>

ፈውስ ሥጋዊ ወ ፈውስ መንፈሳዊ (ከይኄይስ እውነቱ)

ፈውስ ሥጋዊ ወ ፈውስ መንፈሳዊ

 

ከይኄይስ እውነቱ

 

የኢኦተቤክ በማዕጠንት አገልግሎት አማካይነት የምትፈጽመው የጸሎት ሥርዓት መጽሐፍ ቅዱሳዊ፣ቸነፈር በተከሠተ ጊዜ ላገርና ለወገን ባጠቃላይ የሚደረግ መንፈሳዊ ፈውስ ነው፡፡

አንዳንዴ ድንበር ከመተላለፋችን ወይም የማናውቀው ግዛት ውስጥ ገብተን ከመዘባረቃችን በፊት ፍላጎቱ ካለን ዕውቀቱ ካላቸው ጠይቀን ወይም በዘባረቅነው ጉዳይ ላይ የተጻፉ መጻሕፍትን አንብበን ግንዛቤ ማግኘቱ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ከእውነተኛ ጭንቀትና ሥጋት ተነሥቶ በጎ ከማሰብም ይሁን በሌላ መግፍኤ የመጣልንን ሁሉ ያለማስተዋል መጻፍ ታዛቢ እንዳለና ብዙዎችን ሊያስቀይም እንደሚችልም መረዳት ተገቢ ይሆናል፡፡ በተለይም ርእሰ ጉዳዩ ሃይማኖት ነክ ፈትለ ነገሮችን የሚመለከት ሲሆን ጥንቃቄ ማድረጉ አንድም የማስተዋል፣ በሌላ ገጽታው ደግሞ የእምነቱን ተከታዮች የማክበር ምልክት ነው፡፡  

በአሁኑ ጊዜ ‹ኮሮና ቫይረስ› የሚባል ቸነፈር ዓለማችንን እያስጨነቀ እንደሆነ የዕለት ተዕለት ዜናና መርዶ ሆኗል፡፡ ይህ ጽሑፍ በሚዘጋጅበት ሰዓት በመላው ዓለም ወደ ግማሽ አእላፋት የሚጠጉ ሰዎች በደዌው እንደተያዙና ከ22 ሺህ በላይ የሚሆኑ ደግሞ እንደሞቱ ተዘግቧል፡፡ በሳይንሱ ረገድ በሽታው መድኃኒት ስላልተገኘለት ሥርጭቱንና መስፋፋቱን ለመከላከል የሚረዱ ጥንቃቄዎችን በዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት እና በየመንግሥታቱ የጤና ተቋማት እየተነገረ ይገኛል፡፡ ሆኖም ጥንቃቄውን ተግባራዊ የማድረጉ ሁናቴ እንደየመንግሥታቱ ጥንካሬና ለዜጎቻቸው ያላቸው የኃላፊነት ስሜት፣ የኢኮኖሚ ዐቅም፣ የሕዝቦቻቸው ንቃት ደረጃ፣ ባህልና የአነዋወር ዘይቤ ይለያያል፡፡ እንደኛ ዓይነቱ አገር ውስጥ በአገዛዙና በሕዝቡ መካከል መተማመን በሌለበት፣ መልካም የሚመስሉ መልእክቶች ከደንታቢስነት ጋር በተቀላቀሉበት፣ ከፍተኛ የዐቅም ውሱንነት ባለበት፣ የአብዛኛው ሕብረተሰበ የንቃት ደረጃ ዝቅተኛ በሆነበት፣ ባህልና አነዋወራችን ከአብሮነት ለጊዜውም ቢሆን ለመላቀቅ በሚያስቸግርበት ሁናቴ ከ‹መንግሥትም› ሆነ ከእምነት ተቋማት የሚነገሩ የጥንቃቄ መልእክቶችን ሥራ ላይ ለማዋል ፈተናው ቀላል አይደለም፡፡

