ውሱን ሀብትን አላግባብ መጠቀም
ከይኄይስ እውነቱ
የአገዛዞች አንዱ መለያ ባህርያቸው ለመደበኛ ሥራ ሁሉ ዘመቻ/ግርግር ይወዳሉ፡፡ ከዚህም የፖለቲካ ትርፍ ለማጋበስ ይፈልጋሉ፡፡ ሠርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ ዓይነት አሠራር፡፡ ብዙውን ጊዜ በሕግ ያቋቋሟቸውን መ/ቤቶች ተጠቅመው ሕዝብን ለማንቀሳቀስ ሲሠሩ አይታዩም፡፡ አንዳንዶቹ ተቋማትም ዐፅማቸውን ያሉ ሥጋ ያልለበሱ ናቸው፡፡
ቸነፈር (ወረርሽኝ) በዓለምም ሆነ ባገራችን ሲከሠት የመጀመሪያ አይደለም፡፡ መጠኑና ስፋቱ፣ ጊዜው፣ የሚከሠትበት ቦታ፣ ለአደጋው ተጋላጭ/ተጠቂ የሆነው ሕዝብ የዕድገት ደረጃ፣ የሚጠይቀው ዕውቀትና ሀብት ችግሩን ለማቃለል/ለመፍታት የበኩሉን ድርሻ ይኖረዋል፡፡
በዚህ ረገድ የጤናም ሆነ ሌሎች የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ ሲከሠቱ ከሚመለከታቸው የአገር ውስጥም ሆነ ዓለም አቀፍ ተቋማት እንዲሁም ሕዝብን በማስተባበር፣ አስፈላጊውን የሰው ኃይልና ሀብትን በማደራጀት (mobilize በማድረግ) አደጋን አስቀድሞ ለመከላከል እና ከተከሠተም በኋላ ለመቈጣጠር የሚያስችል የተደራጀ አሠራር ለመምራት የተቋቋሙ ተቋማት አሉ፡፡ በጤናው መስክ የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት (በተለምዶ ‹ፓስተር› እያልን የምንጠራው) እና ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አሉ፡፡ ባንፃሩም ጤናን ጨምሮ ማናቸውንም ዓይነት አደጋዎች በቅድሚያ ተዘጋጅቶ ለመከላከልና ሲከሠትም ለመቈጣጠር የሚያስችል ከደርግ ዘመን ጀምሮ ልመናን ተቋማዊ ያደረገ ‹የልመና ብሔራዊ› ተቋም ነበረን፡፡ አሁንም ስሙን ቀይሮ አለ፡፡ ይህ በየጊዜው የስም ተፋልሶ የገጠመው ተቋም የዕርዳታ ማስተባበሪያና ማቋቋሚያ ኮሚሽን፣ የብሔራዊ አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚሽን፣ አሁን ደግሞ ብሔራው የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ይባላል፡፡ ይህ ተቋም በሀገር አቀፍ ደረጃ የተፈጥሮም ይሁን ሰው ሠራሽ አደጋ ከማጋጠሙ በፊት ዐቅም የፈቀደውን ዝግጅት በማድረግ ሊደርስ የሚችለውን ጥፋትና ጉዳት ለመቀነስ የሚያስችል የተደራጀ አሠራር እንዲሠራ ታስቦ የተቋቋመ ነው፡፡ ተቋሙ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበርና በማስተባበር በመጠባበቂያነት ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን እና ለዚሁ ዓላማ የተመደበ ጥሬ ገንዘብ እንደሚይዝ በማቋቋሚያ ሕጉ ተመልክቷል፡፡ መሬት ላይ ያለውን ጽድቅ የምትጠይቁኝ ከሆነ በሕግና ተግባር መካከል ሁሌም የገደል ያህል ክፍተት ያለበት አገር ውስጥ ነን ያለነው፡፡
