>

የምርጫው ዕጣ ፈንታ?!? (በፈቃዱ ኃይሉ)

የምርጫው ዕጣ ፈንታ?!?

 

በፈቃዱ ኃይሉ
ምርጫ 2012 እንደማይካሔድ ብዙ ተሟርቶበት ነበር። ነገር ግን የተፈራው የፀጥታ ጉዳይ ተሸንፎ ያልተጠበቀው የጤና ጉዳይ አሸንፎታል። ምርጫ ቦርድ በዚህ መንቀሳቀስ በማይቻልበት ሁኔታ “ምርጫ ማካሔድ አልችልም” ብሎ ውሳኔውን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳልፎ ሰጥቷል።

ምርጫ 2012 እንደማይካሔድ ብዙ ተሟርቶበት ነበር። ነገር ግን የተፈራው የፀጥታ ጉዳይ ተሸንፎ ያልተጠበቀው የጤና ጉዳይ አሸንፎታል። ምርጫ ቦርድ በዚህ መንቀሳቀስ በማይቻልበት ሁኔታ “ምርጫ ማካሔድ አልችልም” ብሎ ውሳኔውን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳልፎ ሰጥቷል። ምክር ቤቱ ምን ሊወስን ይችላል? ምርጫው እስከመቼ ይራዘም ይሆን? በዚያ መሐል ያለውን ጊዜ አስተዳደሩን ማን ይመራዋል?

ምክር ቤቱን ለማፍረስ፥ ምክር ቤቱን ማስፈቀድ

ምርጫው በወቅቱ መካሔድ ባለመቻሉ ሕገ መንግሥታዊ ቀውስ ተፈጥሯል። ቀውሱ የሚጀምረው ለአምስት ዓመት አገልግሎት እንዲሰጥ “የተመረጠው” የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “ላልተመረጠበት” ጊዜ ውሳኔ የማሳለፍ ኃላፊነት ስለተጫነበት ነው። በዚህ ረገድ ብዙዎች የሚጠቅሷቸው ሁለት አማራጮችን ነው። አንደኛው ምክር ቤቱን በትኖ አሁን ያለው የመንግሥት አካል ምርጫ እስኪካሐፀድ ድረስ እንዲመራ ማድረግ ነወ። ይህ በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 60/1 እና አንቀፅ 60/5 ላይ ተደንግጓል። ሌላኛው በአንቀፅ 93 መሠረት የአስቸኳይ ጊዜ ማወጅ እና ሕገ መንግሥታዊ መብቶችን ጨምሮ ማገድ ነው። ሁለቱም አማራጮች የተለያዩ አጣብቂኞች አሏቸው።

የመጀመሪያውን አማራጭ ስንመለከት፣ አንቀፅ 60/1 “ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሥልጣን ዘመኑ ከማለቁ በፊት አዲስ ምርጫ ለማካሔድ በምክር ቤቱ ፈቃድ ምክር ቤቱ እንዲበተን ለማድረግ ይችላል” ይላል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሹመት የተወሰነው በፓርቲያቸው ሲሆን፥ ምክር ቤቱ ሹመታቸውን እንዲያውቅ ተደረገ እንጂ፥ እጁን አውጥቶ ድምፅ አልሰጠበትም። ነገር ግን ይኸው ምክር ቤት እጁን አውጥቶ ላልመረጣቸው ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲያፈርሱት ፈቃድ መስጠት ይጠበቅበታል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተሾሙ ወዲህ በርካታ ለውጦች አሉ። የሾማቸው ፓርቲ/ግንባር ፈርሶ በምትኩ ሌላ ውሕድ ፓርቲ መፈጠሩ እና ሕወሓት ተቃዋሚ ፓርቲ መሆኑ የምክር ቤቱን እና የጠቅላይ ሚኒስትሩን ግንኙነት የተለየ ገጽታ ይሰጠዋል። የሆነ ሆኖ አሁንም የምክር ቤቱ አብላጫ ወንበሮች በአዲሱ ብልፅግና አባላት የተሞላ መሆኑና የምክር ቤቱ የአገልግሎት ጊዜ ማለቁ ስለማይቀር፣ ምክር ቤቱ በዚህ ረገድ ተባባሪ ሊሆን ይችላል። በዚህ መንገድ አስተዳደሩ ስድስት ምርጫ የማዘጋጃ ወራት ማግኘት ይችላል። ይኼ ግን ሌላ ጥያቄ ይወልዳል።

የክልሎቹ ምክር ቤት ጉዳይ!

የፌዴራሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የክልል ምክር ቤቶች የአገልግሎት ጊዜ ተመሳሳይ ነው። ስለዚህ ጠቅላይ ሚነከስትሩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ሲበትኑ የክልሎቹስ ምክር ቤቶች ዕጣ ፈንታስ ምን ይሆናል?

