>
5:26 pm - Monday September 17, 3387

እምነቴና ኮረና...!!!   (ዲያቆን ብርሃን ዘበአማን አድማስ)

እምነቴና ኮረና…!!!

  ዲያቆን ብርሃን ዘበአማን አድማስ
ኮረና ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ ግምቶቻችን ብዙ ጊዜ የተቀያየሩ ይመስለኛል፡፡ በተለይ ወደሀገራችን ገብቶ ጓዳችን አንኳኳ ከተባለ ጊዜ ጀምሮ የብዙዎቻችን ልብ ርዷል ተንቀጥቅጣል፡፡ በሚዲያ ብቅ የምንለው የእኔ ቢጤ ሰዎች ደግሞ መፍትሔ የመሰለንን ለማካፈል ሞክረናል፡፡ ሆኖም ጭንቀቱና ውጥረቱ እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አልመጣም፡፡
 በተለይ ከሰሞኑ በኢትዮጵያ ከ28 -30 ሚሊዮን ሰዎች ሊያዙ ይችላሉ የሚለው ሳይንሳዊ ግምት ብዙዎችን እንዳስጨነቀ ይሰማኛል፡፡ አንዳንዶችም በውስጥ መስመር ጭንቀታቸውን አጋርተውኛል፡፡ ከዚህ ጋር ዐለምአቀፍ የሆኑ የሴራ ትንታኔዎች፣ ሳይንስን መሠረት ያደረጉ የምሁራን መላምቶች፣ ሁኔታዎችን ሁሉ ተጠቅመው ዐለምን ወደ አንድ እጅ አዙር አስተዳደር ለመክተት የሚታትሩ የቴክኖራሴ አቀንቃኞችን የሚቃወሙ ምሁራንና ሌሎችም የየመሰላቸውን ይናገራሉ፤ ብዙዎችም እነዚህን ሁሉ በማድመጥም ይታወካሉ፡፡ እኔም ራሴ የብዙዎችን ሰምቻለሁ፡፡ ከዚህ ሁሉ ጋር ደግሞ ቫይረሱ አይተላለፍበትም ተብሎ በሚገመተው እንደሚተላለፍ ሲነገር፣ ቤት የዋሉትም ሰዎች ሳይቀር ሲያዙ፤ ባሕል መድኃኒት አዋቂዎችም የየራሳቸውን የመፍትሔ ሀሳብ ከተፈጠሩባቸው የአለመደመጥ ቅሬታዎች ጋር ሲሰነዝሩ ብዙዎችን ያስጨንቃል፤ ይረብሻልም፡፡ አኔም ደግሞ በዚህ ጭንቅ ጊዜ ስለሁኔታው የማምነውን የማስበውን ለምን አላካፍልም ብዬ አሁንም በጽሑፍ መጣሁ፡፡
እምነቴ ያልኩትም እምነቴ ስለሆነ ብቻ ነው፡፡ ያመንኩትም ከሚታመኑት ስላገኘሁት ነው፡፡ ባለፈው ዐመት መገባደጃ ላይ ከማምንባቸው አበው ከዛሬ ስምንት ዐመት በፊት ጀምሮ የሰማኋቸውንና በደንብ ሰከታተላቸውና ሲፈጸሙ ያየኋቸውን ነገሮች መሠረት አድርጌ ማስጠንቀቄ ማሳሰቤ የሚታወስ ይመስለኛል፡፡ በዚሁ መሠረት ስለኮረናም ከሰማሁት ውስጥ እኔ የተረዳሁበትን መንገድ ላቅርብ፡፡ አስተውሉ፤ ቃል በቃል የሰማሁትን ሳይሆን የሰማሁትን የተረዳሁበትን ነው የማካፍለው፡፡ ከዚያ በፊት ግን የገዳም አባቶች መልእክት የሚለው በርከት ብሎ ነገር ግን መልእክቱ ተለያይቶ ስለማየው አንድ ነገር ልጠቁም፡፡ ምክንያቱም ለአባቶች የሚናገረው እግዚአብሔር ከሆነ ቢያንስ የመልእክቱ ጭብጥ ሊለያይ አይችልም ነበር፡፡ ተለያየ ማለት ትክክል ያለሆኑ ስዎች መልእክትም አለ ማለት ነውና፡፡