ቸነፈር (ወረርሽኝ) በመላው ዓለም ሲከሠት በሳይንሱ ዓለም ለደዌው በመንስኤነት የሚጠቀሱት ምክንያቶች እና በመንፈሳዊው ዓለም የሚቀርቡት ምክንያቶች ለየቅል ናቸው፡፡ ሳይንሱ ተሐዋስያን (ቫይረስ/ባክቴርያ ወዘተ.) ሲል፣ በመንፈሳዊው ዓይን ደግሞ የኀጢአት፣ የመተላለፍ፣ የግፍና በደል ጽዋ ሞልቶ መፍሰስ፣ ወዘተ. በዚህም ምክንያት ከእግዚአብሔር የመጣ መዓት፣ ቁጣ፣ ተግሣፅ ተደርጎ ሊታይ ይችላል፡፡ የኋለኛውን ምክንያት በአገራችንና በዓለም ደረጃ በምሳሌ ለማየት፤ ኢሕአዴግ የተባለው በጐሠኛነት ቸነፈር ኢትዮጵያውያንን የመታው ግፈኛና ጨካኝ አገዛዝ ኢትዮጵያኖችን በመግደል (የሰው ልጅ ተዘቅዝቆ ሲሰቀል እና በቆርቆሮ ተገዝግዞ ሲታረድ በዝምታ በማለፍ ወዘተ) አካል በማጉደል፣ በግፍ በማሰር (በየእስር ቤቱ የተፈጸሙትን ስቃያት ያስታውሷል)፣ ከቤት ንብረታቸው በገፍ በማፈናቀል፣ ደሀውን በመበደልና ፍርድ በማጓደል፣ ባጠቃላይ ነውር የተባለን ሁሉ ንቅስ አድርጎ በመፈጸም የግፍ ጽዋው በምድረ ኢትዮጵያ ሞልቶ እንዲፈስ አድርጓል፡፡ አሁንም ያባራ አይመስለም፡፡ በዓለም ደረጃ ስናየው ኃያላን የሚባሉት የምዕራቡም ሆነ የምሥራቁ መንግሥታት በየአገሮች ጣልቃ በመግባት የሚፈጽሙት ግፍና በደል፣ በሰብአዊ መብት ሽፋን የሚፈጸመው ግብረ ሰዶምና ግብረ ገሞራ፣ አልፎ ተርፎም እንስሳትንና ሰውን እስከማጋባት የሚታየው ከአእምሮ ጠባይዕ የተጣለ፣ ከተፈጥሮ ሕግና ሥርዓት የወጣ ቅጥ ያጣ ነውር ወዘተ. የእግዚአብሔርን ቁጣ የማይጋብዝበት ምን ምክንያት አለ? እዚህ ላይ ለኢትዮጵያ ወገኖቼ አንድ ጥያቄ ላንሳ፡፡ ይህ ወረርሽኝ በዕብደትና በድንቁርና በሕዝብ ላይ ግፍና በደል የሚፈጽሙ ግለሰቦች፣ ቡድኖችና በዘረኝነት ለተለከፉ የፖለቲካ ድርጅቶች የማንቂያ ደወል ሆኖ ወደ አእምሮአቸው ወደ ቀልባቸው ይመልሳቸው ይሆን? 

ወደ ቀደመ ነገሬ ልመለስና የተከሠተውን ቸነፈር ለመዋጋት የሳይንሱ ማኅበረሰብ (በተለይም ባደጉት አገሮች የሚገኘው) ክትባትም ሆነ በእንክብል መልክ የሚሰጥ መድኃኒት ለማግኘት እየተመራመረ/ እየሠራ እንደሆነ ይሰማል፡፡ ባንፃሩም በባህላዊ ሕክምናውም ረገድ በየአገራቱ ያሉ የባህላዊ መድኃኒት ዐዋቂዎች ሀገር-በቀል መፍትሄ የሚሉትን ከምክር ጋር እየጠቆሙ ይገኛሉ፡፡ ዘመናዊውም ሆነ ባህላዊው ሕክምና ጥናትና ሥርዓትን ተከትለው መፍትሄ ለማግኘት የሚያደርጉት ሙከራ የሚበረታታ ነው፡፡ በዚህ መልኩ የሚገኘውን ፈውስ ነው ፈውስ ሥጋዊ የምለው፡፡ 

