>
1:57 am - Wednesday July 6, 2022

ዘረ ያዕቆብና ገብረ ህይወት ባይከዳኝ፤ ሁለት የዘመናዊነት ኢትዮጵያ  እሳቤዎች!!! (በፍቃዱ ጌታቸው)

ዘረ ያዕቆብና ገብረ ህይወት ባይከዳኝ፤ ሁለት የዘመናዊነት ኢትዮጵያ  እሳቤዎች!!!

 

 

በፍቃዱ ጌታቸው
 
* በኢትዮጵያ ፍልስፍና በፋሲል መርአዊ ሌክቸረር ፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፍልስፍና ት/ክፍል
አጻጽሮተ ፅሁፍ፣
ዘመናዊነት ከግለ ሰብአባዊ ነፃነት፣ ማህበረሰባዊ ለውጥና በምክንያት ከሚመራ የህሊና አብርሆት ጋር ይገናኛል፡፡ የሰው ልጅ ከወግና ከባህል እራሱን ነጻ በማውጣት ምክንያትን ተጠቅሞ እራሱንና አካባቢውን የበለጠ መረዳት ይችላል በሚል ሃሳብም ላይ ተመርኩዟል፡፡ ምንም እንኳን ዘመናዊነት ከምዕራባዊው ዓለም ሰልጣኔ ጋር መነጣጠል እንደማይችል ቢታሰብም፣ ነገር ግን የዘመናዊነት ሀሳብ የማህበረሰቦችና የታሪክ አጋጣሚዎች በተለዩየ የዓለም ክፍሎች ተንፀባርቋል፡፡ እዚህ ላይ ዘመናዊነት በኢትዮጵያ ታሪክ፣ ባህልና አመለካከት ውስጥ ምን ይመስላል የሚለውን ጥያቄ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ዘመናዊነት በምክንያት የሚመራ የነጻነት ጉዞ ነዉ፡፡ በተጨማሪም ዘመናዊነት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ መቼ ተጀመረ፤ ለዘመናዊነት መዳበር አስተዋጽኦ ያደረጉ የኢትዮጵያ ሊቃውንት እነማን ናቸው፤ እንዲሁም ዘመናዊነት ከኢትዮጵያዊያን አስተሳሰብ ጋር ምን ዓይነት መስተጋብር አላቸው የሚሉትን ጥያቄዎች ያነሳል፡፡ የዚህ ፅሁፍ አላማ በኢትዮጵያዊው ፈላስፋ ዘረያዕቆብና የፖለቲካል ኢኮኖሚው ምሁር ነጋድራስ ገብረህይወት ባይከዳኝ ስራዎች ላይ በመመርኮዝ ዘመናዊነት በኢትዮጵያ ያለውን ገፅታ ለመዳሰስ ይሞክራል፡፡
ኢትዮጵያዊው ፈላስፋ ዘረያዕቆብ “ሐተታ” የተሰኘውን የፍልስፍና መንገድ በኢትዮጵያ ውስጥ ላለው የሃይማኖት ግጭትና አለመግባባት እንደመፍትሄ አድርጎ ለማስቀመጥ ይሞክራል፡፡ በዚህ ፍልስፍና ውስጥም ከፈጣሪ ህልውና፣ የእውነት ተፈጥሮ፣ በዓለም ላይ ያለውን ግጭትና መንስኤው እና የስነምግባር ፍልስፍና ለማዳበር ይሞክራል፡፡ ይህንን ሀሳብ የበለጠ በማዳበር ኢትዮጵያዊው የፖለቲካ ኢኮኖሚ ምሁር ነጋድራስ ገብረህይወት ባይከዳኝ የኢትዮጵያን ዕድገት ለማፍጠን በግዜው የነበረውን አመለካከት “አጤ ምኒሊክና ኢትዮጵያ” እና “መንግስትና የህዝብ አስተዳደር” በተሰኙት ስራዎች ላይ በመተቸት አዳብሯል፡፡ በነዚህ ስራዎች ውስጥም ኢትዮጵያዊ ባህልና ምዕራባዊ ስልጣኔን ያጣመረ የዕድገት መስመር ለመንደፍ ይሞክራል፡፡ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ የዘረያዕቆብና የነጋድራስ ገብረህይወት ባይከዳኝን ሀሳቦች በመመርመር ዘመናዊነት ከኢትዮጵያ ባህልና ወግ ጋር መጣጣም እንዳለበት ለማሳየት እሞክራለሁ፡፡
የአይነታዊ ባህሪ (qualitative) ጥናታዊ መንገድን በመከተል ጥናታዊ ጽሁፉ በዘረያቆብና በነጋድራስ ገ/ህይወት ባይከዳኝ የተጻፉ ስራወችን ለመመርመር ይሞክራል፡፡ በዚህም መሰረት የዘረያቆብን ሐተታ የተሰኘ ጽሁፍና የነጋድራስ ገ/ህይወትን አጤ ምኒልክና ኢትዮጵያ እና መንግስትና የህዝብ አስተዳደር የተሰኙ ስራወችን ለማጥናት ይሞክራል፡፡ በዚህም ላይ በመመርኮዝ ጥናቱ ሁለቱ ጸሃፍት በኢትዮጵያ ውስጥ በሃገር በቀል ባህልና የዘመናዊነት እሳቤወች፣ በተጨማሪም ሃገር በቀል የሆነ የዘመናዊነት እሳቤ ለማዳበር በሚደረገው ጥረት ውስጥ መሰረታዊ የሆነ አስተዋጽኦ አድረገዋል በማለት ይከራከራል፡፡
ዋቢ ቃላት፣ ዘመናዊነት፣ ሐተታ፣ ዘመናዊ ስልጣኔ፣ ህገ ልቦና፡፡
መግቢያ
