>

ቀበሌ/ወረዳ የሕዝብ ቢሆን? (ከይኄይስ እውነቱ)

ቀበሌ/ወረዳ የሕዝብ ቢሆን?

 

ከይኄይስ እውነቱ

 

ቀበሌ የሚለው ቃል ከደርግ የአገዛዝ ሥርዓት ጋር ተያይዞ የመጣ የሚመስላቸው ዜጎች ቊጥር ቀላል አይደለም፡፡ ቃሉ ነባር ሲሆን፣ በቀድሞው (በነገሥታቱ) ዘመን ወረዳ በሚባለው የአስተዳደር ዕርከን ውስጥ የሚገኝ ሕዝብ የሰፈረበት የከተማ ትናንሽ ክፍልፍል ወይም በጊዜው አጠራር ‹ጭቃ› (አስተዳዳሪውም የጭቃ ሹም) የሚባል ንዑስ የከተማ ክፍል ነው፡፡ ወታደራዊው አገዛዝ ሕግ አውጥቶ በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ ከተሞች የአስተዳደር መዋቅር ውስጥ ዝቅተኛው/ንዑስ የአስተዳደር ዕርከን አድርጎ አዋቀረው፡፡ የመንግሥት መዋቅር ሆነ፡፡ የፖለቲካ አስተዳደር ክፍል አደረገው፡፡

ከመነሻው የቀበሌ አስተዳደር መዋቅር የታሰበው ያለመንግሥት ጣልቃ ገብነት ሕዝቡ/ነዋሪው በአካባቢው ራሱን በራሱ የሚያስተዳድርበት አካል ለመፍጠር ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ይህ አሳብ በወቅቱ በነበሩ ፖለቲከኞች (በደርጉ ብቻ ሳይሆን በተቃራኒው በተሰለፉ ኃይሎች በሙሉ) ተጠልፎ የአገዛዝ መሣሪያ ሆነ፤ ለተቃዋሚዎችም የትግል መሣሪያነት ዋለ፡፡ በመሆኑም ከደርግ አገዛዝ ጀምሮ አሁን እስካለው የዐቢይ ኢሕአዴጋዊ አገዛዝ ቀበሌ ሕዝብን የመጨቈኛ፣ የማፈኛ፣ መብት መግፈፊያ፣ ነፃነት ማሳጫ፣ ወደነዋሪዎች ጠጋ ብሎ ሕዝብን መደቆሻ መዶሻ ሆኖ እያገለገለ ነው፡፡ ዛሬ ይሄ አፍራሽ ሚና ወረዳ ተብሎ በሚታወቀው (እንደሁናቴው 3/4 ቀበሌዎችን አዋሕዶ) የከተሞች መዋቅር ተተክቶ ሕዝብን ማዋከቢያ መሣሪያ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ 

ላለፉት ሦስት ዐሥርታት የሚጠጉ ዓመታት ቀበሌ/ወረዳ (ክ/ከተማ የሚባለውን ጨምሮ) ዋናው ተግባሩ ነዋሪዎችን ከቤት ንብረታቸው በማፈናቀል ከርታታ ማድረግ፣ የሕዝብን ሀብት መዝረፍና ነዋሪውን ሥር በሰደደ ንቅዘት ማማረር እና በዘረኝነት ለተጠመዱት አገዛዞች የስለላ/የአፈና መዋቅር ሆኖ ማገልገል ነበር፤ አሁንም ነው፡፡ በዘመነ ወያኔና በወራሹ የዐቢይ አገዛዝ የቀበሌ/ወረዳ/ ሹመኞች የተሾሙበት ቀበሌ/ወረዳ ውስጥ ነዋሪ ያልሆኑ፣ መንደርተኝነትን ለማራመድ በጐሣ መሥፈርት የተመለመሉ፣ ራሳቸውን በጠላት ቀጣና ውስጥ እንዳሉ የሚቈጥሩ፣ ሕዝቡን እንደ ጠላት የሚመለከቱ፣ የሙያ ብቃትም ሆነ ግብረገብነት የሌላቸው፣ የአካባቢውን ማኅበረሰብ ርእይ፣ ፍላጎት፣ አስተሳሰብ የማያውቁ፣ የማያማክሩ ጸጕረ ልውጥ የፖለቲካ ምድብተኞች ናቸው፡፡ ባጭሩ የአገዛዙን ፈቃድ ለመፈጸም  በ‹ወራሪነት› መንፈስ ነዋሪዎች ላይ የተጣበቁ ደም መጣጭ መዥገሮች ናቸው፡፡ አንዳንድ ቦታ በግለሰብ ደረጃ ‹ቅን› ተሿሚዎች ስለሚኖሩ በጅምላ ጨፈለቅካቸው የሚል አመለካከት እንዳለ ዐውቃለሁ፡፡ ለዚህ አስተያየት ዓላማ ግን አጠቃላይ ደንቡን እንጂ ልዩ ሁናቴ (exception) ከግምት ውስጥ አይገባም፡፡