በሌላ በኩል ባለፉት 30 የሚጠጉ ዓመታት አገራችን ላይ የሠለጠነው የዘረኛነት አገዛዝ ያደረሰብን ማኅበራዊና የግብረገብነት ድቀት (social and moral decadence) እንደተጠበቀ ሆኖ፣ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሃይማኖተኛ ነው፡፡ አብዛኛው ሕዝባችን የክርስትና ወይም የእስልምና እምነቶች ተከታይ ነው፡፡ ነዋሪነቱም አብዛኛው በገጠር ነው፡፡ ዘመናዊው ሕክምና በነዚህ አካባቢዎች ባለመስፋፋቱ፣ በዐቅም ውሱንነት፣ እና ሕዝቡ ለእምነቱ በሚሰጠው ከፍተኛ ዋጋ የተነሳ አብዛኛው የሕብረተሰባችን ክፍል በባህላዊው ሕክምና እና በቤተ እምነቶች በሚያገኘው ፈውስ ላይ የበለጠ መተማመን እንዳለው ይስተዋላል፡፡ 

በዚህ ረገድ ጥንታዊቷና ታሪካዊቷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ያላት ሀብት፣ ላገር ያደረገችውና አሁንም እያደረገች ያለችው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑ ከእምነቱ ተከታዮችም ውጭ በእጅጉ የታወቀና የተመሠከረ ነው፡፡ ለባህላዊው ሕክምና ዋና መሠረት ከመሆኗ በተጨማሪ ባንድ ወቅት ያገራችንን የሕዝብ ጤና ጥበቃ ሥራ የምትመራ ተቋም ነበረች፡፡ ቤተክርስቲያኒቱ ለምትሰጠው መንፈሳዊ ፈውስ መሠረቱ ቅዱሳት መጻሕፍት ሲሆኑ በሥጋወደሙ፣ በጸሎት፣ በጠበል (ማየ ፈውስ/ሕይወት)፣ በእመት፣ በልዩ ልዩ መንፈሳዊ ሥርዓቶች የሚገለጽ መንፈሳዊ ሕክምና ነው፡፡ መንፈሳዊው ፈውስ በዘመናዊውና በባህላዊው ሕክምና እንደሚገኘው ፈውስ በሥጋ የሚታዩ ግዙፍ ደዌያትን ብቻ ሳይሆን የማይጨበጠውን/የማይዳሰሰውን ረቂቁን የኀጢት፣ የአእምሮና የነፍስ ደዌያትን የሚያድን ፈውስ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍት መንፈሳዊ ፈውስን በሚመለከት በበርካታ ታሪኮችና ምሳሌዎች የተሞሉ ቢሆንም የዚህ ጽሑፍ ዓላማ እነዚህን ለመዘርዘርና ለመተንተን አይደለም፡፡ 

