>

ባለቅኔዋ እማሆይ ገላነሽ ሐዲስ - ኢትዮጵያዊቷ ሆሜር!!! (ዮሀንስ ተስፋዬ)

ባለቅኔዋ እማሆይ ገላነሽ ሐዲስ – ኢትዮጵያዊቷ ሆሜር!!!

 

 

ዮሀንስ ተስፋዬ
 
“ሴቶች ከወንዶች ጋር እኩል ተሰልፈው መሥራት የኖረ እንጂ እንደ እንግዳ ደራሽ አይደለም!!!”
 
ቅኔ : እንደ አያሌ የጥበብ ዘርፎች የብያኔ ተራሮች የሚጋረጡበት ባይመስልም ውል ያለው ብያኔ ለመስጠት አንድ ወገን መወገን ግድ የሚል ይመስላል:: በሁሉም ዘንድ አግባቢው ተቀነየ ሙሾ አወጣ፡ግጥም ገጠመ፡አራቆ ተናገረ፡ አዜመ፡ መራ ፡ዘፈነ ከሚለው የወጣ ጥሬ ዘር ነው የሚለው ነው::(ማርዬ ይግዛው፡፳፮) መንፈሳዊውን ዓለም ከስጋዊ አራቀው፡ በዙሪያቸውን ያለውን ድሎት ሁሉ ናንቀው ለቅኔ ከሞቱለት መሃል እማሆይ ገላነሽ ሲወሱ ይኖራሉ:: ያለፈውን በመዘከር፤ ያገርቤትን እውቀት ማጎልበትም ሰናይ ነው ብለን ከሰፋው በጠባቡ እንዲህ አቅርበነዋል::
ውልደት
በባህር ዳር ከተማ ዞር ዞር ያለ ከአንድ ቤተ መዘክር ጎራ እንዲል ይገደዳል:: ምክንያቱም ሊደነቅ፡ሊደመም ስለሚወድ ወደ ባለቅኔዋ መታሰቢያ ደጃፍ መጠጋትን ይመርጣልና:: ለመሆኑ፤ከግሪኩ ታዋቂ ባለቅኔ ጋር የተመሳሰሉት እኚህ ሴት በእንዴት ያለ ሁነት የተከሰቱ የጥበብ ሰው ናቸው።
ቄሰ ገበዝ ሐዲስ የ፰ አመት አንድ ፍሬ ልጃቸውን አስከትለው በአንድ ሰንበት ወደ ቤተ መቅደስ ሄደዋል:: የታላቁ ጸሎት ሥነ ስርአት ሲጠናቀቅ ቅኔ መዝረፍ የተለመደ ነው::
አንዱ የጀመረውን ሌላው በቅጣይ አልያ በምላሽ መልክ ይቀኝበታል:: በነገራችን ላይ፡ቅኔ ለመቀኘት ብቁ የሚኮንበት “ቅኔ ቤት” በጥንታዊው ትምህርት የመጨረሻው እርከን ዋነኛ አካል ነው::
ግፋ ቢል ፯ ዓመት ሊፈጅ ይችላል፤ኡንበርስቲ እንደማለት ነው:: በዕለቱም የህጻን ገላነሽ አባት ለቅኔ ዘረፋው ጋቢያቸውን አጣፉ እናም ጀመሩ::
“በታቦ ርሂ አመ ቀነጸ መለኮትከ ፈረስ”
የቅኔው የመጀመሪያ መስመር ነው:: ትርጓሜውም፦መለኮት ፈረስህ በደብረ ታቦር በዘለለ ጊዜ ማለት ነው::
አባት ቅኔውን ሳይጨርሱ ከሴቶች መቆሚያ ያንዲት ልጃገረድ ድምጽ ተሰማ:: ሊያውም የሴት! (ይህ አባባል፡የዚህን ጽሁፍ አቅራቢ ሳይሆን የዘመኑን ዕሳቤ ያመለክታል::)
ኢክህሉ ስሂበት ሙሴ ኤልያስ”
