>

የአንችም (ደብረ ዘቢጥ) ጦርነት 90ኛ ዓመት መታሰቢያ (ልኡል አምደጽዮን ሠርጸድንግል)

የአንችም (ደብረ ዘቢጥ) ጦርነት 90ኛ ዓመት መታሰቢያ

 

 

ልኡል አምደጽዮን ሠርጸድንግል
የአልጋ ወራሽ ራስ ተፈሪ መኮንን የንጉሰ ነገሥትነት መንገድን የጠረገው/ያመቻቸው/ና ራስ ተፈሪከተቀናቃኞቻቸው ጋር ካደረጓቸው ታላላቅ ጦርነቶች መካከል የመጨረሻው ውጊያ የነበረው የአንችም (ደብረ ዘቢጥ) ጦርነት የተካሄደው ከዛሬ ዓመታት በፊት (መጋቢት 22 ቀን 1922 ዓ.ም) ነበር፡፡
መስከረም 17 ቀን 1909 ዓ.ም፣ ልጅ ኢያሱ ሚካኤል ከስልጣን ሲሻሩ ዘውዲቱ ምኒልክ ንግሥት፤ ተፈሪ መኮንን ደግሞ ታላቁን የሰለሞን ኒሻን ተሸልመው ‹‹ራስ›› ተባሉና አልጋ ወራሽ ሆነው ተሾሙ፡፡ የዘውዲቱ ባል ራስ ጉግሳ ወሌ ከቤተ-መንግሥቱ ገለል እንዲሉ ተደረገ፡፡
– – –
ልጅ ኢያሱ ከስልጣን ተሽረው ዘውዲቱና ተፈሪ ከተሾሙበት ጊዜ ጀምሮ ዘውዲቱ ሞተው ተፈሪ መኮንን ንጉሰ ነገሥት እስከሆኑበት ጊዜ ድረስ እጅግ ከፍተኛ የስልጣን ሽኩቻ የታየበት ወቅት ነበር፡፡ ተፈሪ መኮንን ተቀናቃኞቻቸውን በስውርም በግልፅም እያዳከሙ ለከፍተኛው ስልጣን እስከሚበቁበት ጊዜ ድረስ ከወሰዷቸው እርምጃዎች መካከል አብዛኞቹ የንግሥት ዘውዲቱን ስልጣን እየገዘገዙ የተፈሪን ስልጣን ደግሞ ያጎለበቱ ነበሩ፡፡ በዚህም ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ለከፍተኛ ስቃይና ብስጨት እንደተዳረጉ በታሪክ ላይ ሰፍሯል፡፡
– – –
ልዑል አልጋወራሽ ራስ ተፈሪ መኮንን ንጉስ ሚካኤል ዓሊን በሰገሌ ጦርነት፣ እነደጃዝማች አባውቃውንና ሌሎች የዘውዲቱ ደጋፊ መኳንንትን ሴራ በተሞላበት የጉልበትና የድርድር ዘዴ ካሸነፉ በኋላ አንድ ተቀናቃኝ ቀራቸው፤ ይህ ሰው የንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ምኒልክ የቀድሞ ባል ራስ ጉግሳ ወሌ ነበሩ፡፡ ራስ ጉግሳ ከቤተ-መንግሥት እንዲርቁ በመደረጋቸውና የባለቤታቸው የዘውዲቱ ምኒልክ ስልጣን በራስ ተፈሪና ደጋፊዎቻቸው እተገዘገዘ በመሄዱ በራስ ተፈሪ መኮንን ላይ ቂም ከቋጠሩ ውለው አድረዋል፡፡ የሁለቱ ወገኖች ልዩነትና ፀብም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ ሄደ፡፡
– – –
ራስ ጉግሳ ወረኢሉ መጥተው ከራስ ተፈሪ ጋር እንዲገናኙ ቢጠየቁም ‹‹አልመጣም!›› አሉ፡፡ በመንግሥት ላይ ያመፀውን የራያንና አዘቦን ሕዝብ እንዲያረጋጉና ፀጥ እንዲያሰኙ ቢታዘዙም ያመፀውን ሕዝብ ከጎናቸው አሰልፈው ለጦርነት ይዘጋጁ ጀመር፡፡ ከጦርነቱ በፊት እጅ እንዲሰጡ ቢጠየቁም ‹‹አሻፈረኝ!›› አሉ፡፡ ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ምኒልክም ‹‹እባክህ እሺ ብለህ ግባ፤ ከክፉ እንዳትወድቅ›› ብለው ደብዳቤ ቢጽፉላቸውም ‹‹እምቢ›› አሉ፡፡
– – –
ራስ ተፈሪም ለጦርነቱ በቂ ምክንያት አገኙና በጦር ሚኒስትሩ በራስ ሙሉጌታ ይገዙ የሚመራ ጦር ላኩባቸው፡፡ መጋቢት 22 ቀን 1922 ዓ.ም የአንቺም ጦርነት በጌምድር ውስጥ ተካሄደ፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የጦር አውሮፕላኖች ጥቅም ላይ ዋሉ፡፡ ራስ ጉግሳም የጨበጣ ውጊያ ላይ ሳሉ ጭንቅላታቸውን ተመትተው ሞቱ፡፡
– – –
ከእርሳቸው ሞት በኋላም ጦራቸው ውጊያውን ቢቀጥልም ሳይሳካለት ቀረ፡፡ በጦር አውሮፕላኖች የታገዘውና ከራስ ጉግሳ ጦር የተሻለ ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቀው የነራስ ተፈሪ ጦር ባለድል ሆነ፡፡ [‹‹ከእኛ ጎን ተሰልፈህ ራስ ጉግሳን ከወጋህ ስልጣን ታገኛለህ›› ተብለው ጉግሳን ወግተው የጠበቁት ስልጣን ያልተሰጣቸው ደጃዝማች አያሌው ብሩ ‹‹አያሌው ሞኙ፣ ሰው (?) አማኙ›› ተብሎ የተገጠመባቸውም በዚህ ወቅት ነው አሉ]
– – –
ራስ ተፈሪ ተቀናቃኞቻቸውን መንጥረው ጨረሱ፡፡ ዘውዲቱና ዘውዳቸው ብቻቸውን ቀሩ፡፡ ከጦርነቱ ሁለት ቀናት በኋላ (መጋቢት 24 ቀን 1922 ዓ.ም) ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡ ከሰባት ወራት የንግሥና ዝግጅት በኋላ አልጋወራሽ ራስ ተፈሪ መኮንን ‹‹ሞዓ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሥዩመ እግዚአብሔር ንጉሰ ነገሥት ዘኢትዮጵያ›› ተብለው የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገሥት ሆኑ፡፡
Filed in: Amharic