>
2:02 pm - Monday January 30, 2023

አሁንም እምነት ከላይ ጥንቃቄ ከታች  (ሊቀ መምህር አባይ ነህ ካሴ)

አሁንም እምነት ከላይ ጥንቃቄ ከታች

 

 ሊቀ መምህር አባይ ነህ ካሴ
ከሰፊው ስንነሣ እምነት ከእግዚአብሔር ጋር ላለን ግንኙነት ሁሉ መሠረቱ ነው፡፡ ንጽሕት ቅድስት እምነት ስትኖር ምግባርን ትወልዳለች፡፡ በዚህም ምግባር እና እምነት የማይነጣጠሉ ይኾናሉ፡፡ አመነ ሲባል አደረገ ማለትን ያጠይቃል፡፡ መለመላውን የቆመ እምነት ረብ የለሽ ነው፡፡ ለምሳሌ የአጋንንት እምነት ይጠቀሳል፡፡ እስኪንቀጠቀጡ ድረስ ያምናሉ ይላል ታላቁ መጽሐፍ፡፡ ያዕ ፪፥፲፱። አጋንንት ወይ ንስሐ አይገቡ ወይ ምሕረት አይጠይቁ፡፡ ግን አንተ የእግዚአብሔር ልጅ እንደኾንህ እናምናለን እስከማለት ይደርሳሉ፡፡ ሉቃ ፬፥፵፩። ይህ ዕውቀት ግን አይረባቸውም፤ ምግባር አልቦ ነውና፡፡
በጎ ለማድረግ ዐውቆ ለማይሠራው ኃጢአት ነው ሲልም መጽሐፋችን ያክልበታል። ያዕ ፬፥፲፯። እምነት ከሌለ ምግባር የቱንም ያኽል ሠናይ ቢኾን አይጠቅምም፡፡ ምክንያት፡- ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልምና፡፡ ዕብ ፲፩፥፮። ደግሞም ቅዱስ ጳውሎስ “በእምነትም ያልኾነ ሁሉ ኃጢአት ነው” ማለቱን ልብ እንበል። ፩ቆሮ ፲፬፥፳፫። ለዚህም ነው ጥንቃቄ በእምነት ካልኾነ አቅጣጫውን ይስታል የምንለው፡፡ በእምነት ጥላ ሥር ኾኖ መጠንቀቅ የተገባ ሲኾን ጥንቃቄን ከላይ እምነትን ተከታይ ማድረግ ከመጣ የበደል በደል ይኾናል፡፡
ዘወትር በቅዳሴያችን ገባሬ ሠናዩ ቄስ “አአምን አአምን አአምን ወእትአመን እስከ ደኃሪት እስትንፋስ – አምናለሁ፣ አምናለሁ፣ አምናለሁ፤ እስከ መጨረሻዪቱ ሕቅታ እታመናለሁ” ይላል እንጅ እጠነቀቃለሁ እጠነቀቃለሁ እጠነቀቃለሁ እስከመጨረሻዪቱ ሕቅታም እጠነቀቃለሁ አይልም፡፡ ከዚህም በላይ ተሰጥዖ ተቀባዩ ሕዝብ በተደጋጋሚ ጊዜ እምነቱን ይገልጣል፡፡
በሰሞኑን ሁኔታ ጥንቃቄ እምነትን ልርገጥሽ እያለቻት ልቧ አብጦባት ታየችኝ፡፡ ከልኩ በላይ ያለፈ ሁሉ ቅቡልነት የለውም፡፡ አንድን ነገር ከልኩ በላይ ካከበርነው ጣዖት ይኾንብናል፡፡ ከልኩ ካሳነስነውም ኃጢአት ይኾንብናል፡፡ ለዚህም ነው ከእምነት የተነሣ እንጠነቀቃለን እንጅ ከጥንቃቄ የተነሣ አናምንም የምንለው፡፡ አሚን ያለው ሁሉ ጥንቃቄ አለው፡፡ ስለዚህ አሚን እንዲኖረው ስታደርገው እንደ ሌሎቹ ምግባራተ ሠናያት ጥንቃቄም ዘርፏን ይዛ ትገባለች፡፡ ምጽዋት ከእምነት አትበልጥም፡፡ ጾምም ከእምነት አትበልጥም፡፡ ጸሎትም ከእምነት አትበልጥም፡፡ እነዚህ ሁሉ ግን በእምነት የተነሣ ሲፈጸሙ ቦታቸውን ያገኛሉ፡፡ ጥንቃቄ ደግሞ ከጾምም፣ ከጸሎትም፣ ከምጽዋትም ዝቅ ብላ ያለች ደግ ሥራ ናት፡፡
ኹለት ጉዳዮች ላይ ብዥታ መፈጠራቸውን ታዝቤአለሁ፡፡ አንደኛ ቋሚ ሲኖዶሱ ያወጣው የቤት ዋሉ መመሪያ ጥቅልል ስለኾነ ዘርዘር ተብሎ ሊቀርብ ይገባል መባሉ ሲኾን ኹለተኛው ደግሞ ከመጠኑ ያለፈ ጥንቃቄ ግኖስቲካዊነት ይኾናል መባሉን ይመለከታል፡፡
