>

ያልተበረዙ የዘመን እንጉርጉሮዎች! (አሰፋ ሀይሉ)

ያልተበረዙ የዘመን እንጉርጉሮዎች!

 

 

አሰፋ ሀይሉ
  • የምሥራቅ ጎጃም ገበሬዎች የፖለቲካ ግጥሞች – ከዘመነ አፄ እስከ ኢህአዴግ
* ‹‹ምሽቴን ማን ተኝቷት?›› አይሉም፣ አይሉም
‹‹መሬቴን ማን አርሶት?›› አይሉም፣ አይሉም
‹‹አጥሬን ምን ነቅንቆት?›› አይሉም፣ አይሉም
ቀን የከፋ ለታ ይደረጋል ሁሉም፡፡
የዛሬ 20 ዓመት በፈረንጆች ሚሊኒየሙ ማብቂያ ገደማ በጀርመን ሐምቡርግ ዩኒቨርሲቲ ለሚገኘው የአፍሪካና የኢትዮጵያ ጥናቶች ተቋም አንድ መሳጭ የጥናት ጽሑፍ ቀርቦ ነበር፡፡ የጎጃም ገበሬዎች ብቸኛ ሀብታቸው በሆነው ዘይቤያዊና ቅኔ ለበስ አማርኛ ቃልግጥም (ስነቃል) በመጠቀም ስሜትን የሚኮረኩሩና ልብን የሚነኩ መልዕክቶችን ያስተላለፉባቸው የቃል ግጥሞች፡፡ አቅራቢው ዶ/ር ጌቴ ገላዬ የተባሉ ኢትዮጵያዊ ምሁር፣ የጥናቱ ርዕስም ‹‹ከ1983 የመንግሥት ለውጥ በኋላ የምሥራቅ ጎጃም ገበሬዎች የገጠሟቸው ፖለቲካዊ ግጥሞች›› የሚል ነበር፡፡
በጥናቱ የተካተቱት ከምሥራቅ ጎጃም ገበሬዎች የተሰበሰቡት እነዚህ የቃል ግጥሞች – በተለይ ከ1983 ወዲህ ባሳለፍናቸው ዓመታት – በገጠሩ ማኅበረሰብ ዘንድ እየተባባሰ የመጣውን መንግሥትን የመጠራጠር፣ የእርስበርስ ጥላቻና ተቃውሞ፣ የምግብ እጥረት፣ የምርት ማሽቆልቆል፣ ድህነት፣ ስደትና በሰላም አብሮ የመኖር ተስፋ መጨለም በገሃድ ያሳያሉ፡፡ያን የዶክተሩን ጥናት ኋላ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም በአንጋፋ ምሁራኑ አርትዖት ሠርቶለት ለህትመት አብቅቶታል፡፡ አጥኚዎቹንና ዋነኛ ተናጋሪዎቹን በቅድሚያ እያመሰገንኩ ለዛሬ በቻልኩት መጠን ጥናቱን በአንድ ፖስት ሥር አጠቃልዬ ለወዳጆቼ ለማካፈል ወደድኩ፡፡ በጥቂት ትዕግሥት ከዘለቃችኋቸው፣ የቃል ግጥሞቹንና እንጉርጉሮዎቹን ልክ እንደ እኔው እንደምትወዷቸው ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ መልካም ንባብ፡፡
በእርግጥ የዚህ ጥናት አዘጋጆች ሥራዎች ውስጥ ስላልተካተቱ ትቼያቸው ነው እንጂ፣ በጎጃም ገበሬዎች አንደበት የተነገሩና ሳይረሱ ለዚህ ዘመን የበቁ – ቢያንስ ከ1899ዎቹ ጀምሮ – በየዘመኑ ስለተፈራረቁ የጎጃምም ሆነ የመላ ኢትዮጵያ አስተዳዳሪዎችና ነገሥታት በደልም ሆነ ምወድስ ብዙ እንደቅርስ የሚታዩ ስነቃሎችና የቃል ግጥሞች አሉ፡፡ ለአሁኑ ግን በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን ማብቂያ ግድም ከተነገሩትና አስቀድሞ በሰዉ ልብ ውስጥን የሥርዓት ውድቀት እንደሚፀነስ ከሚያመላክቱት በአጼ ዘመነ መንግሥት ከተነገሩ (እና በጥናቱ ከተካተቱት) ጥቂት ስንኞች እንጀምር፡፡