ሁለት ነገር ከስንክሳር
በስንክሳር ተጽፈው ከማነባቸው ሁለት ነገሮች የአሁኑ ዘመናችን ውዝግብ ለማስረዳት የሚጠቅሙ ይመስለኛል፡፡ የመጀመሪያው ታናሹ ቴዎዶስዮስ የገጠመው ታሪክ ነው፡፡ ንጉሡ ደግ ቢሆንም ልጅ አልነበረውም፡፡ ታዲያ እርሱ ሳይጨነቅ ሌሎች ተጨነቁ፡፡ ስለዚህም ከሕግ ሚስቱ ውጭ ሄዶ ልጅ እንዲወልድ መከሩት፡፡ እርሱ ምክሩን ለመቋቋም ቢሞክርም ጫናው በረታበት፡፡ በዚህ ጊዜ ወደ ገዳመ አስቄጥስ አባቶች ላከ፡፡ ገዳማውያኑም እግዚአብሔር ልጅ አልሰጥህም ብሎሃልና አርፈህ ተቀመጥ ብለው ላኩበት፡፡ እርሱም ምክሩን ተቀብሎ አርፎ ተቀመጠ፡፡ ሆኖም ገፋፊዎቹ እንደገና አስጨነቁት፡፡ እግዚአብሔር ለእርሱ ልጅን እንደማይከለክለው አሳሰቡት፡፡ አንተ ደግ ነህና በዙፋንህ የሚተካ ደግ ልጅ ያስፈልግናል እያሉ አጓጉት፡፡ በዚህ ላይ ብዙ እናውቃለን እኛንም እግዚአብሔር ያሳየናል የሚሉ አይጠፉበትም፡፡ እርሱ ግን አሁንም በምናኔያቸው ወደሚታወቁትና በእግዚአብሔር ስም የራሳቸውን ስሜት ወደማይጭኑት አባቶች ድጋሜ ላከ፡፡ ድጋሜ የተላኩት መልእክተኞች ወደ ገዳሙ በደረሱ ጊዜ በመጀመሪያው መልእክቱ ወቅት የእግዚአብሔርን መልስ የተናረው አባት አርፎ ተቀብሮ ነበር፡፡ ሁለተኛውን መልእክት የተቀበሉት አባቶች የመጀመሪያውን ቢጠራጠር አይደለም ደግሞ የላከው ብለው መልእክተኞቹን ይዘው ወደዚያ አባት መቃብር ሔዱና ንጉሡ ድጋሜ የላከውን ደብዳቤ መቃበሩ ላይ አስቀመጡት፡፡ ያ አባትም ከመቃብሩ በእግዚአብሔር ኃይል ተነሥቶ ለምን ሁለተኛ ላከ? እግዚአብሔር ልጅ አልሰጥህም ብሏል ብለን ነግረነው የለምን? የሚቀጥለው ትውልድ በሃይማኖት የሚዘብት፣ በክርክርና በኑፋቄ የሚጠቃ፣ ለሃይማኖት በመከራከር ሰበብ እግዚአብሔርን የሚሰድብ ስለሆነ የአንተ ልጅ ከእነርሱ እንዳንዱ ሆኖ ሲሰድበኝ ማየት ስለማልፈልግ ልጅ አልሰጥህም ብሎሃል እግዚአብሔር ብላችሁ ንገሩት ብሎ ያ አባት ተመልሶ አንቀላፋ፡፡ ሁኔታው መልአክተኞቹንም አስደነገጠ፣ አስገረመም፡፡ ንጉሡም ሲሰማ ተደንቆም አዝኖም መልእከቱን ተቀብሎ አርፎ ተቀመጠ፡፡
