>

«ኢትዮጵያ የምትኖረው በአሜሪካ በጎ ፈቃድ ሳይሆን በራሷ ጥንካሬ ነው!!!»  (ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ)

«ኢትዮጵያ የምትኖረው በአሜሪካ በጎ ፈቃድ ሳይሆን በራሷ ጥንካሬ ነው!!!» 

ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህርና የዓባይ ውሃ ጉዳይ ተመራማሪ
አስቴር ኤልያስ – አዲስ ዘመን
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅን ሁሉም ኢትዮጵያዊ በእጅጉ ይናፍቃል፡፡የግንባታውን መጠናቀቅ በኢትዮጵያዊም ሆነ በትውልደ ኢትዮጵያዊ በእጅጉ በጉጉት የመጠበቁን ያህል ግንባታው ከፍፃሜ እንዳይደርስ የሚፈልጉ አካላት ጣልቃ በመግባት የተለያዩ ደንቃራዎችን ሲያስቀምጡ ኖረዋል፤ ዛሬም እንደዚያው፡፡
ኢትዮጵያ ህዝቧ ከድህነትና ከጨለማ ጋር እየታገለ የሚገፋውን የመከራ ህይወት ታሪክ ለማድረግ ስትል የዛሬ ዘጠኝ ዓመት በአባይ ወንዝ ላይ የህዳሴ ግድብን ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ በማስቀመጥ የጀመረችው ግንባታ በመንግሥትና በህዝቡ ጥረት አፈፃፀሙ አሁን 71 በመቶ ቢደርስም፤አንዳንድ ድምፆች ግን መሰናክል ለመሆን ሲጥሩ ቆይተዋል፡፡ ሀገሪቱ ከየትኛውም የዓለም ክፍል ለግድቡ ግንባታ የሚውል ምንም ዓይነት ብድር እና ድጋፍ እንዳታገኝ ያልተፈነቀለ ድንጋይ እንደሌለም ይታወቃል፡፡
ይህ ሁሉ ታልፎ እንቅስቃሴው ሲጀመር ደግሞ አንዴ «ኢትዮጵያ ምን ቆርጧት ነው በአባይ ወንዝ ላይ ግድብ የምትገድበው?» ሌላ ጊዜ «የግድቡ ሂደት በዓለምአቀፍ ሙያተኞች ክትትል ሊደረግበት ይገባል፡፡» ሲባል ቆይቷል፤ሌላ ጊዜ ደግሞ ››ከህዳሴ ግድቡ ልታመነጭ ያሰበችውን የኃይል መጠን መቀነስ ይኖርበታል» እየተባለ ዛሬ ላይ ደርሳለች፡፡
ዛሬም ቢሆን ፈተናዎች መልካቸውን እየቀያየሩ መምጣቸው አልቀረም፡፡ በቅርቡ ደግሞ አሜሪካ ኢትዮጵያን፣ሱዳንና ግብፅን አደራድራለሁ በሚል ስትንቀሳቀስ ቆይታለች። በዚህም አሜሪካ ወገንተኝነቷ በግልፅ ወደግብፅ ያጋደለ በሚመስል ሁኔታ በኢትዮጵያ ላይ ጣልቃ ገብታለች፡፡ ይህ የአሜሪካ አቋም አንዱ የፈተናዎቹ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚችል ብዙዎች ይስማማሉ፡፡
ይህን የአሜሪካ አካሄድ እንኳን የግድቡ ባለቤት የሆነችውን ኢትዮጵያንና ህዝቧን ቀርቶ፣አሜሪካውያንን ጨምሮ ሌሎች ታዋቂ ግለሰቦች እና ፖለቲከኞች ክፉኛ ተችተውታል። በዚህ የአሜሪካ የወገንተኝነት ሚና እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ አዲስ ዘመን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህርና የዓባይ ውሃ ጉዳይ ተመራማሪ ከሆኑት ከፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ ይዘን ቀርበናል። መልካም ንባብ ይሁንልዎ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ቀደም ሲል አንስቶ ብዙዎች በቀጣዩ ዘመን እንዳለፉት የዓለም ጦርነቶች በአገራት መካከል ጦርነት ሊፈጥር የሚችል ከሆነ ምክንያቱ የውሃ ጉዳይ ይሆናሉ ሲሉ ቆይቷል፤ አሁን ኢትዮጵያና ግብፅ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የገቡበትን ፍጥጫ ከዚህ አንጻር እርስዎ እንዴት ያዩታል?
