>
5:13 pm - Friday April 19, 1297

ድብትርና ደብተራ ወደ ትክክለኛው ትርጉም ስንገባ ከደብተራው ልሳን እነሆ...!!! (አማን ነጸረ)

ድብትርና ደብተራ ወደ ትክክለኛው ትርጉም ስንገባ ከደብተራው ልሳን እነሆ…!!!

 

 

አማን ነጸረ
ደብተራ :-
ይህቺ ጽሁፍ በጨዋ ቋንቋ ልትሞነጫጨር ከተወጠነ በኋላ በደብተራ ላይ የሚሰነዘሩ ጽርፈቶች አብሾአችንን በማስነሳታቸው ያልተገቡ ቃላት ተጨማምረዋል! አሹ! እሰይ! የቃሉ ትርጕም፣ በኪነ ጥበብ፣ በተረት፣ በድርሰት፣ በአብዮት፣ በየሃይማኖቱና በብሔር ፣ … የቀረበበት ዐውድ ከኃይለ ቃል ጋራ ይዳሰሳል፡፡
የደብተራ ትርጓሜ በመዛግበተ ቃላት ወጥበባት
ደስታ ተክለ ወልድ በመዝገበ ቃላቸው፡-
  ‹‹ደብተራ – ድንኳን፡፡ ደበተረ – ደብተር ዘረጋ፣ ጻፈ፣ ከተበ ፡፡ ተደበተረ – ተዘረጋ፡፡ ደብተራ – የድንኳን ስም፡፡ ደብተራ – ዜማ. ቅኔ፣ ሳታት (ሰዓታት) የሚያውቅ፣ በደብተራ (በድንኳን) ውስጥ የሚመራ፣ የሚቀኝ፣ የሚዘምር፣ መንፈሳዊ አገልጋይ፣ ካህን፣ አወዳሽ ሳታት ቋሚ፡፡ ደብቴ – ከፊለ ስም ወይም ቁልምጫ፣ የደብተራ ወገን፣ የኔ ደብተራ ማለት ነው፡፡›› ይሉናል፡፡
ግእዙም፡- 
 ‹‹ደብተረ› ማለትን በአወራረዱ ሕግ በተንበለ ቤት አስገብቶ ሲያበቃ ‹‹ተከለ›› ሲል ይተረጕምና ለድንኳን ይሰጠዋል፡፡
ግእዝ ድንኳን ለሚለው ቃል ከደብተራ በተጨማሪ ኀይመትና ደበና ማለትን ይጠቀማል፡፡ ደበና የንጉሥ ድንኳን የሚጠራበት ስም ነው፡፡ ደበናንሳ (ባለእጅ) የሚለው ቃል ከዚህ ስም ጋራ ስለመያያዝ አለመያያዙ አላውቅም!
የፕ/ር ሥርግው አማርኛ የቤ/ክ መዝገበ ቃላት፡- ‹‹ደብተራ የቃሉ ቀጥተኛ ትርጕም ድንኳን ማለት ነው፡፡ ግን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በቅኔ ማኅሌት የያሬድን ዜማ የሚዘምር፣ የሚመረግድ እንዲሁም ቅኔን የሚቀኝ ደብተራ ይባላል፡፡›› ብሎናል፡፡
በኢንሳይክሎፒዲያ ኢትዮፒካ፡- 
ደብተራ የሚለው ቃል እንደ ወረደ ከግሪክ የተቀዳ ሲሆን ትርጓሜውም እንደ ድንኳን የሚያገለግል ውጥር ቆዳ /ሌዘር/ ማለት እንደሆነ  ተገልጧል፡፡ ደባትርን በቤ/ክ ካሉ ምሁራን ሁሉ ለይቼ the most educated clerics ያልኳቸው እኔ አይደለሁም፤ እንደነ ደንጎለጥ አንጠልጥሎ ሳይሆን አንጠርጥሮ የተረዳቸው ፈረንጅ ነው፡፡ በቤ/ክ የውስጥ አገልግሎት የቅዳሴና ውዳሴ ይባላል፡፡ የውዳሴው ድርሻ የደባትር ነው፡፡ የሚያወድሱት አምላካቸውን ነው፡፡ ውዳሴ የሃይማኖት አገልግሎት ስለሆነ በመደበኛ ፍ/ቤት እንኳ አይዳኝም፤ በመንፈሳዊ ፍ/ቤት ብቻ ነው! እኒያ እግራቸው እስኪቀበተት ቆመው የሚያነጉ አገልጋይ ምሁራን ከውጪ በድውያን መጽልማነ ስም ስማቸው ተቀረደደ፤ በውስጥም ቤተ ክርስቲያንን እየጋጡ በሰቡና በረቡ አምስት ከለባት ተዘነጠሉ እንጂ አገልግሎታቸውስ ‹‹ስቡሕ ወውዱስ ዘሣረረ ኵሎ ዓለመ – ዓለምን የፈጠረ (እርሱ) ፈጽሞ የተመሰገነ ነው›› እያሉ ማወደስ ነበር፡፡ እነርሱ ቢጽፉ ጠንቋይ፣ ቢያሸበሽቡ ደናሽ፣ በፈሊጥ ቢናገሩ ቃላቸው ‹‹ቃለ ደብተራ››፣ ቢቀኙ ሰዓት ገዳይና ምዕመን አሰልቺ፣ ሕክምና ባልነበረበት ጊዜ ቁስል በቅጠል ቢያደርቁ ‹‹ሥር ማሽ ቅጠል በጣሽ›› ተባሉ እንጂ የሙሉ ሰዓት አገልግሎታቸውስ ውዳሴ አምላክ ነበር፡፡ ሙያዎች ሁሉ በተከበሩበት፣ የሃይማኖት ነጻነት በታወጀበት፣ የቡድን መብቶች ሁሉ ልዕልና አግኝተዋል በተባለበት ዘመን እነሆ ‹‹ደብተራ›› የወግ ማሳመሪያ ሆነ፡፡
ልዩ ልዩ ሕዝባዊ ትርጕም፡-
ደብተራ – ተማሪ፣ መምህር ያልሆነ አዲስ ምሩቅ፣ ቄስም መነኩሴም ወይም ዲያቆን ያልሆነ፣ ሥልጣነ ክህነት የሌለው፣ ያፈረሰ፣ የድብትርና መሬት የያዘ፣ ጸሀፊ፣ መድኃኒት ዐዋቂ፣ ጥፈት የሚጥፍ … ደግነቱ ሁሉም መማሩን አይክዱበትም፡፡ ‹‹ቃለ ደብተራ›› የተባለ እንደሁ የአሽሙርና የኵሸት ማበረታቻ (ወደ ተንኮል የሚገፋ) ንግግር ነው፡፡ ‹‹ዕፀ ደብተራ›› የምትባል የኵሸት ዕፅ አለች፤ ቀጠጥናም ትባላለች፡፡
መንፈሳዊ ተምሳሌት፡-
እመቤታችን፣ መስቀል፣ የጌታ ሥጋ፣ ቤተ መቅደስ ሁሉም ደብተራ ይባላሉ፡፡ ቅጽል ከፊቱ እየገባና እየተዛረፈ ‹‹ደብተራ ብርሃን፣ ደብተራ ፍጽምት፣ …›› ይዜማል፤ ይመሰጠራል፡፡ ሐዋርያው በዕብራውያን 9 እና 10 ነገረ ድኅነትን ይተርክበታል፤ ሐዲስን ከብሉይ ያነጻጽርበታል – ደብተራን፡፡
ትርጕሙ ሲጠቃለል፡-
 ደብተራ ማለት በመደበኛ ትርጓሜው ማኅሌታዊ ማለት ነው፡፡ መዓርጉ ‹‹ተማሪ›› የመባል ያህል ይመስላል፤ ከማንም አይሰጥም፤ ግን ደግሞ ለማንም አይሰጥም፡፡ ዜማ፣ ቅኔና አቋቋም መሞካከርን ይጠይቃል፡፡ በመርህ ደረጃ መነኮሳት ደብተራ አይባሉም፡፡ በዚህ ረገድ ዲ/ዳንኤል ክብረት አባ ባሕርይን በደብተራ መዓርግ መተንተኑ ጥያቄ ሳያስነሳ አይቀርም፡፡
አብዮታውያን ደባትር:-
የኅሩይን ዲፕሎማሲ ቆፍጣናነት፣ የመርስዔ ኀዘንን የማይነጥፍ ትሁት ብዕር፣ የዮፍታሔን እልህና ፀፀት የተቀላቀለበት የሀገር ፍቅር፣ የታከለ ወልደ ሐዋርያትን ዙፋን ነቅናቄ ጀግንነትና ለውጥ ናፋቂነት ያላስተዋለ የብሔር ሞራ ዐይኑን የጋረደው ወለፈንዴ ሁላ ደርሶ ‹‹ደብተራ …›› እያለ ሲለፋደድ ያስነጥሰኛል! ክላ! በየጠርሙሱ ገብቶ የሚቅጨለጨል ቃጭል ራስ ሁላ የኢህአፓው ብርሃነ መስቀል ረዳ ስማቸውን በትግሉ ወራት ለአባት መጠሪያነት የመረጠው ፊታውራሪ ታከለ የእንጦጦ ራጉኤል ደብተራ የነበሩ ስለመሆናቸው እንኳ ከBahru Zewde, Pioneers of Change in Ethiopia, 73-74 ሳያጣራ ‹‹ደብተራ …!›› ኧግ እልም ያርግህ! ክላ! ታጥቦ እማይጠራ የዘመን እድፍ! የራጉኤሉ ደብተራ የደብተራ ልጅ ብርሃኑ ድንቄ ከቀኃሥ ሲላተም፣ አበየ – አምቢ አለ ማለትን ሲተረጕም፣ አብዮት (እምቢታ) ሲፈጥር አንተ የት ነበርክ! ተራኪነትና ጠራቂነት የተምታታበት ሁላ!
