>
5:13 pm - Sunday April 19, 7648

“እቴጌ ጣይቱ ብጡል ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ!!!" (ጥበቡ በለጠ)

“እቴጌ ጣይቱ ብጡል ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ!!!”   

 ጥበቡ በለጠ
“ኢትዮጵያ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊ እና የሃይማኖታዊ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ድርሻ እና አስተዋፅኦ ያላቸው ሴት ናቸው። በዘመናቸው ሀገራቸው ኢትዮጵያን ከቅኝ አገዛዝ አፋፍ ላይ በደረሰችበት ወቅት በቆራጥነትና በአይበገሬነት ተጋፍጠው ትውልድን እና ሀገርን ለዘላለም ታድገዋል። ዛሬ የምናነሳሳቸው እቴጌ ጣይቱ ብጡል ብርሃን ዘኢትዮጵያ ናቸው።
“በአድዋ ጦርነት ውስጥ ብዙዎች ወድቀዋል። ሕይወታቸውን ለሀገራቸው ቤዛ አድርገዋል። ድምፀ-ተስረቅራቂዋ ድምፃዊት እጅጋየሁ ሽባባው /ጂጂ/ ውብ በሆነው ድምጿ እና ግጥሟ የአድዋን ጀግኖች ገድል አዜማለች። ‘ሰው ሊኖር ሰው ሞቶ’ እያለች ዘክራቸዋለች።
“ታዲያ ከነዚህ ሁሉ አልፍ ኢትዮጵያዊያን ጀግኖች ውስጥ ደግሞ በሴትነታቸውና በጦርነቱ ውስጥ የመሪውን ገፀ-ባሕሪ በመጫወት ከፊት ድቅን የሚሉት እቴጌ ጣይቱ ብርሃን ዘኢትዮጵያ ናቸው፤ ዛሬ አነሳሳቸዋለሁ። እቴጌ ጣይቱ ልክ እንደ አፄ ቴዎድሮስና አፄ ምኒሊክ ሁሉ የደራሲያንን እና የኪነ-ጥበብ ሰዎችን ቀልብ የሚገዛ ታሪክ ባለቤት ናቸው።
“ታላቁ ፀሐፌ-ተውኔትና ባለቅኔ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን ምኒልክ በሚሰኘው ረጅም ቴአትሩ ላይ የእቴጌ ጣይቱን ታላላቅ ሰብዕናዎች አሳይቶናል። ደጃዝማች ግርማቸው ተ/ሃዋርያትም አድዋ በተሰኘው የቴአትር ፅሁፋቸው ውስጥ ጣይቱን አሳይተውናል። ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማም አድዋ በተሰኘው ጥናታዊ ፊልማቸው ውስጥ የጣይቱን ስብዕና ጠቁመዋል።
“ሌሎችም የኪነ-ጥበብ ሰዎች እቴጌ ጣይቱን በልዩ ልዩ ስራዎቻቸው ዘክረዋቸዋል። ወደ ታሪክ ፀሐፊዎች ስንመጣ ደግሞ ጣይቱ ብጡል የአያሌዎች ፅሁፍ ማድመቂያ ናቸው። ለምሳሌ ከሀገር ውስጥ ብቻ ያሉትን ፀሐፊዎች ስንቃኝ በአጤ ምኒልክ ዘመነ መንግስት ውስጥ የነበሩት ፀሐፌ-ትዕዛዝ ገ/ሥላሴ በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ። ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደስላሴም የጣይቱን ብርሃንማነት በሰፊው አነሳስተዋል።