በአሁኑ ጊዜ በሀገር በቀል ባህልና በዘመናዊ ምዕራባዊ ስልጣኔ መካከል የሚገኝውን ግንኙነት ለመረዳት ጥረት በመደረግ ላይ ይገኛል፡፡ እዚህም ላይ ዘመናዊነት መቼ ተጀመረ በዘመናዊነት ግቦችና የአንድ ማህበረሰብ ባህል መካከል ምን አይነት መስተጋብር ይገኛል፤ ለዘመናዊነት ግቦች መሳካት የተለያዩ ማህበረሰቦች አስተዋጽኦ ምን ይመስላል፤ የመሳሰሉትን ጥያቄዎች መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የዘመናዊነት ሀሳብ በአብዛኛው ማዕከላዊ የሆነ መንግሥት ከመመስረትና የምዕራባዊው ዓለምን ስልጣኔ ከመከተል ጋር ይቆራኛል፡፡
በዚህ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ ለዘመናዊነት መዳበር የተለያዩ ምሁራን ያደረጉትን አስተዋፅኦ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ጽሁፍ ውስጥ የዘመናዊነት ግቦች በኢትዮጵያ ስልጣኔ ውስጥ ሊኖራቸው የሚገባዉን ሚና ለመረዳት የሁለት ጸሀፍትን ሀሳቦች ለመርመር እሞክራለሁ፡፡ የመጀመሪያው የኢትዮጵያዊው ፈላስፋ ዘረ ያዕቆብ ፍልስፍና ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የኢትዮጵያዊው ምሁር ነጋድራስ ገብረ ህይወት ባይከዳኝ አስተሳሳብ ነው፡፡
“ሐተታ” በተሰኘዉ ስራው ውስጥ ኢትዮጵያዊው ፈላስፋ ዘረያዕቆብ በምክንያት የሚመራ ማህበረሰባዊና ግለሰባዊና አስተሳሰብ ለአንድ ማህበረሰብ መሠረት እንደሆነ ያሳየናል፡፡ የዘረያዕቆብ ፍልስፍና የሃይማኖት ግጭትን ለማስቀረትና በዓለም ላይ በሃይማኖት ስም የሚደረገውን እልቂት ለማሰቀረት በህገ ልቦና ላይ የተመሰረተ አስተሳሰብ መዳበር እንዳለበት ያሳያል፡፡ ህገ ልቦና ለሰው ልጅ ፈጣሪ የሰጠዉ የማሰብ ችሎታ ነዉ፡፡ ከአካላዊና የማሰብ ችሎታ በተጨማሪም የሰው ልጅ ልብ ዉስጥ የማሰላሰል ችሎታ አለዉ፡፡ ሐተታ በተሰኘው ስራው ውስጥ ዘረያዕቆብ ከግለሰብ ነፃነት፣ ማህበረሰባዊ ፍትህና እኩልነት ጋር የተገናኙ እሳቤዎችን ለማዳበር ይሞክራል፡፡
ነጋድራስ ገብረ ህይወት ባይከዳኝ ዘረያዕቆብ በፍልስፍና ዘርፍ ያዳበረውን አስተሳሰብ በፖለቲካዊ ኢኮኖሚ መስክ ለማዳበር ይሞክራል፡፡ እንደ ገብረ ህይወት ከሆነ የምዕራባዊ ስልጣኔንና ሀገር በቀል ባህልን ያጣመረ የዕድገት መንገድ መንግስት የመቅረፅ ግዴታ አለበት፡፡ ይህም መንገድ በግለሰባዊ ነፃነት፣ የሃይማኖት እኩልነትና የራስን ማንነት ጠብቆ ከሌሎች ከመማር ጋር ይዛመዳል፡፡ በዚች ጽሁፍ ውስጥ ዘረያዕቆብና ገብረ ህይወት ለኢትዮጵያ ዘመናዊነት ያላቸውን እሳቤዎችን ለመመርመር እሞክራለሁ፡ ፡
ጽሑፌን የዘመናዊነትን ምንነትና ትርጉም በኢትዮጵያ በመዳሰስ እጀምራለሁ፡፡ በመቀጠልም የዘረ ያዕቆብ ሀተታና የገብረህይወት ባይከዳኝን አጤ ምኒልክና ኢትዮጵያ እና መንግስትና የህዝብ አስተዳደር ከዘመናዊነት እሳቤ አንፃር ለመመርመር እሞክራለሁ፡፡ በመጨረሻም የዘረያዕቆብና ገብረህይወት ቋሚ የሆኑ አስተዋፅኦዎችን ለመዳሰስ እሞክራለሁ፡፡
1. የዘመናዊነት ምንነትና ትርጉም በኢትዮጵያ
በሰው ልጅ ታሪክ ውሰጥ የዘመናዊነት ሀሳብ አንድ ማህበረሰብ ስለሌላው ማህበረሰብ፣ አንድ የታሪክ ክፍል ከቀደመው የታሪክ ክፍል በተፈጥሮው በመሰረታዊነት አንደሚለይና አንደሚሻል የሚያሳይ ሀሳብ ሆኖ ቀርቧል፡፡ እዚህ ላይ ጀርመናዊው ፈላስፋ ሀበርማስ እንደሚያሳየን ከሆነ ዘመናዊ /modern/ የሚለው ቃል “ሞዶ“ እና “ሞደርነስ“ ከተሰኙት የላቲን ቃላት የመጣ ሲሆን የክርስትና እምነት ከጥንት የሮማውያን አመለካከት የተሻለ እንደሆነ ያሳያል፡፡ (ሀበርማስ፣ 2001፣ 131) ከዘመናዊ ሀሳብ ጋር በተያየዘ የሚነሱ ብዙ አከራካሪ የሆኑ ሀሳቦች ይገኛሉ፡፡
ዘመናዊነት መቼ ተጀመረ? ዘመናዊነት ግለሰባዊ አመለካከት ነው ወይስ የታሪክ ገፅታ? 