ደብተራ በተረት:-
ደብተራ የዘኬ ጎተራ፡፡
ደብተራ የዘኬ ጎተራ፣ ዘኬውን ሲቋጥር፣ አነቀው ነብር፡፡
ደብተራና ተማሪ ሰናፊልና ሱሪ፡፡
ደብተራ ሲኮራ እቤተ ክርስቲያን ገብቶ ጭራ የይዛል፡፡
ለደብተራ መቋሚያና ጭራ
አይጥፍ ደብተራ ክንፍ የሌለው አሞራ፡፡
ደብተራ በዘፈን:-
አየሺወይ ደብተራ፣
ቅኔ ሲመራ፡፡
በል እርገጥ እርገጥ እርገጥ ዳንኪራ፣
እንደ ቄሱ ልጅ እንደ ደብተራ፡፡
ተማሪ ቆሞለት ይበላል ደብተራ፣
ትልቅ ሲወድቅ ነው የትንሽ ወግ ተራ፡፡
ደብተራና ድርሰት:-
አዳም ረታን ሞቱን ሡራፊ የሞተ ዕለት ያድርግለት፤ ሞቱን ቅዱስ ገብርኤል የሞተ ዕለት ያድርገው! ይችላላ! እሱ እንዲህ ይላል፡- ‹‹ከመካከለኛው ዘመን ጀምሮ የእኛ ብቻ ሳይሆን የምዕራብ አውሮጳም ታሪክ የተጻፈው በደብተራዎች ነው፡፡ ቄስ ወይ ደብተራ ያልነካው የታሪክ መጽሐፍ የለም፡፡ ታሪካችንን ማጣጣል የፈለጉ ማርከሻ ሲያጡ ይሄ የደብተራ ታሪክ ነው ብለው ያሽሟጥጣሉ፡፡ (ከቴም … ተሸሟጠጠ!) ፡፡ በልቦናቸው ቢፈሩትም … የውሸት ይንቁታል፣ በአድማ ያጣጥሉታል፡፡ በተቃራኒው የባዕድ ደብተራ … የጻፈውን ግን ያምኑታል፡፡ … ቀሽም ቢሆን እንኳ እንደ ደብተራ አይቆጠርም፡፡ ቢዋሽ እንዲዋሽ አይደረግም፡፡››
 ህም! እነ ሳሙኤል ጎባት፣ ኢዘንበርግ፣ ክራፕፍ፣ ጉሊሊሞ ማስያስ፣… ሲጽፉ ሁሉም እምብጥ እምብጥ! የነጄምስ ብሩስ፣ ቼሩሊ፣ ዲ.አባዲ፣ ኢግናዚዮ ጕይዲ፣ … ሲሆን ሁሉም ዘንበጥ ዘንበጥ! As the well known writer state it ጳራራም ፓራራም! ቲሽ! ልሳነ ደብተራ በልሳነ አፍርንጅ ስለተገለበጠ ብቻ ማፋደስ ማፋቸል … ኡፍፍፍ ያናድዳል! በዚህ ላይ የታላቁ ሰው ግጥም በላያችን ሲወርድ እግዚኦ፡-
የግፉዐንን ግፍ ለመተረክ ደብተራ ላይ መቀኘት:- 
ጋሽ ጸጋዬ ገብረ መድኅን ይገጥማል! በቃ እርሱ ግጥም ይችላል! ደባትርን ግን የግፉዐንን ልብ የሚልሱ ባለሹል ምላሶች አድርጎ እንዲህ ይሥላልል – ማነህ? በሚለው ግጥሙ ላይ፡-
ማነህ?