ፕሮፌሰር ያዕቆብ፡- በመጀመሪያ ነገር ቀጣዩ ጦርነት ሊካሄድ የሚችለው በውሃ ላይ ነው የተባለው ትክክለኛ አባባል አይደለም። በአንድ ወቅት የግብፅ ሚኒስትር ዴኤታ ግብፅና እሥራኤል በካምፕ ዴቪድ ከተስማሙ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፤ ከእሥራኤል ጋር ጦርነት ውስጥ ሲከቱን በነበሩ ጉዳዮች ላይ ስምምነት አድርገናል። ከዚህ በኋላ ግን ጦርነት ውስጥ የምንገባ ከሆነ በውኃ ምክንያት ነው ማለታቸው ግልፅ ነው።
ይህ አባባል ለአድማጮቻቸው ያማረ ንግግር ለማቅረብ ብለው የተናገሩት ሲሆን፣ እግረ መንገዳቸውን ደግሞ ከሌላ አቅጣጫ የሚመጣ ስጋት የለብንም ለማለት ፈልገው የተናገሩት ነው፤ ይሁንና እሱም የተሳሳተ አባባል ነው የሚል እምነት አለኝ። ምክንያቱም በውኃ ላይ የሚያዋጋ ነገር አልነበራቸውም፤ እስከአሁንም የለም። ለወደፊቱም ሊኖር አይገባም ባይ ነኝ።
በርካታ የዓለም ሀገሮች የሚጋሯቸው ወንዞች እንዳሏቸው ይታወቃል። ወንዞቹ በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ናቸው። ውኃው የጋራ ሀብታቸው የሆኑ አገሮች በስምምነት፣ በድርድር፣ በመተሳሰብ እንዲሁም በመተማመን ነው የሚጠቀሙት እንጂ በጦርነት አይደለም። ምክንያቱም የጋራ ሀብታቸውን መጠቀም መብታቸውንም ማስከበር የሚኖርባቸው በጋራና አንዱ ሌላውን በማይጎዳ ሁኔታ እንጂ ቃታ በመሳሳብና እርስ በእርስ በመዋጋት አይሆንም።
አዲስ ዘመን፡- በእርግጥ እርስዎ ያሉት እንደተጠበቀ ሆኖ በአሁኑ ወቅት ግብፅ ሰራዊቷን በተጠንቀቅ እንዲቆም አዛለች ይባላል፤ቀጣዩ ሁኔታ ምን ሊሆን ይችላል ብለው ያስባሉ?
ፕሮፌሰር ያዕቆብ፡- ግብፅ በኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ በያዘችው አቋም የተነሳ እኔ ያልኩት ካልሆነ በሚል ጦር እሰብቃለሁ የምትል ከሆነ በጣም የተሳሳተ አካሄድ ይሆንባታል። ይህን ካደረገች ምናልባትም በዓለም ላይ በውሃ ላይ ጦርነት ቀስቅሳ እጅግ በጣም አደገኛና ስህተት የተሞላበት ሥራ ልትሠራ የምትችል አገር ተብላ የምትጠቀስ ልትሆንም ትችላለች።
ምክንያቱም በአሁኑ ወቅት በየትኛውም ጉዳይ ላይ ስምምነት ማድረግ የሚቻል ሆኖ እያለ፤ መነጋገርና መወያየትም እየታቸለ በተፈጥሮ የተቸርነውን ውኃ በመተሳሰብ መጠቀም እየተቻለ ይህን ለማድረግም ጊዜውም ሁኔታውም የሚፈቅድ ሆኖ እያለ ጦርነት ይሉ ጉዳይ ውስጥ የሚያስገባት ስለምንድን ነው? ውኃ የከለከላትስ ማን ነው? ለመከልከልስ ያሰበ ማን አለ?