ሁለተኛው ታሪክ ደግሞ ታላቁ አባ መቃርሰ ከፈጸማቸው ገቢረ ተአምራት በአንዱ የተገለጠ ነው፡፡ በስንክሳሩ እንደተገለጠው አውሲም ይባል በነበረ ሀገረ ስብከት አንድ ባሕታዊ መነኩሴ ተነሥቶ ብዙ ሕዝብ ካስከተለ በኋላ ያ ያደረበት መንፈስ ቀስ ብሎ ትንሣኤ ሙታንን አስካደው፡፡ ሕዝቡም እርሱን ተከትለው ካዱ፡፡ የሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ የነበረው ትክክለኛውን ትምህርት ቢያስተምርም ብዙ ሰው ባሕታዊውን ተከትሎ አልሰማው አለ፡፡ በዚህ የተጨነቀው ሊቀ ጳጳሱም ነገሩን ገልጦ ወደ አባ መቃርስ ላከ፡፡ አባ መቃርስም ሊቀ ጳጳሱን ረድቶ ሕዝቡን ከጥፋት ለማዳን ወደ አውሲም ሔደ፡፡ አባ መቃርስ ባሕታዊውን አግኝቶ ሲያነጋግረውም የሞተ ሰው ተነሥቶ ካላየሁ አላምንም አለው፡፡ በዚህ ጊዜ አባ መቃርስ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ እግዚአብሔርም ከመሞቱ በፊት ከሐዲ የነበረ አንድ ሰውን ለአባ መቃርስ አሥነሣለትና በሲኦል ያየውን ሕይወት መሰከረ፡፡ ሰውየውም በምድር እንደገና መኖር ተሰጠውና በክርስትና አምኖ ተጠመቀ፡፡ አባ መቃርስም የምንኩስና ልብስ አለበሰው፤ ሰባት ዐመታትንም ቆይቶ ቸእንደገና አረፈ፡፡ ያ ባሕታዊና ተከታዮችም በዚህ ተአምራት ምክንያት በትንሣኤ ሙታን አመኑ፡፡
ከሁለቱም ታሪኮች ብዙ ነገሮች ልንማር ብንችልም እኔ ሁለቱን ብቻ ላስታውስ፡፡ የመጀመሪያው ነገር ባሕታዉያን ነን በሚሉ፣ ብዙ ተከታዮች ባላቸውና መኖራቸው እንኳ በማይታወቅ ፍጹማን መካከል ያለውን ልዩነት መገንዘብ በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡ ቴዎዶስዮስና ሊቀ ጳጳሱ የተጠቀሙትም በሕዝብ የሚታወቁ እናውቃለን የሚሉትን ሳይሆን ከሰው ተለይተው ሰው የማያውቃቸውን ተከታይ የሌላቸውን አባቶች ነው፡፡
አባቶችም ለሁለቱም ታዝዘዋቸዋል፡፡ በተለይ ሊቀ ጳጳሱን በሕዝቡም እንዳይይሰማ ያደረገውና አባ መቃርስ በተአምራት ድል የነሣው ባሕታዊ መነኩሴ ምን ያህል እንዳስቸገረ መረዳት ተገቢ ነው፡፡
ከዚሁም ጋር ሊቀ ጳጳሱ እንደ ባሕታዊው ሐሰተኛ ተአምር እንደ አባ መቃርስም እውነተኛ ተአምር ባለማድረጉ ሊነቀፍ አይችልም፡፡ እንኳን እርሱ በዘመኑ ተራራ የፈለሰለት ደጉና ጻድቁ አብርሃም ሶርያዊም እመቤታችን ተገልጣ ስታነጋግረው አንተ በአስተዳደር ሥራ ስላለህ ይህን ማድረግ አይቻልህም ብላ የመራችው እርሱ ወደማያውቀው ወደ ስውሩ ጻድቅ ወደ ስምዖን ጫማ ሰፊው ነበር፡፡ ፓትርያርኩ አብርሃም ሶርያዊ  ስምዖንን አግኝቶ ሲያናግረው ደሃ በሀገር አይኑር ብለህ ነው ብሎ እምቢ ካለ በኋላ እሽ ያለው እመቤታችን ልካኝ ነው ሲለው ነው፡፡ እሽ ካለም በኋላ ሕዝቡ እንዲሰበሰብና እግዚኦታ ምሕላ እንዲያደረስ አድርጎ ተአምራቱ በሕዝቡ እግዚኦታ ብቻ እንደተፈጸመ እንዲቆጠር አድርጓል፡፡ ምንም እንኳ አብርሃም ሶርያዊ እውነታውን ስለሚያውቅ በኋላ አጽፎት ቀጣዩ ትውልድ ቢያውቅም በጊዜው ግን ከአብርሃም ሶርያዊ ውጭ የሚያውቅ አልነበረም፡፡