አሁን የምንኖረው ዘመናዊ ወይስ ድህረ ዘመናዊ አለም ውስጥ ነው? ዘመናዊነት በሁሉም ባህሎች ውሰጥ ዳብሯል ወይስ የምዕራባዊው አለም መገለጫ ነው? እና ዘመናዊነት የበለጠ የሰውን ልጅ ነፃ ያወጣል ወይስ ጦርነትና እልቂትን ያባብሳል የመሳሰሉ ጥያቄዎች አሁንም ቢሆን አከራካሪ ናቸው፡፡
እንደ ሀበርማስ ከሆነ ስለ ዘመናዊነት (modernity) ስናስብ፣ ከዘመናዊነት ሀሳብ ተያይዘው የሚነሱ ሶስት መሰረታዊ ሀሳቦች አሉ፡፡ እነዚህም “ሞደርናይዜሽን፣ ሞደርኒዝምና ፖስት_ሞደርኒዝም“ በተሰኙት ሀሳቦች መግለጽ ይቻላል፡፡ “ሞደርናይዜሽን” የዘመናዊነትን ግቦች በኢኮኖሚያዊ ዕድገት፣ የከተሞች መስፋፋትና የሳይንስና ቴክኖሎጂ መዳበር ሲዳሰስ፣ “ሞደርኒዝም” ደገሞ ስነ ጥበብ ለአንድ ማህበረሰብ ዕድገትና ለውጥ ያለውን አስተዋፅኦ ለማሳየት ይሞክራል፡፡ በመጨረሻም “ፖስት _ሞደርኒዝም” የዘመናዊነት ግቦች እንደከሸፉና አሁን የምንኖረው በእውነት፣ በነፃነትና በህሊና አብርሆት በማናምንበት ድህረ ዘመናዊ ዓለም እንደሆነ ያሳያል፡። (ቤንሀቢብ፣ 1997) በዘመናችን የዘመናዊነት ሀሳብ በኢትዮጵያ ውስጥ አንዴት ዳበረ የሚለውን ጥያቄ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡
እንደ ጳውሎስ ሚልክያስ ከሆነ የዘመናዊነት ሀሳብ በኢትዮጵያ ከምዕራባዊው ዓለም ትምህርት ከመስፋፋት፣ የሀገር በቀለ ባህል ትችትና በዘውዳዊ ስርዓትና ምዕራባዊ አመለካከት መካከል ካለው ግጭት ጋር ተነጣጥሎ መታየት አይችልም፡፡ ስለዚህም ዘመናዊነት በኢትዮጵያ ውስጥ በተሰፋፋ ቁጥር የእውቀት ማዕከላት የነበሩት የሃይማኖት ተቋማት በዘመናዊ ትምህርት ቤቶች መተካት ጀመሩ፡፡ ጳውሎስ እንደሚያሳየን ከሆነ ዘመናዊ ስልጣኔ ማለት ዘመናዊ ተቋማት፣ ዘመናዊ ትምህርትና ዘመናዊ አስተሳሰብ ማለት ነው፡፡ (ጳውሎስ፣ 2008፣93) ጳውሎስ በተጨማሪም የአፄ ቴዎድሮስ የመንግስት ምስረታና ማዕከላዊ የሆነ አስተዳደር የዘመናዊነት ግቦች በኢትዮጵያ እንዴት ከሃይማኖት ወግና ባህል ጋር እንደሚጋጭ ያሳዬናል በማለት ሀሳቡን ይደመድማል፡፡ ነገር ግን አፄ ቴዎድሮስ የማዕከላዊ መንግስትን ለመመስረት የቤተክርስትያንን የረዘመ እጅ እንጅ የተቃወመዉ የቤተ ክርስቲያንን ጥበብና አሰተምህሮ አልነበረም፡፡
እንደ አንድርያስ እሸቴ (2002) ከሆነ ዘመናዊነት መቼ ተጀመረ፣ ከቅድመ ዘመናዊው አለም እንዴት ይለያልና ግለሰቦችን ከስርዓት ነፃ አውጥቷል ወይ የሚሉትን ጥያቄዎች በቀላሉ መመለስ ከባድ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የዘመናዊነት ሀሳብ የተለያዩ መሰረቶችና መነሻዎች አሉት፡፡ ከነዚህም መሀል የዘረ ያዕቆብን የተፃፈ ፍልስፍና፣ ደቂቅ እስጢፋኖስ ውስጥ የሚገኘውን የሀይማኖት ግጭትና የነጋድራስ ገብረህይወት ባይከዳኝን አስተሳሰብ በኢትዮጵያ ውስጥ እንደዘመናዊነት መሠረት መመልከት ይቻላል፡፡ አንድርያስ በተጨማሪም የዘመናዊነት ሀሳብ በኢትዮጵያ የተገለፀባቸውን ሁለት መንገዶች ለማሳየት ይሞክራል፡፡ በአንድ በኩል የኢትዮጵያ የተማሪዎች ንቅናቄ ዘውዳዊ ስርአቱን፣ በባላባትና ጭሰኛ መካከል የሚገኝውን ግንኙነት የእኩልነት፣ ፍትህና ነፃነትና ሀሳቦች በማቀንቀን ለመጠየቅ ሞክሯል፡፡ (አንድርያስ፣ 2002፣22) በሌላ በኩል የዘመናዊነት (የሞደርኒዝም) እና የስነጥበብ ትችት የነባራዊውን ሁኔታ በስነጥበብ ስራዎች ውስጥ ለማሳየት ተሞክሯል፣ ነገር ግን ለአንድርያስ በተማሪዎች ነቅናቄና የስነ ጥበብ ትችት መካከል ቀጥተኛ ግንኙነት አልነበረም፡፡ በተጨማሪም የተማሪዎች ንቅናቄ የሶሻሊዝም ርዕዬተ ዓለምን በመከተል ግራ ዘመምተኝነት እንዲስፋፋ አድርጓል፡፡
