>
5:13 pm - Thursday April 18, 1016

‘ኢትዮጵያ እናቴ፣ ጥበብ ሚስቴ፣ ሥራዎቼ ልጆቼ!!!’’  ( ሠዓሊና ገጣሚ ገብረክርስቶስ ደስታ ነገዎ)

‘ኢትዮጵያ እናቴ፣ ጥበብ ሚስቴ፣ ሥራዎቼ ልጆቼ!!!’’ 

ሠዓሊና ገጣሚ ገብረክርስቶስ ደስታ ነገዎ

በአሰፋ ሃይሉ
ገብረክርስቶስ ደስታ ከአለቃ ደስታ ነገዎ እና ከወይዘሮ ዓጸደ ማርያም ወንድማገኘሁ ጥቅምት 5 ቀን 1924 ነበር በሐረር ከተማ የተወለደዉ፡፡ ለወላጆቹም በመጨረሻ የተገኘ አስረኛ ልጅ ነበር፡፡ ገብረክርስቶሰስ ገና የስድስት ወር ልጅ እያለ ነበር እናቱን በሞት ያጣዉ ያደገዉም ከአባቱ ጋር ነበር፡፡
ብዙዉ የልጅነት ወቅቱ ያልተስተካከለና ያልተመቻቸ ነበረ፡፡የሶስት ዓመት ህጻን ሳለ ጣሊያን በሀረር በወልወል ግጭት ሰበብ የመጀመርያዉን ወረራ ሲፈጽም ገብረክርስቶስም በልጅነት እድሜዉ ስደትን ጀመረ፡፡ በ1927 ከሐረር ወደ አዲስ አበባ መጣ በዚህም ጣሊያን የካቲት 12/1929 ህዝቡን ሲጨፈጭፍ በልጅነት አእምሮዉ አይቶ ነበር፡፡ አባቱንም ጣሊያን ስላሰረበት የግድ አዲስ አበባ መቆየት ነበረበትና እዚሁ ቆይቶ በኋላም አባቱ ሲፈቱለት ወደ ሀረር ተመለሰ፡፡
የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በሐረሩ የራስ መኮንን ትምህርት ቤት አጠናቆ ወደ አዲስ አበባ ተመለሰ፡፡ ገብረክርስቶስ መሳል የጀመረዉ ገና በህጻንነቱ እዉቅ ከነበሩት ቁም ጸሀፊ፣ መጻህፍት ደጓሽና ባህላዊ የሀይማት ስዕሎች ሰዓሊ አባቱ ከአለቃ ደስታ ነገዎ ስር ሁኖ ነዉ፡፡ ባገኘዉ ነገርም ቅርጻ ቅርጽ መስራት ይወድ ነበር፡፡ለስእል በነበረዉ አድልዎም በልጅነት ቀልቡ መንፈሳዊና ስጋዊ ስእሎች በፈጠራ ይሰራ እንደነበር የቅኔና የግጥምም ዝንባሌ በረቂቁ እየጸነሰ ማደጉን ቤተሰቡም ሆነ የትምህርት ቤት ባልእንጀሮቹ ዛሬ ድረስ በትዉስታ ያነሱለታል፡፡ ለዚህም በክብር ተቀምጣለት በጉልምስና ዘመኑ ትዝታ ከበቁለት ስራዎቹ መሀል የሰባት ዓመቱ ብርቅየ ስዕሉ “ምስለ ፍቁር ወልዳ” ምስክር ናት፡፡
የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን ከሐረር አጠናቆ እንደመጣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በያኔዉ የቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በዛሬዉ ኮተቤ መምህራን ማሰልጠኛ እና ያኔ ገና በተከፈተዉ የጄኔራል ዊንጌት ትንህርት ቤት በ1942 አጠናቀቀ፡፡
ገብረክርስቶስ በኢትዮጵያ ስነጥበብ ረቂቅ ሥዕል ወይም አብስትራክት ለተባለዉ የዘመናዊ ስዕል ዝንባሌዉን ያሳየዉ እዚሁ ዊንጌት ይማር በነበረበት ጊዜ ሲሆን አድናቆትንም አትርፎለት ነበር፡፡