ስለዚህም ሁለቱም ዐይነት አባቶች በገዳም አካባቢ እንደሚኖሩ ማወቅ በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡ ምክንያቱም ስሕተቱ የገዳሙ ወይም የብሕትውናና የምንኩስና ሳይሆን ገዳም ገብተው ወይም ባሕታዊ ነኝ ወይም እግዚአብሔርና ቅዱሳን ያናግሩናል በሚሉ የሳቱ ሰዎች የሚነገሩ እጅግ ብዙ የስሕተት መልእክቶች ከጥንት እስካሁን አሉና መለየት በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡
ዳግመኛም ልክ የቴዎዶስዮስን ታሪክ እግዚአብሔር ያስጻፈው ለዚያ ዘመን ትውልድ ብቻ ሳይሆን ከዚያ ዘመን አንሥቶ እስከ ዕለተ ምጽአት ላለው ሁሉ ትውልድ ስለሆነ እኛንም ይመለከተናል ብዬ አምናለሁ፡፡ ስለዚህ ለሃይማኖት በመቆርቆርና በመቅናት ሰበብ ኃጢአት የምንሠራ ፣ ያልተገቡ ንግግሮችንና መጻጻፎችን፣ ክርክሮችንና ከለስላሳ ውሳጣዊ የተሳልቆ እና የአሽሙር ስድቦች ፊት ለፊት በባለጌ ስድብ እስከምንሰዳደበው ሰዎች ድረስ በእውነት ራሳችንን ማየትና ማስተካከል አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡ ለእኔ እንደሚመስለኝ ከሆነ ልክ በዚያ ዘመን እንደነበረው በእኛም ዘመን ሃይማኖት ሆነ ብለው በሚያጠፉት ብቻ ሳይሆን እናስጠብቃለን በምንለውና ለሃይማኖት ቆመናል በምንለውም ከፍተኛ መዋረድ ደርሶበታል፡፡ እንደ ቴዎዶስዮስ አድርጎ እግዚአብሔር የሚወዳቸው ደግሞ በማናውቀው መንገድ ይጠበቃሉ፡፡ ስለዚህ ለክርክራችንና ለውይይታችንም እግዚአብሔርን መፍራት ባይለየው መልካም ነው፤ እግዚአብሔርን ለአንተ ብየ ነው ብለን በማስረዳት ከፍርዱ ልናመልጥ አንችልምና፡፡ እንኳን ካልተገባ ነገራችን በስሙ ተአምራት እስከማድረግ ብንደረስም አላውቃችሁም ሊለን እንደሚችል አስቀድሞ አስጠንቅቆናልና፡፡
በእንተ ኮረና