ለዚህ አስተያየት መነሻ የሆነኝ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽን አስመልክቶ የዐቢይ አገዛዝ የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ እንዲያውጅ አቶ ያሬድ ኃይለማርያም ያቀረበው ጽሑፍ ነው፡፡ የዚህ አስተያየት አቅራቢም ለሕዝብ ጤንነት ብሔራዊ አደጋ የሆነውን ወረርሽኝ አስመልክቶ የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ ማወጁ ዘግይቷል ከሚባል በቀር እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ያምንበታል፡፡ ያለንን ዐቅምና ዝግጁነት ከግምት በማስገባት አደጋው ከመስፋቱ በፊት ብዙ ወገኖችን ከወዲሁ መታደግ እንደሚያስችል ይታመናል፡፡ እንደ አሜባ ቅርፁን የሚቀያይረው ኢሕአዴግ የተባለው አገዛዝ ለብሔራዊ ደኅንነት አስቦ ሳይሆን ሥልጣኔ አደጋ ላይ ነው ብሎ ሲያስብ ‹ምዉት ሸንጎውን› ተጠቅሞ በዜጎች ላይ በደል ለመፈጸም በተደጋጋሚ የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ ማወጁን እናስታውሳለን፡፡ ጸሐፊው በዚህ ረገድ ያነሳውና አገዛዙን የተቸበት መንገድ ተገቢ ቢሆንም ይህንን ጥሪ አስታኮ ከፈውስ መንፈሳዊ አገልግሎቶች አንዱ የሆነውን የማዕጠንት አገልግሎት በሚመለከት የማቃለል በሚመስልና እንዳይደረግም ጥሪ ያደረገበት የጽሑፉን ክፍል ግን አጥብቆ እቃወማለሁ፡፡ በሳይንሳዊው መንገድ የተገለጹትን ጥንቃቄዎች ተግባራዊ ማድረግ የሚደገፍና አንድ ጉዳይ ሆኖ ሳለ፣ ለሕዝብና ላገር በሙሉ የሚደረገውን የማዕጠንት ጸሎት መቅረት አለበት፤ አገዛዙም የሃይማኖት አባቶችን ሳያማክር ርምጃ መውሰድ አለበት ማለት (ሃሳቡ ከቅንነት የመነጨ ቢሆን እንኳን) የእምነቱ ተከታይ ለሆነም ሆነ ላልሆነ ሰው እላፊ ንግግር፣ ነውርና መተላለፍ የሌለበትን ድንበር መሻገር ይመስለኛል፡፡  ሥርዓቱ ሲፈጸም አስፈላጊው የጥንቃቄ ርምጃ ይደረግ የሚለው ተገቢ ነው፡፡ ምእመናን በማይገኙበት በካህናቱ ብቻ እንዲፈጸም ማድረጉም የጥንቃቄው አንድ አካል መሆን ይኖርበታል፡፡ አገልግሎቱ የሚያስፈልገው እኮ እንዲህ ዓይነቱ ቸነፈር ሲከሠት ነው፡፡ በርእሰ መጻሕፍቱ እንደተመዘገበው ሥርዓቱን የሠራው ባለቤቱ ልዑል እግዚአብሔር ሆኖ ሳለ፣ ሥርዓቱን መፈጸም በየትኛው መመዘኛ ነው እርሱን መፈታተን የሚሆነው? እናስተውል እንጂ! ዘመናዊው/ሥጋዊው ሕክምና ያለ ሕክምና ዐዋቂዎቹ እንደማይታሰብ ሁሉ፣ መንፈሳዊውም ሕክምና የእግዚአብሔር አገልጋይ/እንደራሴ ከሆኑት ካህናት ውጭ የማይታሰብ ነው፡፡ ቢያንስ በተዋሕዶ እምነትና ሥርዓት መሠረት፡፡

ወረርሹን ለመከላከል ብሎም ለማጥፋት በሳይንሱም ሆነ በእምነቱ የሚደረገው እንቅስቃሴ የመጨረሻ ዓላማ የሰውን ሕይወት ለመታደግ መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡ ዋናው ቁም ነገር ባህላዊውም ሕክምና በባለሙያዎች የታገዘ መሆን ይኖርበታል፡፡ በየስርቻው የሚወራውን እንቶ ፈንቶ እየሰሙ በሕዝብ መከራ ሊያተረፉ ያሰፈሰፉ ነውረኛ ‹ነጋዴዎች› ሰለባ መሆን የለብንም፡፡ በእምነትም ረገድ የሚፈጸመውን ሥርዓት ከጥንቃቄ ርምጃዎች ጋር ጎን ለጎን ማከናወኑ በአካል ከሚታየው ሕማም አልፎ በኅብረተሰቡ በተለይም በአማኞች ዘንድ የሚኖረውን ሥጋትና ጭንቀትንም በመፈወስ በኩል ኃይል እንዳለው ይታመናል፡፡ ሁሉንም ዓይነት መፍትሄዎች አቀናጅቶ ማስኬዱ ለእኛ ኅብረተሰብ የምርጫ ጉዳይ አይመስለኝም፡፡ 

ከዚህ የወጣውና በእምነት የሚፈጸምን የፈውስ ሥርዓት አቁሙ ማለት ግን የስንፍና ንግግር ይመስላል፡፡ 

ጽሑፌን የምቋጨው ወንድሜ ዲ/ን ዳንኤል ‹እምነትና ጥንቃቄ› በሚል ርእስ ካቀረበው ጽሑፍ ውስጥ ለዚህ አስተያየት አግባብነት ያለውንና እኔም የምጋራውን ሃሳብ በመጥቀስ ይሆናል፡፡ ‹‹እምነትና ጥንቃቄ የሚግባቡ እንጂ የሚወዛገቡ አይደሉም፡፡ … የምንወስደው የጥንቃቄ ርምጃም እምነትን የሚያጠፋ መሆን የለበትም፡፡›› 

 

እግዚአብሔር አምላክ መዓቱን በምሕረቱ ቀጣውን በትዕግሥቱ ያርቅልን፡፡

Filed in: Amharic