ገብረክርስቶስ ለሀገሪቱ የመጀመሪያ የሆነዉ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በ1943 ሲከፈት የሳይንስ ተማሪ ሆኖ እርሻ ለማጥናት ሳይንስ ፋኩልቲ ገባ፡፡ የሁለተኛ አመት ተማሪ እያለ ግን በጠና በመታመሙ ምክንያት ዩኒቨርሲቲዉን ጥሎ ወጣ፡፡
ከኮሌጅ ሕይወቱ በኋላ ቀጣዮቹ አምስት አመታት ማለትም ከ1944-1948 ድረስ በጣም አታካችና የፈተኑት ነበሩ፡፡ ራሱንና ፍላጎቱን ለማግኘት ያልገባና ያልወጣበት ስፍራ፣ ያልሞከረዉ ያልተፈተነዉ ነገር አልነበረም፡፡ ዉስጡ የነበረዉን ከፍተኛ የጥበብ ፍላጎት ማርካት አለመቻልና ያለስራ ቁጭ ማለት በመንፈስ ግጭት አናጉት፡፡
ይሁንና ስራ መያዝ ስለነበረበት መጀመርያ በአዉራ ጎዳና መስሪያቤት ተቀጠረ፡፡ የአፈር ምርምር ባለሙያ በመሆንም በዚህ ድርጅት ጥቂት ጊዜያት ሰራ፡፡ በስራዉ ግን የመንፈስ እርካታ ማግኘት ባለመቻሉ ጥሎት ወጣ፡፡ ጥቂት ጊዜ ቤት ከተቀመጠ በኋላም ሲንክላር የተባለ የነዳጅ ድርጅት ቀጠረዉ፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ በጊዜዉ እጅግ ዘመናዊ በሆነዉ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስታትስቲሺያን ሆኖ ተቀጠረ፡፡ ወደበኋላ ላይ ደግሞ ነፋስ ስልክ አካባቢ በሚገኘዉ የስብስቴ ነጋሲ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመምህርነት ተቀጥሮ መስራት ጀመረ፡፡ሆኖም ይሄንንም ዓመት ሳይሞላ ተወዉ፡፡
በመጨረሻ ራሱን ሲፈልግ የነበረዉ ገብረክርስቶስ ስራ የሚባል ነገር ትቶ በቤቱ ዉስጥ በስዕል ስራዉ ላይ አተኮረ፡፡ያለእረፍትም መሳል ጀመረ፡፡ከዚህ በኋላም ነበር በህይወቱና በዝንባሌዉ የመጀመርያ እርካታ ያገኘበትን ፍሬ የቀመሰዉ፡፡
በ1946 በኢትዮጰያ ሥነ ጥበብ መድረክ ብቅ አለ፡፡ በወቅቱ የአሜሪካ ማስታወቂያ ድርጅት በነበረዉ ቤተ መጻህፍት ዘመናዊ የአሳሳል ስልቶችን የሚያስተዋዉቁ ሥዕሎቹን ኤግዚቢሽን አሳየ፡፡ በዚህ መሀል ግን በህይወቱ በጣም ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸዉን አባቱን በሞት አጣ፡፡ በዚህም በጣም ከፍተኛ ሀዘን ዉስጥ ወደቀ፡፡ ከወራቶች በኋላም ለመጀመርያ ጊዜ በወደፊት ህይወቱ ቀና መንገድ በከፈተለት ድርጅት ዉስጥ ስራ ጀመረ፡፡ በፊት ፓይንት ፎር ይባል በነበረዉ የአሜሪካ የትምህርት የባህል ድርጅት በህጻናት የመማሪያ መጻህፍትና እትሞች ዝግጅት ክፍል በሰዓሊነት ተቀጠረ፡፡ ሙሉ ጊዜዉን፣ ፍላጎቱንና ዝንባሌዉን አስተባብሮ በስራዉ እየረካ የግል ሥዕል ስራዎቹንም ፍሬያማ በሆነ መንገድ እያከናወነ ለሁለት ዓመታት ያህል ሰራ፡፡