ትርጉሙ፦ ሙሴና ኤልያስ ሊስቡት አልቻሉም ማለት ይሆናል
አባት የጀመሩትን ልጅ ነጠቀችና መላችው በምላሿ ያልተደመመ አልነበረም አባት ለልጃቸው “ ልጄ ሆይ ተይ ጳወሎስ እንዳያይ ንግግርሽን በጉባኤ ላይ” የሚል ወዛም ቅኔ መለሱላት::
ሴት ልጅ ከጉባኤ ወጥታ እንዳታስተምር ሐዋርያው ቅ/ጳውሎስ የተናገረውን በማስታወስ:: ገላነሽ በዚያች ቀን ተወለደች:: በወቅቱ በቤተ ክርስትያኑ አካባቢ የነበሩ ሰዎች፤ እንደ ንግስት ወግ በአልጋ ላይ ተሸክመዋት፡ ዙሪያዋን እየጨፈሩላት ከቤት አደረሷት:: ከዚያ ቀን በቀደም ልምዳቸው አንዲት ህጻን ምስጢር ስታመሰጥር ሳይሆን ጌሾ ስትወቅጥ ነበርና የምትታይ፤ታሪክ ተቀየረ::
በተመሳሳይ ዘመን በህጻኗ ላይ ሌላ ለውጥ ተገኘባት:: በኩፍኝ በሽታ ሳቢያ ያይን ብርሃኗን ለማጣት ተገደደች:: የማየት ተፈጥሯዊ ችሎታ ታትረው የሚያገኙትን ብልሃት፡ ጥበብ፡ የኑሮ  ፈር በፍጹም አያሳጣም ስትል ገላነሽ የወቅቱን ትምህርት ጀመረች:: በአጭር ጊዜ ወስጥ ዓይነ ስውሯ ገላነሽ የዳዊት መዝሙር፡ውዳሴ ማርያም፡ ቅዳሲ ማርያምና ሙሉ መጽሃፍ ቅዱስን ከነትርጓሜው ፉት ለማድረግ ቻለች:: እስከ ፲፱፻፳፰ ዓ.ም ድረስ በአባቷ ጉባኤ ውስጥ በተራ የመምህርነት ወንበሩን በመቆናጠጥ ማስተማሩን ተያያዘችው::
የቅኔ ሊቅነት
ለብዙ ሰዎ ች ዓይነ ስውር መሆን ድቅድቅ ጨለማን ያህል ከባድ ነው:: ክብደቱን ከገፈፉት መሃል እንደ ተአምረኛ የምትወሳው ሄለን ኪለር እንዲህ ብላ ነበር::
“እኔን ተመልከቱ፤ የዐይን ብርሃን የለኝም:ግን አያለሁ ጆሮዎቼም አይሰሙም ግን አደምጣለሁ:: አንደበቴ ተዘግቷል ፤ ነገር ግን ዲዳ አይደለሁም።”
 በአካል ሳይሆን በተግባር የእውቀት ፍቅር የኛዋን ባለቅኔ ከሄለን ኪለር ያጣመራቸው ይመስላል:: የአቅመ ሔዋን ጥያቄ ገላነሽን ለትዳር አሳጫት:: በአደገችበት ገዳም መንፈሳዊ ትምህርትን የተማረ ሰው ወላጆቿ አጋቧት::
ትዳር ትመስርት እንጂ ከቤተሰቦቿ ደጅ መራቅን አልመረጠችም:: በማኀበራዊ ህይወት ተሳትፎ ሳትታማ እንደኖረች ስለታሪኳ የከተቡ ጋዜጦችና መጻህፍት ምስክር ይጠራሉ::
ፋሺስት ኢጣሊያ ወረራውን ሲያኪያሂድ አሳዛኝ ጠባሳ በባለቅኔዋ ህይወት ላይ አረፈ:: የጽላሎን ብቸኛ ገዳም በማቃጠል ህዝቡን ለማጥቃት ያቀደው የጠላት ሠራዊት፡ያመለጠው ቢያመልጥም የተገኙትን ድባቅ ሊመታ ቃል ለምድር፡ ቃል ለሮም ብሏል::
