>
5:13 pm - Sunday April 18, 9526

ሚስት መራጩ የናዚ ፓርቲ <<የኑረምበርግ ህግ>> እና ልባሙ ጀርመናዊ  (በአማንዳ ማኪያስ) 

ሚስት መራጩ የናዚ ፓርቲ <<የኑረምበርግ ህግ>> እና ልባሙ ጀርመናዊ

 

 በአማንዳ ማኪያስ 
“….የአይሁድ ዝርያ ያላትን ሴት በእጮኝነት መያዙ ወሬ በናዚ ፓርቲ ውስጥ በመዛመቱ …..”
የጀርመኑ ናዚ ፓርቲ እ.ኤ.አ. በ1931 የናዚ ሰላምታ ወይም <<Siege hiel>> ወይም በእንግሊዝኛ <<hail victory> በመባል የሚጠራውን የሰላምታ አሰጣጥ ማንኛውም ጀርመናዊ ዜጋ ለፉህረሩ (ለመሪው) ፣ ለናዚ ፖርቲና ለሃገሩ ያለውን ታማኝነት ማሳያ ምልክት እንዲሆንና ሁሉም የሃገሪቱ ዜጎች እንዲተገብሩ አስገዳጅ ህግ ወጣ።
እ.ኤ.አ. በ1934 የጀርመኑ ፉህረር አዶልፍ ሂትለር በተገኘበት የተደረገ ሰልፍ ላይ አንድ ያልተለመደ ክስተት ተፈጠረ። <<ኦገስት ላንሜሰር>> የተባለ ለናዚው ፓርቲ ታማኝ የነበረ ጀርመናዊ ባልተለመደ መንገድ የቀኝ እጅን ከትከሻ ትይዩ በመዘርጋት የሚሰጠውን የናዚ ሰላምታ ባለመስጠትና እጆቹን አጣምሮ በመቆም በስርአቱ ላይ ያለውን ተቃውሞ በጀግንነት አሳይቷል። ላንሜሰር የናዚውን ፓርቲ እ.ኤ.አ. በ1931  የተቀላቀለ ሲሆን በሃገሪቱ ብቸኛ በሆነው በዚህ የፖለቲካ ስርአት ውስጥ በተለያዩ የስራ እርከኖች ውስጥ አገልግሏል።
ላንሜሠር ተቃውሞውን ካሰማ ከሁለት አመታት በኋላ የአይሁድ ዝርያ ካላትና የጀርመን ዜጋ ከሆነችው ከወ/ት <<ኢርማ ኤክለር>> ጋር በፍቅር ወደቀ። የፍቅሩን ታማኝነት ለመግለፅና አብሮነታቸውን ሞት እስኪለያቸው ድረስ ለማፅናት  እ.ኤ.አ. በ1935 ለፍቅሩ እመቤት የጋብቻ ጥያቄ አቀረበላት። ይሄንን ተከትሎ የአይሁድ ዝርያ ያላትን ሴት በእጮኝነት የመያዙ ወሬ በናዚ ፓርቲ ውስጥ በመዛመቱ ፓርቲው ላንሜሰርን ከአባልነት በመሠረዝ ከፓርቲው አባርሮታል።
ላንሜንሰርና እጮኛው ኢክለር በፍቅር ስለፍቅር  ተማምልዋልና፤  አንዳቸው ለአንዳቸው ተፈጥረዋልና በናዚ ፓርቲ ውሳኔ ተስፋ ባለመቁርጥ ጋብቻቸውን ህጋዊ ለማድረግና በህግ ለማስፀደቅ ሃምቡርግ ውስጥ ጥያቄ ቢያቀርቡም በወቅቱ የአይሁድ ዝርያ ያላቸው ጀርመናውያን ከሌሎች ያለተቀየጡ ጀርመናውያን ጋር ማንኛውንም ጋብቻ እንዳይመሰርቱና የተቃራኒ ፆታ ግንኙነት እንዳይፈፅሙ በሚከለክለው “የኑረምበርግ ህግ” መሰረት ጥያቄአቸው ውድቅ ተደረጎባቸዋል። ምንም እንኳን ጋብቻቸው ህጋዊ ድጋፍን ባያገኝም ጥንዶቹ በኦክቶበር ወር 1935 እ.