>

የዐቢይ አሕመድ ኹለት ዓመታት! (በፍቃዱ ዘ ሀይሉ)

የዐቢይ አሕመድ ኹለት ዓመታት!

 

በፍቃዱ ዘ ሀይሉ
 
[ስለ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ውዳሴ ብቻ መስማት የሚፈልጉ ሰዎች እንዲያነቡት አይመከርም]
***
አባባዩ ጠ/ሚንስትር:-
ከወር በፊት፣ ከጓደኞቼ ጋር የሆነ ኮንሰርት ልንገባ በር ላይ ስንደርስ ከኛ የቀደሙት ትኬታቸውን ሊያስመልሱ ሲከራከሩ ደረስን። በር ላይ ያለው ሰውዬ ለማግባባት በማሰብ ትኬት ይመለስልን የሚሉትን ወጣቶች “የኛ የመጀመሪያው ኪሳራችን እናንተን ማስከፋታችን ነው” አለ። አንዱ ጎረምሳ ከአፉ ነጥቆ “ባክይ ዐቢይ አሕመድ አትሁንብኝ” ብሎ ሁላችንንም በሳቅ አፈረሰን።
እዚሁ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ “ቅቤው” እያሉ ሲጠሯቸው እሰማለሁ፤ በአራዳ ልጆች አነጋገር “ፎጋሪው” እንደማለት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባለፉት ሁለት ዓመታት ያረጋገጧቸው ነገሮች ቢኖሩ በንግግራቸው አባባይ መሆናቸውን ነው።
ንግግራቸው ታዲያ ብዙዎችን ያስደስት እንጂ፥ የኔ ቢጤዎችን ግን ብዙ ጊዜ ያበሽቃል። የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ንግግሮች ከፕሮቴስታንት አስተምህሮ፣ ከመንፈስ ማነቃቂያ መጽሐፍት ምክሮች እና ከሳይንሳ ለበስ ግምቶች አያልፉም። ዐቢይ ለጆሮ የማይጎረብጥ ነገር የሚያወሩት ስለ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሲያወሩ ብቻ ነው ባይ ነኝ።
 