ገላነሽን እና ቤተ ክርስትያኗን ጥሎ ወደ ጫካ ለመሸሸግ ያልሞከሩት ቤተሰቦቿ በሙሉ ያንድ ዕለት ሽኝት ተካሄደባቸው:: “ይቺስ ዓለሙን የት አይታ?!\” በሚል የስላቅ ሃዘኔታ ወጣቷን ሳይገድሏት አለፉ፤ የጣልያን ወታደሮች_አበጁ::
ስንት የኪነ ጥበብ ሰዎች፡የዝማሬና የቤ/ያን ሊቆችን የምታፈራ ሴት ለጠሏት ኢትዮጵያ ተዉላት:: ያለአጋር የቀረች ቢመስላትም ጫካ የገባ ባለቤቷ ሰላም እንደማለዳ ጀምበር ፍንጥቅጥጥቅታዋን በጽላሎ አማኑኤል ጉልላት ላይ ማሳረፍ ስትጀምር ወደ ርስዋ ተመለሰ:: በልጆቿና ወላጆቿ ሞት በማዘኗ የትዳር ጣዕሙን በምንኩስና ለመቀየር ወሰነች:: አንቱታው ተጀመረ_እማሆይ ገላነሽ::
እማሆይነት
እማሆይ ገላነሽ፡ የቅኔ ፍልስፍናን ከየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ሊቃርም የሚጎርፍ ተማሪን በማስተናገድ ግማሽ ምዕት አስተምረዋል:: በዚህ ዘመናቸው የቅኔ ፕሮፌሰር ናቸው ማለት ለተገቢ ሥራ፡ ለታመነ ሰው ማዕረግ እንደመስጠት ተቆጥሯል:: ዳግማዊት ሆሜር ተብለው መወደሳቸውም ከታሪካቸው ጋር በመገጣጠሙ ነበር::
ሆሜር የጥንት ግሪካዊ ባለቅኔ ነው:: ከዓይነ ስውርነቱ በተጨማሪ የዕለት ጉርሱን ለማግኘት አንዳንድ ቅኔዎቹን እንደገንዘብ በመለወጥ ነበር ነፍሱን የሚያቆያት:: እማሆይ
የሆሜርን ያህል ባይጠናባቸውም ከቤተሰቦቻቸው ሞት በኋላ አስታዋሽ አጥተው የተቸገሩ መምህርት ነበሩ በወቅቱ አንድ ጋዜጣም ይህን ዘግቧል።
“ ዳግማዊት ሆሜር የተባሉት እማሆይ ገላነሽን በቅኔያቸውና በሙያቸው እየተደነቅን እናመሰግናቸው ይሆናል:: በሌላ በኩል ደግሞ በእርጅና ምክንያት ድሮ የሚሰሩትን የእጅ ሥራ ለመስራት ባለመቻላቸው የደረሰባቸውን ችግርን በመሰማት እናት አገራቸው ለምን አትረዳቸውም? እያልን እናዝን እንቆረቆር ይሆናል::
የኢትዮጵያ የሴቶች በጎ አድራጎት ድርጅት በሴቶች በኩል በቅድሚያ ወደ ሥራ ዓለም ተሰማርተው፡ ለሴቶች ምሳሌ ሆነው የቆዩ አንጋፋ እናት በመሆናቸው በችግራቸው ሁሉ ቢረዳቸው ያስመሰግነዋል:: “ ደምጸ ተዋህዶ ጋዜጣ፡ቁ. ፹፭፤ ፲፱፻፷፫ ዓ.ም
የባለቅኔ አርአያነት