“ነጋድራስ ገብረህይወት ባይከዳኝም ያንን ዘመን ከመዘከር አልፈው የጣይቱን ማንነት አሳይተውናል። ብላታ መርሰዔ ኃዘን ወልደቂርቆስም ጣይቱን ዘክረዋል። ቀኛዝማች ታደሰ ዘውዴ ጣይቱ ብጡል የተሰኘ መፅሐፍ ቀደም ባለው ዘመን አሳትመዋል።
“ታሪክ ፀሐፊው ተክለፃዲቅ መኩሪያ፣ ጋዜጠኛውና ደራሲው ጳውሎስ ኞኞ፣ የአፄ ኃይለሥላሴን ታሪክ የፃፉት በሪሁን ከበደ እና ኮ/ል ዳዊት ገብሩ /የከንቲባ ገብሩ ልጅ/ ብሎም በዚሁ በእኛ ዘመን ደግሞ ፋንታሁን እንግዳ እና እስክንድር ነጋን የመሳሰሉ ፀሐፊያን ጣይቱ ብጡልን በተለያዩ መንገዶች አነሳስተዋል።
“ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት እና ባለቤታቸው ወ/ሮ ሪታ ፓንክረስትም በተለያዩ ፅሁፎቻቸው ውስጥ ጣይቱን አነሳስተዋል።ወደ ውጭ ሀገር ፀሐፊያን ስንሄድም በርካቶች የአድዋን ጦርነት እና ጣይቱን እየጠቃቀሱ ፅፈዋል። የዓለምን የፊልም ታሪክ በመፃፍ የምትታወቀው ክሪስ ፕሩቲም ጣይቱ ብጡልን በተመለከተ ፅፋለች።
“እንግዲህ ሁሉንም ፀሐፊያን መጠቃቀሱ ሰፊ ሊሆን ስለሚችል እሱን እዚህ ላይ ገታ እናድርገውና እነዚህ ሁሉ ፀሐፊያን ጣይቱን እንዴት ገለጿቸው የሚለውን ርዕሰ ጉዳይ በጥቂቱ እንመልከተው።
“እቴጌ ጣይቱ የተወለዱት ነሐሴ 12 ቀን 1832 ዓ.ም ጐንደር ውስጥ ደብረታቦር ከተማ ነው። ጣይቱ ገና ልጅ ሳሉ አባታቸው በጦርነት ውስጥ ሞቱባቸው። ከዚያም ጣይቱ ወደ ጐጃም መጥተው በደብረ መዊዕ ገዳም ገብተው በዘመኑ ይሰጥ የነበረውን ትምህርት በሚገባ ተከታትለው መማራቸው ይነገራል። ፅህፈትን፣ ንባብን፣ ግዕዝና አማርኛ ቅኔን፣ ታሪክን እና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በሚገባ ተምረው አጠናቀዋል።
“እቴጌ ጣይቱ የዘር ሐረጋቸው የሚመዘዘው ከኢትዮጵያ ነገስታት ተዋረድ ውስጥ በመሆኑ በስርዓትና በእንክብካቤ ያደጉ ናቸው። ትምህርትም በመማራቸውና በተፈጥሮም በተሰጣቸው የማሰብና የማስተዋል ፀጋ በዘመናቸው በእጅጉ የታወቁ ሴት ሆኑ።
“ስለ እርሳቸው በየቦታው ይወራ ነበር። አጤ ቴዎድሮስ ወደ ሸዋ ዘምተው አጤ ምኒልክን ማርከው ወደ ጐንደር ወስደዋቸው በሚያሳድጓቸው ወቅት፣ ምኒልክ በተለያዩ ሰዎች አማካይነት ጣይቱ ስለምትባል ሴት ብልህነትና አርቆ አሳቢነት ወሬ በተደጋጋሚ ይሰሙ ነበር። ጣይቱ ማን ናት? ምን አይነት ሰው ናት እያሉ ልባቸው መንጠልጠል ጀመረች።