የጋሼ መሥፍን ወ/ማርያም ሥራዎችን ባሰባሰውና ‹‹አድማጭ ያጣ ጩኸት›› በሚለው የመጀመሪያው መድበል ውስጥ ቀበሌ/ወረዳ (ያለ መንግሥት ጣልቃ ገብነት በሕዝብ እጅ ሲሆን) ለመንግሥተ ሕዝብ (የዴሞክራሲ ሥርዓት) – ሕዝባዊ ሥልጣን እንዴት እንደሚመሠረትና በተግባር እንደሚውል –  መሠረት እንደሚሆን በሚገባና በዝርዝር ተገልጾአል፡፡ በተለይም ፖለቲከኞች ነን የምትሉ በሙሉ በማስተዋል ብታነቡት አገርንና ወገንን የምትጠቅሙበት ይሆናል፡፡ 

ከመንግሥት ወይም የፖለቲካ ቡድኖች (ፓርቲዎች) ምስለኔዎች የፀዳ የቀበሌ/ወረዳ አስተዳደር ክፍል በሕዝብ ባለቤትነት ሥር ሲሆን ከዕለት ተዕለት ኑሮው ጀምሮ በአገር አቀፍ ደረጃ በማኅበራዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ እና ፖለቲካዊ ሕይወት ቀጥታ ተሳትፎ በማድረግ የአገር ባለቤትነቱን (ዜግነቱን) የሚያረጋግጥባቸው ‹ነፍስ› ያላቸው መድረኮች ይሆናሉ፡፡ በአገር ጉዳይ ላይ የበዪ ተመልካች ሳይሆን ያገባኛል የሚል፣ በኑሮው የሚተባበር፣ ለጋራ ዕድገት በኅብረት የሚሠራ፣ ሲለማ የሚያወድስ÷ ሲጠፋ ነቅፎ/ተችቶ የሚያስተካክል ዜጋ ለመፍጠር ያስችላል፡፡ የቀበሌ/ወረዳ አስተዳደር ተሳታፊ ለመሆን ነዋሪነት፣ በነዋሪው ሕዝብ መመረጥ፣ ከዚያም ነዋሪው በስምምነት እስከፈቀደለት የጊዜ ገደብ እንደየችሎታውና ሙያው የወከለውን ማኅበረሰብ ማገልገል ይሆናል፡፡ ተመራጩ የብቃት ማነስ ካሳየ ወይም ሕዝባዊ ሥልጣንን አላግባብ ከተጠቀመበት በነዋሪው የሚነሳበት ሥርዓት ይበጃል፡፡ በዚህ፣ ሕዝባዊ መንግሥት በተግባር ሥራ ላይ በሚውልበት ዝቅተኛው የአስተዳደር ዕርከን ዳር ቆሞ ተመልካች የሚሆን ነዋሪ አይኖርም፡፡ በተለያዩ ማኅበራዊ አገልግሎቶችና ፕሮግራሞች ተሳታፊ ይሆናል፡፡ ነዋሪው በሚኖርበት ቀበሌ/ወረዳ ለሚደረጉ ማናቸውም ማኅበረሰቡን በአንድ ወይም በሌላ መልኩ ለሚነኩ እንቅስቃሴዎች ኃላፊ ነው፡፡ ከቤተሰብ እስከ ማኅበረሰብ ላሉ ሕፀፆች፣ ሳንካዎች በያገባኛል መንፈስ በኅብረት የሚንቀሳቀስ ኃይል ይሆናል፡፡ ከመንግሥት የሕግ አስከባሪ ኃይሎች ጋር በመሆን አካባቢው ከወንጀል የፀዳ እንዲሆን ንቁ ዘብ ይሆናል፡፡ የአንዱ መንደር/ሠፈር ሕማም የራሱ መሆኑን ተረድቶ በቸልታ የሚያልፈው ሳይሆን በጋራ ለጋራ ሰላምና ደኅንነት በትብብር የሚሠራ ሥልጡን ኃይል ይሆናል፡፡ ባጠቃላይ የሥልጣን ባለቤት የሆነ ሕዝብ በነፃነት የማሰብና የመሥራት ዕድል ስላለው ለመማር፣ ለማወቅ አእምሮው ክፍት ይሆናል፤ ይጠይቃል፣ ይመረምራል፡፡ አዳዲስ ሃሳቦችን ለማፍለቅ ለፈጠራ የተጋ ስለሚሆን ዕድሜ-ጠገብ ችግሮችን ጊዜን በዋጀ ዘመናዊ መፍትሄ ለመፍታት የማያቋርጥ ጥረት ያደርጋል፡፡