በጤናው መስክ ደግሞ ከፍ ብዬ የጠቀስኳቸው መ/ቤቶች ጥናትን መሠረት አድርገው ለአስቸኳይ ጊዜ ሊውሉ የሚችሉ መድኃኒቶችን፣ የሕክምና መሣሪያዎችንና ቁሳቁሶችን ከዓለም አቀፍ ተሞክሮ በመውሰድና ወረርሽም ወይም ሰፊ ሥርጭት ያላቸው ተላላፊ በሽታዎች ከተከሠተባቸው አገሮች ልምድ በመቅሰም አገራዊ ሀብት በፈቀደ መጠን ዝግጅት እንዲያደርጉ ይጠበቃል፡፡ ይህንንም ዝግጁነታቸውን በየአገሩ ያሉ መንግሥታት/አገዛዞች የፖለቲካ ቁርጠኝነት፣ ለሕዝባቸው ያላቸው የተቈርቋሪነት ኃላፊነት ስሜት፣ በፖሊሲ ደረጃ ቅድሚያ የሚሰጧቸው ዘርፎችና ውሱን ሀብታቸውን ዕውቀትንና ጥበብን መሠረት አድርገው የሚጠቀሙበት መንገድ ይወስነዋል፡፡ እነዚህ ተቋማት መንግሥታዊ ከሆኑና ካልሆኑ ዓለም አቀፍ የጤና ድርጅቶች ጋር በቅርበት ስለሚሠሩ፣ ከፍተኛ የሆነ የውጭ ርዳታ ከሚያገኙ መንግሥታዊ ተቋማት በመጀመሪያው ረድፍ የሚገኙ ናቸው፡፡ በተቋማቱ በተለይም በኢንስቲትዩቱ ላገር ለወገን የሚደክሙ በሳል ባለሙያዎች እንዳሉ ሁሉ በሀገር አቀፍ ደረጃ ባህል ከሆነው ሥር የሰደደ ንቅዘት የፀዱ ባለመሆናቸው የሚያገኙት ሀብት ሁሉ ባግባቡ ሥራ ላይ ይውላል ማለት አይቻልም፡፡ ኢንስቲትዩቱ እንደ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ከወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ብሔራዊ የመድኃኒትና የሕክምና መሣሪያዎች ክምችት (national stockpiles) ይይዝ እንደሆነ ግልጽ አይደለም፡፡ ዝግጁነቱ፣ መልስ መስጠቱ እና የመልሶ ማቋቋም ዐበይት ተግባራቱ በአሁኑ ሰዓት በምን ደረጃ እንደሚገኝ ለሕዝብ ይፋ አልሆነም፡፡ ባጠቃላይ የጤናውን ዘርፍ ዐቅም ለመገንባት የሚገባውን ያህል ሥራ ተሠርቷል ለማለት አይቻልም፡፡ ወረርሽኝ ሲከሠትም የሚሰጡት መልስ በዚሁ አግባብ የሚታይ ይሆናል፡፡
በሌላ በኩል በሠለጠኑትም ሆነ በልማት ወደ ኋላ በቀሩ አገሮች በአስቸኳይ ጊዜ/ሀገር አቀፍ አደጋ ሲከሠት አስተማማኝና ከፍተኛ ድጋፍ ሰጭ ኃይል ተደርጎ የሚወሰደው የአገር መከላከያ ሠራዊት ነው፡፡ አደረጃጀቱም ከወታደራዊ ሳይንሱ ጎን ለጎን በከፍተኛ ትምህርትና ዕውቀት የታነፀ፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂን ገንዘቡ ያደረገ፣ ግንባር ቀደም የፈጠራና የአዳዲስ ግኝቶች ባለቤት እንዲሆን ታስቦ በመሆኑ፣ ዛሬ በበለጸጉት አገራት ያለው የመከላከያ ኃይል በአገራቱ ላሉ ታላላቅ ኢንዱስትሪዎችና የፈጠራ ማዕከላት መሠረት የሆነ ተቋም ነው፡፡ ለአስቸኳይ ጊዜና አገራዊ አደጋ ሲከሠት አስፈላጊ ምርቶችን በማምረትም የታወቀ ኃይል ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አገሩንና ወገኑን የሚወድ፣ ታማኝነትና ተገዢነቱን ላንድ ሰንደቅ ዓላማና ሕዝብ ላመነበት የበላይ ሕግ ያደረገ፣ ያገሩን ዳር ድንበርና ሉዐላዊነት ከጠላት የሚከላከል ብሔራዊ የመከላከያ ኃይል ወገኑ አደጋ ሲደርስበት አለኝታነቱ የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡
ዛሬ በኢትዮጵያ አገራችን ያለው ‹የመከላከያ ኃይል› ከላይ የጠቀስነው ዓይነት ብሔራዊ ቁመና አለው ወይ? ዕውቀቱ/ሳይንስና ቴክኖሎጂውን ለጊዜው እንተወውና፤ ለሕዝብ ደኅንነት፣ ለአገር ሉዐላዊነትና ለግዛት አንድነት ዋስትና ሆኖ ለማስከበር የቆመ ነው ወይ? አደረጃጀቱ አገዛዙ ደጋግሞ እንደነገረን በዘር ተዋጽኦ የተደራጀ፣ አገዛዙን እና ከአገዛዙ ጋር ተመሳሳይ ግብ ላላቸው ጎሠኞች መሣሪያ ለመሆን የቆመ ኃይል አይደለም ወይ? ይህስ በተግባር አልታየም ወይ? ሜቴክ የሚባለው የነቀዞችና ማፈሪያዎች መናኸሪያ የአገር ሀብት ሙልጭ አድርጎ አልዘረፈም? በጣት ከሚቈጠሩቱ በስተቀር ለፍርድ ሳይቀርቡ እንደ ልባቸው የሚፈነጩበት አገር ውስጥ አይደለም ያለነው? ‹ከፍተኛ መኮንኖች› ከተልእኮአቸው ወጥተው አንዳንዶች የፖለቲካ እና የሲቪል አስተዳደር ሥራ ውስጥ አልገቡም ወይ? ለሕዝብና ላገር ለመቆም የሚፈልጉ ቊጥራቸው በርካታ የሆኑ ተራ ወታደሮች ወይም የበታች መኮንኖች በዘር መሥፈርት አናታቸው ላይ በተቀመጡ የበላይ መኮንኖችና በውስጥ በተዘረጋው ወታደራዊ የደኅንነት መረብ መላወስ አቅቷቸው የማያምኑበትን ተልእኮ እየፈጸሙ አይደሉም ወይ? በመደበኛ የፖሊስ ሠራዊት የሚፈጸሙ የሕዝብን ሰላምና ጸጥታ ማስከበር ተግባራት የመከላከያ ኃይሉ ክፍሎች መደበኛ ሥራ አልሆነም ወይ? በተደጋጋሚ የውጭ ኃይሎች ድንበር/ጠረፍ አልፈው ሲገቡ ማየት አገዛዙም ሆኑ ሠራዊቱ ለአገር ሉዐላዊነት ቆመዋል ማለት ይቻላል ወይ? ይህ ታላቅ ውርደት ነው፡፡ አስቀድሞስ ጠረፍ ጠባቂ ኃይል የለንም ወይ? የአገር ውስጥ ሽብርተኛ ቡድን ጫካ ውስጥ ገብቶ የሕዝብን ሰላማዊ ሕይወት ሲያውክ ማስታመሙ ለምን አስፈለገ? በዚህም ምክንያት ይህ በስም እንጂ በተግባር ብሔራዊ ያልሆነ የመከላከያ ኃይል የተከሠተውን ወረርሽኝ ለመዋጋት ደጀን ኃይል መሆን ይችላል? መልሱን ለሕዝቡ እተዋለሁ፡፡ ያም ሆኖ አሁን የተከሠተውን ቸነፈር በመከላከል ረገድ የሚያደርገው አስተዋጽኦ ካለ የሚመለከተው ቢያስብበት መልካም ይመስለኛል፡፡
ለጤና፣ ለትምህርት እና ሌሎች የልማት ሥራዎች ሊውል የሚችል ሀብት ከማዕከላዊ አገዛዝ ባፈነገጡ ክፍላተ ሀገር የጎሣ አለቆች (በተለይም ወያኔ ኦሮሚያ ብሎ በፈጠረው ግዛት፣ በአገዛዙ ቡራኬ ጭምር) አማካይነት ለርስ በርስ መተላለቅ በፖሊስ ኃይል ሽፋን ሕገ ወጥ የሆነ ልዩ ኃይልና የሚሊሺያ ሠራዊት በማሠልጠን እሽቅድድም ላይ ተጠምደው ከፍተኛ የሆነ የአገር ሀብት እየባከነ አይደለም ወይ? ይህ እየባከነ ያለ ሀብት ስንት ሆስፒታል፣ ስንት ጤና ጣቢያ፣ ስንት የጤና ኬላ ይገነባ ይሆን? ምን ያህል መድኃኒቶቸና የሕክምና መሣሪያዎች ለደሀ ኅብረተሰባችን ለማሟላት ያስችል ይሆን? ባጠቃላይስ ኢትዮጵያ የአገሪቱን ከፍተኛ በጀት የሚወስድ፣ አገሩ ሰላም አጥታ ያልበላውን ለማከክ ‹በሽያጭ› መልክና ‹በሰላም ማስከበር ተልእኮ› ስም የሚሠማራ ግዙፍ የመከላከያ ኃይል (ለዚያውም ብሔራዊ ቁመና የሌለው) መገንባት አስፈላጊና ቅድሚያ የምትሰጠው አጀንዳ ነው ወይ? ተጠያቂነት ቢኖር የአገር ሀብት እንዲህ በከንቱ አይባክንም ነበር፡፡
ሌሎችም ፍጻሜ የሌላቸው፣ ከፍተኛ የአገር ሀብት በንቅዘት የባከነባቸው፣ እዚህም እዚያም ተዝረክርከው የቀሩ ግዙፍ ፕሮጀክቶች የፖሊሲ፣ የዕቅድ፣ የሥራ አመራርና የባለቤትነት እጦት ችግሮች ውጤት አይደሉም ወይ? ለነዚህ ባለቤት ላጡ ፕሮጀክቶች ባገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር በብድር የፈሰሰው በቢሊዮን የሚቈጠር የሕዝብ ገንዘብ በርካታ አገራዊ ቁም ነገሮችን