በጳውሎስና በአንድርያስ ሀሳብ ላይ በመጨመር ባህሩ ዘውዴ እንደሚያሳየን ከሆነ በአዲሱ ምዕተ ዓመት ላይ ሆነን ሁለት ዓይነት የዘመናዊነት እሳቤዎችን በሁለቱ ዘረያዕቆቦች አመለካከት ውስጥ ማየት እንችላለን። የመጀመያውን ዘረያዕቆብ ንጉሥ ዘረያዕቆብ ሲሆን የተገዢዎችን መብት ሙሉ በሙሉ በመጠቅለል ማዕከላዊ የሆነ አስተዳደር ለመገንባት ሞክሯል፡፡ ሁለተኛውም ፈላስፋው ዘረያዕቆብ ሲሆን ግለሰባዊ ነፃነት የህሊና አብርሆት እንዲዳብር ለማድረግ ሐተታ የተሰኘ የፍልስፍና አመለካከት አዳብሯል፡፡
2. ሐተታ፣ ዘረያዕቆብና ዘመናዊ የኢትዮጵያ ፍልስፍና
Screen Shot 2019-12-11 at 2.21.24 PMዘረያዕቆብ
የምዕራባዊ ፍልስፍና አቀንቃኞች ፍልስፍና የተጀመረው በምዕራባዊው ዓለም እንደሆነና፣ ሌሎች ማህበረሰቦች ለፍልስፍና መዳበር ምንም ዓይነት አስተዋፅኦ እንደሌላቸወ ይከራከራሉ፡፡ እዚህ ላይ የአፍሪካ ፈላስፎች አፍሪካ ውስጥ ሀገር በቀል ጥበብና ፍልስፍናዊ የሆነ አስተሳሰብ እንዳለ የመከራከርያ ሀሳብ ያቀርባሉ፡፡ አፍሪካዊው ፈላስፋ ዲስማስ ማሶሎ እንደሚያሳየን ከሆነ የአፍሪካ ፍልስፍ በከፊል የምዕራቡ ዓለም ቅኝ ግዛታዊ የሆነ አስተሳሰብ ትችት ተደርጐ ሊቆጠር ይችላል፡፡፡ (ማሶሎ፣ 2003፣22) አፍሪካ ውስጥ ከሚገኙት ፍልስፍናዊ አስተሳሰቦች ውስጥ የኢትዮጵያዊው ፈላስፋ ዘረያዕቆብ ፍልስፍና ይገኛል፡፡
ቴዎድሮስ ኪሮስ እንደሚያሳየን ከሆነ ካናዳዊው ፈላስፋ ክሎድ ሳምነር በኢትዮጵያ ፍልስፍና ላይ ያደረጉትን ጥናት ተከትለን ሶስት የኢትዮጵያ ፍልስፍና መገለጫዎችን ማየት እንችላለን፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ የተፃፈ ፍልስፍና በዘረያዕቆብና ወልደ ህይወት ስራዎች ውስጥ አናገኛለን፡፡ ሁለተኛም በሀገር በቃል ተረቶች አባባሎችና ወጐች ውስጥ ፍልስፍናዊ ይዘት ያላቸውን ሀሳቦች እናያለን፡፡ በሶስተኛ ደረጃም በሌላው ዓለም የዳበሩ ፍልስፍናዊ አስተሳሰቦችን ኢትዮጵያዊ መልክና ቅርፅ ለማስያዝ የሚደረግ ጥረት እናያለን፡፡ (ቴዎድሮስ፣ 1996፣41) በዚህ ሀሳብ ላይ ሙዲንቤ በመጨመር የኢትዮጵያ ፍልስፍና የራሱ የሆነ ማንነት፣ ይዘትና ተፈጥሮ እንዳለው ያሳየናል፡፡ (ሙዲንቤ፣ 1988፣ 203)
የዘረያዕቆብ ፍልስፍና መሠረት በዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠረው የሃይማኖቶች አለመግባባትና ክርክር ነው፡፡ ዘረያዕቆብ እንደ ፈላስፋ በሃማኖታዊ ስርዓትና ትምህርት ውስጥ ነው ያደገው፡፡ ሐተታ በተሰኘ ስራው ውስጥም ሀሳቡን ሲያዳብር ፈጣሪ የፍልስፍና ጉዞውን እንዲያቀናለት በመጠየቅ ነው፡፡ ሐተታ ውስጥ ዘረያዕቆብ እንደሚነግረን ሁሉን በፈጣረ ፈጣሪና ለሰው ልጅ ህገ ልቦና በሰጠ አምላክ ስም በህይወቴ የገጠመኝን ነገሮች በዚች መጽሀፌ ውስጥ አቀርባለሁ በማለት ነው፡፡ (ስምነር 1976፣3)