 

ቀበሌ/ወረዳ የእኛ (የተራው ሕዝብ) ቢሆን ምን አገልግሎት ይስጥ?

ቀበሌ/ወረዳ የሕዝብ ከሆነ፣ ለነዋሪዎቹ የሚሰጡ አገልግሎቶች ዘርፈ-ብዙ እና ፈርጀ-ብዙ በመሆናቸው የተጠናቀቀ ዝርዝር ለማቅረብ አይቻልም፡፡ ሆኖም ለአብነት ያህል ዐበይት የሆኑትን እና እንደ አካባቢው ዕድገትና ሁናቴ እያደገ ሊመጣ የሚችለውን የማኅበረሰቡን ፍላጎቶች ግምት ውስጥ የሚያስገቡ አገልግሎቶች ማሰብ ይቻላል፡፡ 

አገልግሎቶቹን በጥቅሉ/በዘርፍ ደረጃ ለማየት

1ኛ/ ትምህርት

እንደሚታወቀው አብዛኛው ሕዝባችን በገጠር ነዋሪ ሲሆን፣ የትምህርትን ዕድል አላገኘም፡፡ ማይም ነው፡፡ በከተሞችም ከማንበብና ከመጻፍ ጨዋ የሆነው የሕዝባችን ክፍል ቊጥሩ ቀላል አይደለም፡፡ ዘርፈ-ብዙ ለሆነው ኋላ ቀርነታችን ከሚጠቀሱት ዐበይት ምክንያቶች አንዱ ፊደል ያልቈጠረ ዜጋ ይዘን 21ኛውን ክፍለ ዘመን መዝለቃችን ነው፡፡ ጭቈና እና ጨቋኞችን አዝለን ለመኖራችንም የጎላ ድርሻ አለው፡፡ አገዛዞች ከጭቈና መሣሪያቸው አንዱ ራሳቸው ደንቁረው ሕዝብን ማደንቆር ነው፡፡ ያልነቃ፣ ያላወቀ፣ የማይጠይቅ ሕዝብ ለአገዛዝ መፋፋት ለም መሬት ነውና፡፡ እስከ ዐቢይ የዘለቀው የወያኔ አገዛዝ በዚህ ረገድ የተሳካላቸው ይመስላል፡፡ የለየለት ማይሙን ብቻ ሳይሆን ‹የተማሩ› ደናቁርትን በገፍ ማፍራት የተቻለበት ዘመን ነው፡፡ ትውልድ ገዳይ ስለሆነው የትምህርት ፖሊሲያቸውም ብዙ የተባለለት ነው፡፡ በጐሣ ተቧድኖ በደንጊያ እና በዱላ የሚጨፋጨፍ ትውልድ አፍርቷል፡፡ አለትምህርት ሁለንተናዊ ዕድገትና ብልጽግና የማይታሰብ ነው፡፡ ስለሆነም ሕዝባዊ አስተዳደርን በቀበሌ/ወረዳ ደረጃ ማስፈን ከተቻለ ማኅበረሰቡ ቀን ከሌት ተግቶ ማከናወን ካሉበት ተግባራት አንዱ፣