በ1949 ኒዉደልሂ ላይ በተደረገ የዓለም አቀፍ የወጣቶች ሥዕል ትርዒት ለመካፈል ወደ ህንድ የመሄድ ዕድል አጋጠመዉ፡፡ ከኢትዮጵያ የሥነ ጥበብ አደባባይ ዘልቆ ለመጀመርያ ጊዜ በባህር ማዶ አደባባይም ይፋ ሆነ፡፡ ከህንድ አድናቆትን አግኝቶ ከተመለሰ በኋላ ግን በተደጋጋሚ ለህመም ተጋለጠ፡፡ በመንፈስም በገንዘብም ይረዱት የነበሩት አባቱ መሞት ተደምሮ ወደ ዉጪ ሀገር ሄዶ ለመማር ያደርግ ለነበረዉ ጥረት እንቅፋት የሆኑት ነገሮች በጣም እንዲታመም ምክንያት ሆኑት፡፡ ከዚህ ህመሙ አገግሞ ሲነሳ ነበር ህይወቱን ሙሉ ያልተለየዉ የለምጽ ምልክት በፊቱና በእጁ ላይ የወጣበት፡፡ በዚህ ወቅት ገብረክርስቶስ ገና የሃያ አምስት ዓመት ጉብል ነበረ፡፡
ከዚያ ወቅት በኋላ በሰዓሊነት ለመግፋት ቁርጣኛ ዉሳኔ አደረገ፡፡ ሆኖም የዚህን የሥነ ጠበብ ፍላጎት ሀገሪቱ ልታስተናግድለት አልቻለችም ነበር፡፡ በመሆኑም ተላልኮ ባገኘዉ የትምህርት እድል የኮሎኝ የጥበብ አካዳሚ በሰጠዉ እስኮላርሺፕ ለመሳተፍ በ1950 ወደ ምዕራብ ጀርመን ሄደ፡፡ በኮሎኝ የጥበብ አካዳሚ የግራፊክስና የቀለም ትምህርቱን ለሁለት ዓመት፣ በኮሎኝ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ የሥነ ጥበብ ታሪክ አጥንቷል፡፡ የጀርመን መንግስት በሰጠዉ አንድ አመት የተጨማሪ ጊዜ ፈቃድ ጀርመን ሥዕሎቹን ሲሰራ ቆይቶ በቦንና በኮሎኝ ከተሞች የመጀመርያዉ አፍሪካዊና ኢትዮጵያዊ ድንቅ ሠዓሊ ተብሎ አድናቆትንና ክብርን አግኝቶ መጋቢት 20፤1954 ወደ ሀገሩ ተመለሰ፡፡
ገብረክርስቶስ በምርጫዉ ከ1955 እስከ 1967 ድረስ በአዲስ አበባዉ ሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት በሥዕል መምህርነትና በምክትል ዳይሬክተርነት ደረጃ ለ12 ዓመታት በትጋት ሰርቷል፡፡ በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት የባህል ማእከልም በመድረክ ገጽ አዘጋጅ ሆኖ ሰርቷል፡፡ በእነዚህ አመታት በሀገር ዉስጥ ሆነ በዉጭ ሀገር ተደናቂ ያደረጉትን ሥዕሎቹን ኤግዚቢሽን በየጊዜዉ ያሳየ ሲሆን በተመሳሳይ ድንቅ ገጣሚነቱንም አስመስክሯል፡፡
ገብረክርስቶስ ስለሥዕሉ ሲናገር፡- ‘’. . .ለሠዓሊ እንደእምነቱ ነዉ ሥዕል፡፡ ወይም ኪነጥበብ እንደ ሀይማኖት ሊወሰድ የሚችል ነገር ነዉ፡፡እንደ እኔ ሠዓሊ ከእዉነት መራቅ ያለበት አይመስለኝም፡፡ደግሞ የሚያምንበትንና አምንበታለሁ ብሎ የተነሳበትን ሁኔታ መስራቱ በእዉነቱ ለሰዓሊዉ እንደ ክብርም ሊሆን ይችላል፡፡ እንደትግልም ሊሆን ይችላል፡፡ በእዉነቱ በዚህ ዓይነት የተሰማራ ሰዓሊ ካመነበት መፍራት ያለበት አይመስለኝም፡፡’’
