጉ በእዚህ መርህ መሠረት መሆን እንዳለበት በማሳሰብ ዘርዝሯል፡፡
እነዚህ አመላካቾች ከፍርድ ቤት ፊት ሲቀርቡ፣በሕግ ሚዛን ላይ ሲቀመጡ ግርታን የሚፈጥሩ፣አፍን ሞልቶ ትርጉማቸው እንዲህ ነው ለማለት አዳጋች መሆናቸውን የተለያዩ የዓለም አቀፍ ሕግ ምሑራን ተናግረዋል፡፡ ድንበር ዘለል ወንዝን በጋራ በርትዓዊና ሚዛናዊ ሁኔታ ለመገልገል የተሻሉ አመላካቾች ስለሆኑ፣ ኢትዮጵያም የሕዳሴው ግድብን የውሃ አሞላልና አለቃቅ በሚመለከት ከግብጽና ሱዳን ጋር በምትደራደርበት ጊዜ ድርድሩ ውጤት ወደ ስምምነት ከመቀየሩ በፊት ብሔራዊ ጥቅም፣ አሁን ባይሆን እንኳን መጭውን ትውልድ የሚጎዱ እንዳይሆኑ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡
ድርቅ፣ከባድ ድርቅና ተደጋጋሚ ድርቅ የሚሉት ግብጽ ወለድ ብያኔዎችን መቀበል፣ የ1997ን ዓለም አቀፍ ስምምነት እንዲሁም የሔልስኒኪ ደንብን ምርኩዝ በማድረግ ሲታይ የ1929ኙ እና የ1959ኙን የግብጽና የሱዳን ስምምነትን መቀበል ይመስላል፡፡ በእርግጥ፣ርትዓዊና ሚዛናዊ ግልጋሎት እንዲለካ ከላይ የተገለጹት ስምምነትና ደንብ በመስፈርትነት የወሰዷቸው በርከት ያሉ ቢሆንም በዚህ ጽሑፍ የስምምነቱን የመጀመሪያዎቹን መሥፈርቶች ብቻ በመውሰድ እንመለከታለን፡፡ ቀሪዎቹን እንመለስባቸዋለን፡፡
ከአመላካቾቹ የመጀመሪያው  የመልክአ ምድር፣ሃይድሮግራፊ፣የውሃው መጠንን (ሃይድሮሎጂ) የሚመለከት ነው፡፡  የውሃው ምንጭ፣መጠንና የመሳሰሉትን ታሳቢ ስለሚያደርግ ሰማኒያ ስድስት ከመቶ ዉሃ የምታዋጣው ኢትዮጵያ ስለሆነች ውሃ በማዋጣት ምንም አስተዋጽኦ የሌላቸው ግብጽም ትሁን ሱዳን ከኢትዮጵያ ያነሰ ነጥብ ነው የሚያገኙት፡፡ ለኢትዮጵያ የተሻለ አመላካች ነው ማለት ይቻላል፡፡
መልክአ ምድራዊ ሽፋኑን ከግምት ሲገባ፣በዓባይ ተፋሰስ ጋር ተስስር ያለው የደቡብ ሱዳንና ሱዳን መሬት በስፋት ከኢትዮጵያም ከግብጽም ይልቃል፡፡  በተለይ በምታዋጣው የውሃ መጠን ኢትዮጵያ ርትዓዊና ሚዛናዊ የሆነ ግልጋሎት በማገኘት ረገድ ከሁሉም  የናይል ተፋሰስ አገራት ተደምረው ከሚኖራቸው ድርሻ ከፍ እንደሚል ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ የባሮ አኮቦና የተከዜን ውሃ ሳይጨምር 37 ቢኪሜ እንደዝቅተኛ መለኪያ በመውሰድ ይህን ያህል ውሃ  ሕዳሴው ግድብ ውስጥ ማቆር ይቅርና ሰተት ብሎ እንዲያልፍ መስማማት በተዘዋዋሪ የ1929ኙንም ሆነ የ1959ኙን የግብጽና ሱዳን የውሃ ክፍፍል ውል ዕውቅና መስጠትም ማጽናትና ማጽደቅም ነው የሚሆነው፡፡