“አዳኝም መንገድም”
ዐብይ አሕመድ የኖሩበት የፕሮቴስታንት ባሕል ሳይጫናቸው የቀረ አይመስለኝም፥ ችግሮችን ሁሉ በስብከት እና በምክር እንዲሁም በመተቃቀፍ መፍታት የሚቻል ይመስላቸዋል። ብዙ ንግግሮቻቸው በምክር የተሞሉ ናቸው። ብዙዎቹ መግለጫዎቻቸው እና ንግግሮቻቸው ውስጥ የአማካሪያቸው ሙዓዘ ጥበባት ዳንኤል ክብረት የረዥም ዓመታት የተረታ ተረት ዘይቤዎች ይስተዋላሉ። (አንድ ጊዜ “እየወጋች በምትጠቅመው መርፌ” መስለው ያወጡት መግለጫ ሥር “እናመሰግናለን ዳንኤል ክብረት” የሚል አስተያየት አይቼ እስከዛሬ ያስቀኛል።) ይህ ዘይቤ የችግሮቻችን ሁሉ ምንጭ ከሥነ ምግባር ዕጦት የመነጨ ነው ከሚል የሚመነጭ ስለሆነ፥ እንዲህ ብትሆኑ እና ብታደርጉ ኖሮ እንዲህ አትሆኑም የሚሉ ናቸው። በዚህም ምክንያት መንግሥት የሥነ ምግባር አስተማሪ፣ መካሪ ወላጅ ወይም አሳዳጊ (paternalistic) ሚና ለራሱ ሰጥቷል። በዚህ አሠራር ሕዝብ ታዳጊና አጥፊ ሕፃን ነው ማለት ነው። ለዚህ ነው መንግሥት በቲቪ የምታዩትን ማስታወቂያ፣ በማኅበራዊ ሚዲያ የምታነቡትን መረጃ እኔ እመርጥላችኋለሁ ማለት እየቃጣው ያለው።
ዐቢይ አሕመድ በፓርቲ ውስጣዊ የሥልጣን ትግል የተዋጣላቸው መሆኑ ግልጽ ነው፤ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ብልፅግና ፓርቲን በገዛ ፍላጎታቸው ልክ ለመመሥረት የፓርቲ አጋሮቻቸውን ሁሉ ያስገበሩበት መንገድ ለዚህ እማኝ ነው። ሕዝባዊ ተቃውሞዎችን ኢሕአዴግ ውስጥ የነበረ የእኩያሞች ትግል ለማጧጧፊያነት ተጠቅመውበታል። በዚህም የኢትዮጵያን የሥልጣን ቁንጮ ተቆናጠዋል። ነገር ግን ዘላቂ የዴሞክራሲ፣ የብልፅግና እና የሰላም ፍኖተ ካርታ ማውጣት ላይ በተግባር ራሳቸውን ማስመስከር አልቻሉም። በሥልጣናቸው አፍላ ጀንበር ሰሞን ከተቃዋሚዎች ጋር የነበራቸው ወዳጅነትም ይሁን ከኤርትራ መንግሥት ጋር የነበራቸው የፍቅር ግንኙነት የጋራ ጠላታቸውን ሕወሓትን ለማጥቂያና ሥልጣን ለማደላደያነት ከመዋሉ በቀር ዘላቂ ሥምምነት እና ሰላም ማስፈኚያ ሲያደርጉት አላየንም። ይልቁንም በዚህ አደራ የተሰጣቸውን የሰላም ኖቤል ሽልማት የብፁዕነታቸው መለኪያ አድርገው ወስደውታል ብዬ መጠርጠር ጀምሬያለሁ። በቅርብ የማግኘትና የማነጋገር ዕድሉ የገጠማቸው አንድ ሰው ዐቢይ አሁን ያሉበትን ሁኔታ የገለጹልኝ፥ “Arrogant and Ignorant” ሆነዋል በሚል ነበር።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በዓለም ዐቀፍ ሜዳዎች ጎልቶ መውጣት እንደ ዓላማ አንግበዋል፤ በኢትዮጵያ ክልላዊ መስተዳድሮች ውስጥ ያለውን ኩርፊያ ቸል ብለው፣ በአፍሪካ ቀንድ ያሉ ግጭቶችን ለመፍታት እየሞከሩ ነው። ሙከራው አይከፋም፣ በራሳቸው ንግግር ‘እኛ በሰላም እንድናድር፣ ገረቤቶቻችን ሰላም ማደር አለባቸው’። በቅርቡ በሶማሊያ እና ሱማሌላንድ አመራሮች መካከል ዕርቅ ለመፍጠር መሞከራቸውም ጥሩ ነገር ነው። ነገር ግን ከአካላዊ መተቃቀፍ ተጨማሪ ነገር መያዝ እንዳለባቸው አማካሪዎቻቸው ሊያስታውሷቸው ይገባል። ባለፈው ዓመት የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኞች የሆኑትን ሳልቫ ኪር እና ሪክ ማቻርን በግፊት ሊያስተቃቅፉ የሞከሩበት መንገድ አሳፋሪ ትዕይንት ነበር።
