>
5:13 pm - Tuesday April 18, 1093

የተቃዋሚዎች ጎራ የምርጫ ሽር ጉድ!! (በፍቃዱ ዘ ሀይሉ)

የተቃዋሚዎች ጎራ የምርጫ ሽር ጉድ!!

በፍቃዱ ዘ ሀይሉ
የፖለቲካ ምኅዳሩ ሲሰፋ ማኅበራዊ መሠረት መያዝ፣ መዋቅር መዘርጋት እና ፖሊሲ መቅረፅን የመሳሰሉት ከባድ ነገር ግን ትክክለኛ የፖለቲካ ሥራዎች ከፊታቸው ተደቀኑ። ትግሉ ሽቅብ ከገዢው አካል ጋር ብቻ መሆኑ ቀርቶ፣ አግድም ከእኩዮቻቸው ጋር መሆኑ ግልጽ ሆነ።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር በ2010 በሩ ገርበብ ብሎ ሲከፈት ብዙ የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች ግራ መጋባታቸው ተስተውሎ ነበር። ምክንያቱም ከዚያ ቀደም ገዢው ፓርቲን ማብጠልጠል እና ለድክመታቸው አፈናውን እንደምክንያት እየያወሱ  ያለ ተጠያቂነት ከርመው ነበር የሚለው ብዙዎችን ያስማማል። የፖለቲካ ምኅዳሩ ሲሰፋ ግን ማኅበራዊ መሠረት መያዝ፣ መዋቅር መዘርጋት እና ፖሊሲ መቅረፅን የመሳሰሉት ከባድ ነገር ግን ትክክለኛ የፖለቲካ ሥራዎች ከፊታቸው ተደቀኑ። ትግሉ ሽቅብ ከገዢው አካል ጋር ብቻ መሆኑ ቀርቶ፣ አግድም ከእኩዮቻቸው ጋር መሆኑ ግልጽ ሆነ። በፊት በፊት የገዢው ፓርቲ ተደጋጋሚ ጥፋት የተቀባይነታቸው ምንጭ እንደነበረ ሁሉ፤ በለውጡ የተቀባይነታቸው ተሻሚ ሆኖ መጣ። ይህ ሒደት ከጀመረ አሁን ሁለት ዓመታት ሆኖታል፤ ምርጫው ደግሞ ከ6 ወራት ያነሰ ጊዜ ይቀረዋል።

ያለፉትን ሁለት ዓመታት እነማን ሠሩበት? እነማን አባከኑት? እነማንስ እውነተኛ ቀልድ እየቀለዱበት ነው? ከመድረክ እስከ ኢዜማ፣ ከኢዴፓ እስከ ቅንጅት፣ ከባልደራስ እስከ ፊንፊኔ ባላደራ በጨረፍታ እንመልከታቸው።

ነገረ መድረክ

ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች ባሕሪ አንዱ ምርጫ ሲመጣ ጥምረቶችን መፍጠር ነው። ይሁን እንጂ ከገዢው ግንባር ውጪ ከሁለት ምርጫ በላይ መዝለቅ የቻለው የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፌዴራላዊ አንድነት መድረክ የተባለው ጥምረት ነው። ሌሎቹ በድኅረ ምርጫ ወቅት መልሰው ይከስማሉ። ምርጫ 2012ን ልዩ ከሚያደርጉት ነገሮች ውስጥ ገዢው ግንባር ራሱ ከስሞ ውኅድ ፓርቲ ሆኖ መምጣቱ አንዱ ነው። ያለፉት ሁለት ተከታታይ ምርጫዎች ላይ ከተቃዋሚዎች ሁሉ የተሻለ ይባል የነበረው መድረክ አሁንም አለ። ከመድረክ አባላት አንዱ የሆነው የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ፤ ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር እና ከኦሮሞ ብሔራዊ ፓርቲ ጋር ቅንጅት ለዴሞክራሲያዊ ፌዴራሊዝም የሚባል ጥምረት መሥርቷል። ይሁንና የመድረክ ሕገ ደንብ አባላቱ ሌላ በጥምረቱ ሥር ያለ ጥምረት እንዳይመሠርቱ ያግዳል። ስለዚህ የኦሮሞ ፓርቲዎቹ ቅንጅት እንዲፀና አንድም ኦፌኮ ከመድረኩ መውጣት አለበት፣ አሊያም ኦፌኮ ሕገ ደንቡን ማሻሻል አለበት።