ዘረያዕቆብ የሃይማኖት ትምህርትን በሚያስተምርበት ወቅት ከተለያዩ የኃይማኖት ተከታዬች ጋር በቀን ተቀን ሕይወቱ ውስጥ ክርክር ውስጥ ይገባ ነበር፡፡ በዚህ ግዜም የሁሉም ሃይማኖት ተከታዬች ፀረ ሃይማኖታዊ የሆነ የአስተሳሰብ ፈሊጥ እንደሚከተሉና የነሱን አስተሳሰብ ለመናድ እንደተነሳ አድርገው ይቆጥሩ ነበር፡፡ ዘረያዕቆብ አንደሚያሳየን ከሆነ በአካባቢዉ የሃይማኖትን ትርጓሜ ሲያስተምር ከሁሉም የሃይማኖት ተከታዬች ጋር ግጭት ውስጥ ገባ፡፡ (ሰምነር፣ 1976፣4) ከጊዜ በኋላም በአስተሳሰቡ ምክንያት ቅጣት ይደርስብኛል ብሎ ስላሰበ ዘረያዕቆብ ስደትን መረጠ፡፡
ተከዜ አካባቢ በምትገኝ አንድ ዋሻ ውስጥ ተደብቆ ዘረያዕቆብ ሐተታ የተሰኘ የፍልስፍና መንገድን ማዳበር ቀጠለ፡፡ እዚህ ላይም ከፀሎት በኋላ ምንም ዓይነት ስራ ላይ በማይጠመድበት ጊዜ ዘረያዕቆብ በፈጣሪ ህልውናና በዓለም ላይ ስለሚታየው ስቃይ፣ የሃይማኖት አስተምህሮና በሃይማኖት መካከል ስለሚገኘው ግጭት ለማሰብ ይሞክር ነበር፡፡ በዚህ ግዜም ዘረያዕቆብ እንደሚነግረን “ከግዜ በኋላም እራሴን ጠየቅኩ ሁሉ በቅድሳን መጻሕፍት ላይ የተጻፈው ነገር እውነት ነው?” (ሰምነር፣ 1976፣7) በመጨረሻም ዘረያዕቆብ ለሰው ልጅ ህገ ልቦና የሰጠ አምላክ ለዓለምና ለነገሮች መፈጠር ምክንያት መሆኑን፣ ዓለም ላይ የሚታየው እልቂት በሰው ልጅ ገደብ የለሽ ፍላጐት መምጣቱንና ሁሉም ሰዎች በፈጣሪ ፊት እኩል መሆናቸውን ድምዳሜ ላይ ደረሰ፡፡
በዘረያዕቆብ ፍልስፍናዊ አመለካከት ውስጥ የወግ፣ የባህልና የሃይማኖት ትችት እናገኛለን፡ የዘረያዕቆብ ሀተታ በተፈጥሮው የነገሮችን መሠረት በመመርመርና በመጠየቅ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ በዚህ ፍልስፍና ውስጥ ዘረያዕቆብ ከፈጣሪ ህልውናና የሰውልጅ ተፈጥሮ፣ የማህበረሰባዊ ፍትህና የግብረገብ መርሆች ጋር የተገናኙ ጥያቄዎችን ለማንሳት ይሞክራል፡፡ ተሾመ አበራ እንደሚያሳየን ከሆነ በዘረያዕቆብ የግብረገብ አስተምህሮት ውስጥ በሰው ልጅ ምክንያታዊ የሆነ ተፈጥሮ፣ የተፈጥሮ ህግጋትና የፈጣሪ ህልውና መካከል ቅርብ የሆነ ቁርኝነት እንመለከታለን፡፡ ስለሆነም ለዘረያዕቆብ እውነትና የግብርገብ መርሆች ዓለም አቀፋዊ የሆነ ተፈጥሮ አላቸው፡፡ ይህንንም ተፈጥሮ የሰው ልጅ በተፈጥሮ በተሰጠው ምክንያት አንጂ በጊዜና በቦታ በተወሰኑ አመለካከቶች መረዳት አንችልም፡፡ (ተሾመ ፣ 2016፣ 232)
ዘረያዕቆብ በፍልስፍናው ውስጥ እንደሚጠይቀው ከሆነ የሁሉም ሃይማኖት ተከታዮች የራሳቸው እምነት ከሌሎች የተሻለ እንደሆነ ለማሳየት ይሞክራሉ፡፡ በመሠረታዊነት ደረጃ ግን እውነት አንድ ናት፡፡ ለዘረያዕቆብ የአንድን ሃይማኖት አስተሳሰብ ከመከተል ይልቅ በህገ ልቦና የእውነት ተፈጥሮን መመርመር ያስፈልጋል፡፡ የአንድ ማህበረሰብም እድገት በሰዎች እኩልነት፣ በምክንያታዊነትና ማህበረሰባዊ ፍትህ ላይ መታነፅ እንዳለበት ዘረያዕቆብ ያሳየናል፡፡
3. ገብረህይወት ባይከዳኝና ዘመናዊነት እንደ ህዝብ አስተዳደር
እንደ ዶናልድ ሌቪን ከሆነ አፍሪካ ውስጥ ዘመናዊነትን ለመተግበር የሚደረጉ ጥረቶች በባህልና በዘመናዊ፣ በዘመናዊ አስተሳሰብና በሀገር በቀል እውቀትና ምዕራባዊ ስልጣኔ መካከል አላስፈላጊ የሆነ ልዩነት ይፈጥራሉ፤ ከሁሉም ነገር በላይ ግን ለሌቪን በባህሎችና አስተሳሰቦች መካከል ያለውን መስተጋብርና መማማር ማጥናት ያስፈልጋል፡፡ (ሌቪን፣ 2007፣ 42) እዚህ ላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ልዩ የሆነ የዘመናዊነት አመለካከት ለማዳበር ከጣሩ ምሁራን መካከል የነጋድራስ ገብረህይወት ባይከዳኝን ስራዎች እናገኛለን፡፡