ተመሳሳይ አማራጮች መኖራቸውን ለማረጋገጥ የኦሮሚያን እና የትግራይን ሕገ መንግሥቶች ተመልክቼ ነበር። ሁለቱም ላይ ስለጨፌው ወይም ስለ ምክር ቤቱ መበተን ምንም ድንጋጌ የላቸውም።  የሌሎቹም ክልሎች ሕገ መንግሥቶች ተመሳሳይ እንደሚሆኑ በመገመት ሌላኛውን አማራጭ እንመልከት።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለመንግሥት የተለጠጠ ሥልጣን ሰጥቶ የዜጎችን መብት መንፈግ ያስችለዋል። መንግሥት ይህንን ማድረግ የሚችለው መጀመሪያ ቢበዛ ለስድስት ወራት ነው። ከዚያ በኋላ በድጋሚ ለአራት ወራት ለማራዘም የምክር ቤቱን ፈቃድ ማግኘት አለበት። ነገር ግን በዚያን ወቅት ምክር ቤቱ ሥልጣን አይኖረውም። የክልሎቹ ሕገ መንግሥትም ተመሳሳይ ይዘት አለው። ይህ ሕገ መንግሥታዊ ቀውስ አለው። በሌላ በኩል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚታወጅባቸው ምክንያቶች የተለዩ ናቸው። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የምርጫ ወቅት ለማራዘም ብሎ ማወጅ አይፈቀድም። ያንዣበበውን ወረረሽኝ ምክንያት አድርጎ አዋጅ ለማወጅ ከአሁን የተሻለ ጊዜ የለም። ለምርጫው ጊዜ ለማግኘት ተመራጩ ጊዜ መስከረም ላይ ማወጅ ነው። ያኔ ደግሞ ወረርሽኙን ምክንያት ማድረግ የሚቻልበት ጊዜ አይሆንም፣ ከሆነም ምርጫውን ያኔም ማድረግ አይቻልም ማለት ነው።

ሁለቱም አማራጮች ሕገ መንግሥታዊ አጣብቂኝ ያስከትላሉ።

ሦስተኛ አማራጮች

ሌሎቹ አማራጮች አዲሱ አስተዳደር ከመጣበት ዕለት ጀምሮ በአንዳንዶች ሲጠየቅ የነበረው የሽግግር መንግሥት ወይም አምባገነናዊ አስተዳደሮች ናቸው።

የሽግግር መንግሥት መመሥረት በኢትዮጵያ ነባራዊ ፖለቲካ ሁኔታ የሌላ ቀውስ አዲስ ምዕራፍ መክፈቻ ነው የሚሆነው። በመጀመሪያ ሕገ መንግሥቱን ለጊዜው ወይም እስከ ዘላለሙ ከሥራ ውጪ ማድረግ ይጠይቃል። በዚህ ጉዳይ ስምምነት ላይ መድረስ አይቻልም። በሆነ ተዓምር የፖለቲካ ቡድኖቹ በዚህ ጉዳይ መሥማማት ይችላሉ ብንል እንኳን፣ በሽግግር መንግሥቱ አወቃቀር ላይ መሥማማት አይቻልም። ምክንያቱም የሽግግር መንግሥቱም ምክር ቤት ይፈልጋል። የምክር ቤቱ አባላት እንዴት ነው የሚመረጡት? በማን ነው የሚመረጡት? የሚዳኛቸው ሕግ ምንድን ነው? ይህ ሥራ ሌላ ምርጫ ከማሰናዳት የበለጠ ጊዜ እና ጥረት ይጠይቃል። ስለሆነም የሽግግር መንገሥት የመፈጠር ዕድሉ አነስተኛ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ስለዚህ ጉዳይ ሲጠየቁ “እኔ አሻግራችኋለሁ” ያሉበት ምክንያት ይህ ውስብስብ ጉዳይ አሳስቧቸው ይሆናል።

በዚህ አጣብቂኝ ክስተት ምክንያት አምባገነንነት ሌላው በኢትዮጵያ ላይ ያንዣበበ አደጋ ነው። የፌዴራሉ እና የክልሎቹ ሕገ መንግሥታት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ለፕሬዚደንቶቻቸው እንደሁኔታው ከምክር ቤቶቻቸው ዕድሜ የረዘመ የኃላፊነት ዘመን ሊሰጥ እንደሚችል ይደነግጋሉ። ያም ሆነ ይህ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በእጃቸው ብዙ ሥልጣን የመውደቅ ዕድሉ ሰፊ ነው። ምክር ቤቱ ከተበተነ ሕግ እና መመሪያ ማውጣት ባይፈቀድላቸውም፣ በአስተዳደራዊ ሁኔታዎች ሁሉ የፈላጭ ቆራጭነት ኃይል ይጎናፀፋሉ። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የውሳኔዎች ሁሉ የበላይ ይሆናሉ። አማራጮቹ ሲመረመሩ የምርጫው መራዘም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በአዋጅ የመግዛት ዕድል ሊሰጥ ይችላል። ይህ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እንደ አንድ ግለሰብ ሳይሆን ለማንኛውም ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የአደገኛ አማራጮች መዘርዝር (ሜኑ) ነው።

ይህንን አደጋ ለማስቀረት የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት እንዲሁም የሕግ እና ፖለቲካ አዋቂዎችን ሰብስቦ በግልጽ በማወያየት የተሻለ፣ ምናልባትም ከላይ ያሉትን አማራጮች በማዳቀልም ቢሆን መፍትሔ ማበጀት ያስፈልጋል። በሒደቱ ብዙኃኑ ቅር የማይሰኙበት መፍትሔ ማምጣት ካልተቻለ ያለፈው ሁለት ዓመታት ተስፋ መቋጫ ይህ ሊሆን ይችላል።

Filed in: Amharic