ምንም አንኳ ከቅዱሳኑ በተጨማሪ የአቡሻሕር መምህራንም እንዲህ ያለውን ዘመን የሚረዱበት ዕወቀት ቢኖራቸውም በእኔ እምነት ኮረና ቅዱሳን በዓለሙ ትውልድ በሁላችን ያልተገባ ድርጊት ምክንያት በሚያዝኑት ሐዘን የመጣ በሽታ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ እንዲህ ያለ በሽታ ( ከአባቶች የሰማሁትን በተረዳሁበት መንገድ) የእግዚአብሔርን ሳይሆን የሰይጣንን ፈቃድ በመፈጸማችን ምክንያት እርሱ ሰይጣን እንዲቀጣን ተፈቅዶለት (እርሱ ባመጣው ቫይረስ ይሁን ባክቴሪያ) በሆነ ተሐዋስ የሚዳረስ በሽታ ነው፡፡ በእኔ እምነት የሳይንስ ሰዎች የተወሰኑትን መተላለፊያ መንገዶች ቢረዷቸውም ሁሉንም መንገዶች ሊረዷቸው አይችልም፡፡ በዘመናት በተፈጸሙ ታሪኮች ውስጥ ክፉው መንፈስ በሚያመጣቸው መቅሰፍቶችም ጭምር እንደሚታወቀው እርሱ ራሱ በሕመሙ ባደረባቸው ሰዎችም ከዚያ ውጭ በሆነ መንገድም ሰዎችን እያጠቃ ሲጥል ኖሯል፤ የአሁኑም የኮረና በሽታም ከዚህ የተለየ እንዳልሆነ ለመረዳት አያዳግትም፡፡
መጠበቂያው
ታዲያ እንዲህ ያለ በሽታ ብዙ ጊዜ በመጠንቀቅም የሚድኑበትም ነው፡፡ እኔም ራሴ ከልጅነቴ ጀምሮ ለዚህ ዐይነት ባሕል እንግዳ ባልሆንም አሁንም ስለሁኔታው ያወቅሁት ቀደም አድርገው በምችለው መጠን እንድጸልይ እንድበረታና እንድጠነቀቅና እንድታዘዝም ጭምር አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ሁሉ ከሚልኩልኝ አባቶቼ ነው፡፡ እነርሱን በደንብ ስለማውቃቸው እነርሱ ካሉት ምክር በምንም ፈቀቅ አልልምና እምነቴን ለማካፈል የተነሣሁትም ለዚህ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ጠባቂው እምነት መሆኑ የታወቀ ነው፡፡  እንዲህ ያለው መቅሰፍት የሚመጣው ራሱ በአለመታዘዝ ስለሆነ መፍትሔው እውነተኛ ንስሐና መታዘዝ ነው፡፡ በብዙ ጊዜ አለመታዘዝ የመጣ መቅሰፍት ለመዳን ተስፋ ያላቸውን እንኳ በትንሽ አለመታዘዝ ሊቀስፍ ይችላል፡፡ ይህን ደግሞ ከሎጥ ሚስት መማር ይችላል፡፡ ምክንያቱም በትልቁ ኃጢአት ከመጣው መቅሰፈት ልትድን መላእክት ቢሸከሟትም ዞር ብላችሁ አትዩ የምትል በጣም ቀላል ትእዛዝ ተላልፋ የጨው ሐውልት መሆኗን እናውቃለንና፡፡ አሁንም በእኔ እምነት ባለመታዘዝ የመጣን እንደገና በአለመታዘዝ አናመልጠውም፡፡ የሚሻለው በየዋሐት ሆኖ መታዘዝ ነው፡፡ ከመጠናቀቅ መታዘዝ ሁልጊዜም ይሻላል፡፡
ከዚሁ ሳልወጣ አንድ ነገር ማስታወስ የሚገባ ይመስለኛል፡፡ ዘመናዊው የመጨባበጥና የመተቃቀፍ (ኸግ) ሰላምታ ከተሞቻችን ከመውረሩ በፊት የሀገራችን ሰላምታ በርቀትና ባለመነካካት ነበረ፡፡ ይህም ዝም ብሎ የተፈጠረ አይደለም፡፡ መነሻው እነዚሁ ነገሮች ናቸው፡፡ ባለመነካካቱ ሦስት መሠረታዊ ጥቅሞችን ያገኝ ነበር፡፡ የመጀመሪያው ከሰዎች መካከል ማን በምን