እስከ አሁን ግብፅ ናት ውኃ አመንጪ አገሮች ካለ እኔ ፈቃድ ውኃ መጠቀም የለባቸውም እያለች ስትከልክል የኖረችው፤ ይህ አካሄድና አስተሳሰብ ደግሞ በየትኛውም ሚዛን ቢለካ በጣም የተሳሳተ ነው።ይህን አመለካከቷን የሚቀበላትም አይኖርም። ውይይቱም ፣መተሳሰቡም አይሆነኝም፤ ጦሬን እሰብቃለሁ የምትል ከሆነ ደግሞ ድርጊቷ የጤነኛ አገር አይሆንም፤ይልቁንም የእብድ ተግባር ሊባል ይችላል።
አዲስ ዘመን፡- ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ ከተቀመጠለት ጊዜ ጀምሮ ግብፅ በእጅ አዙር ኢትዮጵያ ላይ የውክልና ጦርነት ስታካሂድ መቆየቷ ይታወቃል፤ አሁንም በግድቡ ላይ በያዘችው አቋም የተነሳ ይህ ሊቀጥል ይችላል ብለው የሚያስቡ ወገኖች አሉ? እርስዎ በዚህ ላይ ምን አስተያየት አለዎት?ከቀጠለስ በእርስዎ አመለካከት መፍትሔው ምንድን ነው?
ፕሮፌሰር ያዕቆብ፡- ግብፅ እንደተጠቀሰው የኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግሥትን የሚቀናቀኑ ኃይሎችን ስትደግፍና ስትረዳ ኖራለች። በተለይ ደግሞ በትክክል በታሪክ የሚታወቀው ለኤርትራ ነፃ አውጪ ድርጅት በካይሮ የሬዲዮ ጣቢያ አቋቁማ እንዲንቀሳቀስ ደግፋለች፤ የነፃነት ድርጅቱ በነፃ እየተደራጀ እንዲንቀሳቀስ እና በኋላም የኢትዮጵያን መንግሥት እንዲያውክ ሳታሰልስ ለብዙ ዘመናት ሠርታለች። በዚህ መልኩ የኢትዮጵያን መንግሥት ሉዓላዊነት የግዛት አንድነትንም የሚያውክ ኃይል ከተገኘ መንግሥትን ለማዳከም ስትል ከመርዳት ወደኋላ የምትል አይመስለኝም። ምክንያቱም የቀደመ ተግባሯ ሲያመላክት የቆየው ይህንኑ ሁኔታ ነውና።
ይህ አካሄድ የተሳሳተ ነው። አካሄዱ እስከአሁንም ስትከተል የቆየችው ዓይነት አካሄድ ነው፤ወደፊትም ለማድረግ ብታሰብ የሚያስደንቅ አይደለም። ነገር ግን ዞሮ ዞሮ ግብፅ የኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግሥትን የሚቀናቀኑ ኃይሎችን እየደገፈች የኢትዮጵያን መንግሥት እጥላለሁ፤ እንደፈለኩም እሆናለሁ፤ አዝበታለሁ የሚል ህልም ካላት አሁንም እጅግ የተሳሳተ አካሄድ ይሆንባታል። ስለዚህ ይህ ዓይነቱ አሠራርና አካሄድ ለራሷ ለግብፅም አይበጅም፤ተቀባይነት የሌለው አሠራርም ነው።
በሌላ አገር ውስጥ ጠላትነት ባለው መንገድ ጣልቃ መግባት ማለት ለራሱ ጣልቃ ለሚገባውም አገር ለነገም ሆነ ለዛሬ አይጠቅምም። የተሳሳተም አካሄድ በመሆኑ በዓለም ላይ ይህንን የሚደግፍ ምንም ዓይነት አሠራር በማንም ዘንድ ደግሞ ተቀባይነት ያለው የፖለቲካ አካሄድ የለም።
አዲስ ዘመን፡- በዚህ ላይ በኢትዮጵያ በኩል መፍትሔ ሊሆን የሚችለው አካሄድ በእርስዎ አተያይ ምን ሊሆን ይችላል?