“ ‘ጣይቱ የምትባል ብልህ ሴት ትወለዳለች’ እየተባለ በወቅቱ የሚነገር ንግርት እንደነበር ፀሐፊያን ይገልፃሉ። ጣይቱ ከብልህነቷ የተነሳ ኢትዮጵያን ትመራለች እየተባለ ለረጅም ጊዜ ሲነገር ቆይቷል። ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደስላሴ የሕይወት ታሪክ በተባለው መፅሐፋቸው ይህንኑ ስለ ጣይቱ የተነገረውን ታሪክ ያስታውሱናል። እንደ ኅሩይ ገለፃ ጣይቱ የምትባለው ሴት ተወልዳ ወደ ንግስና እንደምትመጣ ይወሳ እንደነበር ጠቁመዋል። እንዲህም ብለዋል፡-
“ “ጣይቱ በምትባል ሴት የኢትዮጵያ መንግስት ታላቅ ይሆናል እየተባለ ሲነገር ይኖር ነበርና ከአፄ ምኒልክ አስቀድሞ የነበሩ አንዳንድ ነገሥታት ስሟ ጣይቱ የምትባል ሴት እየፈለጉ ማግባት ጀምረው ነበር። ነግር ግን ጊዜው አልደረሰም ነበርና አልሆነላቸውም። ዘመኑ በደረሰ ጊዜ ግን አፄ ምኒልክ እቴጌ ጣይቱን አገቡ። እቴጌ ጣይቱም የብሩህ አዕምሮ ባለቤት ስለነበሩ በመንግሥቱ ስራ ሁሉ አፄ ምኒልክን ይረዱ ነበር። እንደ ንግርቱም ቃል ኢትዮጵያ በእቴጌ ጣይቱ ዘመን ታላቅ ሆነች” ብለዋል ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወ/ስላሴ በ1915 ዓ.ም ባሳተሙት የህይወት ታሪክ በተሰኘው መፅሐፋቸው። እናም ባለ ንግርቷ ጣይቱ ተወለደች ብለን እናስብ።
“ፋንታሁን እንግዳ ታሪካዊ መዝገበ ሰብ በተሰኘው ማለፊያ መፅሐፉ “ይህን ሁሉ አጥንተው የሚያወቁት ንጉሥ ምኒልክ ሚያዚያ 25 ቀን 1875 ዓ.ም በአንኮበር መድሐኒያለም ቤተ ክርስትያን ከእቴጌ ጣይቱ ብጡል ጋር በቁርባን ጋብቻውን ፈፀሙ። አምስት ዓመታት ቆይቶም ጥቅምት 27 ቀን 1882 ዓ.ም ጣይቱ ብጡል እቴጌ ተብለው ተሰየሙ” በማለት ፅፏል።
“ደራሲው ፕሮፌሰር /ነጋድራስ/ አፈወርቅ ገ/እየሱስን ጠቅሶ ስለ ጣይቱ ብጡል በወቅቱ የፃፉትን አስቀምጧል። አፈወርቅ ገብረእየሱስ ዳግማዊ አጤ ምኒልክ በተሰኘው መፅሐፋቸው ስለ ጣይቱ የሚከተለውን ፅፈዋል፡-
“የሸዋ ቤተ-መንግሥት ዓለሙ የዚህን ቀን ተጀመረ። የሸዋ ቆሌ፣ የሸዋ ደስታ የዚህን ቀን ተጀመረ። የሸዋ መንግሥት ከጣይቱ በኋላ ውቃቢ ገባው፣ ግርማና ውበት ተጫነው፣ ጥላው ከበደ፣ የእውነተኛው አዱኛ፣ የእውነተኛው ደስታ ከጣይቱ ብጡል ጋር ገባ” ብለው ፕ/ር አፈወርቅ ፅፈዋል።
