>
5:16 pm - Thursday May 24, 8863

ለጊዜው ቢመስልም፤ለኔ የተለኮሰች እሳት ላንቺ አትመለስም!!! (መስፍን ተፈራ)

ለጊዜው ቢመስልም፤ለኔ የተለኮሰች እሳት ላንቺ አትመለስም!!!

መስፍን ተፈራ
በአንድ ገበሬ ቤት የምትኖር አንዲት አይጥ ነበረች። ታዲያ ከለታት አንድ ቀን ይቺው አይጥ ገበሬው እና ባለቤቱ እቃ ሸምተው ወደ ቤታቸው ሲገቡ ትመለከትና ለእኔ የሚሆን ምን ገዝተው ይሆን? ብላ በቀዳዳ አጮልቃ ስታይ ፍፁም ያልጠበቀችው ነገር፡፡ የተገዛው የሚበላ ነገር ሳይሆን የአይጥ ወጥመድ ሆኖ እርፍ! ያዝ እንግዲህ!!
እሜቴ አይጥ በድንጋጤ ውስጥ ሆና ከጉድጓዷ ወጥታ እየሮጠች በግቢው ውስጥ ወዳሉት የቤት እንስሳት ሄደች፡፡ መጀመሪያ ያገኘችው ዶሮን ነበር፤ ጫር ጫር እያደረገች ጥራጥሬዋን ትለቅማለች፡፡
“ማነሽ አንቺ ዶሮ፣ ኧረ ጉድ አልሰማሽ! ቤት ውስጥ ወጥመድ ተገዝቷል!!” አለቻት እሜቴ አይጥ ካሁን ካሁን ዶሮዋ ደንግጣ “እስኪ ሙች በይኝ! እውነትሽን ነው?”እስክትላት እየጠበቀች፡፡
ዶሮዋ እቴ እንኳን ልትደነግጥ ጭራሽ እየተቆናጠረች “እና ምን ይጠበስ! አንቺ ተጨነቂበት እንጂ እኔን ምን ያሳስበኛል!?” አለቻት፡፡
አይጧ እየተበሳጨች ስትሮጥ ወደ በግ ሄደችና “ስማኝማ አቶ በግ፣ ቤት ውስጥ የአይጥ ወጥመድ ተገዝቷል፤ እባክህ አንድ ነገር እናድርግ!!” ስትል በተማፅኖ ጠየቀችው፡፡ አቶ በግ ካቀረቀረበት ሳር ላይ ቀና ሳይል “በጣም ያሳዝናል! ግን ልረዳሽ አልችልም፤ ራስሽ ተወጪው” አላት፡፡
አሁንም አይጥ ቁና ቁና እየተነፈሰች፣ ወደ በሬ ዘንድ ሄደችና ቤት ውስጥ ስለተገዛው ወጥመድ ነገረችው፡፡ በሬውም ምንም ሳይመስለው “እንዴው ምን ይሻልሻል? ባይሆን በግና ዶሮ ይርዱሽና አንድ ነገር አድርጊ፤ እኔን እንኳን ተይኝ፡፡” አላት፡፡
አይጧ ሚጢጢ አናቷ በብስጭት እየዞረባት “ኧረ ተው አንድ ነገር ብናደርግ ይሻላል… ለጊዜው ቢመስላችሁም  ችግሩ የጋራችን ነው!!” ስትል ተማጸነች፡፡
ሁሉም ተያይተው ተሳሳቁ፡፡ “ቀልደኛ ነሽ!” እየተባባሉ፡፡ “አይታያችሁም አንድ የአይጥ ወጥመድ የጋራ ችግራችን ሲሆን?” እያሉ፡፡
አይጥም ተስፋ ቆርጣ ሄደች ወደ ጉድጓዷ፡፡ የዚያን እለት ሌሊቱን ሙሉ እንቅልፍ በአይኗ ሳይዞር አደረች፡፡
ማታ ወጥመዱ ተጠምዶ እያለ ቀጭ የሚል ድምፅ ሲሰማ የገበሬው ሚስት ተስፈንጥራ ተነሳች. . .  ወጥመዱ የያዛትን አይጥ ለማየት፡፡ ጭለማ ስለነበረ በዳበሳ ወደ ወጥመዱ ሄዳ ወጥመዱን ስትነካው በአይጥ ፋንታ የተያዘው መርዘኛ እባብ ኖሮ ነደፋት፡፡ በነጋታው የገበሬው ሚስት ከሀኪም ቤት ስትመለስ ራስ ምታት እንዳያስቸግራት ተብሎ ዶሮዋ ታረደችና ሾርባ ተዘጋጀላት፡፡ የገበሬው ሚስት ህመሙ እየጠናባት ሲሄድ በቶሎ እንድታገግም ተብሎ በግ ታረደላት፡፡ ሆኖም ግን ሴትዮዋ ማገገሟ ቀርቶ ሞተች፡፡ ይህንን ተከትሎ ዘመድ አዝማድ ለለቅሶ ሲመጣ ለተስካር በሚል በሬውም ታረደ፡፡
እሜቴ አይጥም ቁጭ ብላ እያለቀሰች ሦስቱም ሲታረዱ አየች።
አንዳንዴ ችግር ሲመጣ ለጊዜው አንድ ሰውን ብቻ የሚጎዳ ይመስላል፡፡ ያኔ ሁሉም አያገባኝም ይላል፡፡ ቆይቶ ግን ይጎዳል የተባለው በህይወት እያለ ያላገጡ ሰዎችን ማዕበሉ ጠራርጎ ሲወስዳቸው ለመታዘብ ይበቃል፡፡ የተለኮሰ እሳት ባለበት ቦታ ይቀር ይመስል እጃቸውን አጣጥፈው የሚጠብቁትን አመድ አድርጓቸው ይሄዳል፡፡
Filed in: Amharic