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ በኮቪድ-፲፱ የተነሣ ዝርዝር ውሣኔ ሰጥቶ ነበረ፡፡ ውሣኔው ከዚያ በኋላም እንደአስፈላጊነቱ ውሣኔዎች ሊወሠኑ እንደሚችል አመላካች ነበረ፡፡ ሰላምታ እንደ ሰሙነ ሕማማቱ በእማኄ እንዲኾን፣ በዓለ ንግሥ እንዲተላለፍ፣ የሕዝብ ጉባኤያት እና ጉዞዎች እንዲቋረጡ፣ ሥጋ ወደሙን የሚቀበሉ ብቻ ወደ ቤተ መቅደስ እንዲገቡ ሌላው ሕዝብ በውጭ ዘርዘር ብሎ ቆሞ እንዲያስቀድስ፣ . . . ፡፡ ግሩም ውሣኔዎች ናቸው፡፡
ከዚያም የነገሩን መባባስ የተረዳው ቋሚ ሲኖዶስ ተጨማሪ መመሪያ ማስተላለፍ አስፈላጊነቱ ስለታየው አንድ ድፍን ያለ መመሪያ አስተላለፈ፡፡ በቤታችሁ ቆዩ የሚል ኾነ፡፡ የፊተኛው የምልዐተ ጉባኤውን ውሣኔ የሚሽር ይመስላል፡፡ እዚህ ላይ የሲኖዶሳዊ መዋቅር ጥያቄም ያስነሣል፡፡ የሕግ አውጭ የሥልጣን ተዋረድ መጠበቅ አለበትና፡፡ የኋለኛው የፊተኛውን ይሽራል የሚል አጠቃላይ የሕግ መርሕ አለ፡፡ ከዚያ አንጻር ሥልጣኑ አለው ከተባለ ሽሮታልን ያስከትላል፡፡ ሥልጣኑ የለውም ከተባለ ደግሞ ምልዐተ ጉባኤ እስኪሰበሰብ ድረስ መሸጋገሪያ ነው ሊል ይችላል፡፡ ያኛው ቤተ ክርስቲያን መሔድን አይከለክልም፤ ይኽኛው ግን ድፍን ያለ አትሒዱ ባይ ነው፡፡
❖ በቤታችሁ ቆዩ ሲል አስቀዳሾችን ሁሉ ነውን?
❖ በቤታችሁ ቆዩ ሲል ቆራብያኑንም ይጨምራልን?
❖ ክርስትና የሚነሡትንስ?
❖ ብዙዎቹ በሀገር ቤት ያሉት አብያተ ክርስቲያናት ሰፋፊ ቅጽረ ግቢ አላቸው፡፡ በሰፋፊዎቹ ቅጽሮቻቸው ምእመናን ርቀት ጠብቀው መቆም አይችሉምን?
❖ ተዝካር እና ቀብር እንዴት ነው የሚፈጸመው?
❖ የጠበል ቦታዎች ዕጣ ፋንታ ምንድን ነው?
❖ ውሣኔው በገጠር አብያተ ክርስቲያናት እንዴት ተግባራዊ ይደረጋል?. . . እና የመሣሰሉትን ጥያቄዎች መመለስ ይገባል የሚል አሳብ ተነሣ፡፡ በዚህ ምክንያት የሲኖዶስን ውሣኔ መቃወም እንደኾነ ተደርጎ ከግራ ከቀኝ መላጋት መጣ፡፡ መልሱም ቀላል ነው፡፡ መሠረታዊ ልዩነት ከሌለ የፊተኛው ውሣኔ እንደተጠበቀ ኾኖ ማለት እና ጥቂት ልዩነቶች ካሉ እነርሱን የመዘርዘር ጉዳይ ነው፡፡
ጥያቄ መጠየቅ ኢሲኖዶሳዊነት አይደለም፡፡  አይደለም በፓትርያርክ የሚመራ እና ቢያንስ ዐራት ብፁዓን አበው ውሣኔ የሚያስተላልፈው ቋሚ ሲኖዶስ ቀርቶ አንድ ካህን እንኳ ጊዜአዊ እግድ በምእመናን ላይ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ይህንን አምናለሁ እቀበልማለሁ፡፡ አንድ የገጠር ቄስ በዓል የሻረ ገበሬም ይኹን ሌላ ሠራተኛ በድንገት ቢያገኝ ገዝቼሃለሁ ብሎ ያስቆመዋል፡፡ ይህንን እያየሁ ያደግሁ እንደመኾኔ ከፍ ያሉት ሲያደርጉት የምቃወምበት አንዳችም ምክንያት የለኝም፡፡ ስንኳን በጉባኤ የተሰየሙት አበው አንዱ ኤጲስ ቆጶስ ብቻውን ስንት ዓይነት ቀኖናዊ ርምጃ ሊወስድ እንደሚችል እናውቃለን፡፡ ውሣኔው በይግባኝ ካልተሻረ በቀር ቋሚ ሊኾን የሚችልበትም ሥልጣን አለው፡፡