ኤ.አ. የበኩር ሴት ልጃቸው የሆነችውን ኢንግሪድን ወልደው ለመሳም በቅተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ እ.ኤ.አ. ጁን ወር 1936 .ሂትለር አዳዲስ የውጊያ መርከቦችን ለመመረቅ ንግግር በሚያደርግበት መድረክ ላይ ለፉህረሩ አዶልፍ ሂትለር የናዚ ሰላምታ በሚቀርብበት ጊዜ ላሜንሰር  ከመንጋው በመነጠልና የሌሎችን ቀልብ በሚስብ ሁኔታ ሁለት እጆቹን አጣምሮ በመቆም በፉህረሩና በናዚ ፓርቲው ላይ ያለውን ተቃውሞ በድጋሚ አሰምቷል።
በናዚ ስርአት የግፍ አገዛዝ የተማረረው ላንሜንሰር ልጁንና ሚስቱን ይዞ ከሃገሩ ጀርመን በመጥፋት ወደ ዴንማርክ ለመኮብለል ሲሞክር በድንበር ጠባቂዎች ተይዞ የኑረንበርጉን “Racial infamy” ወይም “የአይሁድ ዝርያ እያለው ከንፁህ ጀርመናውያን ጋር መጋባት የሚከለክል ህግ” ተላልፎ ተገኝቷል በማለት የሃሰት ክስ የመሰረቱበት ሲሆን ይህንኑ ክስ የሚያስረዳ ማስረጃ ባለማግኘታቸው በድጋሚ የአይሁድ ዝርያ ካላት የልጆቹ እናትና ሚስቱ ጋር እንዳይገናኝ አስጠንቅቀው ለቅቀውት ነበር።
ይሁን እንጂ ሞት ካለያቸው በቀር በህይወት ሳለች በዘሯ ምክንያት ላይተዋት የማለላት ሚስቱን ኤክለርን ለመተው የሚጨክን ልብ በማጣቱና ሊተዋት ባለመቻሉ ላንሜሰር በድጋሚ እ.ኤ.አ. በ1938 አይሁዶች የሚታሰሩበት ኮንሰንትሬሽን ካምፕ ውስጥ እንዲታሰር የተፈረደበት ሲሆን ከዚህ በኋላ የህይወቱን ፍቅር፣ የሚስቱን ዐይን በድጋሚ ለማየት አልታደለም።
የላንሜንሰርን እስራት ተከትሎ የጀርመን መንግስት የሚስጥራዊ የፖሊስ ቡድን ሁለተኛ ልጃቸውን ልትወልድ ደርሳ የነበረችውን ሚስቱን ልጇን እስክትወልድ ድረስ በመደበኛ እስር ቤት ያቆዩዋት ሲሆን ሁለተኛ ሴት ልጃቸውን ኤሪንን እንደተገላገለች ሴቶች ብቻ ወደሚታሰሩበትና “የማደንዘዣ ማእከል” ወደሚባለው የሴቶች ማሰቃያና መግደያ ኮንሰንትሬሽን ካምፕ ከተዘዋወረች በኋላ በግድያ ጣቢያው ውስጥ በጨካኙና በአረመኔው ናዚ እጅ ከሌሎች 14,000 ሴቶች ጋር በኬሚካል ተመርዛ ተገድላለች።
ላንሜሰር የእስራት ጊዜውን አጠናቆ እንደወጣ አንዳንድ ሰራዎችን ለመስራት እየሞከረ ከቆየ በኋላ እ.ኤ.አ. በ1944 ወደ ጦር ግንባር የተላከ ቢሆንም ከጥቂት ወራት በኋላ በክሮሺያ ውስጥ መጥፋቱ ሪፖርት ተደርጓል።
——-
ምንጭ: ኢንዲፐንደንት ድረገፅ
ትርጉም: በጥላሁን ግርማ
Filed in: Amharic