ባህሩ ዘውዴ Pioneers of Change in Ethiopia, The reformist thinkers of the twentieth century በተሰኘው መጽሐፋቸው ውስጥ እንደሚያሳዬን ከሆነ እንደነጋድራስ ገብረህይወት ባይከዳኝ ያሉ የኢትዮጵያ ምሁራንን የዕጣ ፈንታ ልጆች አድርገን መቁጠር እንችላለን፡፡ እዚህ ላይ ነጋድራስ ገብረህይወት በአጋጣሚ ነው አውሮፖ ውስጥ ትምህርታቸውን የተከታተሉትና የምዕራቡን ዓለም እውቀትና ትምህርት ለመቅሰም የቻሉት፡፡ (ባህሩ፣ 2016፣36) እንደ ባህሩ ዘውዴ ከሆነ “አጤ ምኒልክና ኢትዮጵያ” በተሰኘው ስራቸው ውስጥ በነጋድራስ ገብረህይወት አስተሳሰብ ላይ ሁለት ተፅዕኖዎችን እናያለን ፡፡ የመጀመሪያው በሱዳንና በኤርትራ የነበራቸው ቆይታ ባሳደረባቸው ተፅዕኖ ገብረህይወት ቅኝ ግዛት በተገዙና በነፃነት በኖሩ ህዝቦች መካከል ስላለው ልዩነት የሚያዳብሩትን ንፅፅር እናያለን፡፡ በተጨማሪም ንግሥት ጣይቱ ለኢትዮጵያ ዕድገት ያበረከቱትን አስተዋፅኦ እንመለከታለን፡፡ ለባህሩ ዘውዴ፣ ገብረ ህይወት የኢትዮጵያን ስልጣኔ ለማሳደግ የምዕራቡን አስተሳሰብ ብቻ መቀበል መፍትሄ ነው ብለው አያምኑም ነበር፡፡
“አጤ ምኒልክና ኢትዮጵያ” በተሰኘው ስራቸው ውስጥ ነጋድራስ ገብረህይወት ባይከዳኝ የአንድ ማህበረሰብ የታሪክ አጻጻፍና ማህበረሰባዊ ዕድገት እንደማይነጣጠሉ አሳይተውናል፡፡ በዚህ ላይ በመመርኮዝ ቅን የሆነ ልቦና፣ አለማዳላትና በቅንነት የታሪክ ሁነቶችን ለሌሎች ማሳወቅ፣ አንድን ማህበረሰብ የራሱን ማንነት የበለጠ እንዲረዳ አንደሚያደርጉ አሳይተውናል፡፡ ስለዚህም የጤና መሠረት የሌለው ቤት ብዙ ዕድሜ ያገኛል ተብሎ እንደማይታመን ሁሉ እንዲሁም መንግስታችን መሠረት ያለው ሥርዓት እስኪያገኝ ድረስ ሀይሉ ብዙ አመታት ይቆያል ተብሎ አይታመንም፡፡ (ገብረህይወት፣ 2007፣9) እንደ ገብረህይወት ከሆነ ዘመናዊ ማህበረሰቦች መንግስት በዜጐች መካከል ስምምነት እንደሆነና የተመረጠበትም ምክንያት የህዝቡን ፍላጐት ማርካት እንደሆነ ይረዳሉ፡፡
በአንድ አገር ውስጥ ጠንካራና ተራማጅ መንግስት እንዲኖር ንቃተ ህሊናው የዳበረና መንግስትን የሚጠይቅ ህዝብ ያስፈልጋል፡፡ በተቃራኒው ራዕይ የሌለው ማህበረሰብ የመሪዎቹን ሀሳብ ጠይቆና በደንብ መርምሮ መቀበል አይችልም፡፡ ገብረህይወት በ”አጤ ምኒልክና ኢትዮጵያ” መጽሐፋቸው ውስጥ ሌላው ዓለም የበለጠ ሲሰለጥን፣ ሲለወጥ አሁንም እኛ ኢትዮጵያን ለምን በኋላ ቀርነት እንኖራለን ብለው ይጠይቃሉ፡፡ ስለዚህም ለገብረ ህይወት በመላው ዓለም ላይ ሰላም ሲሰፋ አእምሮም ስትበራ እኛ በጨለማ እንኖራለን፡፡ (ገብረህይወት፣ 2007፣ 19) በአጠቃላይ ለገብረ ህይወት በኢትዮጵያ ውስጥ የዘመናዊነት ግቦች እንዲሳኩ አስር መንገዶች መተግበር ይኖርባቸዋል፡፡
በመጀመሪያ ደረጃ የህዝብ ሀብት ከንጉሡ ግላዊ ንብረት በአግባቡ መለየት ይኖርበታል፡፡ ሁለተኛም በግለሰብ ሀብትና የግብር መጠን መካከል ቀጥተኛ የሆነ ግንኙነት መኖር አለበት፡፡ ሶስተኛ፣ ሁሉም ግለሰብ በአንድ ዓይነት መገበያያና ገንዘብ መጠቀም ይኖርበታል፡፡ አራተኛ፣ የሁሉም መግባቢያ የሆነው የአማርኛ ቋንቋ የበለጠ መጠናት ይኖርበታል፡፡ በመቀጠልም አምስተኛ፣ ፍተሐ ነገሥታችን ከዛሬው ያደባባይ ሥርዓት ጋር አይስማማም (ገብረህይወት፣ 2007፣25) ስድስተኛ፣ ዘመናዊ የሆነ ሠራዊት ማቋቋም ያስፈልጋል፡፡ ሰባተኛ፣ በአገራችን የመገበያያ ስርዓትና ገንዘብ ላይ ማሻሻያ መተግበር ያሰፈልጋል፡፡ ስምንተኛ በህግ የሚመራ የንግድ ስርዓት መተግበር ያስፈልጋል፡፡ ዘጠነኛ ጠንካራ የሆነ የመንግሥት አስተዳደር መተግበር አለበት፡፡ በመጨረሻም፣ አሥረኛ የሃይማኖት አርነት ይታወጅ (ገብረህይወት፣ 2007፣27)