ይህንን ተግዳሮት በተመለከተ ከፓርቲዎቹ አመራር አባላት ለማጣራት ባደረግኩት ሙከራ የተረዳሁት ሁለት ነገሮችን ነው። የመጀመሪያው፣ መድረኩ የኦሮሞ ድርጅቶቹን ቅንጅት ማቀፍ የሚያስችለውን የሕገ ደንብ ማሻሻያ ለማድረግ እየሠራ መሆኑን ነው። ሆኖም ግን የቅንጅቱ አባላት ቅንጅታቸውን በማጠናከር ረገድ ሙሉ ቁርጠኝነት የላቸውም፤ ቅንጅቱ እስካሁን ሊቀመንበር ያልመረጠ ሲሆን፥ አባል ፓርቲዎቹ በአንድ የምርጫ ምልክት መወዳደር አለመወዳደራቸውን የሚያረጋግጥ ውሳኔ እስካሁን አላሳለፉም። የዚህ ጉዳይ መጨረሻ በአጭር ጊዜ መታወቅ ያለበት ሲሆን፣ ከተሳካላቸው መድረክ ለሦስተኛ ጊዜ ጉልህ ሥም ያለው ተቃዋሚ ፓርቲ ሆኖ ለምርጫ ይቀርባል። ይህ ጥምረት ከተሳካ እና ምርጫው ነፃ ከሆነ ከተቃዋሚ ድርጅቶች ሁሉ በርከት ያለ የምክር ቤት ወንበር ያገኛል ብለው ብዙዎች የሚገምቱት ስብስብ ይሄ ነው። ምክንያቱም ምርጫው በብሔርተኞች እና በዜግነት ድርጅቶች መካከል ነው። በአሁኑ ወቅት ብዙ ደጋፊ ያላቸው ደግሞ ብሔርተኛ ድርጅቶች ናቸው ተብሎ ይገመታል።

ነገረ ኢዜማ

የፖለቲካ ምኅዳሩ እንዲሰፋ ከተደረገ ወዲህ «አንገቱን ደፍቶ እየሠራ ነው» እየተባለ የሚወራለትም፥ «ለገዢው ፓርቲ ያሸረግዳል» እየተባለ የሚተቸውም የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ነው። ኢዜማ መዋቅሩን በመዘርጋት ደረጃ የሚወዳደረው ተቃዋሚ ፓርቲ የለም፤ ከ300 በላይ የሚሆኑ የምርጫ ወረዳዎች ውስጥ ምክር ቤት አቋቁሜያለሁ ብሏል። አልፎ ተርፎም 45 የፖሊሲ ሰነዶችን አዘጋጅቻለሁ እያለ ነው። ይሁን እንጂ በየክልሉ የበላይነት ባላቸው የብሔርተኛ ድርጅቶች «ዓይንህ ላፈር» እየተባለ ነው። ኢዜማ ይህንን ጉዳይ ለምርጫ ቦርድ ሳይቀር በአቤቱታ መልክ አስገብቷል።

ኢዜማ ምንም እንኳን ከፖለቲካ ፓርቲ የሚጠበቀውን ቢሠራም በኢትዮጵያ የጦዘ የብሔርተኝነት ፉክክር ምክንያት የሥራውን ያክል አያገኝም ብለው የሚጠረጥሩት ብዙ ናቸው። ነገር ግን የክርክር ጊዜው ሲጀመር የመከራከሪያ በቂ ዝግጅት በማድረጉ ምክንያት ጎላ ብሎ ሊታይ ይችላል።

ነገረ ኢዴፓ እና ቅንጅት

የኢዴፓ ነገር ከሁሉም ግራ አጋቢው ትዕይንት ነው። የኢዴፓ የመጨረሻው ሊቀ መንበር ፓርቲዬ ከስሞ ኢዜማን ተቀላቅሏል ባይ ናቸው፤ አሁን የኢዜማ አመራርም ናቸው። ምርጫ ቦርድ በበኩሉ ከኢዴፓ ለመክሰም የሚያበቃውን ሁኔታ ያሟላ ሰነድ አልደረሰኝም ብሏል። በልደቱ አያሌው የሚመራው የኢዴፓ አመራር ደግሞ «ፓርቲው አሁንም በሕይወት አለ» እያለ ነው። ነገር ግን ለምርጫ አልተዘጋጀም። እንዲያውም ልደቱ አያሌው ምርጫው ተራዝሞ የሽግግር መንግሥት መመሥረት አለበት የሚል ባለ 26 ገጽ ምክረ ሐሳብ አቅርበዋል። ልደቱ አለበለዚያ በድኅረ ምርጫው ወቅት ኢትዮጵያ በብጥብጥ ትፈራርሳለች የሚል ስጋታቸውን አስነብበዋል። በምክረ ሐሳባቸው ለጠቆሙት የሽግግር መንግሥትም «የሕዳሴ መንግሥት» የሚል ሥም አውጥተውለታል።