እማሆይ በዝና ሊተዋወቋቸው ከውጭ ሃገር የሚመጡ እንግዶች ጭምር አስተዋይነታቸውን ይገነዘቡላቸው ነበር:: የሰዎች (የተማሪዎቻቸው) ሸክም መስለው እንዳይታዩ የጓሮ አትክልትን በመኮትኮት ስፌት እና ስጋጃ ሰርቶ በመሸጥ ራሳቸውን ያስተዳድሩ ነበር:።
ሴት መሆን በራሱ ለማጀት ሥራ አለመፈጠር መሆኑን በዚያ ወቅት ያሳዩት የከተማ ሥልጣኔን ተምረው የነጮችን ታሪክ አንብበው አልነበረም:: ይህ አስተውሎታቸው እንዲደነቁ አድርጓቸዋል::
መማርም ሆነ ማስተማር ብርታትን እንጂ ጾታን አይመለከትም ሴቶች ከወንዶች ጋር እኩል ተሰልፈው መስራት የኖረ እንጂ እንደ እንግዳ አይደለም::”
በማለት ባህላቸውንም ፍጹም መኮነን እንደማይችሉ ይናገሩ ነበር:: ከማብራሪያቸው ሁሉ ቀጣዩ የተመረጠ ነው:: መምህርነት ምንም እንኳን በጥንታዊው የትምህርት ዓለም ለወንድ የተተወ ቢመስልም እማሆይ መርቻ ቃል
እረፍት
“የኔ ህይወት ቅኔ ነው” የሚሉበት ሕይወት መድከም በጀመረበት ማግስት እማሆይ አልጋ ላይ ወደቁ:፡ ከማይጠገብ ለዛቸው ጋር ፹ ዓመታትን ደፍነው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፤ ሐምሌ ፲፪፡ ፲፱፻፸፰ ዓ.ም:: ሴቶች ቦታ ባላገኙባት በገጠሪቱ ኢትዮጵያ በሥነ ምግባር ታንጸው፡ ማየት ቢሳናቸውም ምንም ሳይገደቡ፡ ነጥረው የወጡ ስመጥር ሴት ናቸው::
ለዚህም ነው ዓለም የ፳ኛው ክፍለ ዘመን አስገራሚ ሴቶች ካላቸው ከእነ ሄለን ኪለር ተርታ የእማሆይን ስም ከስነ ጽሁፉ ዓለም ወግነን ለማንሳት የሞከርነው:፡ ቤተ መዘክር ሰርቶ ሥራዎቻቸውን ህያው ለማድረግ ከተደረገው ጥረት በላይ፡ሰፊ ጥናት ለማከናወን የስነ ጽሁፍ፡የግዕዙ ሊቃውንት ቢጋበዙ መልካም ነው እንላለን:: ክብር ለቅኔዋ እመቤት ነፍስ!!!
ማጣቀሻ:
● ከፍ ያለው መራሒ(ቀሲስ) ” ሴቶች በኢትዮጵያ” ፲፱፻፹፰ ዓ.ም(ምስላቸው ገጽ 34 ላይ ይገኛል)
● ማርዬ ይግዛው ”ቅኔያዊ የዕውቀት ፈጠራ”ጎቴ ማእከል ፳፻፮ዓ.ም
● ዮሃንስ አድማሱ “ስለ ሰምና ወርቅ ቅኔ ጽንሰ ሃሳብ” አአዩ ለአርት ባችለር ዲግሪ ማሟያ የቀረበ ጥናት ፲፱፻፶፱ ዓ.ም
● ድምጸ ተዋህዶ ጋዜጣ፡ቁ. ፹፭፤ ፲፱፻፷፫ ዓ.ም
● ጠብታ ፡ቅጽ ፪፡ቁ፲፱ ሰኔ ፳፻ ዓ.ም
Filed in: Amharic