>
9:03 am - Thursday June 8, 2023

የዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ እናት ማን ናቸው?  (አቻምየለህ ታምሩ)

የዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ እናት ማን ናቸው? 

 

አቻምየለህ ታምሩ
ታዬ ቦጋለ አረጋ ኢልመ ደሱ ኦዳ ሰሞኑን ደጋግሞ ባሰማው ዲስኩር የዐፄ ምኒልክ እናት ኦሮሞ መሆናቸውን ተናግሯል። ታዬ እጅግ ጥንቃቄ በሚጠይቀው የታሪክ ዘርፍ ውስጥ ተሰማርቶ ያለቀዳሚ ማስረጃ እንዲህ አይነት ድምዳሜ ላይ መድረሱ ትክክል አይደለም። በዘመኑ ተመዝግቦ የምናገኘው ታሪክ ስለ ዐፄ ምኒልክ እናት የሚነግረን ታሪክ ታዬ ካቀረበው ትርክት ጋር  የሚቃረን ነው።
በርግጥ ታዬ ብቻ ሳይሆን በርካታ ሰዎች የዳግማዊ ዐፄ ምኒልክን እናት በሚመለከት የተለያዩ ሰዎች የተለያዬ ነገር ሲናገሩ ይሰማል። ለምሳሌ  የቁልቢው ልጅ ደራሲና ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞ «አጤ ምኒልክ» በሚል ርዕስ አዘጋጅተው በ፲፱፻፹፬ ዓ.ም. ባሳተሙት መጽሐፍ ገጽ 13 ላይ ስለ ግርማዊ ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ እናት እንዲህ ብሎ ጽፏል፤
«ብዙ የታሪክ ፀሐፊዎች እንደሚሉት ወይዘሮ እጅጋየሁ ውብና ከደህና ቤተሰብ መወለዳቸውን ይገልፃሉ። የአባታቸውን ስም ግን የሚገልጽ የለም። ለማ አድያሞ ይባላሉ። ይህም ሲተነትኑም አንዳንዶቹ ከጉራጌ አገር የተማረኩ ባሪያ ናቸው ይሏቸዋል። ባርያ ማለት በገንዘብ የሚሸጥ ብቻ ሣይሆን በጦርነት የሚማረክ ሁሉ ባርያ ይባላል። ይህ ሁሉ ይቅርና ዋናው ቁም ነገር ታሪክ መሥራት እንጂ ትውልድ አይደለም። ታላቁ ናፖሊዮን እንደዘመኑ አፃፃፍ ወደላይ የሚቆጠር ዘር አልነበረውምና ታሪኩን የሚጽፈው ፀሐፊ ቀርቦ «የትውልድ ታሪክዎን ከየት ልጀምር?» ቢለው «ያለፈውን ትተህ ከኔ ጀምር አለው እንደሚባለው ነው።»
የታዬን ምንጭ ባላውቅም የዐፄ ምኒልክን እናት በሚመለከት ብዙ ሰው ሲጽፍ በአመዛኙ የሚጠቅሰው ወይንም የሚስማማው ከፍ ሲል የቀረበውን የደራሲና ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞን ትርክት ዋቢ ያደርጋል። ሆኖም ግን ይህ ትርክት ትክክለኛ ታሪክ አይደለም።
የዳግማዊ ዐፄ ምኒልክን እናት  ማምነት በሚመለከ ንጉሠ ነገሥቱ በሕይወት ሳሉ የተመዘገበው  የታሪክ እውነት ከዚህ ቀጥሎ የሰፈረውን ይመስላል።  የዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ እናት ትክክለኛ ስም እጅጋየሁ ኃይሉ ነው። ደራሲና ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞ እንደጻፈው ወይዘሮ እጅጋየሁ ኃይሉ ባርያ አይደሉም። ወይዘሮ እጅጋየሁ ኃይሉ የጎጃም ተወላጅ የጎዛምን ሰው ናቸው። ይህን ታሪክ የሚነግሩን በ1889 ዓ.ም. «የጎጃም ትውልድ በሙሉ ከአባይ እስከ አባይ» በሚል የመዘገቡት አለቃ ተክለ እየሱስ ዋቅጅራ ናቸው። የአለቃ ተክሌ «የጎጃም ትውልድ በሙሉ ከአባይ እስከ አባይ» እናት መዝገብ በኢትዮጵያ ጥናት ማዕከል ላይበራሪ የሚገኝ ሲሆን እናት መዝገቡ እኔ ክምችት ውስጥም ይገኛል።
አለቃ ተክለ እየሱ ዋቅጅራ በ1860 ዓ.ም. በዛሬው ወለጋ ክፍለ ሀገር ሆሮ ጉድሩ ቅርብ ከሆነች አልባሳ በሚባል ስፍራ የተወለዱና በንጉሥ ተክለ ሃይማኖት የጎጃም አስተዳደር ዘመን በሰዓሊነትና በጸሓፊነት አገራቸውን ያገለገሉ ስመ ጥር ሊቅ ናቸው። «የጎጃም ትውልድ በሙሉ ከአባይ እስከ አባይ» በሚል ርዕስ ያሰናዱትን የትውልድ መድብል ለመጀመሪያ ጊዜ በ1889 ዓ.ም. ሲጠናቅቁ 11 ዓመታት የፈጀ መረጃ የማሰባሰብ ስራ ሰርተዋል።