በ1929ኙ ስምምነት የሱዳን 4.5፣ የግብጽ ደግሞ ከ49.5  የነበረ ሲሆን፣ በ1959ኙ ግን የሱዳን ድርሻ 14.5፣ የግብጽ ደግሞ 55.5 ቢሊዮን ኩዩቢክ ሜትር ነው፡፡
 ከባሮ-አኮቦ 14 ቢኪሜ፣ከተከዜ 10 ቢኪሜ ውሃ ለዓባይ ስለሚገበር የእነዚህ ግማሽ እንኳን ይህ 37 ቢኪሜ ላይ ከተደመሩ 49 ቢኪሜ ውሃ እንዳለ ማሳለፍ ግድ ይሆናል፡፡ ለዚያውም ከጥቁር ዓባይ ውሃ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ለሱዳንና ለግብጽ እንዳለ መለገስን ወዶና ፈቅዶ መስማማት እንደማለት መሆኑ ነው፡፡
ይሄ መቼም በርትዓዊና ሚዛናዊ ግልጋሎት መለኪያ ይቅርና ዓበይት ጉዳት ያለማድረስ መርህንም አልፎ፣ ልሙጡን ጉዳት ያለማድረስ መርህን (No Harm Rule) ወደ መቀበል የተቃረበ ነው፡፡
ለዚያውም በድርቅ ወቅት በሚሆንበት ጊዜ ይህን ያህል ውሃ ለመልቀቅ መስማማት “የራሷ አሮባት የሰው ታማስል” እንዲሉ በድርቅ ምክንያት ወደ ግድቡ የሚደርሰውን እንጥፍጣፊም ሳታስቀር ውሃ ለመስጠት፣ከዚህ መጠን በሚያንስበት ጊዜ ደግሞ ቀድማ በግድቡ ያቆረችውን እንድትሰጥ ውል ማድረግ ነው-ትርፉ፡፡
የዓየር ጠባይና የአካባቢው ሌሎች ተፈጥሯዊ ሁኔታዎችን ከግምት አስገብቶ በውሃው መገልገል ሌላኛው አመላካች ነው፡፡ በናይል ተፋሰስ ከሚተሣሰሩ አገራት መካከል በርሃማና የገጸ ምድር ውሃ ባለመኖር ቀዳሚዋ ግብጽ ስትሆን ድርቅን ጨምሮ የሕዝብ ህልውናን ከሚፈታተኑ ክስተቶች አንጻር ኢትዮጵያም የዓባይን ውሃ መጠቀም አማራጭ የለውም፡፡
ምናልባት የታላላቅ ሐይቆች አገራት ከግብጽና ከኢትዮጵያ አኳያ የተሻለ ተስማሚ የዓየር ጠባይና የተፈጥሮ ሁኔታዎች አላቸው፡፡ በመሆኑም ሁለቱም አገራት በከፍተኛ ሁኔታ ከናይል የመጠቀም ቅድምና ይኖራቸዋል ማለት ይቻላል፡፡ ይህ ማለት ግን በድርቅ ወቅት ሳይቀር በዚህ መጠን ግብጽ ዓባይን መበዝበዝ፣ ኢትዮጵያ ደግሞ የበይ ተመልካች እንድትሆን እንዳያደርግ መጠንቀቅ ያሻል፡፡
ማን ምን ያህል ውሃ ይደርሰዋል?
