>

ተንከባካቢዎቻችንን ለመንከባከብ ምን ያህል ዝግጁ ነን? (እንዳለ ጌታ ከበደ)

ተንከባካቢዎቻችንን ለመንከባከብ ምን ያህል ዝግጁ ነን?

እንዳለ ጌታ ከበደ
ከእለታት አንድ ቀን ግን ከአንድ ታማሚ ሕጻን ተላላፊው በሽታ ተላለፈበት። ቃተተ፤ ተሰቃየ፤ ሞተም!!!
 
ዕውቁ የአጭር ልቦለድ ደራሲ፣ ሩሲያዊው አንቷን ቼክኾቭ አንድ አይረሴ ሐኪም ገፀባህርይ ፈጥሮ በጭንቅላቴ ተቀርጾ ቀርቷል። ሐኪሙ ጊዜውን በምርምርና ሕጻናትን በማከም ራሱን ሙሉ ለሙሉ ከማስገዛቱ የተነሳ እምትወሰልት ሚስቱን መግራት እንኳን  አልሆነለትም ነበር። ስለሕመምተኞቹ የታመመ ነበር።
በዐጼ ቴዎድሮስ ዘመን ተስቦ ገባ። ወረርሽኙ የዐጼውን የቅርብ አጃቢዎቹን ሳይቀር ገደለ። ቁጥራቸው ተመናመነ። በዚህም የተነሳ በሰፈሩበት ደብረታቦርና በአካባቢው ሁከትና ጭንቅ ሆነ።
ወረርሽኙን ለመግታት ከባሕል ሕክምና አዋቂዎች ሌላ በዶክተር ሄንሪ ብላንክ ትከሻ ላይ ወድቆ ነበር። Rassam እማኝ ሆኖ በጻፈው “BRITISH MISSION THEODORE” መጽሐፍ ውስጥ፣ ሄንሪ ብላንክ ተላላፊው እንዳይተላለፍበት እንዴት ይጠነቀቅ እንደነበር ጽፏል።
መርስዔ ሀዘን ወልደቂርቆስ፣ “የሐያኛው ክፍለዘመን መባቻ” በሚለው መጽሐፋቸው፣ እኛ “የኅዳር በሽታ” ብለን ስለምንጠራው (ስፓኒሽ ፍሉ) ወረርሽኝ እኛ አገር ስለተከሰቱ እጅግ አሰቃቂ እውነቶች በጥቂቱ ከትበዋል።
ይህ በሶስት አራት ቀን የሚገድለው በሽታ ሙሉ ቤተሰብ አሳጥቷል። በአንድ መቃብር ሁለት ሶስቱ እንዲቀበሩ አድርጓል። ሰዎች ሬሳ
ተሸካሚ በማጣት በየግቢያቸው ውስጥ ቀብረዋል። “ባል የሚስቱን አባት የልጁን ሬሳ እየተሸከመ ወስዶ ቀበረ።/—/”
መርስዔሀዘን በወቅቱ የነበረውን የመንፈስ ድቀትና ውድቀት ለማቃናት በጎ አድራጊዎች ምን ይሰሩ እንደነበርና ስለገጠማቸው እጣፈንታም እንዲህ ይተርኩልናል።
“የኔታ ወልደጊዮርጊስ በሰፈራቸው በጉለሌ ክፍል በየቤቱ እደዞሩ ለበሽተኞችና ለገመምተኞች እንጀራና ውሐ ሲያድሉ ሰነበቱ። በእግዚአብሔር ቸርነት ከበሽታው አምልጠን ነበርና እኔንና ጎጃሜ ኃይለማርያምን ውሐ እያሸከሙ እሳቸው ቁራሽ እንጀራ ይዘው ይሄዱና ከቤቱ ደጃፍ ሲደርሱ እኛን እውጪ አስቀርተው ውሐውንና ቁራሹን ይዘው ይገቡ ነበር። እኛን ማስቀረታቸው በሽታው እንዳይዘን ስላሰቡልን ነው።/—/
“—መንፈሳውያን ሰዎች ነበሩ። ለምሳሌ ሙሴ ሴደርኩዊስት የተባሉ ሽማግሌ (የስዊድን ሚሲዮን አስተማሪ) በየሰፈሩ እየዞሩ ለበሽተኞች እህልና ውሐ መድሐኒትም በመስጠት ትሩፋት መስራታቸውን ሰምቻለሁ። እኒህ ሽማግሌ ሚሲዮናዊ ከጥቂት ቀናት በሁዋላ በዚሁ በሽታ ታመሙና ሞተው ጉለሌ ተቀብረዋል።”
—-
ከላይ እንደተጠቀሱት አይነቶች በጎ አድራጊዎች በየዘመኑና አገሩ አሉ። ሌላውን አድናለሁ ሲሉ ራሳቸው በተላላፊው ታድነው መስዋዕትነት የከፈሉ ጥቂቶች አይደሉም። የሕክምና ባለሙያዎች፣ ፍቃደኛ በጎ አድራጊዎች፣ ከጉዳዩ ጋር በቅርበት የሚሰሩ የመንግስት ሹማምንትና ሌሎችም—
ተንከባካቢዎችችንን መንከባከብ ማለት ለራሳቸው ጊዜ እንዲሰጡ፣ ራሳቸውንም እንዲጠብቁ ማገዝ ማለት ነው።
ተንከባካቢዎቻችንን መንከባከብ ማለት ራስን መንከባከብ ማለት ነው።
ተንከባካቢዎቻችንን መንከባከብ ማለት ሌሎች ታማሚዎችንና ገመምተኞችን እንዲንከባከቡልን ማድረግ ማለት ነው።
አገር የምታድገውም የምትታደገውም በተንከባካቢዎቿ እጅ ነው!
ይህ የሚሆነው ደግሞ ራሳችንን ስንጠብቅና እርስ በርስ ስንጠባበቅ ነው።
እናስ? ተንከባካቢዎቻችን ራሳቸውን በጥንቃቄ ተንከባክበው፣ ሌላውንም አክመው በሕይወት ለመቆየት ምን ያህል ተዘጋጅተዋል?
እኛስ ተንከባካቢዎቻችንን ለመንከባከብ ምን ያህል ዝግጁ ሆነናል?
Filed in: Amharic