“መንግስትና የህዝብ አስተዳደር “በተሰኘው ሁለተኛ ስራቸው ውስጥ ገብረ ህይወት እንደሚያሳዩን ከሆነ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ የሰለጠኑት ማህበረሰቦች ኋላ የቀሩትን፣ ያደጉ ህዝቦች ደግሞ ያላድጉትን ሲገዙና ሲያስተዳድሩ ይታያል፡፡ እዚህ ላይም በመመርኮዝ ሀብት ማለትም የምድርን ግዛት መለኪያ ነው፣ ድሃ የሆነ ህዝብ የምድር ሎሌ ነው፡፡ (ገብረ ህይወት 2007፣ 83) ስለዚህም የአንድ ማህበረሰብ ሀብት ምን ያህል አንድ ህዝብ ተፈጥሮን አንደተቆጣጠረና እንደገዛ ማሳያ ተደርጐ ሊወሰድ ይችላል፡፡
ለአንድ ማህበረሰብ ዕድገት በህዝብ ቁጥር ዕድገትና ለስራ በደረሰው ዜጋ መካከል መጣጣም እንዲኖር ያስፈልጋል፡፡ በተጨማሪም የማህበረሰቦች ዕድገት ከስራ ባህል ጋር ተነጣጥሎ መታየት አይችልም፡ ለገብረህይወት ነፃነት መንግሥትን መመስረት ብቻ ሳይሆን እራስንም መቻል ነው፡፡ ገብረህይወት የሚከተለውን ጥያቄ ያቀርባሉ፡፡ እስቲ አሁን እኛ የኢትዮጵያ ህዝብ አርነት አለን ሊባል ነውን? አርነት ያለው ህዝብ ማለት እውነተኛ ትርጉሙ ለብቻው መንግሥት ያለው ህዝብ ማለት ብቻ አይደለም፡፡ ራሱንም የቻለ ህዝብ ማለት ነው እንጂ፡ (ገብረህይወት፣ 2007፣105) በዋናነት ለገብረህይወት በአንድ አገር ህጐችና በህዝቡ ንቃተ ህሊና መካከል ክፍተት እንዳይኖር ዘመናዊ ትምህርትና ስልጣኔ ትልቁን ሚና ይጫወታል፡፡
4. ዘረያዕቆብ፣ ገብረህይወትና የዘመናዊነት ግቦች በኢትዮጵያ
በአሁኑ ጊዜ ላይ ሆነን ዘረያዕቆብና ነጋድራስ ገብረህይወት ባይከዳኝ ለዘመናዊነት ግቦች በኢትዮጵያ መሳካት ያደረጉትን ሚና በተለያየ መንገድ መረዳት እንችላለን፡፡ በመሠረታዊነት ዘረያዕቆብ የማህበረሰባዊ ፍትህና የግለሰብ ተፈጥሮ ላይ ሲያተኩር፣ ገብረህይወት ባይከዳኝ ደግሞ የመንግስት አወቃቀርና የህዝብ አስተዳደር ላይ ለማተኮር ሞክረዋል፡፡
የዘረያዕቆብ ፍልስፍና የአንድ ማህበረሰብ መሰረት በምክንያታዊነት የተመራ የግለሰብ ጉዞ እንደሆነ ያሳያል፤ ስለዚህም የማህበረሰባዊ ለውጥ፣ አብሮ የመኖር ምስጢርና የማህበረሰባዊ ፍትህ በግለሰባዊ ነፃነትና ምክንያታዊ የሆነ ተፈጥሮ ላይ ይመረኮዛል፡፡ በተጨማሪም የዘረያዕቆብ ፍልስፍና የሁሉንም ሰዎች መሠረታዊ አኩልነት እንደ መነሻ አድርጐ ይቆጥራል፡፡
አንድን ሃይማኖት ከሌላው ከማስበለጥና በሃይማኖት አስተዋምህሮት ላይ የተመረኮዘ እሴትና የስነ ምግባር ህጐች ከማዳበር ይልቅ ዘረ ያዕቆብ ህገልቦና አንዴት የዕውነት መሠረት እንደሆነ ሊያሳየን ይሞክራል፡፡ ይህም ህገ ልቦና በሁሉም የሰው ልጆች ውስጥ በተፈጥሮ የሚገኝ የማሰብና የማመዛዘን ችሎታ ነው፡፡ እዚህ ላይ ተሾመ እንደሚያሳየን ከሆነ የዘረያዐቆብ “ሐተታ” የስራን ክብርና አብሮ የመኖርን እሴቶች ለማዳበር ይኖራል፡፡(ተሾመ፣ 2016፣ 436) ስለዚህም ሐተታን፣ የመቻቻል አብሮ የመኖርና ምክንያታዊ የሆነ የማህበረሰባዊ ጉዞ መሠረት አድርገን መረዳት እንችላለን።