ፕሮፌሰር ያዕቆብ፡- ኢትዮጵያ የራሷ ሉዓላዊ መንግሥት አላት። ኢትዮጵያዊ ደግሞ አገሩን የሚወድ፣ ነፃነቱን የማያስደፍር ብሎም ማንነቱን የሚያከብርና ንብረቱን በሚገባ የሚጠብቅ ከመሆኑም በላይ በዚህ ጉዳይ ቀናኢ ነው፤ በታሪኩም ይህንን ሲያደርግ ኖሯል። ስለዚህ ሌላ አገር በኢትዮጵያ ጉዳይ ጣልቃ ገብቶ የሚያመሰቃቅልበትን ሁኔታ ህዝብም አይፈቅድም። ለህዝብ የቆመ መንግሥትም ቢሆን ይህን ዓይነቱን ነገር በጭራሽ አይፈቅድም።
ስለዚህ መፍትሔው አንድነትን መጠበቅ ነው። የአገርን ክብርና ጥቅምም ማስጠበቅ ጭምር ነው። ህብረተሰቡ ካለበት ችግር ወጥቶ ወደተሻለ የኑሮ ደረጃ ከፍ በማለት ወደብልፅግና የሚያመራበትን መንገድ መከተል ነው። በእኔ እምነት መፍትሔው ይህ ነው። ሁሌም ቢሆን ኢትዮጵያ ራሷን ከወራሪም ሆነ ከጣልቃ ገብ የመጠበቅ ልምዷ አዲስ አይደለም። አንዳች የአገር ጠንቅ በመጣ ጊዜ መንግሥትና ህዝቡ እጅና ጓንት ሆነው በአንድ ልብ ጣልቃ ገብነትን ሲከላከሉ ኖረዋል።
ይህን የማያውቅ ካለ የታሪክ መዛግብትን አገላብጦ መረዳት ግድ ይለዋል። ዓድዋ ላይ ከጣሊያኖች ጋር ሲደረግ በነበረ ትግል እንዲሁም የሶማሊያ መንግሥት ወደ 700 ኪሎ ሜትር ያህል ወደ ኢትዮጵያ ዘልቆ ገብቶ ያደረገውን ወረራ ለመቀልበስ የተደረጉ ትግሎች ለኢትዮጵውያን ብርታት እና ጀግንነት ማረጋገጫዎች ናቸው። ምንም እንኳ አሁን ግንኙነታችን መልካም ቢሆንም፣ የቅርብ ጊዜ ትዝታ የሆነው የኤርትራ መንግሥት በሰሜን ኢትዮጵያ ወረራ ሲያካሄድ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት ተዋግተው ነው ማንነታቸውን ያስከበሩት። እናም የኢትዮጵያ ታሪክ እንደሚያስገነዝበው የኢትዮጵያ ህዝብ እና መንግሥት ለውጭ ወረራና ጣልቃ ገብነት እስከአሁን ድረስ ተንበርክከው አያውቁም፤ ለወደፊትም በዚህ መቀጠሉ በእኔ እምነት አማራጭ የሌለው ነው የሚመስለኝ።
አዲስ ዘመን፡- ስለዚህ ግብፅ በተለያዩ አቅጣጫዎች በመንቀሳቀስ የቤት ሥራዎችን ለተለያዩ አካላት በመስጠት በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር ብትሞክርም ኢትዮጵያን የሚያሰጋት አንዳች ነገር አይኖርም ነው የሚሉት?