ከናይል ተጋሪ አገራት ሳያካትት፣ አብዝኃኛዎቹ በድንበር ዘለል ወንዞች የተሳሰሩ አገራት ውሃን በጋራ ለማስተዳደርና ለመገልገል ስምምነት አድርገዋል፡፡ ውሃውንም እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው የሚያስተዳድር የጋራ ተቋም ያላቸውም አሉ፡፡ ናይልን በሚመለከት ግን ግብጽና ሱዳን ለብቻቸው መጠቀምን እንጂ መጋራትንና መተባበርን ባለመሻታቸው ስምምነትም ተቋምም ሊኖር አልቻለም፡፡ እርግጥ ነው የተለያዩ ጥረቶች እንዳሉ ይታወቃል፡፡
 የናይል ውሃ ለብቻቸው ለመካፈል ስምምነት ሲያደርጉ የኖሩት ሁለቱ አገራት ብቻ ቢሆኑም በተለይ ጥቁር ዓባይን በሚመለከት ማለትም ባሮ-አኮቦን ኢትዮጵያ፣ደቡብ ሱዳን፣ሱዳንና ግብጽ፣ዓባይን ኢትዮጵያ፣ሱዳንና ግብጽ፣ተከዜ-አትባራን ኢትዮጵያ፣ኤርትራ፣ሱዳንና ግብጽ በጋራ የሚጠቀሙበትን ማእቀፍ ማዘጋጀት ለዚህም መተባበር አማራጭ የለውም፡፡
በሕዳሴው ግድብ አልፎ የሚሔደውን ውሃ፣ዓመታዊ መጠኑ 37 ቢኪሜ ከሆነ ኢትዮጵያ በቀጥታ እንድታሳልፍ ስምምነት ማድረግ፣ለሱዳንና ለግብጽ ዝቅተኛው ድርሻቸው ቢያንስ ይሄን ያህል እንደሆነ ዕውቅና መስጠት ነው፡፡ ይሄ የውሃ መጠን ዓመታዊ መጠናቸው 14 እና 10 ቢኪሜ ገደማ የሆኑትን የባሮ-አኮቦና የተከዜን ውሃ ሳይጨምር መሆኑ ነው፡፡ ወደ ሕዳሴው ግድብ የሚገባው የውሃ መጠን በአማካይ 49 ቢኪሜ ገደማ ነው፡፡ 37 ቢኪሜ ወደ ግድቡ ከሚገባው የዓባይ ውሃ ከሁለት ሦስተኛው በላይ ነው፡፡ ለዚያውም ሱዳንና የግብጽ ድርሻ ይህ እንዲሆን ሳይሆን በድርቅ ወቅት የሚፈልጉት ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ስምምነት ማድረግ፣ ድርቅ በማይሆንበት ጊዜ ከእዚህ በላይ ድርሻ እንዳለቸው ዕውቅና መስጠት ሆኖ መቆጠሩ አይቀርም፡፡
የሕዳሴው ግድብን መሙላት አንድ ነገር ነው፡፡ አንድ ጊዜ ከሞላ በኋላ በሌላ ጊዜ መለቀቅ ያለበትን ውሃ ለመወሰን መስማማት፣ እግረ መንገዱንና በግልጽ ባይጻፍም ቢያንስ የኢትዮጵያን በአንድ በኩል፣የሱዳንና የግብጽን በሌላ በኩል የውሃ ድር የሚያመላከት ነው፡፡
ከጥቁር ዓባይ ላይ ኢትዮጵያ፣ሱዳን (ደቡብ ሱዳንንም ጨምሮ) እና ግብጽ ምን ያህል ውሃ ያግኙ የሚለውን ምክረ ሐሳብ ያቀረቡ ባሉሙያዎች አሉ፡፡ ዊቲንገተን እና ማክከሌላንድ የተባሉ ምሑራን የግብጽንና የሱዳንን (ደቡብ ሱዳንንም ጨምረው) መልክአ ምድራዊና የዓየር ንብረት ሁኔታ፣ በናይል ላይ የተንጠለጠሉ መሆናቸውን፣ አማራጭ የላቸውም በሚሉና በሌሎች ምክንያቶች መነሻነት ሦስቱ አገራት ከጥቁር ዓባይ ውሃ ግብጽ 65 በመቶ፣ሱዳንና ኢትዮጵያ እያንዳንዳቸው  17.5 በመቶ እንድያገኙ ሐሳብ አቅርበዋል፡፡