በአፄው ዘመን ምስኪኑ የጎጃም ገበሬ በዘመኑ የጭቃ ሹም፣ ነጭ ለባሽ፣ የጎበዝ አለቃ፣ ምስለኔ፣ አጥቢያ ዳኛ እየተባሉ ይሾሙ የነበሩት በገበሬው ላይ ላደረሱበት ሰብዓዊ በደል ብሶቱንና እሮሮውን በእንጉርጉሮ እንዲህ ብሎ ገልጾት እናገኛለን፡-
በሬዬን አረደው፣ ከብቴንም ነዳው፣ ምሽቴንም ተኛት
ጎጆዬን አቃጥሎ አስተኛኝ መሬት
ሲጨንቀኝ ሲጠበኝ ዘመድ አረግሁት፡፡
ታገር እኖር ብዬ፣ ልጅ አሳድግ ብዬ
ለጭቃው ዳርሁለት ምሽቴን እቴ ብዬ፡፡
‹‹ምሽቴን ማን ተኝቷት?››
‹‹በሬዬን ማን አርሶት?›› አይሉም፣ አይሉም
ቀን የከፋ ለታ ይደረጋል ሁሉም፡፡
በደርግ ዘመን ደግሞ በሕዝቡ ላይ በኃይል ለመተግበር የተሞከሩት ብዙ ጊዜ-አመጣሽ እንቅስቃሴዎች ወይም ወከባዎች (የግብርና ልማት ፕሮጀክቶች፣ የመንደር ምሥረታና የሰፈራ ፕሮግራሞች፣ የገበሬዎች ኅብረት ሥራ ማኅበራት እንቅስቃሴዎች፣ የመሬት ክፍፍልና አስተዳደራዊ አፈጻጸሞች፣ የግዳጅ ኮታ ክፍያዎች፣ የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላዎች፣ ወዘተ.) ገበሬውን አስመርረውት ነበር፡፡ በዚህ መሐል ለመንደር ምሥረታና ለሰፈራ ብለው የደርግ ካድሬዎች ቤቱን በግዳጅ ያፈረሱበት ገበሬ ብሶቱን፣ ምሬቱንና ቁጭቱን እንዲህ ብሎ በእንጉርጉሮ ገልጾት እናገኛለን፡-
መሬቴንም ውሰድ ደጄንም እረሰው
የምኖርበትን ቤቴን አታፍርሰው፡፡
ወይ አልተጣላን አልተደባደብን
ሰተት ብለው መጥተው ቤት አፍርሱ አሉን፡፡
እኽሉንም እንኩ፣ ልጃችንን እንኩ
የሬሳችንን መውጫ ቤታችንን አትንኩ፡፡
በኋላ ላይ ግን ሶሻሊስታዊው የደርግ መንግሥት መውደቅን ተከትሎ ደርግን በማሸነፍ ለጊዜውም ቢሆን መረጋጋትን ያመጣላቸውን የኢህአዴግ መንግሥትና በተለይም ደግሞ የትግራይን ተጋዳዮች (ተጋዳላዮች) በግጥም ማወዳደስ ጀምሮ ነበር የጎጃም ገበሬ፡-
ደስ ይበልህ ጎጃም ድፍን ኢትዮጵያ
ያ ቀማኛ መንግሥት ገባ ምድረ ትቢያ፡፡
ተጥዬ ነበረ እንደ አሮጌ ቁና
ብድግ አርጎ አነሳኝ ኤሃዴግ መጣና፡፡
ትግሬ ተንቀሳቅሶ ኤሃዴግ ባይመጣ
ትንሽ ቀርቶን ነበር ነፍሳችን ልትወጣ፡፡
እኛ ምንተዳችን ያ መጣ፣ ያ መጣ?