ፕሮፌሰር ያዕቆብ፡- እንግዲህ ሌላ አገር በጠላትነት ቆሞ ጎረቤት አገርን እወራለሁ ካለ ስጋቱ ይኖራል። ነገር ግን እያንዳንዱ አገር ኢትዮጵያን ጨምሮ አገርን የመከላከል ኃላፊነት የተጣለባቸው እንደ መከላከያ ሠራዊት ያሉ ተቋማት አሉ፤ስለሆነም ተወራሪው አገር አጁን አጣጥፎ የሚጠብቅ አይመስለኝም። ይህ ደግሞ በኢትዮጵያ ሊጀመር አይችልም። ምክንያቱም ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ይህ ዓይነቱ ነገር በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ እስከአሁን ተደርጎ አይታወቅም። እስከምናውቀው ድረስ ከዚህ በኋላም አይደረግም። አገርን ከጣልቃ ገቦች የመጠበቅና ሉዓላዊነቷን የማስከበር ባህሏን ስናስተውል ፣ስጋት አለ ቢባልም ስጋቱ በትህትና የሚስተናገድ ሳይሆን በኃላፊነት የሚመከት ይመስለኛል።
አዲስ ዘመን፡- በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ አሜሪካ በአደራዳሪነት ሰበብ ሰነድ በማዘጋጀቷና ኢትዮጵያንም እንድትፈርም
 ለማድረግ መሞከሯን ተከትሎ መንግሥት የራሱን አቋም ወስዷልና ይህን የመንግሥት አቋም እንዴት ያዩታል?
ፕሮፌሰር ያዕቆብ፡- መንግሥት የወሰደው አቋም ትክክለኛ ነው። ዋናው ነገር ከዚህ ሌላ አማራጭ አለ ወይ የሚለው ነው። ምናልባትም በአሜሪካ የቀረበው ሰነድ ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ሀብት እንዳትጠቀም የሚከለክል ነው። እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ትልቅ አገር ናት። የራሷን መብትና ሉዓላዊነት በሚገፋ ነገር ላይ ማንነቷን አሳልፋ አትሰጥም። ይህንንም ሁሉም ያውቃል።
አዲስ ዘመን፡- አሜሪካ በአደራዳሪነት ስም የወሰደችው አቋም በተለያዩ አካላት ከመተቸቱም በተጨማሪ የአንድን አገር መብት ይጥሳል እየተባለ ነውና እርስዎ በአሜሪካ አቋም ላይ ያልዎት አስተያየት ምንድን ነው?
ዶክተር ያዕቆብ፡- አሜሪካ ሦስቱ አገሮች ማለትም ኢትዮጵያ፣ግብፅና ሱዳን በህዳሴ ግድብ አሞላልና በግድቡ የሥራ እንቅስቃሴ ያልተስማሙባቸው ጉዳዮች ስላሉና ከዚህም የተነሳ ረዘም ያለ ጊዜ ወስደው እየተነጋገሩ ሲጨቃጨቁ በመቆየታቸው እስኪ እኔ ከዓለም ባንክ ጋር ሆኜ ታዛቢ ልሁንና ላግዛችሁ በሚል ትህትና የተሞላበት ጥያቄ በማቅረቧ ሦስቱም አገሮች በታዛቢነት ተቀብለዋታል።
እንግዲህ መጀመሪያ አካባቢ ታዛቢ ልሁን ብላ ወደ ሦስቱ አገራት ቀርባ ሥራዋን አንድ ብላ የጀመረችው አሜሪካ ኋላ ላይ ግን ወደ አመቻችነት ተቀይራ ቁጭ አለች። ቀጥሎም ራሷን ወደ አደራዳሪነት ከፍ በማድረግ ራሷን በራሷ ሾመች።