 • ከመንግሥት አካላት ጋር በመቀናጀት ተከታታይነት ባለው የመሠረተ-ትምህርት መርሐ ግብር (basic literacy program) ወገናችንን (ወጣቶችን እና ጎልማሶችን) ከማይምነት ማላቀቅ ነው፡፡ ጎን ለጎንም በሚመጥናቸው መልኩ የዜግነት (የሲቪክ) ትምህርት እንዲያገኙ ማድረግ፡፡ የዓፄ ኃይለሥላሴና የደርግ አገዛዞች እንደ ቅደም ተከተላቸው በ‹‹ፊደል ሐዋርያ›› እና ‹‹መሠረተ ትምህርት ዘመቻ›› ሕዝባችንን ከማይምነት ለማላቀቅ ያደረጉት ጥረት የሚያስመሰግን ተግባር መሆኑን ለማንሳት እወዳለሁ፡፡ ይህም አስተያየት አቅራቢ በኋለኛው ዘመቻ ተሳታፊ በመሆን የአባቶችና እናቶችን ምርቃት ለማግኘት በቅቷል፡፡
 • ከሚመለከተው የመንግሥት አካላት እና ባለሀብት ከሆኑ ነዋሪዎች ጋር በመተባበር በቀበሌው/ወረዳው የሚገኙ ትምህርትቤቶችን ማስፋፋትና ማጠናከር፤በበጎ ፈቃደኝነት ወጣት ተማሪዎች ወገናቸውን ከማይምነት ለማላቀቅ በሚካሄደው መርሐ ግብርም ሆነ በመደበኛ ት/ቤት ትምህርታቸውን ለሚከታተሉ ተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት መስጠት፡፡ 
 • በየቀበሌው/ወረዳው ቢያንስ አንድ የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት ማዘጋጀት

2ኛ/ ጤና

 • የአንድ ጊዜ የዘመቻ ተግባር ሳይሆን በቋሚነት የአካባቢ ፅዳትን በጋራ መጠበቅ
 • ከመንግሥትና በቀበሌው/ወረዳው ነዋሪ ከሆኑ የግል ባለሀብቶች ጋር በመተባበር የማኅበረሰቡን አቅም ያገናዘቡ አዳዲስ ጤና ጣቢያዎች እንዲቋቋሙ የማድረግና ያሉትንም በሰው ኃይል፣ በመድኃኒት እና በመሣሪያ አቅርቦት እንዲጠናከሩ የማድረግ
 • ለማኅበረሰቡ የጤና አጠባበቅ ትምህርቶችን በተከታታይነት መስጠት