መንግሥቱ ወደቀ የማታ የማታ፡፡
አዲስ የመጣው ወያኔ መራሹ ኢህአዴግ በበኩሉ ሥልጣን ላይ እንደወጣ (በነገራችን ላይ ገበሬዎቹ ወያኔንም ሆነ የወያኔን መንግሥት በወንድ ፆታ ሳይሆን በአንስታይ ፆታ ነበረ የሚጠሩት – ‹‹ወያኔ ከመጣች ወዲያ…›› እያሉ!) – እና ኢህአዴግ ሥልጣን ላይ እንደወጣ ለጎጃም ህዝብ ብዙ ነገሮችን ቃል ገባ፣ ብዙ መልካም ብሥራቶችንም አወጀለት ለገበሬው፡- ህዝቡ ራሱ የሰላምና መረጋጋት ኮሚቴዎችን እንዲመርጥ፣ በደርግ ዘመን በኃይል ይተገበሩ የነበሩ የመሬት ድልድል፣ ኮታ፣ የግብርና መዋጮዎች፣ ያምራቾች የህብረት ሥራ ማኅበራት ሁሉ ሙሉ ለሙሉ እንዲፈርሱ፣ ገበሬዎች ቀድሞ በመንግሥት ትዕዛዝ በሰፈራ መንደር የሰሩትን ቤት አፍርሰው ያሻቸው ቦታ ሔደው ቤታቸውን እንዲቀልሱ፣ የግዳጅ ብሔራዊ ውትድርና ምልመላ እንደማይኖር፣ ወላጆች ልጆቻቸውን ለአቅመ አዳምና ሄዋን ባይደርሱም እንደፈለጉ እንዲድሩ፣ ባካባቢያቸው የሚንቀሳቀሱትን ሌቦችና ሽፍቶች ለማጥፋት ኢህአዴግና የኮር አባላት የሚባሉት አዳዲስ ምልምል ካድሬዎች ከጎናቸው እንደሚቆሙ፣ እና በተለይ ደግሞ ገበሬው የጦር መሣሪያ እንደፈለገው እንደሚታጠቅና ዲሞክራሲያዊ መብቱ እንደሚረጋገጥለት ተነገረው!
ተጠራጣሪው የጎጃም ገበሬ ግን ቀስ በቀስ ቢጠብቅ፣ ቢጠብቅ ሁሉም ስም እየቀየረ ያው የተለመደው አዋጅና ቃላት ብቻ ሲሆንበት.. ቀደም ሲል የጀመረውን ውዳሴ ጋብ በማድረግ… ነገሩን በግጥም እንዲህ በማለት ይገልጠው ጀመር፡-
እኔስ ኤሃዴግን ላመሰግነውም፣ ላማውም ቸገረኝ
አምኘ ብጠጋው ክላሽ ከለከለኝ፡፡
‹‹ዲሞክራሲ›› ብሎ አወጀ ለሕዝብ
ምንም ለማይጥፈው ምንም ለማያነብ፡፡
ኤሃዴግ ተመጣ አላረግሁም ካልሲ
ይዞልኝ የመጣ ባዶ ዲሞክራሲ፡፡
እንዲህ ለውጡን በትዝብት ማየት የጀመረው የጎጃም ገበሬ ብዙም ሳይቆይ ነ1983 እና በ1984 ዓ.ም. በየቀበሌው የተደረጉትን መጠነኛ የሜት ክፍፍሎች ተመለከተ፡፡ የመቴት ክፍፍሉ ባብዛኛው ባገር ሽማግሌዎች የተከናወነ ነው ቢባልም ሥልጣን ላይ የወጡትና አዳዲስ ሹመት የተሰጣቸው የኢህአዴግ ተመራጮችና የኮር አባላት፣ የኮሚቴ ሊቀመንበር፣ ሞቢላይዜሽን፣ ካድሬ፣ ምኒሻና ታጣቂ በሚባሉት አማካይነት ነበረ በተግባር ክፍፍሉ የተደረገው፡፡ ቀስ በቀስም በመሬት ክፍፍሉ ጊዜ ልክ በደርግ ዘመን ይደረግ እንደነበረው ለኢህአዴጎቹ ሹማምንቶችም ጉቦ መስጠት፣ ድግስ ማብላትና ማጠጣት፣ ወዘተ በግልፅም በድብቅም እንደ መደበኛ ተግባር መከናወን ጀመሩ፡፡ በዚህን ጊዜ የያዘው ወይ የተዛመደው ኮሚቴ የሌለው ምስኪን ገበሬ እንዲህ በማለት ነበረ ያንጎራጎረው፡-