ቆለኛ ሸክላ ሠሪ ነህ፣
ያገር ዕድል ያገለለህ፡፡
ለጥበብህ እንደ መካስ፣
በደባትር ትንታግ ምላስ፣
ዘለዓለም ልብህ የሚላስ፡፡
ዲስኩር በደባትር ላይ:-
ፕሮፍ መስፍን ትልቅ ሰው ናቸው፡፡ አንድ ወቅት ከዲ/ዳንኤል ጋራ ቢጎናነጡ ጉዳያቸውን እንደ ግለሰብ ከእርሱ ጋራ ብቻ ማድረግ ሲችሉ ዳንኤልን እንደ ደባትር ወኪል ወሰዱና መላውን ስመ ደባትር ለማነወር ናዳ ለቀቁብን! ኦሪታችን ‹‹አክብር ገጸ አረጋዊ›› ባትል ኖሮ ነገራቸውስ የሚያናግር ነበር፡፡ በምዕራቡ ዓለም የመኖራቸውን ያህል በማቴሪያሊዝም ሳይተዳደፉ ዝቅ ብለው የትውልድ አገናኝ ለመሆን ሲጥሩ የማያቸው ዶ/ር ዳኛቸው ‹‹ህግ መንግሥቱ የደብተራ መጽሐፍ ያህል ክብር የለውም!›› ብለው እርፍ! ህም! ደብተራ ጽሁፉን እንዴት እንደሚጽፍ፣ የጻፈውን እንዴት እንደሚደጉስ፣ የደጎሰውን እንዴት በሱቲ እንደሚሸፍን፣ በሱቲ የሸፈነውን እንዴት ማኅደር እንደሚሠራለት፣ ማኅደር የሠራለትን ጽሁፍ ሲያወጣና ሲያስገባ እንዴት በጥንቃቄ እንደሚይዝ፣ ሲያነብ ምራቅ ነጥቦ ጽሁፉን እንዳያበላሽና የእጁ ላብ እንዳያደበዝዝበት ስለሚያደርገው ጥንቃቄ ያላጤነ ሰው … ህም! ‹‹ሕገ መንግሥቱ የደብተራ መጽሐፍ ያህል ክብር የለውም›› የሚል ጸያፍ ማንጸሪያ ይደረድራል! ደብተራ አስቦ ለጻፋት ጽሁፍ ያለውን ክብር ሰፊው ሕዝብ ታስቦ የሚጻፍ ሕገ መንግሥትና ለዚሁ ሕገ መንግሥት ሁለንተናዊ ክብር ቢኖረው የትናየት በደረስን! ነገሩ ደባትርን ካለማወቅ ነው!
ድብትርና ከሃይማኖትና ብሔር አንጻር:-
ድብትርናን ከኦርቶዶክሳዊነት ብቻ ቀላቅለህ ካየህ ለሚሲዮናውያውን ያደሩትን፡- ደብተራ ተክለ መድኅን፣ ደብተራ አሰጋኸኝ፣ ደብተራ ዘነብ፣ እነ አለቃ ታየ፣ ከጸጐችም እነ አለቃ ክፍለ ጊዮርጊስን፣ ዐፅሜን ታሪክ ተዘከር፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ ከመካከለኛው ዘመን ጀምሮ ደባትር በመሬት ሥሪት ውስጥ እንደ አንድ መደብ ይታዩ ነበር፤ መደብ የሚለውን የማ/ሰብ ክፍል አድርገህ እየው! ምነው ለፕሪጁዲስ ያንጦለጡልሀልሳ! ጦላጧላ! ደብትርና ከነዜማው በፈላሾችም ዘነድ የታወቀ ስለመሆኑ Kay Kaufman Shelemay የተባሉ ሊቅ  Zema: A concept of Sacred Music in Ethiopia በሚል ርእስ የጻፏትን መጣጥፍ አስሰህ አንብብ! መቼም ፈረንጅ ካልመሰከርልን ሰው አንሆንም! ያስቃል እኮ!