3ኛ/ ሕግና ሥርዓትን በነዋሪው የማስከበር/የነዋረውን ደኅንነት የመጠበቅ ተግባራት

 • ከፖሊስ ኃይል ጋር በመተባበር የአካባቢ ሰላምና ደኅንነትን በጋራ የመጠበቅ
 • በመንግሥት በኩል ያለው የፍትሕ ሥርዓት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ማኅበረሰቡ ቀለል ያሉ የወንጀል መተላለፎችን እና የፍትሐብሔር ጉዳዮችን ራሱ በሚሰይማቸው ዳኞቸ እንዲዳኝ የማድረግ፤ ከዚሁ ጎን ለጎን በዕርቅ፣ በይቅርታና መጠነኛ ካሣ ሊታለፉ የሚችሉ ጥፋቶችን የአካባቢ ሽማግሌዎችንና የሃይማኖት አባቶችን በመጠቀም መፍትሄ የመስጠት ባህላዊ ሥርዓትን ማዳበር

4ኛ/ ብሔራዊ መታወቂያ መስጠትን ጨምሮ ልደት፣ ሞት፣ ጋብቻ፣ ፍቺን የመመዝገብና ምስክር ወረቀት የመስጠት አገልግሎት

5ኛ/ የሰውነት ማጎልመሻና መዝናኛ ሥፍራዎቸን ማዘጋጀት፡፡ 

 • በነዋሪዎች የሚተዳደር (የሕፃናት፣ የወጣቶች፣ የጎልማሶችና የአረጋውያንን ፍላጎት ግምት ውስጥ ያስገባ) የስፖርት ማዘውተሪያ እንዲሁም የመዝናኛ ማዕከል ማቋቋም

5ኛ/ የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች

 • በየቀበሌው/ወረዳው ቢያንስ አንድ የመናፈሻ/የመዝናኛ ዐፀድ (ፓርክ) ማዘጋጀት፡፡ ቀበሌው/ወረዳው በሚገኝበት የከተማ አስተዳደር ዕቅድን ባገናዘበ መልኩ ለዚሁ ዓላማ የሚውል ቦታ ማዘጋጀት፤ 
 • በቀበሌው/ወረዳው ወንዞች ካሉ ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ጋር በመተባበር በማፅዳት፣ ዛፎችና ልዩ ልዩ ዕፅዋትን በመትከል የመናፈሻ ዐፀዱ አካል ማድረግ 
 • በመኖሪያ ቤቶች አካባቢ (ባለንበት ዘመነ ኢሕአዴግ ልቅ እንደሆነውና የድምፅ፣ የአየርና ፈሳሽ ኬሚካሎች ብክለት የመደበኛ ሕይወታችን አካል እንደሆኑት) ለጤናማ አነዋወር ምቾት የሚነሱና አደጋ የሚያደርሱ የንግድ ሥራዎችን (ጋራዥ፣ የመኪና መሸጫ፣ ጥቃቅንና አነስተኛ ፋብሪካዎች ወዘተ) ከመኖሪያ አካባቢ ተለይተው አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ፣ ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ጋር በመተባበር የሕግ ክልከላ ማድረግ፣ በሥራ ላይ ያለውን ሕግም ማስከበር (ርግጡን ለመናገር ሕጉ ሳይኖር ቀርቶ አይደለም፡፡ ተግባራዊ እንዲሆን ካለመፈለግ እንጂ)፤ በነገራችን ላይ እስካሁን በዘለቀው የኢሕአዴግ አገዛዝ የቀበሌ/ወረዳ ‹አስተዳዳሪዎችና ሠራተኞች› አንዱ የንቅዘት ምንጭ በመኖሪያ ቤቶች/መንደር ውስጥ የነዋሪዎችን መብት በመጋፋት ከሕግ ውጭ ለንግድ ሥራ የሚሰጡ ፈቃዶች ናቸው፡፡ 

6ኛ/ አነስተኛ የመሠረተ ልማት፣ የመኖሪያ ቤትና የሕንፃ ግንባታዎች 

 • የየከተማውን መሪ ዕቅድ መሠረት አድርጎ የውስጥ ለውስጥ መንገድ ግንባታዎችን፤ የሽንት ቤቶችና የሌሎች ፍሳሾች ማስወገጃ መሥመሮችን፤ የመኖሪያ ቤት እና የሕንፃ ግንባታዎችን እና የነዚህኑ ዕድሳትና ጥገና ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ጋር በመተባበር ለማኅበረሰቡ ምቹ የመኖሪያ አካባቢ መፍጠር