ዐይነት መንፈስ እንደተያዘ ማወቅ ስለማይቻል አንዳንድ መናፍስትን ባለመነካካት ከትንኮሳቸው ወይም ከፈተናቸው መጠበቅ ይቻል ነበር፡፡ ሁለተኛም በመነካካት በቀላሉ ከሚተላለፉ በሽታዎች መጠበቅ ይቻል ነበር፡፡ ሦስተኛው ደግሞ ከሽንገላ ሰላምታም መዳን ይቻላል፡፡ በልብ ቅሬታ ወይም ደስ አለመሰኘት እያለ መሳምን ያህል ሽንገላ ሊኖር አይችልምና፡፡ በገጠር መሳሳም የሚኖረው ብዙ ጊዜ ተለይተውት ናፍቀውት ያገኙትን ዘመድ በእውነትና በፍቅር  እንጂ እንዲሁ በየዕለቱ የሚያገኙትንና እንደ እኛ ትውልድ አንዳንዶቻችን የምናደርገውን የለበጣውን  ዐይነት አልነበረም፡፡ የእኛን ትውልድ ካየነው ደግሞ ዝሙት ቀስቃሽ ከሆነ (የኸግ) ባሕልም ብንላቀቅ ምን ያህል ጠቃሚ ነበር፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ እግዚአብሔር በዚህ መንገድ ካሳየን እንደ እኔ ይህን ትርጉም አልባና የለበጣ ወይም ደግሞ ጾር ቀስቃሽ የሆነውን ብንቶወውና ወደ ቀደመ ልማዳችን ብንመለስ ምንኛ ጥሩ በሆነ ነበር፤ እግዚአብሔር ይርዳን፡፡
እግዚአብሔርን ተስፋ እናድርግ
በእኔ እምነት (ከሰማሁት በተረዳሁት) በሸተኞቹ በምርመራ የታወቁትና በክትትል ያሉት ብቻ አይመስሉኝም፡፡ የገባበት ጊዜም ቀደም ያለ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ እርሱ መሆኑ ሳይታወቅ የቀሰፋቸውም ብዙ ሳይሆኑ አይቀርም፡፡ ይህም በእኛ ሀገር ብቻ ሳይሆን በሌሎች ሀገሮችም ጭምር ነው፡፡ ሆኖም በሳይንሳዊ ግምት እንደተሰጠው 28 – 30 ሚሊዮን ኢትዮጵያዊ ይያዛል የሚለው የሚሠራ አይመስለኝም፡፡ መቅሰፍት ባይሆን ሊሆን ይችል ነበር፡፡ ይህ ግን መቅሰፍት ስለሆነ ምንም ያህል የማንታዘዝ አመጸኞችና ደፋሮች ብንሆንም ለአባቶቻችን ሲባል በሌላው ሀገር የሆነውን ያህል ሊሆን አንደማይቻል አምናለሁ፡፡ ከሌላው ዘግየት ብሎ የገባውም አንዱ ለዚሁ ይመስለኛል፤ የሚይዝ ይዞት፡፡
በዚህም ላይ አሁን ከአንድ ሳምንት በኋላ ጌታችን ስለእኛ በፈቃዱ የተቀበለውን መከራ የምንሳተፍበት ቅዱሱ ሳምንት ሕማማት ስለሚጀምር ከሆሣዕና በኋላ ጉልበቱ ይሰበራል፤ ኃይሉም ይደክማል፤ እስከዚያ ካልበረታብን ከዚያ በኋላ ከእኛም ከዐለምም ይከለከላል ብዬ አምናለሁ፡፡ ምንም እንኳ ከለከፋቸው (በበሽታው ከተያዙት) አንዳንዶቹን መጉዳቱ የማይቀር ቢሆንም ከዚያም እርሱ ባወቀ እንደ ገድል የሚቆጠርላቸውንና አንዳንድ ዐመፀኞችንም (አሁንም ለመታዘዝ ልቡናችን የሚቸገረውን) መለካከፉ የማይቀር ቢሆንም እንደ እስካሁን መጋለብ እንዳይችል ሆኖ ይቀየዳል፤ ወደመኖሪያውም ማዝገም ይጀምራል፡፡ ከዕለተ አድኅኖ ከስቅለት፤ ከዕለት ኅሪት ከትንሣኤ በኋላ ደግሞ ከለከፋቸው ውጭ እንዳይነካ ጨርሶ ይከለከላል ብዬ አምናለሁ፡፡ አምናለሁ ነው ያልኩት፤ ተብላችኋል ወይም አስደርጋለሁ አይደለም፡፡ ይህን ግን በጥብቅ አምናለሁ፤ በእርሱም ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ኮረና አለፈ ማለት ግን ሌላ መቅሰፍ አይታዘዝም ማለት አይደለምና ሁልጊዜም ወደ እግዚአብሔር እንመለስ፤ አንጠንቀቅ፤ ሕጉን በመፈጸም እንጠበቅም፡፡
ርኅራኄና ጥንቃቄ
ይህም ሆኖ ግማሽ ቀን እንደቀረው እግዚአብሔር ተገልጾ ቢነግረን እንኳ ቀኑ አጭር አይምሰለን፡፡አይደለም  በግማሽ ቀን በአንድ ሰዓት በመቶ ሺሕ የሚቆጠር የሰናክሬምን ሠራዊት እግዚአብሔር ምን እንዳደረገው እናውቃለንና፡፡ ቦሦሰት ቀናት ስንት ሺሕ የእሥራኤል ሰዎች እንደተቀሰፉም አንረሳውምና፡፡ በግማሽ ቀን ሃያ አራት ሺሕ ሰዎች እንደረገፉ ተመዝግቧልና፡፡ ስለዚህ በእግዚአብሔር ፊት አጭር ረጂም የሚባል ሰዓት የለም፡፡
ነገሩን የሚያስተካክለው የእኛ መመለስና የእርሱ ምሕረት ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ መዘናጋቱ የሚጠቅም፣ ቸለተኝነቱም የሚረባን አይመስለኝም፡፡ ሳይደናገጡና ሳይረበሹ ተገቢውን ማድረግ ከባድና አስቸጋሪ አይመስለኝምና በሚቻለን ሕሊናችንን ቀና አድርገን ለአንድም ቀን ቢሆን ብንታዘዝ መልካም ነው፡፡ ንስሐ እንግባ፣ እንዲራራልን ደግሞ ለሌሎች ይልቁንም ተስፋ ለማይታያቸው እንራራ፡፡ ለገዳማውያን፣ ለአብነት መምህራንና ተማሪዎች፣ በየመንደራችን ላሉ ችገረኞች በተለይም በይፋ ለልመና ላለውጡ ከልብ እንራራ፤ ለቤተ ክርስቲያን ያለ ማቅማማት እንታዘዝ፡፡ አናጉረምርም፡፡ የሰዎችን ኃጢአት እየቆጠርን ራሳችንን የምንሻል አድርጎ እንደማሰብ ያለ ሌላ ምንም ዓይነት ከባድ ኃጢአት የለምና ዐይኖቻችን ወደረሳችን ይመልከቱ፤ ራሳችንንም ብቻ በመውቀስና በመናዘዝ በመታዘዝም ከመቅሰፍቱ ለማምለጥ እግዚአብሔርን እንለማመጥ፡፡ የማይታዘዙትን ለመቅጣት ለእግዚአብሔር ፍርድ አናስተምረውምና ኅሊናችን እናርመው፤ አፋችንም እንከርክመው፡፡
ለቅዱሱ ሳምንት ለሰሙነ ሕማማት፤ ለዕለተ አደኅኖ ለስቅለት በመጨረሻም ለዕለት ኅሪት ለዕለተ ኃይል ለብርሃነ ትንሣኤው እግዚአብሔር በሰላም ያድርስን፤ አሜን፡፡
Filed in: Amharic