>
5:16 pm - Thursday May 24, 5055

‹‹ይህች ጊዜ መጣች፣ መጣች ለፈተና አንተም ለዚህች ጊዜ፣ ተፈጥረሃልና!› (እንዳለጌታ ከበደ)

‹‹ይህች ጊዜ መጣች፣ መጣች ለፈተና

አንተም ለዚህች ጊዜ፣ ተፈጥረሃልና!››    

እንዳለጌታ ከበደ
ከላይ ያነበባችሁት ስንኝ፣ አሁን እንደገጠመን ያለ ፈተና በሀገር ላይ ሲያንዣብብ፣ አንድ ስሙ ያልታወቀ (ያላወቅሁት) ግለሰብ የገጠመው ነው፡፡ 
እያንዳንዱ ትውልድ፣ እያንዳንዱ ዘመን፣ እንዲሻገረው የተመቻቸለት ፈተና አለው፡፡ ማንነቱም የሚለካውም ይህን ድልድይ ለመሻገር በሚያደርገው ጥንቃቄና ሌሎችን በሰላም ለማሻገር በሚያደርገው ጥረት ነው፡፡
በእኛ ጊዜ ከገጠሙን (ከዓለም ጋር በእኩል ደረጃ የምንጋራው) ፈተናዎች መሃል ዋነኛው ኮሮና ቫይረስ ነው፡፡ ብርቱዎች፣ ጥንቁቆች፣ የዲሲፕሊን ተገዢዎች በዚህ ወቅት እፊታቸው የተዘረጋውን የመከራ ድልድይ ይሻገሩታሉ፤ ፈተናውንም በድል ይወጡታል፡፡ ደካሞች፣ ዝንጉዎች፣ ለራሳቸውና ለሌላው ዋጋ የማይሰጡ ደግሞ ተንሸራትተው ይወድቃሉ፤ የናቁትና ያልተጠነቀቁት ቫይረስ ይጥላቸዋል፡፡ የመከራ፣ የሕማምና የሞት ወንዝም ይወስዳቸዋል፡፡
‹አላህን አምናለሁ፤ ግመሌንም አስራለሁ› የሚል የቆየ የአረቦች አገላለጽ አለ፡፡ ንብረታችንን በቅጡ የማንጠብቀው፣ ጤንነታችንን የማንከባከበው በፈጣሪ ላይ እምነት ስለሌለን አይደለም ለማለት ነው፡፡ ኖረን እንዳየነው፣ እምነት ብቻውን ዋጋ የለውም፤ ሥራ ይፈልጋል፤ ተግባር ይፈልጋል፡፡
እንደምናምነው፣ የጤና ባለሙያዎች አድርጉ የሚሉንን መርህ ብቻ በመከተል ራሳችንን መታደግ እንችላለን፡፡ ሚዲያዎች፣ ባለስልጣናት፣ ተቋማትና ተጽዕኖ አሳዳሪ ግለ-ሰቦች ደግሞ፣ የጤና ባለሙያዎችን ምክር መሰረት በማድረግ፣ ‹ሳይደናገጡ የመጠንቀቅን› ጥበብ እያስተማሩን ነው፡፡ ሆኖም፣ በሚዲያ እንደምንከታተለው፣ ጋዜጠኞችና የመንግስት ባለስልጣናት፣ ‹ራሳችሁን ጠብቁ› ብለው የሚክሩን፣የሚገስጹንም ራሳቸውን ለአደጋ በሚያጋልጥ እንቅስቃሴ ውስጥ ሆነው ነው፡፡ ጥንቃቄ ለመውሰድ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን በየፋርማሲው ለመግዛት፣ ሰዉ እንዴት እንደሚርመሰመስና ይህም ልክ አይደለም የሚሉን ጋዜጠኞች እነሱ ራሳቸው ‹ስህተቱ› ውስጥ ተዘፍቀው፣ ትርምስምሱ ውስጥ ሆነው ነው የሚዘግቡልን፡፡ ጓንት የለም፤ አፍ መከለያ የለም፤ እጃቸውን ሲታጠቡ ማሳየት የለም፤ከሌላው ሰው ርቀትን ጠብቆ መቆም የለም፡፡ (በነገራችን ላይ ሰልፍ በሚበዛባቸው አካባቢዎች፣ እጅ ከማስታጠቡና አልኮሆል ከመስጠቱ በተጨማሪ፣ ሰልፈኞች/ባለጉዳዮች ርቀው ተራርቀው እንዲቆሙ የሚያደርግ አስተባባሪ በየመሥርያ ቤቶቹ አማካይነት፣ ቢያንስ አንድ አንድ ሰው መመደብ ያስፈልጋል)