“አጤ ምኒልክ ከቀድሞው ባለቤታቸው ከወ/ሮ ባፈና ጋራ ፍቺ ፈፅመው ከጣይቱ ጋር መጋባታቸው የሚያስቧቸውን ራዕዮች ሁሉ ለማሳካት እድል እንደገጠማቸው ፀሐፍት ያወሳሉ። በተለይ ኢትዮጵያን ለማዘመን በተነሱበት ጊዜ የእቴጌ ጣይቱ እገዛ እና ተጨማሪ ሃሳቦች ጥርጊያውን በሚገባ አፀዳድተውታል። ጣይቱ ያልተሳተፉበት ልማት አልነበረም። ስልኩ፣ ባቡሩ፣ ኤሌክትሪኩ፣ ፊልሙ፣ ውሃው፣ መኪናው፣ ት/ቤቱ፣ ሆስፒታሉ፣ ሆቴሉ፣ መንገዱ ወዘተ መገንባት እና መተዋወቅ ሲጀምር ጣይቱ የባልተቤታቸው የአፄ ምኒሊክ ቀኝ እጅ ነበሩ።
“እቴጌ ጣይቱ በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ሕያው አድርጓቸው በየትኛውም ዘመን እንዲጠሩ ካደረጓቸው ነገሮች መካከል የጥቁር ህዝቦች ሁሉ አበሳ የነበረውን የቅኝ አገዛዝ ስልትን አሻፈረኝ ብለው፣ እምብኝ ብለው ወጥተው ጦርነት ገጥመው በድል ያጠናቀቁበት ታሪክ ነው። የጣሊያን አጭበርባሪዎች ኢትዮጵያን አሳስተው ውጫሌ ላይ የተደረገውን የሁለቱን ሀገሮች ውል ቅኝ ግዛት መያዣ ሊያደርጉበት አሲረው ነበር። እናም ይህንን ሴራ ከተረዱ በኋላ እቴጌ ጣይቱ በልበሙሉነት ከኢጣሊያ መንግስት ጋር ጦርነት ለመግጠም ያለ የሌለ ወኔያቸውን ሰብስበው ተነሱ።
“የኢጣሊያውን ዲፕሎማት አንቶኔሊን ጣይቱ እንዲህ አሉት፡- “ያንተ ፍላጐት ኢትዮጵያ በሌላ መንግስት ፊት የኢጣሊያ ጥገኛ መሆኗን ለማሳወቅ ነው። ነገር ግን ይህን የመሰለው የምኞት ሃሳብ አይሞከርም!! እኔ ራሴ ሴት ነኝ። ጦርነት አልፈልግም። ነገር ግን ይህን ውል ብሎ ከመቀበል ጦርነትን እመርጣለሁ!” ሲሉ ተናግረዋል። በሀገራቸው ሉዐላዊነት ላይ ምንም ዓይነት ድርድር እንደማያደርጉ በትንታግ ንግግራቸው አሳውቀዋል። ከዚያም ሦስት ሺ እግረኛ ወታደር እና ስድስት ሺ ፈረሰኛ ጦር እየመሩ ከአጤ ምኒልክ ጐን እና ከሌሎችም የአድዋ ጀግኖች ጋር ሆነው ዘመቱ።
“በጦርነቱ ወቅትም የጀግኖች ጀግና ሆነው በኢጣሊያ ሠራዊት ላይ ድል ተቀናጁ። እቴጌ ጣይቱ ቅኝ አገዛዝን ተዋግተውና ድል አድርገው ሀገርን በነፃነት በማቆየት ሂደት ውስጥ በዓለም የሴቶች ታሪክ ውስጥ ትልቅ ስፍራ የሚሰጣቸው እንደሆኑ ወ/ሮ ሪታ ፓንክረስት በአንድ ወቅት ተናግረዋል። ወ/ሮ ሪታ የፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ባለቤት ናቸው።
“ይህችን ሀገር ከቅኝ ገዢዎች መንጋጋ ፊልቅቆ በማውጣት በጦርነት ውስጥ ገናን ስም እና ዝና ያላቸው እቴጌ ጣይቱ በተቃራኒው ደግሞ ፍፁም መንፈሳዊ ሴት ነበሩ። በአድዋ ጦርነት ዝግጅት እና በጦርነቱ ዘመቻ ወቅትም ማታ ማታ በፀሎት ከፈጣሪያቸው ዘንድ እየተማፀኑ ሀገራቸውን ነፃ ለማውጣት ፈጣሪም አብሯቸው እንዲሰለፍ ይማፀኑ እንደነበር በርካታ ፀሐፊያን ገልፀዋል። እቴጌ ጣይቱ ጦርነቱን በመንፈስም በነፍጥም ነበር ያካሄዱት።
