>

ጠባቂ ብቻ ሳይሆን ሠጪም ሆነን እናውቃለን!!! (ስንታየሁ ሀይሉ)

ጠባቂ ብቻ ሳይሆን ሠጪም ሆነን እናውቃለን!!!

ስንታየሁ ሀይሉ
 
<< በፕሮፌሰር አክሊሉ ለማ የተሠየመው “ለማቶክሲንን (Lemmatoxin)” መድሀኒት ለዓለም ህዝብ በማቅረብ ለሚሊዮኖች ስቃይ መድሀኒት ሆነናል።
 
• ለህክምና ምርምር በዓለም ከሚፈለጉ 8ሺ እፅዋቶች ከ7ሺህ ያላነሱ እፅዋቶች በሀገራችን ይገኛሉ
• ዘመናዊ ህክምና ከመዳረሱ በፊትም ሆነ አሁን ድረስ በባህል ህክምናና መድሀኒት ብዙዎች ተፈውሰዋል።
ጃፓን፣ እስራኤል፣ አሜሪካና ፈረንሳይ የኮሮና ቫይረስ መከላከያና ክትባትን ሞክረው ባይሳካላቸውም እየጣሩ ነው። ዛሬ በሀገራችን የተሠማው ተስፋ ሰጪ የምርምር ውጤት ነገ ላይ ቢሳካም ባይሳካም የሚበረታታ ተግባር እንጂ የሚተች ነገር የለውም።
ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በመላው አለም ላይ በብልሀርዚያ በሽታ ይሰቃዩ ለነበሩ ከ200 ሚልየን በላይ ዜጎች ስቃይ መፍትሄ የሆኑና መድሀኒትን ያገኙት ኢትዮጵያዊ ሳይንቲስት የፕ/ር አክሊሉ ለማ ሀገር ነች።
《ለማቶክሲን (Lemmatoxin)》በማለት በስማቸው መድሀኒቱ የተሠየመላቸው ፕሮፌሰር አክሊሉ የቢልሃርዚያን መድሀኒት ለማግኘት ምርምር በሚያደርጉበት ወቅት እውቅናቸውን ለመንጠቅ የተለያየ ሀገራት ጥረትና የማጣጣል ሙከራ ቢያደርጉም የምርምር ስራቸው ለብዙ ሚሊዮኖች ስቃይ መድሀኒት መሆናቸው አይዘነጋም።
ዛሬም የኮሮኖ ቫይረስን ለማከም የሚያስችል ሀገር በቀል እውቀትን በሳይንሱ በማገዝ ተስፋ ያለው ግኝት እንዲሆነ ለኢትዮጵያዊ ተመራማሪዎች ከልብ የመነጨ ምኞት ጋር ድጋፌን እገልፃለው።
የባህል መድሀኒት ምርምር ውጤታማ መሆንኑን በቻይናውያንም ሆነ በሌሎች ሀገራት እንዲሁም በሀገራችን የኃላ ታሪክ ማስታወስና መገንዘብ ያስፈልጋል።
ጤና ጥበቃ ምኒስትርም ለዘርፉ ተገቢውን ትኩረትና ክብር በመስጠት በኦፊሻል ገጹ እንዲሁም በመገናኛ ብዙሀን ይህን መግለጫ አውጥቷል:-
ባህላዊ ህክምናን እና ሳይንሳዊ ምርምርን በማጣመር ከእጽዋት የኮሮና ቫይረስ መድሀኒት ለማግኘት ባለሙያዎች እያደረጉ ያለው ሙከራ የመጀመሪያ የቤተ ሙከራ ሂደትያለፈ ሲሆን ወደቀጣይ የምርምር ሂደቶች እንዲሸጋር የኢትዮጵያ መንግስት ድጋፍ ለማድረግ የጤና ሚንስቴር እና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚንስቴር ተፈራርመዋል።
ምርምሩ በመድሀኒት ግኝት ሂደት መመሪያ መሰረት ብዙ ወሳኝ የምርምር ሂደቶች የሚቀሩትና ጊዜ የሚወስድ ሲሆን በቀጣይ በሚደረጉ የእንስሳትና የክሊኒካል ምርምሮች በዓለም አቀፍ እና አገር በቀል ባለሙያዎች ጥምረት የሚካሄድ  ይሆናል።
ይሄ እንቅስቃሴም ሌሎች አገራትም ለበሽታው ክትባትና መድሀኒት ለማግኘት  በአለም አቀፍ ደረጃ ለሚደርገው የምርምር ጥረት አንዱ አካል መሆኑን እያስገነዘብን በአሁኑ ወቅት ያለው ብቸኛ አማራጭ በሽታውን ለመከላከል በመንግስት እና በጤና ሚኒስቴር እየተወሰዱ ያሉትን እርምጃዎችን እና የተሰጡ የጤና ምክሮችን መተግበር መሆኑን ለማሳሰብ እወዳለሁ ።
ሀገራችንን ከክፉ ሁሉ ይጠብቅልን
Filed in: Amharic