ድብትርናን የአንድ ብሔር አፋዳሽ ጸሀፍት ጥርቅም ለማድረግ የሚደረገው እሽኮለሌና መንደቅደቅ ያስቃል እኮ! በታሪካችን ታላቋ ሥፍራ በደብረ ጽዮን በርእሰ አድባራት አክሱም ጽዮን የድብትርና ሥርዓት ያልነበረ ይመስል ድንገቴዎች ፉፉዜላውን ወደ አንድ መንደር ሲነፉት አቅለ ቀላል ከተገኘ ያርዳል እኮ! ንሳማ ከመጽሐፈ አክሱም፡- ‹‹ንሕነ፡ ሐደስነ፡ ወሠራዕነ፡ ወወሰነ፡ ወአውገዝነ፡ ከመ፡ ኢየሠየም፡ መኑሂ፡ እምባዕዳን፡ መኳንንት፡ ኀበ፡ ገበዘ፡ አክሱም፡ ቤተ፡ መንግሥትነ፡ ዘእንበለ፡ ሰብአ፡ ርስት፡ ዘተወልዱ፡ ውስቴታ፡፡ ወደብተራ፡ እሙራን፡ እምሰብአ፡ ቤታ፡፡ እመሂ፡ እምሰብአ፡ ሲሬ፡ ወሰራዌ፡ አው፡ ዘተንቤን፡ ወአጋሜ፡ ወበኵሉ፡ ምድረ፡ ትግሬ፡ ወአምሐራ፡ ወካልዓን፡ መካናተ፡ ንጉሥ፡ አመ፡ መጽኡ፡ ሊቃውንት፡ ወደብተራ፡ ዘሀለዉ፡ በበመዓርጊሆሙ፡ ከመ፡ ኢይሰየሙ፡ ሠራዕነ፡ ወሐደስነ፡ ወአዖድነ፡ ግዘተ፡፡›› አክሱም ላይ በድብትርና ርስት ለመተከል አክሱማዊ መሆን አለብህ! ኤጭ! አታካብደው! መርጡለ ማርያምም ብትመጣ ተመሳሳይ ታሪክ ትሰማለህ! ከቦታዎቹ ጥንታውያን መሆን ጋራ በተገናኘ ተቆርቋሪነትን ከተወላጅነት ጋራ አያይዞ ከማየት የተነሣ ነው! ሲጀመር ርእሱም እርሱ አይደለም! ድብትርና የአንድ ብሔር …! ኧህ! የምን መሸፋፈን! የአማራ ጸሀፍት መጠሪያ ብቻ መስሎህ አትሟዘዝ ለማለት ነው! ክላ! ስታካብድ፣ ስታዘጠዝጥ፣ አሙቁልኝ እሽኮለሌ፣ … መጫወት አምሮህ ዘመን አናውዞህ እንጂ የትግራይና አማራ ሥነ ጽሁፍና ማኅበራዊ ኑሮን በምንታዌ ለመተረክ መሞከር ንስጥሮሳዊነት መሆኑ ጠፍቶህ አይደለም! የትግራይን ታሪክ ከማዕከል በተቃርኖ ለመተረክ ብትዘምት አድማስህ ደብተራ ፍስሐ ጊዮርጊስ ናቸው! እዚህም እዚያም አለን ለማለት ያህል ነው! ሸዋ ብትመጣ የደብተራ ደስታ ነገዎ (ኋላ አለቃ) እና የጎኀ ጽዮኑ ደብተራ ገብረ ኢየሱስ ደበሌ (ኋላ አለቃ) ታሪክ አይፋታህም፡፡ ሰማህ ወይ?! ዘመን በታሪክ ኑፋቄ አሳድፎህ  በየወንዝህ መጻጕዕ የሆንክ ሆይ! እግዜር ይማርህ! ወይ ይዞህ ይሂድ!
ደብተራ በአወደልዳይ አጥማቂዎችቻችንና ፓስተሮቹ እንዲሁም ማሊያ በቀየሩት:-
በዚህ ዘመን የደብተራን ስም ሸቅጦ እንጀራ የሚያበስለው ከደባትር እጥፍ እጥፍ የትናየት … ሆኗል፡፡ ይሄ ‹‹ምቀኛ አለህ›› ሲባል የሚያረበርብ ድንጉጥ ማ/ሰብእ ሁሉ የአወደልዳይ ንግርት፣ የደንጎለጥ ትንቢት፣ የቀደመ ማንነቱን ጠቅልሎ ካልሸጠ ያመነ የማይመስለውን ተሐድሶ ነኝ ባይ አሙቁልኝ ተረክ ተቀብሎ በየቦታው በደባትር ላይ እሽክም! እሽክም! ደብተራው ግን ይመልሳል፡-
•ጠያቂ፡- ስለ እነዚህ ሰዎች ሐሜት ምን ትላለህ
•ደብተራ፡- ለአህያ ፈስ አፍንጫ አይያዝም፡፡
•ጠያቂ፡- እህ! ተው እንጂ! አትሳደብ! እነሱኮ እግር አንስተው መንፈስ የሚያስወጡ ናቸው!
•ደብተራ፡- ባክህ አታስቀኝ! እግር በማንሳት ፈስ እንጂ መንፈስ ሲወጣ አላየንም!
Filed in: Amharic