“የሀገሪቱ ታቦታት ወደ አድዋ እንዲዘምቱ በማድረግ ተፅዕኖ ፈጣሪ ነበሩ። ሐገረ ኢትዮጵያ ከሌለች ሃይማኖቷም የለም ብለው ታቦታትን ይዘው ዘመቱ። እንዲህ ነው ጀግንነት። በውስጡ ትዕቢት የለም። ውስጡ ነፃነትን መሻት ብቻ ነው። ጣይቱ ብጡልን በጦርነቱ ውስጥ አይተው ከፃፉ ደራሲዎች መካከል ፀሐፌ- ትዕዛዝ ገብረስላሴ ናቸው። እርሳቸው ስለ ጣይቱ ሲፅፉ ከጀግነታቸው ባሻገር ለአርበኛው ሁሉ መነቃቂያ ነበሩ፤ ሴት ሆነው እንደዚያ መዋጋታቸው ለወንዶቹ ፅናት ነው፣ ይበልጥ መጠንከሪያ ነው እያሉ ፀሐፌ ትዕዛዝ ፅፈዋል።
“እቴጌ ጣይቱ በዘመናቸው እጅግ ገናን ተፅዕኖ ፈጣሪ ሴት ነበሩ። ዛሬ የአፍሪካ መዲና ተብላ የምትጠራውን አዲስ አበባን የመሠረቱ የግዙፍ ስብዕና ባለቤት ናቸው። በእስራኤል ውስጥ በተለይም በእየሩሳሌም ውስጥ ያለውን የዴር ሱልጣን ገዳምን በመርዳት እና የኢትዮጵያ መሆኑን አስረግጠው ያስመሰከሩ ሃይማኖተኛ ወ ፖለቲከኛ ነበሩ። ኢትዮጵያ በጦርነቱም፣ በስልጣኔውም፣ በፖለቲካውም፣ በመንፈሳዊውም ዓለም ጠንክራ እንድትወጣ ብዙ ብዙ ጥረዋል። ተሳክቶላቸዋልም።
“መቼም ሁሉም ነገር እንዳማረበት አይፈፀምም። ታህሳስ 3 ቀን 1906 ዓ.ም አጤ ምኒልክ አረፉ። የቤተ-መንግስት ሹማምንቶች እቴጌ ጣይቱን በመፍራት ስልጣን ከሸዋ እጅ ወጥቶ ወደ ጐንደር ሊሄድ ነው ብለው ፈሩ። ስለዚህ ዶለቱ። እቴጌም የዱለታው ሰለባ ሆኑ። እንጦጦ ማርያም ሄደው በግዞት እንዲቀመጡ ተደረጉ። በጣሙን አዘኑ። በዚያው የሐዘን ስሜታቸው አፍሪካዊቷ ጀግና እቴጌ ጣይቱ የካቲት 4 ቀን 1910 ዓ.ም ሌሊት ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።
“በኢትዮጵያ ሴቶች ታሪክ ውስጥ እንደ ከዋክብት ብርሃን ለዘላለም የሚንፎለፎል ማንነት አኑሮው ያለፉት እቴጌ ጣይቱ፣ ዛሬ በጥቁር ዓለም ውስጥ በነፃነቷ ኮርታ ለሌሎችም ምሳሌ የምትሆነውን ኢትዮጵያ ተረባርቦ ለማቆም በተከፈለው መስዋዕትነት ውስጥ ጣይቱ ብጡል ትልቁን ስፍራ ይረከባሉ። እቴጌ ጣይቱ ብጡል ብርሃን ዘኢትዮጵያ እየተባሉ በትውልድ ውስጥ ሲጠሩ ይኖራሉ።”
እንደ መውጫለማርች 8 – ለዓለማቀፉ የሴቶች ቀን – ለኢትዮጵያውያን የተሰነዘረ ሀሳብ፡-
ለሀገር ላበረከተችው ተስተካካይ የሌለው አስተዋፅዖዋ ሲባል እቴጌ ጣይቱ ለምን በብራችን ላይ ምስሏ አይታተምላትም???
እቴጌ ጣይቱ ብጡል ብርሃን ዘ ኢትዮጵያንም – ከወገባችን ዝቅ ብለን በአክብሮት እጅ ነሳን፡፡
እምዬ ኢትዮጵያ ለዘለዓለም በፍቅር ትኑር!
Filed in: Amharic