አለቃ ትክለ እየሱስ የጻፉት የጎጃም ትውልድ መድበል ለሕትመት የበቃው ረቂቁ ካዘጋጁት ከ114 ዓመታት በኋላ በ2003 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ አሳታሚነት በግርማ ጌታሁን አዘጋጅነት ነበር። አለቃ ተክለ እየሱ ዋቅጅራ ጽፈውት በግርማ ጌታሁ አዘጋጅተው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ የታተመው የአለቃ መድበል ገጽ 73 ላይ እንደሚታየው የዳግማዊ ምኒልክ እናት ወይዘሮ እጅጋየሁ ኃይሉ ሲሆኑ የትውልድ ክፍለ ሀገራቸው ጎጃም ሲሆኑ ትውልዳቸው ከጎዛምን ነው።
አለቃ ተክሌ በጻፉት የጎጃም ትውልድ መድበል መሰረት የዳግማዊ ምኒልክ እናት ወይዘሮ እጅጋየሁ ኃይሉ የጎዛምን 3ኛ ትውልድ የሆነው የተከብጀን የልጅ ልጅ ልጅ ሲሆኑ የሚወለዱት ጎጃም ጎዛምን እነራታ፣ የብራጌ፣ ዳሊገውና የደረት አካባቢ ነው። በነገራችን ላይ እነዚህ የገጠር ቀበሌዎች ደብረ ማርቆስ ከተማ ዙሪያ የሚገኙ የገበሬ ቀበሌ ማኅበራት ናቸው።
የዳግማዊ ምኒልክን እናት ውበትና ቁንጅና በሚመለከት የቁልቢው ልጅ ደራሲና ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞ «ወይዘሮ እጅጋየሁ ውብ ናቸው» ሲል የገለጸው ትክክል ሊሆኑ ይችላሉ። ነፍሱን ይማረውና ድምጻዊ ተስፋዬ ወርቅነህ የወደዳት የጎጃም ቆንጆ «ስዕለ ማርያም» እንደምትመስል የዳሊገው ጊዮርጊሷን ቆንጆ «ዉቢቱ ጎጃሜ» በሚለው ዘፈኑ፤
አልጋ ላይ ስትጥይ ቀበቶ አስፈትተሽ፣
ማሩኝ ታሰኛለሽ ወንድ ልጅ አስተሽ፤ ሲል ይገልጻታል።
የሆነው ሆኖ የወይዘሮ እጅጋየሁ ኃይሉ ሙሉ የቤተሰብ ሀረግ እንደሚከተለው ነው። የጎጃም እነራታ፣ የብራጌ፣ ዳሊገውና የደረት አካባቢ ተወላጅ የሆኑት ተከበጀን ታላቅ ቤትን ወለዱ፤ ታላቅ ቤት ዮሐንስን ወለዱ፤ ዮሐንስ ማሮን ወለዱ፤ ማሮ ኃይሉን ወለዱ፤ ኃይሉ እጅጋየሁን ወለዱ፤ እጅጋየሁ ዳግማዊ ምኒልን ወለዱ።
ልብ በሉ! ይህ  የዳግማዊ ምኒልክ እናት ታሪክ የተመዘገበው ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ራሳቸው በሕይወት እያሉ በ1889 ዓ.ም. ነው። ከዚህ ዘመን በኋላ የተመዘገበ ታሪክ የዘመን ታሪክ ተደርጎ እንደማስረጃ ሊቀርብ አይችልም። ስለዚህ የዐፄ ምኒልክን እናት ማንነት የሚነግረን ይህ አለቃ ተክሌ  በ1889 ዓ.ም. ያዘጋጁት «የጎጃም ትውልድ በሙሉ ከአባይ እስከ አባይ» መዝገብ ብቻ ነው።
ይህ ብቻ አይደልም! የዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ አያት፣ የኃይለ መለኮት እናት ዘመነ ወርቅም ትውልዳቸው ከጎጃም ነው። ይህንን ታሪክም የምናገኘው አለቃ ተክሌ በ1889 ዓ.ም. ባሰናዱት «የጎጃም ትውልድ በሙሉ ከአባይ እስከ አባይ» መዝገብ ውስጥ ገጽ 48 ላይ ነው።
ስለዚህ የዳግማዊ ምኒልክ እናት በተለምዶ እንደሚባለው እጅጋየሁ አድያሞ ሳይሆኑ እጅጋየሁ ኃይሉ ናቸው። የትውልድ ሀረጋቸውም ጎጃም ደብረ ማርቆስ ከተማ ዙሪያ ባሉ የጎዛምን የገጠር ቀበሌዎች ውስጥ ነው።
ከታች የታተሙት ገጾች አለቃ ተክለ እየሱስ ዋቅጅራ የጻፉት የዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ እናት እና አያት የትውልድ ሀረግ የሚያሳዩ ናቸው። የዐፄ ምኒልክን እናት ኦሮሞ በማድረግ ትልቅ ድምዳሜ ላይ የደረሰው ታዬ ቦጋለ  ከዚህ  ጥንታዊ  እናት መዝገብ ያለው ቀዳሚ የታሪክ ምንጭ  የተሻለ የታሪክ ማስረጃ  ካለው ያውጣና  የመረጃ ምንጩን ያሳየን! ይህን ማድረግ ካልቻለ ግን ያሳሳታቸውን ተከታዮቹን ይቅርታ ሊጠይቅ ይገባል!
Filed in: Amharic