ገብረክርስቶስ ደስታ በወቅቱ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የሽልማት ድርጅት ይሰጥ የነበረዉን የኢትዮጵያን የሥነ ጥበብ ሽልማት ከሜተር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ቀጥሎ በ1958 ተቀብሏል፡፡ ከሀገሩም ዉጪ በግልና በቡድን በአዉሮፓ፣ በአሜሪካ፣ በእስያና በአፍሪካ ራሱንና ሀገሩን ወክሎ የዘመናዊ ህይወታችንን አንድ ገጽታ ለዓለም አስተዋዉቆ ያለፈ ታዋሽ ኢትዮጵያዊና ዓለማቀፋዊ የጥበብ ሰዉ ነበር፡፡
‘‘ኢትዮጵያ እናቴ፣ ጥበብ ሚስቴ፣ ሥራዎቼ ልጆቼ’’ ይል የነበረዉ ገብረክርስቶስ ደስታ ባጭሩ የእድሜ ዘመኑ በሰዓሊነቱና በባለቅኔነቱ የሀገሩን ሥነ ጥበብና ሥነ ግጥም ከባህላዊዉ እስከ ዘመናዊዉ ድረስ ዘልቆና በአዳዲስ መንገድ ተርጉሞ ያቀረበ ሰዉ ነበረ፡፡
ገብረክርስቶስ ደስታ ከስዕሎቹ በተጨማሪ ‹መንገድ ስጡኝ ሰፊ› በሚል በወዳጆቹ አሰናጅነት የታተመ የግጥም መጽሀፍ ያለዉ ሲሆን ስድስት ኪሎ በሚገኘዉ የጀርመኑ ‹ጎተ› ዉስጥ ደግሞ በስሙ የተሰየመና በዉስጡም የሱን ስራዎች የያዘ ማዕከል ይገኛል፡፡
ሠዓሊ ገብረክርስቶስ ደስታ በህይወት ለመኖር የታደለዉ ለ49 ዓመታት ብቻ ነበር ከ1924-1973 ሀገሩ ላይ በነበረዉ ፖለቲካ ምክንያት ለስደት የተዳረገዉ ገብረክርስቶስ በተሰደደ ልክ በሁለት ዓመት ከስድስት ወሩ ላይ መጋቢት 21 ቀን 1973 በአሜሪካ ኦክላሆማ ስቴት ህይወቱ አለፈች፡፡ የቀብሩ ስነ ስርዓትም በዚያዉ አሜሪካ ተፈጽሟል፡፡
ገብረክርስቶስ ደስታ ሠዓሊ፣ ገጣሚና ባለቅኔ ጸሀፊ እና ድንቅ ተዋናይ የግጥም አንባቢ፣ አንደበተ ርቱዕ የሥነ ጥበብ መምህር፣ ስፖርተኛ፣ የሙዚቃ ሰዉ ወዘተ . . . ነበር፡፡
(የጽሑፉ ምንጭ (ከከበረ ምስጋና ጋር)፡- Maree Books- ማሬ መፅሐፍት. April 16, 2019 • ማሬ መጽሐፍት ደግሞ ከ‹እፍታ ቅጽ4› መጽሐፍ እና በ2002 ዓ.ም ይታተም ከነበረዉ የ‹ዜን› መጽሄት ላይ መረጃዎቹን አሰባስቦ ያቀረበው፡፡ ሥዕሉ፡- ገብረክርስቶስ የሚታወቅበት 280ሺኅ ዶላር በጥበብ ገዢዎች የተገመተ፣ ነገር ግን እርሱ ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ለኢትዮጵያ ሕዝብ መታሰቢያዬ ሆኖ ይቀመጥልኝ በማለት በሥጦታ የሰጠውና፣ ገብረክርስቶስ ደስታ በሞተ በ30 ዓመቱ ከጀርመን ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰው፣ “ጎልጎታ” ወይም “Crucifix” የተሰኘው ሥዕሉ ነው፡፡)
ለከርታቴውና ረቂቁ ሲበዛም ሰብዓዊው ሠዓሊና ገጣሚ የገብረክርስቶስ ደስታ ነገዎን ነፍስ ባለችበት የተዋበ የሠማያት ቅፅር ምስጋናችንና ናፍቆታችን ይደርሳት፣ እና አብዝቶ ያረሰርሳት ዘንድ ከልብ ተመኘሁ፡፡
በመጨረሻ — ከመልካም የሆነች ጥበብ ታሸንፋለች!
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!
Filed in: Amharic