ኢሊየን ዳርቢ የሚባሉ ሌላ ምሑር በበኩላቸው የኢትዮጵያ ለናይል 86 ከመቶ ውሃ ማዋጣቷንና የኢትዮጵያዊያንን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ሁኔታ ከግምት በማስገባት፣ሱዳንና ግብጽም ያለ ናይል መኖር አዳጋች (እንደውም እንደማይቻላቸው) በማተት፣የኢትዮጵያ ድርሻ 44 ከመቶ፣የግብጽ 29 ከመቶና ሱዳን (ሁለቱም) 27 በመቶ እንዲሆን “የናይል ወንዝ ተፋሰስ” (Nile River Basin) በሚል እ.አ.አ. በ2005 ባሳተሙት መጽሐፍ ሐሳብ አቅርበዋል፡፡
ጴጥሮስ ጄ.ገበቶ የተባሉ ኢትዮጵያዊ ምሑር በበኩላቸው፣ ”No More Thirst: The Citizens of the Nile” በሚል ርዕስ እ.አ.አ. በ2010 አቆጣጠር ባሳተሙት መጽሐፋቸው ላይ በርካታ ምክንያቶችን በማስቀመጥ እንደገለጹት ኢትዮጵያና ግብጽ እያንዳንዳቸው 40 በመቶ፣ሱዳን (ሁለቱም) ደግሞ 20 በመቶ እንዲሆን ነው፡፡
ከላይ የቀረቡት የጥቁር ዓባይን ውሃ ማከፋፈያ ቀመር እንዳለ ሆኖ፣ ናይልን በብቸኝነት መጠቀም የሚታሰብ ባለመሆኑና የተሻለው መፍትሔ ርትዓዊና ሚዛናዊ የውሃ ግልጋሎት መርህን መከተል ነው፡፡ ስለሆነም፣በሔልንስኪ ደንብ እና በ1997ቱ ዓለም አቀፍ ስምምነት ላይ የተዘረዘሩትና ሌሎች አመላካቾችንም ከግምት በማስገባት በናይል ውሃ ለመጠቀም መስማማት ነው፡፡ ለመስማማት ደግሞ በቅንነት መተባበር ከተጋሪ አገራት የሚጠበቅ ቅድመ ሁኔታ ነው፡፡
ሱዳንና ግብጽ በ1929ኙ እና በ1959ኙ የሁለትዮሽ ስምምነታቸው ላይ በተምኔት ተንጠልጥለው፣እነዚህ ላይ የሙጥኝ ብለው የሚመጣ ስምምነት አይኖርም፡፡ በተለይ ግብጽ የጋራ ተቋም ለመፍጠር የሚያስችል የመተባበሪያ የስምምነት ማዕቀፉን (Cooperative Framework Agreement) ባለመፈረም አሻፈረኝ በማለት በቀጠለችበት ሁኔታ፣ካርቱም ላይ እ.አ.አ. በ2015 የተደረገውን ስምምነት ወደ ጎን በመተው ግብጽ በዓለም ባንክና በአሜሪካ ፊት እንደራደር የሚል ጥሪ ለኢትዮጵያ ስታቀርብ ሰተት ብሎ በመግባት አሁን የተፈጠረው ዓይነት ቅርቃር ውስጥ ገብተናል፡፡
ድርድሩ የትና በማን ፊት ይቀጥል የሚለው እንዳለ ሆኖ፣ ዋሽንግተን ላይ የቀረበው የሕዳሴው ግድብ ውሃ አሞላልና አለቃቀቅ ረቂቅ ስምምነት ከወቅታዊ የቴክኒክ ጉዳዮች ባለፈ ወደፊት የሚጎትተውን ሕጋዊ መዘዝ በጥልቀት ማጤን ግድ ነው፡፡ ወደ ሕዳሴው ግድብ ከሚገባውና ከገባው ውሃ፤ በድርቅ፣በከባድ ድርቅና በተደጋጋሚ የድርቅ ዓመታት የግብጽና የሱዳን የውሃ ፍላጎት የ1929ኙን የሚያስንቅ፣የ1959ኙን የሚመስል ስምምነት ነው፡፡
Filed in: Amharic