እነዚህንና ሌሎች ማኅበረሰብ አቀፍ ሥራዎችን በነዋሪዎች ሙሉ ተሳትፎ ማከናውን ይቻላል፡፡ ይህ ዓይነቱ ሕዝባዊ አስተዳደር እንዲሰፍን በየደረጃው የሕዝቡን የሥልጣን ባለቤትነትን ማረጋገጥ ይጠይቃል፡፡ ሕዝቡ የሥልጣን ባለቤት እንዲሆን ደግሞ ለዘመናት እግር ተወርች ጠፍሮ ከያዘን የአገዛዝ ሥርዓት መላቀቅ የግድ ይላል፡፡ የአገዛዝ ሥርዓትን (በተለይም በጐሣ ፖለቲካ የተበከለውን) ለማስወገድ ደግሞ ሕዝቡ እንደ ሁኔታው በማኅበረሰብ (ሲቪል) ድርጅትም ሆነ በፖለቲካ ማኅበር ተደራጅቶ በኅብረት ሰላማዊ ትግል ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ 

ዜግነትን መሠረት ላደረገ መንግሥተ ሕዝብ (ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት) የቆማችሁ የፖለቲካ ማኅበራት የቀበሌን/የወረዳን አስተዳደር የመንግሥትም ሆነ የየትኛውም ፖለቲካ ማኅበር ጣልቃ ገብነት ሳይኖር ቀበሌ/ወረዳ የሕዝብ የሥልጣን ባለቤትነት የሚረጋገጥባቸው መሠረታዊ የአስተዳደር ዕርከኖች መሆናቸውን አምናችሁ በፓርቲ ፕሮግራማችሁ ከቀረፃችሁና ለተግባራዊነቱም የምትሠሩ ከሆነ፣ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጎናችሁ እንደሚቆም አትጠራጠሩ፡፡  ለመጪው ምርጫ ላይሆን ይችላል፡፡ ባንድ በኩል ምርጫው ስለመካሄዱ ዋስትና የለም፤ ቢካሄድም እንኳን ከወዲሁ ነፃ፣ ገለልተኛ እና ፍትሐዊ እንደማይሆን ከበቂ በላይ ምልክቶች ታይተዋል፤ (ለተጨማሪ መረጃ ይህንን አገናኝ ይጫኑ https://www.ethioreference.com/archives/21333) በሌላ ወገን ምርጫው ቢካሄድና የዐቢይ ኢሕአዴግ (መላ አገሪቱን የተቈጣጠረበትን – የሠራዊት፣ የደኅንነት፣ የፖሊስ፣ የልዩ ኃይል፣ የመንግሥት ፋይናንስ፣ የሚዲያ ወዘተ. – መዋቅር ተጠቅሞ) ተመርጫለሁ ቢል ኢሕአዴግ የሚባለውን ነውረኛ አገዛዝና ኢትዮጵያ ላይ የጫነውን ‹የዕዳ ደብዳቤ› (የማስመሰያ ‹ሕገ መንግሥቱን›) ቀዳዶ ለሕዝባዊ መንግሥት መሠረት የሚጥል የሥርዓት ለውጥ ያመጣል ብሎ መጠበቅ ፀሐይ በስተምዕራብ ትወጣለች እንደማለት ይሆናል፡፡ መንግሥተ ሕዝብ የሚሠለጥንበትን ሥርዓት (ዴሞክራሲ) አለሥነሥርዓታዊ ፍትሕ (በየደረጃው ያሉ ሂደቶች እውነተኛነትና ፍትሐዊነት)  ማሰብ አይቻልም፡፡

Filed in: Amharic