ልደቱ አሁን ያቀረቡትን ጥያቄ የዛሬ ሁለት ዓመት ብዙ ሰዎች አንስተውት የነበረ ነገር ነው፤ ምክረ ሐሳባቸው በጣም ከረፈደ የደረሰ ነው። በበኩሌ የፓርቲ ውስጥ የቤት ሥራቸውን ባለመጨረሳቸው ምክንያት እንደቀረበ ማስተባበያ ነው የወሰድኩት። ይህ ሌሎቹ ብዙዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያሉበትንም ሁኔታ ይገልጽልናል። በመጪው ምርጫ ውስጥ ምንም ዓይነት ጉልህ ድርሻ እንደማይኖራቸው ባለማወቃቸው ያለ የሌለ አማራጮቻቸውን እየሞከሩ ነው። ከነዚህ ውስጥ ምናልባት በአየለ ጫሚሶ የሚመራውም ቅንጅት ይገኝበታል። ቅንጅቱ የመሥራች ፊርማዎች ብሎ ያቀረባቸው ፊርማዎች ሐሰተኛ ናቸው በሚል ተጠርጥሮ ጉዳዩ ለፌዴራል ፖሊስ ምርመራ ተልኳል።

ነገረ አዲስ አበባ እና ፊንፊኔ

ሌላው እና በፈገግታ ሳንመለከተው ማለፍ የሌለብን የእስክንድር ነጋ «ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ» እና ማሜ ማሜ በሚል ሥም በሚታወቁ ግለሰብ የሚመራው «የፊንፊኔ ባላደራ» ጉዳይ ነው። ሁለቱም ለምርጫ ቦርድ የፓርቲነት ጥያቄ አመልክተዋል። እስክንድር ነጋ «ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ ያላትን ልዩ ጥቅም» በመቃወም የጀመሩትን ሕዝባዊ ንቅናቄ ወደ ፖለቲካ ድርጅትነት ሲቀይሩ፥ ማሜ ማሜ የተባሉት ግለሰብም በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የጀመሩት የስላቅ ምላሽ ንቅናቄ ወደ ፊት ገፍተውበት እና የአባላት ፊርማ አሰባስበው ምርጫ ቦርድን የፓርቲነት ዕውቅና ስጠኝ ብለው ጠይቀዋል። ባልደራሱ በብዙ ወጣቶች ድጋፍ እንዳለው መረዳት ይቻላል። የፊንፊኔ ባላደራው የድጋፍ መሠረት ግን ምን እንደሆነ ገና በቅጡ አይታወቅም። ምናልባትም እስከ ምርጫው ዋዜማ ድረስ የባልደራሱን ቅጂ በተቃራኒው እያራመደ የምርጫ ሰሞን መዝናኛ ሆኖ ይቀጥል ይሆናል።

ባልደራሱ በቅርቡ ከመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ጋር ጥምረት መሥርቻለሁ ብሏል፤ ከሌሎችም ጋር ጥምረት ሊመሠርት እንደሚችል ፍንጭ ሰጥቷል። ምናልባት በዚሁ አካሔድ እንደሚወራው በአማራ ክልል ሰፊ መሠረት ካለው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ጋር ጥምረት መመሥረት የሚችል ከሆነ፥ ሌላ ጉልህ አማራጭ ተቀናቃኝ ሆኖ ሊወጣ ይችላል።

ከላይ የጠቀሰናቸው የተቃዋሚ ቡድኖች ከብዙ ዐሥርቶቹ የተቃዋሚ ድርጅቶች በጣት የሚቆጠሩትን ብቻ ቢሆንም፥ የፖለቲካ ፉክክሩ ከነዚህ እጅ እምብዛም አይወጣም። ምርጫው በቀረበ ቁጥርም እውነተኛ ተፎካካሪዎቹ ግልጽ እየወጡ ነው።

Filed in: Amharic