ከዚያም ቀጥሎ ደግሞ ሦስቱ አገሮች ድርድራቸውን ሳይጨርሱ እና ሊያስማማቸው ወደሚችል ደረጃ በቅጡ እንኳ ሳይደርሱ በዚህ ተስማሙ የሚል ሐሳብ ማቅረብ ጀመረች። ያንኑ የራሷን ሐሳብ ህግ በሚመስል ሰነድ ከሽና በዚህ ላይ ብትፈርሙ ይሻላችኋል የሚል ሐሳብም ነው ያቀረበችው። ይህ ሐሳብ ግን ለግብፅ በሚወግን መልኩ የተከሸነ ነው።
ይህን ማድረግ ትክክል አለመሆኑን የህዳሴ ግድቡ ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ እንዲሁም ሱዳን መግለጻቸው ይታወቃል። አሜሪካ ራሷ ያቀረበችውን ሰነድ ሀገሮቹ መቀበል ካልቻሉ ግድቡንም መሙላት አይቻልም ሲል የአሜሪካ ትሬዠሪ ሚኒስቴር መግለጫ ማውጣቱ ይታወቃል። መግለጫው እንደወጣም ሐሳቡ ኢትዮጵያን እንዳስቆጣት የኢትዮጵያ መንግሥት ከሰጠው መግለጫ መመልከት ይቻላል።
የኢትዮጵያ ህዝብንም በተለያየ መድረክ ስናዳምጠው ከሊቅ እስከ ደቂቅ ያለው በሙሉ ይህን አሜሪካ በአደራድራለሁ ስም ኢትዮጵያ እንድትፈርም ያቀረበችውን ሰነድ አልወደደውም ብቻ ሳይሆን አልተቀበለውም። በእዚህ ላይ ህዝቡ በተለያየ መንገድ ተቃውሞውን እያሰማ ነው። በአሜሪካ የሚገኘውም ኢትዮጵያዊም ሆነ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ይህን በመቃወም በተደጋጋሚ ሰልፎችን አካሂዷል።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን ጨምሮ ዓለም ላይ የአሜሪካን አቋም የሚፃረር ፒቲሽን እየተፈረመ መሆኑ ይታወቃል። ከዚህ በተጨማሪ የአሜሪካ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ የአሜሪካ የምክር ቤት አባላት እንዲሁም የአሜሪካ የቀድሞ ዲፕሎማቶችና የዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰሮች ይህን የአሜሪካ ጣልቃ ገብነት በሉዓላዊ መንግሥት ስልጣን ላይ ያለአግባብ ጫና የመፍጠር ያህል ነው በሚል ተቃውሟቸውን እየገለጹ ናቸው። የአንድን አገር ሉዓላዊነት የመጠርመስ ተግባር አግባብነት እንደሌለው በመጥቀስ ነው እነዚሁ ወገኖች በቃል እና በፅሑፍ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ስለዚህም አሜሪካ የያዘችው አቋም ቢያንስ ስህተት ነው፤ ከዚያ ሲያልፍ ደግሞ ጥፋት ነው። በአሜሪካ የተሳሳተ አካሄድ ሊጎዱ የሚችሉት ኢትዮጵያውያን እንዳሉ ሆነው የአሜሪካ መንግሥት ወገኖችም ጉዳዩን ተገቢ ያልሆነ አቋም በመሆኑ አልተቀበሉትም፤በፅኑ እየተቃወሙትም ይገኛሉ።
አዲስ ዘመን፡- አሜሪካ የወሰደችው አቋም ኢትዮጵያውያኑን ብቻ ሳይሆን በትክክለኛ አካሄድ ለሚያምኑት ለራሷ ወገኖችም አለመዋጡ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ አቋሟ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ወዴት ይወስደዋል ብለው ያስባሉ? ዲፕሎማሲውን አይጎዳውም?
ዶክተር ያዕቆብ፡- የሁለቱ አገሮች ግንኙነትን በተመለከተ ወዴት ይሄዳል በሚለው ላይ ከወዲሁ እርግጠኛ መሆን አይቻልም። አሜሪካ የራሷን ሉዓላዊነት የምታከብረውን ያህል ኢትዮጵያም ተመሳሳይ ፍላጎት እንዳላት ልትረዳ ይገባል። አሜሪካ የራሷን የኢኮኖሚ ጥቅም እንዲሁም ነፃነቷን ትወዳለች፤ የዚያኑ ያህል ኢትዮጵያም ነፃነቷን የምትወድና ተከብራ የኖረችም አገር ጭምር መሆኗን አሜሪካ ማወቅ አለባት። በአሁኑ ወቅት አሜሪካን በማስተዳደር ላይ ያለው አካል ጉዳዩን ለማወቅ ካዳገተው የአሜሪካ ታዋቂ ግለሰቦችና ይህን ሐሳብ የማይደግፉ ወገኖች ጭምር አሜሪካ ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ ይመስለኛል።
ከሁሉም በላይ ደግሞ ኢትዮጵያ እንዲህ ዓይነት ጣልቃ ገብነት በፍፁም የማትቀበል አገር ናት፤ ይህም በዓለም ዘንድ ይታወቃል። ምክንያቱም አንድን ጉዳይ አገራት በስምምነትና በመነጋገር እንዲሁም በወዳጅነት መንፈስ ሊፈጽሙ የሚችሉበትን መንገድ ያበላሻል። ስለዚህም ኢትዮጵያ የምትኖረው በአሜሪካ በጎ ፈቃድ ሳይሆን በራሷ ጥንካሬ ነው።
ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ያላት ግንኙነት የወዳጅነትና የመፈቃቀድ ነው እንጂ የግዴታ አይደለም። ደግሞም አሜሪካ ለኢትዮጵያ ልትጠቅም የምትችለውን ያህል ኢትዮጵያም ለአሜሪካ ልትጠቀም ትችላለች። ይህ ከዚህ ቀደምም ይታወቃል።
በአሁኑ ወቅት ያለው የአሜሪካ አስተዳደር የተሳሳተ ይመስለኛል። ምክንያት ቢባል የአሜሪካ የፖለቲካ ተቋማት የሚደግፉት ዓይነት አሠራር ስላይደለ ነው። ስለዚህ ለወደፊት ስህተቱ ተስተካክሎ በሁሉቱ አገራት መካከል የተሻለ ግንኙነት ይፈጠራል ብዬ አስባለሁ። አሜሪካ በወሰደችው አቋም ምክንያት ኢትዮጵያም የያዘችው አቋም የዚያን ያህል የሁለቱን አገሮች ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ይጎዳል ብዬ አላስብም። የአሜሪካ አቋም ኢትዮጵያን ሊጎዳ ቢችልም ኢትዮጵያ ጥርሷን ነክሳ መቻል ይኖርበታል። ሁኔታው ከዚህ ባስ ካለ ደግሞ የራሷን አማራጭ ትፈልጋለች እንጂ፤ ለልጅ ልጆቿ የሚተርፍ እዳ ተሸክማ አትዘልቅም፤ ይህን የትኛውም ኢትዮጵያዊም አይፈቅድም።
አዲስ ዘመን፡- ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ የሚያስተላልፉት መልዕ ክት ይኖርዎት ይሆን?
ፕሮፌሰር ያዕቆብ፡- የኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ ህዝብ የአገሪቱን ልማት፣ እድገትና ብልፅግና ወደፊት ለማስቀጠል ማድረግ ያለባቸው የመጀመሪያው ነገር ጠንክሮ መሥራት ነው። ከዚህ ሌላ ደግሞ ከጎረቤት አገሮችም ሆነ በሩቅ ካሉ አገሮች ጋር በስምምነትና በወዳጅነት መንፈስ እንዲሁም በመተጋገዝና በመተባበር የመቀጠልን ዓላማ እና መርህን ዋና አድርጎ መያዝ ወሳኝ ነው። ይህንን የሚከተሉ ወዳጆችም ሆኑ ወዳጅ ያልሆኑ አገሮች ካሉ ይህን ለማስረዳት መሞከር ይገባል። ከሁሉም በላይ ደግሞ የራስን ጉዳይ በቁርጠኝነት እና በፅናት እንዲሁም ራስን ባከበረ መንገድ ይዞ ወደፊት መቀጠል ያስፈልጋል።
ይህን አንዳንዶች ብቻ ሳንሆን ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ብናስብበትና በዚህ አቅጣጫ ብንመራ ለዛሬይቱም ሆነ ለነገይቱ ኢትዮጵያ በጣም ወሳኝ እና ጠቃሚ ነው ብዬ አስባለሁ። ይህ የሁላችንም ግዳጅ ነው የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡኝ ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ።
ዶክተር ያዕቆብ፡- እኔም በጣም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 1/2012
Filed in: Amharic