ዐቢይ አሕመድ “የቄሳርን ለቄሳር” የሚል መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምክርም ዘንግተዋል። ከላይ እንደጠቀስኩት መንግሥትን እንደ ወላጅ አሳዳጊ፣ ሕዝብን እንደ ታዳጊ ልጅ የሚመለከት አቀራረባቸው በፖሊሲ እና ሕግ የሥነ ምግባር መመሪያዎችን እንዲያወጡ አድርጓቸዋል። የሞራል አባትነቱ ደግሞ ሃይማኖታዊ ይመስላል። ባለፈው ከአፍሪካ ኅብረት ጥቂት መሪዎች ጋር በጋራ ፀሎት ካደረጉ በኋላ “Jesus Christ is the ultimate solution for African problems” ማለታቸውን ሰምቼ ጥርጣሬዬን አረጋግጦልኛል፤ መቼም መሪዎች የፈጠሩትን ችግር እግዜር ይፈታልናል ብለው እንደመጠበቃቸው ያለ አስደንጋጭ ዜና የለም።
ዐቢይ በቤተ መንግሥት
ዐቢይ “ደሞዜ 4 መቶ ዶላር ብቻ ነው” ብለው ያማረሩበት መድረክ አለ። እዚያው መድረክ ላይ “ሁሉም የከፈለኝ ይመስል ይጨቀጭቀኛል”ም ብለዋል። የምኒልክ ቤተ መንግሥት ውስጥ ትልቅ ሙዚየም (‘አንድነት ፓርክ’ ብለው የሰየሙትን) አስገንብተዋል። ፓርኩን የጎበኙት ሰዎች ሁሉ አድንቀውላቸዋል። አፈፃፀሙንም የእርሳቸውን የዕቅድ አተገባበር ብቃት ማሳያ አድርገው ወስደውታል። እርሳቸውም በሁሉም ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ይህንኑ የደሰኮሩበት ጊዜ አለ። የሆነ ሆኖ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፓርኩ እየተገነባ ሳለ ላገኟቸው ሰዎች “ቤተ መንግሥቱን ለማሠራት ከመንግሥት ሰባራ ሳንቲም አልወሰድኩም” ብለዋል። አሁንም ለብልፅግና ፓርቲ የገቢ ማሰባሰቢያ የመንግሥት ሥልጣኔን አልተጠቀምኩም እንደሚሉ አልጠራጠርም። የሆነ ሆኖ ደሞዛቸው፣ በየወሩ ከሚከፈላቸው እጅግ በብዙ እጥፍ የበለጠው ጥቅማ ጥቅማቸው እንደሆነ እናውቃለን። የጠቅላይ ሚኒስትርነት ሥራም የሚሠራው ስለደሞዙ አይደለም። በሌላ በኩል ፓርኩን ለማስገንባትም ገንዘብ የሚሰጧቸው የውጭ አገራት ወዳጆቻቸው በግል እርሳቸውን ወደው አይደለም፤ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆናቸው በኢትዮጵያ ሕዝብ ሥም ነው። እነዚህን ሐቆች መዘንጋት የመጀመሪያው የመንግሥት መሪ ሀጢያት ነው።
ዐቢይ አሕመድ በውጭ
ዐቢይ አሕመድ ብልጭ ድርግም ከሚል ትችት በቀር በውጭ አገራት ብዙኃን መገናኛዎች በጥቅሉ ለረዥም ጊዜ የሚቆይ መልካም ሥም አፍርተዋል። ሥማቸው ሲነሳ አብሮ የሚነሳው የኖቤል የሰላም ሽልማት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ሪፎርም ማምጣታቸው፣ ሴቶችን ወደ አመራርነት ከፍ ከፍ ማድረጋቸው እና የዛፍ ተከላ አብዮት መጀመራቸው ናቸው። በእርግጥ እነዚህ ነገሮች ላይ አስተዋፅዖ አልነበራቸውም ብሎ መካድ አይቻልም። ከኤርትራ ጋር መዝለቁን ባናውቅም ሰላም አስፍነዋል፣ ራሳቸውንና ፓርቲያቸውን ዴሞክራሲያዊ ማድረግ ባይሆንላቸውም፥ ለዴሞክራሲ ሪፎርም የሚበጁ ለውጦችንም ጀማምረዋል፣ ተተኪ ሴቶችን በእየርከኑ ማዘጋጀቱ፣ እንዲሁም በንግግራቸው Gender-sensitive መሆን ባይሳካላቸውም፥ ካቢኔያቸውን በፆታ ውክልና አመጣጥነዋል፣ የተባለውን ያህል ቁጥር ማስተከላቸው ባይዋጥልኝም፣ ችግኝ ተከላን እንደፋሽን ማስመሰላቸው ይደነቅላቸዋል።
በነዚህ ሁሉ መሐል ግን የኢትዮጵያውያን የረዥም ጊዜ ዘላቂ ሰላም ማምጣት የሚችል ስርዓተ ማኅበር ግንባታ ቸል ተብሏል። የዐቢይ አሕመድ መንግሥት ከምንም ነገር በላይ የገጽታ ግንባታ ላይ ተጠምዷል። ከፖሊሲ ይልቅ ማባበያ ንግግርን መርጧል፤ እናም፣ በዚህ ሰዓት፣ ከምንጊዜውም በላይ ወቃሽ ያስፈልገዋል።
Filed in: Amharic