ኮሚቴም ‹‹እጅ›› አለ፣ እኔም እጅ አጠረኝ
እፎካካው መሬት አምዘግዝጎ ጣለኝ፡፡
ለሊቀመንበሩ አንድ ባውንድ አጥቼ
ለኮሚቴዎቹ አንድ ጠርሙስ አጥቼ
ተማዞሪያው መሬት ቀረሁ ተለይቼ፡፡
እኔ ተኮሚቴ አበልጅ ብናሳ
ይሰጠኝ ነበረ ተድበሉ ማሳ፡፡
ተሰባት ኮሚቴ አበልጅ አጥቼ
አለ በቆሎ እሸት ከረሙ ልጆቼ፡፡
እና በዚህ ወቅት የኢህአዴግን ዘመን አመጣሽ የፖለቲካ ጣጣ ምንተዳዬ ብሎ ቀን ከሌት ከኑሮው ጋር ግብግብ መግጠሙን የተያያዘው አብዛኛው የጎጃም ገበሬ በለውጡ መጀመሪያ ኢህአዴግን እንዳላመሰገነ ሁሉ፣ ሲቆይ ግን ጠብ የሚል ነገር አጣበት፡፡ ገበሬው በለውጡ ማግስት ከልፈፋ በቀር ከቀድሞው የደርግ ዘመን የተለየ ምንም አዲስ አስተዳደራዊ አሰራርም ሆነ የኑሮ ብሥራት ሊያገኝ አልቻለም፡፡ እና በሚታወቅበትና በተለመደው የስላቅ አነጋገር – በደርግ ጊዜ በነበረ የቀድሞ ሹመኛ እንደተነገረ በማስመሰል – የጎጃም ገበሬ እንዲህ ሲል አንጎራጎረ፡-
ዋሽቼ እንዳልበላ ኢሠፓ ፈረሰ
አርሼ እንዳልበላ እጄ ለሰለሰ
ሰርቄም እንዳልኖር ኢህአዴግ ደረሰ
“ኧረ! ምን ይሻላል አብዬ መለሰ?”
ቀጠለና ደግሞ የ1989ኙ የኢህአዴግ ሹሞች የመሬት ሽግሽግ ፖሊሲ እንተገብራለን ብለው ተነሱ በምሥራቅ ጎጃም፡፡ በአማራ ክልል ብቻ በተደረገው በዚሁ የመሬት ሽግሽግ ፖሊሲ የወቅቱ የኢህአዴግ ሹመኞች ገበሬዎቹን በ3 ጎራ ከፈሏቸው፡- ቅሪት ፊውዳል፣ ቢሮክራት፣ እና ጭቁን ወይም ድሃ አርሶአደር በማለት፡፡ በዚህም የገጠር ቀበሌዎችንና ወረዳዎችን ማሸጋሸግ በሚል ማንንም ሳያማክሩ እነዚያ የኢህአዴግ ሹመኞች ያሰኛቸውን ቀበሌዎችንና መንደሮችን ከአንዱ ወደ ሌላው በማጠፍ መጠሪያ ስሞችን ሳይቀር እንደፈለጋቸው ለዋውጠዋል፡፡
ከምንም በላይ ግን ለመንግሥት ሳታሳውቁ የጦር መሳሪያ ደብቃችኋል ተብለው የተንገላቱ፣ የተገረፉና የታሰሩ ገበሬዎች ቁጥር በጣም ብዙ ነበር፡፡ ከመሬት ሽግሽጉ በኋላ መሬት የተወሰደባቸው የጎጃም ገበሬዎች በደላቸውንና አቤቱታቸውን ለማሰማት መንግሥት አለ፣ ፍትህ-ርትዕ አለ ብለው ወደሚያስቡት ወደ አዲስ አበባ በእግር ተጉዘው ነበር፡፡ የጠበቃቸው በፖሊስ ተከበው መረምረም፣ እንዲያም ሲል ተርበውና ተጠምተው ለሳምንታት ከተንገላቱ በኋላ የመሬት ሽግሽጉን ያፀደቀው እዚያው የክልላችሁ የአማራ መንግሥት ስለሆነ ባህርዳር ሄዳችሁ ጠይቁ የሚል ቀጭን መልስ ነበረ፡፡ ሲመለሱ የታሰሩም፣ የተደበደቡም ነበሩ፡፡