መንግስት አሁንም ቢሆን፣ በማረሚያ ቤቶች፣ በተፈናቃይ ማኖርያዎች፣ በገበያዎች፣ በኢንዱስትሪ ፓርክ ሠራተኞች አካባቢ ትኩረቱን መጣል አለበት፡፡ በተለይ ‹‹ማረሚያ ቤቶች›› ያሉ ‹‹ታራሚዎች››፣ የሚፈቱበት ቀን የተቃረቡትን በፍጥነት በመፍታት፣ ጉዳያቸው ከበድ ያለውን ደግሞ፣ ጊዜያዊ ‹መታረሚያ ቤቶችን› በማመቻቸት አደጋውን መቀነስ ተገቢ ነው(አሁን ትምሕርት ስለሌለ ከየትምሕርት ቤቶች ጋር በመነጋገር ሊሆን ይችላል፡፡  በደርግ ዘመን፣ በማዕከላዊ እስር ቤቶች የኮሌራ በሽታ ገብቶ፣ በአንድ ‹‹መታረሚያ ቤት›› ብቻ በጥቂት ቀናት ልዩነት ከ50 ሰዎች በላይ ሊሞቱ ችለዋል፡፡
የጤና ባለሙያዎችና በጎ አድራጊዎች ይህንን ወረርሽኝ ለመታደግ ጥረት የሚያደርጉትንም መጠበቅ፣ መንከባከብ ያስፈልጋል፡፡
አያድርግብን እንጂ፣ ችግሩ እየባሰ፣ እየተባባሰ ከሄደ ቫይረሱ ከሚጥላቸው ዜጎች በላይ የሚበሉት የሚጠጡት አጥተው የሚሞቱ ሰዎች ሊበዙ ይችላሉ፡፡ ጎዳና ተዳዳሪው፣ ለምኖ አዳሪው….ሌላ ሌላውም፡፡ የዕለት እንጀራቸውን በየዕለቱ የሚያገኙ ዜጎች ብዙ ናቸው- ለሦስት ተከታታይ ቀናት ሥራ ቢቆም፣ ‹ቤታችሁ ዋሉ› የሚል አስቸኳይ አዋጅ ቢነገር፣ ሰማይ ምድሩ የሚገለባበጥባቸው፡፡ ጉዳቱ ለሁሉም ነው፡፡ ጥንቃቄ እንውሰድ የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡ ቫይረሱ የመከራ ጠል አይደለም፣ ወጀብ እንጂ! እንኳንስ ቫይረሱ ወጀብ ሆኖ ወርዶብን ካፊያውም፣ ውሽንፍሩም ገፍትሮ ይጥለናል፡፡
በአጭሩ ከቫይረሱ ጋር በቅጡ አልተዋወቅንም፡፡ ሰዉ አሁንም ትከሻ ለትከሻ እየተገፋፋ፣ አፍ ለአፍ እየገጠመ፣ በንክኪና በትንፋሽ ስለሚተላለፈው ቫይረስ እያወራ ነው፡፡
ቻይና ወረርሽኙን ለመቆጣጠር በምታደርገው ጥረት ስኬትን ማስመዘገብ የቻለችው (በእስካሁን ቆይታዋ) ለዲሲፕሊን መገዛት የሚችል ዜጋ ማፍራት ስለቻለች ነው፡፡
እናም፣ ለመርሁ እንታመን!
‹‹ይህች ጊዜ መጣች፣ መጣች ለፈተና
አንተም ለዚህች ጊዜ፣ ተፈጥረሃልና!››
Filed in: Amharic