አይሠራም ነበር? አሁንም ያላባራውና በዝርፊያ የሚባክነውስ የሕዝብ ገንዘብ? እውነቱን እንነጋገር ከተባለ በበደላችን ከመጣው (በምእተ ዓመት አንድ ጊዜ ከሚከሠተው) ቸነፈር ይልቅ ሰው ሠራሹ የዘረኝነት ወረርሽኝ በአገራችንና በወገናችን ላይ ከፍተኛ ሥጋት አልደቀነም፡፡ እስቲ ዘርን መሠረት አድርጎ ሕይወቱን ያጣውን፣ አካሉ የጎደለውን፣ ለንግግር በማይመች ስቃይ ውስጥ ያለፈውን፣ በገዛ አገሩ ከቤት ንብረቱ የተፈናቀለውን፣ የተሰደደውን፣ የተዋረደውን ወገናችንን ለአፍታ እናስበው፡፡ ስንት ነው ቊጥሩ፡፡ ይህንን ድርጊት የሚፈጽሙ ኃይሎችና ሕጋዊና ተቋማዊ ሁናቴውን ያመቻቸላቸው አገዛዝ በዚህ ሰዓት እንኳን ለወገን ዕረፍት አልሰጡትም፡፡ የተቀሩቱ ደግሞ የለመዱትን ሽብር ለመቀጠል አድፍጠው እየጠበቁ ነው፡፡
ወደ ቀደመ ነገሬ ልመለስና አገራዊ የዐቅም ውሱንነትን ስንናገር ከዚህ በላይ ለአብነት የጠቀስናቸው አቅጣጫቸውን የሳቱ የሀብት አመዳደቦችና በንቅዘት የሚባክነውን ሀብት ግምት ውስጥ አስገብተን እንደሆነ ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ ይህ አስተያየት በሚዘጋጅበት ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ በቸነፈሩ የተያዙ ሰዎች ብዛት 25 መሆኑን አገዛዙ ነግሮናል፡፡ ጉዳዩ ‹ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ› እንደሚሆን የብዙዎች ሥጋት ነው፡፡ ይህንን ረዳት የሌለው ምስኪን ሕዝብ በምሕረቱ ጎብኝቶ በተነገረው ቊጥር ቢገታልን፣ አንድም ሰው ባይሞት ጸሎታችንና ምኞታችን ነው፡፡ እምነታችን በሥራ ካልተገለጠ ግን ምዉት ስለሚሆን ቀደም ብለን ያነሳነው የዐቅም ውሱንነትና የሀብት ብክነት እንደተጠበቀ ሆኖ አሁን የተከሠተውን ወረርሽኝ ለመቋቋም ምን እናድርግ?
- በብሔራዊ ደረጃ የተቋቋመው ኃይለ ግብር ተፈትነው የቀለሉ ካድሬዎች ከሚመሩት በእውነተኛ የሕክምና ባለሙያዎች (በተለይም የበሽታን ምንጭ፣ መተላለፍና ሥርጭት ያጠኑ ባለሙያዎችን/epidemiologists፣ ቫይረሶችንና በነሱም ምክንያት የሚመጡ በሽታዎችን ያጠኑ ባለሙያዎችን/virologists) ቢጠናከርና ለሕዝብ እውነተኛ መረጃዎችን ዕለት ዕለት ቢያደርስ፡፡
- ጥናትን መሠረት አድርጎ በተወሰኑ/በተመረጡ አካባቢዎች የናሙና ምርመራ ቢደረግ፤ የወገናችንን ዲስፕሊን ማጣት ሳስበው እጅግ አስደንጋጭ ቊጥሩ ሊያጋጥመን እንደሚችል እገምታለሁ፤ አያድርገውና ይሄ ቢሆን የሕክምና ተቋማት በቫይረሱ በተያዙ ሰዎች ቢጥለቀለቁ እንዴት ነው የምናስተናግደው? ዐቅምን ያገናዘበ ምን ዓይነት ዝግጅት ተደርጓል? አማራጭ ጊዜያዊ ሆስፒታሎች (makeshift hospital) ለማዘጋጀት ታስቧል? ለምሳሌ፤ ሰው ያልገባባቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች፣ ሥራ ያልጀመሩ የባለሀብቶች ሕንፃዎች፣ እስከ ድንኳን ድረስ፡፡
- በልዩ ልዩ የሕክምና ተቋማት (የግሎችን ጨምሮ) የሚገኙ የሕክምና ባለሙያዎችን ለአስቸኳይ ጊዜው እንዲዘጋጁ በሚመለከታቸው አካላት የማስተዋወቂያ መርሐግብር (orientation) መስጠት ተጀምሯል ወይስ ገና አልታሰበበትም?