ግን ጥያቄ ጠይቄአለሁ፡፡ መጠየቅ አለመታዘዝ አይደለም፡፡ የጠየቅሁት የታዘዘውን እየፈጸምሁ ነውና፡፡ ዝርዝሩን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እያዘጋጁ ነው የሚል አንዳንድ ወሬ ተሰምቶ ነበር ከምን እንደደረሰ ባላውቅም፡፡ ከዚህ በመነሣት ሲወረወሩ የነበሩት ጦሮች ግን በርጥብ እንጨት እንዲህ ካደረጉ በደረቁማ እንዴት ያደርጉ ይኾንን ያስጠቅሳል፡፡ ችግር የሌለበትን ጥያቄ መጠየቄ እንዲህ ካስባላቸው ተሳስቼ ቢኾን ምን ሊያደርጉ ነበር? ያስብላል ለማለት ተጠቀሰ እንጅ ምስጢሩ ሌላ ነው፡፡ ወደ ኹለተኛው ልለፍ፡፡
ከመጠን በላይ መጠንቀቅ ግኖስቲካዊነት ነው የሚለውን አሳብ አንሥቻለሁ፡፡ ዛሬም አቋሜ ነው፡፡ ከእምነት ወደ ዕውቀት እናዘንብል ዓይነት አካሔድ አይሰባኝም (አይዋሐደኝም)፡፡ ሣር ቅጠሉ ሁሉ እምነትን አሽቀንጥሮ በሳይንሳዊ መንገድ ብቻ ራሱን ለማዳን ሲራወጥ ሳይ ልቤ ደንግጦብኛል፡፡ እንደዚህ ያለውን ደግሞ ዝም ብሎ ማየት አብሮ ማጥፋት መስሎ ተሰምቶኛል፡፡ እናም መልእክቴን በጊዜው አስተላልፌአለሁ፡፡ እንዲህ ማለቴም ሳይንስን ማውገዝ ተደርጎ እንዳይታሰብም አደራዬ ነው፡፡ የማወግዘው እንዳለ ሁሉ የምቀበለውም ብዙ አለ፡፡
ከመጠን በላይ በተዛነፈ ሥርዓት እምነትን እስከመጋፋት በሚደርስ ደረጃ ጥንቃቄ ላይ ማትኮርን መተቸት ማለት ጥንቃቄ በፍጹም እንዳታደርጉ፣ የአበውንም ውሣኔ እንዳትቀበሉ እስከማለት ተለጥጦ እየተተረጎመ ዛሬም ድረስ ይነሣል ይወድቃል፡፡ ይህ ደግ አልመሰለኝም፡፡ ስለ ጥንቃቄ ማስተማራችን እንደተጠበቀ ኾኖ እጅግ ከፍ ባለ ደረጃ ስለ እምነት ልናስተምር ይገባናል ማለት ካላግባባን ምን ማለት ይቻላል? በዚህም የተነሣ ብዙ የአንተም ተው የአንተም ተው ገላጋይ እግረ መንገዱንም ጎሸም እያደረገ የቻለውን ተረባርቧል፡፡ ክብር ሰጥቼ ተሰብስቤ ቆይቻለሁ፡፡ በሌላ ወገን ግን ሾላ በድፍኑ አባባሉ በአግባቡ ሳይጠቀስ እስካሁን አልቆመም፡፡ ከጠቀመ በመቀጠሉ ተቃውሞ የለኝም፡፡ እንዲህ በማለቴም አሁን ኧረ ተው ባይ መምጣቱ አይቀርም፡፡
እውነተኛ ተከራካሪ የሌላውን ተከራካሪ አሳብ በደንብ ሳይረዳ ነገሩን አይጀምርም፡፡ በተቃራኒው ባለ አሳብ ጫማ ውስጥ ገብቶ ለክቶ ነው የሚከራከረው፡፡ ከሣር ክዳን ቤት አንዲት ዘለላ ብቻ መዝዞ ስለቤቱ መከራከር ይከብደዋል፡፡ ቢያንስ ለናሙናነት በሚበቃ ደረጃ መያዙን ማረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ የተባለውን ትተህ ወዳልተባለው አዘንብለህ ስትሞግት ብትውል አንተም ልክ አትኾንም ሙግትህም ውኃ አያነሣም፡፡ ጭብጡን ስተኸዋል ይልብሃል ሕጉ፡፡
Filed in: Amharic