እንደ መሳይ ከበደ ከሆነ የነጋድራስ ገብረህይወት ፍልስፍና የምዕራባዊ ዓለሙን ስልጣኔ ወደ ኢትዮጵያ የማስገባትና የማስረፅ ሂደት ነው፡፡ መሳይ እንደሚያሳየን ከሆነ ገብረህይወት በስራዎቹ ውስጥ የሚጠይቀው መሰረታዊ ጥያቄ እንዴት የኢትዮጵያ ባህል እንደተቀረው ዓለም መዘመን አልቻለም ነው (መሳይ፣ /2006፣ 817) እንደ መሳይ ግምገማ ከሆነ ገብረ ህይወት ባይከዳኝ የሀገር ባህል እውቀትን ከማጥናትና ከማዳበር ይልቅ ምዕራባዊ ዕድገት፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂን ለኢትዮጵያ ዕድገት መሠረት አድርጐ ይመለከት ነበር፡፡ ከመሳይ ከበደ ሃሳብ በተቃራኒ ሳልቫዶሬ አንደሚያሳየን ከሆነ ገብረ ሀይወት ባይከዳኝ ኢትዮጵያዊ የሆነ መልክ ያለው የእድገት መስመር ለመቀየስ ሲሞክር ነበር፡፡ ይህም መንገድ ፍትሃዊ በሆነ የሃብት ክፍፍል፣ ዘመናዊ ትምህርትና ሀገር በቀል ወግና ባህል ላይ የተመሠረተ ነበር፡፡ (ሳልቫዶሬ፣ 2007፣561)
እዚህ ላይ ኤልሳቤጥ ወልደ ጊዬርጊስ አንደምታሳየን ከሆነ ምንም እንኳን የነጋድራስ ገብረህይወት ስራዎች በኢትዮጵያ ውስጥ ምዕራባዊ ዘመናዊነትን ለማስረፅ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ቢገኝም፣ ነገር ግን ገብረህይወት በኢትዮጵያ ውስጥ ሀገር በቀል ባህሎችና አመለካከቶች ያላቸውን ልዩ ቦታ ለማሳየት ይሞክራል፡፡ (ኤልሳቤጥ፣ 2010፣83) ስለዚህም በስራዎቻቸው ውስጥ የኢትዮጵያ ዘመናዊ ስልጣኔ መሠረትና መጠሪያዎች ምን እንደሆኑ ገብረ ህይወት ያሳዩናል፡፡
በአጠቃላይ ምንም እንኳን የዘመናዊነት መገላጫዎች በኢትዮጵያ ታሪክና ባህል ውስጥ በተለያየ መንገዶች ቢንፀባረቁም፣ የዘረ ያዕቆብ ፍልስፍና፣ የገብረህይወት ባይከዳኝ ሰራዎች ሁለት ዘመናዊ አስተሳሰቦችን ያሳዬናል፡፡ የመጀመሪያው በፍልስፍና ጉዞ ላይ ሲመሰረት ሁለተኛው ደግሞ በማህበረሰብ ትችት ላይ ተመርኩዟል፡፡ ሁለቱም በምክንያታዊነት፣ በግለሰብና በማህበረሰብ ደረጃ መዳበር እንዴት ለማህበረሰባዊ ለውጥ እንደሚያመጣ ያሳዩናል፡፡
መደምደሚያ
በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ የዘመናዊነት ሀሳብ ከአንድ ትውልድ ወደ ሌላ ትዉልድ፣ ከአንድ ዘመን ወደ ሌላው ዘመን እየተሸጋገረ ይሄዳል፡፡ ስለዚህም እያንዳንዱ ማህበረሰብ የበለጠ ዘመናዊና በለውጥ የሚያምን መሆኑን ለማሳየት ይሞክራል፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የዘመናዊነት ሀሳብ መገለጫዎች በተፈጥሮ የተለያዩ ናቸው፡፡ ስለዚህም በስነጥበብ፣ በፍልስፍና፣ በማህበረሰብ ትችና ዘመናዊ ትምህርት ውስጥ የተለያዩ ሀሳቦች ተንፀባርቀው እናገኛለን፡፡
በፍልስፍና መስክ ኢትዮጵያዊው ፈላስፋ ዘረያዕቆብ፣ የባህልና የወግ አስተሳሰቦችን ትችት በማዳበር በማህበረሰቡ ውስጥ ምክንያታዊነትና ማህበረሰባዊ ፍትህ እንዲሰፍን “ሐተታ” የተሰኘ ስራውን ለማዳበር ሞክሯል፤ ከዚህ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያዊው ምሁር ነጋድራስ ገብረህይወት ባይከዳኝ የሀገር በቀል ጥበብንና ምዕራባዊ ስልጣኔን ያጣመረ የዕድገት ጐዳና ለመቀየስ ሲሞክር ነበር፡፡ በነዚህ ሙከራዎች ላይ ተመርኩዘን ዘመናዊነት የበለጠ በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲዳብር ምክንያታዊ የሆነ ማህበረሰብ እንድያብብ ማድረግ  ያስፈልጋል፡፡
Filed in: Amharic