- በቫይረሱ ተይዞ በሕክምና ለመርዳት የሚደረገው ጥረት እንኳን እኛ ከድኅነት ወለል በታች ያለነው ባለጸጎቹ ሀገራትንም በእጅጉ እንደተፈታተነና ከቊጥጥር ውጭ እንደሆነባቸው እየታዘብን ነው፡፡ ስለሆነም ለመከላከል የሚደረጉ የጥንቃቄ ርምጃዎችን አጠንክሮ ተግባራዊ ማድረጉ ላይ ከአገዛዙ ከሚሰጠው መግለጫ፣ ለፎቶ ከሚደረጉ የባለሥልጣናት ቅስቀሳ፣ በየመገናኛ ብዙኃኑ ከሚደረጉ የባለሙያ መልእክቶች ባለፈ፣ እስቲ ለመጀመሪያ ጊዜ ይህንን ወረርሽኝ ለመከላከል አነስተኛ የአስተዳር ዕርከን የሆኑትን የቀበሌዎች/ወረዳዎች መዋቅር በከተማ፤ የገበሬ ማኅበራትን በገጠሩ ብንጠቀምባቸው፡፡
- ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በሚተላለፍ ወጥነት ባለው መምሪያ መሠረት ለገጠሩ የጤና ኬላ ውስጥ የሚሠሩ የጤና ባለሙያዎችን እና ከሚመለከተው ክፍለ ሀገር የተውጣጣ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን፣ ለከተሞች ደግሞ የጤና ጣቢያዎች ውስጥ የሚሠሩ የጤና ባለሙያዎችንና በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን በማስተባበር ማኅበረሰቡ ስለ ወረርሽኑ በቂ ግንዛቤ እንዲያገኝ ቢደረግ፡፡ በእያንዳንዱ ቀበሌ/ወረዳ ነዋሪዎች የቅርብ ክትትል በማድረግ የጥንቃቄ ርምጃዎቹን ዕለት ዕለት ማስተማርና ተግባራዊ እንዲሆኑ ማድረግ አይቻልም?
- እነዚህኑ የአስተዳደር መዋቅሮች በመጠቀም ነዋሪዎች ታክሲም ሆነ የሕዝብ ትራንስፖርት ሳይጠቀሙ መሠረታዊ አቅርቦቶችን (ከወትሮው በተለየ መልኩ – የአቅርቦት ዓይነቶችን በማስፋት) መርሐግብር አውጥተው (ግፊያና ትርምስ/ቅርርብ ሳይኖር) ማስተናገድ ቢቻል የሕዝቡን እንቅስቃሴ ብሎም የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት የሚደረገውን ጥረት ሊያግዝ አይችልም?
- የመመርመሪያ መሣሪያዎችንና ሌሎች የሕክምና ቁሶችን በተለይም ለሕክምና ባለሙያዎች የሚሆኑ የመከላከያ ቁሶቸን ከዓለም አቀፉ አካላት እና ወንድማችን ሊቀ ትጉሀን ታማኝ በየነ ከሚያስተባብረው የግሎባል አሊያንስ እንዲሁም ባገር ውስጥ ያሉ ባለሀብቶች ከሚያደርጉት እገዛ ጋር ባንድነት ቫይረሱን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት፣ በቤት ተወስኖ በመቀመጥ የሚላስ የሚቀመስ የሌላቸውን እጅግ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ወገኖቻችንን ለመታደግ ብሎም በቫይረሱ የተያዙትን ወገኖች በተወሰነ ደረጃ ሕክምና ለመስጠት እንደሚያግዝ ይታመናል፡፡
የሥጋታችንን እንወርውር ለማለት ነው፡፡ የሙያውን ጉዳይ ለባለሙያዎች እተዋለሁ፡፡
ማእምረ ኵሉ እግዚአብሔር መዓቱን ከምንሸከመው በላይ አያድርግብን፡፡ መላ ሕዝባችንን እንዲሁም ዓለምን በምሕረት ዓይኑ ይጎብኝልን፡፡