በዚህ ጊዜ በተለይ በገበሬው ዘንድ ለችግሮቻቸው በዋነኝነት ዝነኛ ሆኖ ብቅ ያለው ስም የኢህአዴግ ‹‹የኮር አባል›› ናቸው ተብሎ የገበሬው መሬት እየተቀማ የተላለፈላቸውና መሣሪያ ታጥቀው የሥርዓቱ ጆሮ ጠቢና በኃይል አስጠባቂ ሆነው የተገኙት ነበሩ፡፡ እና የጎጃም ገበሬ ቁጣ በእነዚሁ የኮር አባል ብሎ በጅምላ በጠራቸው የኢህአዴግ አስፈጻሚ ሹመኞች ላይ እየነደደ የሚከተሉትን ግጥሞች ገጥሞላቸዋል፡-
አሥራት ቀረ ብዬ አርፌ ስተኛ
ኮታ ቀረ ብዬ አርፌ ስተኛ
የኮር አባል መጣ የባሰው ቀማኛ
መሬቴን ወሰደው ሰፍሮ በመጫኛ፡፡
ጣሊያን አልመጣብን ተኩስ አልተተኮሰ
ወይ ወራሪ አልመጣ ችግር አልደረሰ?
በኮር የተነሳ አገሩ ፈረሰ፡፡
ወትሮም ነገረኛ ነበረ ተጥንት
ኮር ነው ያስቸገረን ጠማማው እንጨት፡፡
እኔስ አርስ ነበር የገበሬው ልጅ
እኔስ አርስ ነበር የገባሩ ልጅ
መሬቴን ቢለኩት ቢወስዱት ነው እንጅ፡፡
ቀጥሎ የቀረበው አንድ ግጥም ደግሞ መሬታቸው በኢህአዴግ ካድሬዎች በግድ የተወሰደባቸው የምሥራቅ ጎጃም ገበሬዎች የደረሰባቸውን አሳዛኝ ግፍና ኢሰብአዊ በደል ባጠቃላይ ለአገራቸው ለጎጃም ሕዝብ፣ በተለይ ደግመ ባካባቢያቸው ለሚኖሩ የማቻክል፣ የጎዛምን፣ የበረንታ፣ የጥላትግን፣ የእነሴ፣ የጎንቻ፣ የሣር ምድር፣ የአዋበል እና የአነደድ ወረዳዎች ወገኖቻቸው ጩኸታቸውንና ኀዘናቸውን አቤት የሚሉበት ግጥም ነው፡-
ይታይህ ማቻክል፣ ይሰማህ ጎዛምን
ይታይህ በረንታ፣ ይሰማህ ጥላትግን
እግዚዎ በል እነሴ፣ ጎንቻና ሣር ምድር
እግዚዎ በል አዋበል፣ እግዚዎ በል አነደድ
እንዴት ይወሰዳል መሬታችን በግድ?
ወይ አገሬ ኧረ! አገሬ ጎጃም
ወሰዱት መሬቴን እርስትና ጉልቴን
የራብ መከለያ ልብስና ቀለቤን፣
ወሰዱት መሬቴን ሰፍረው በገመድ
ተእንግዲህ ደካማው፣ ተእንግዲህ አሮጉ
ኧረ! ወዴት ልግባ? ኧረ የት ልሂድ?
እንዲህ እንዲህ እያለ የጎጃም ገበሬ የገጠመው ብዙ ነው፡፡ ያንጎራጎረው መዓት ነው፡፡ ጥቂቱን ብቻ ነው መርጦ ማቅረብ የሚቻለው፡፡ እንዲሁ ደግሞ በኢህአዴግ መሬታቸው የተወሰደባቸው የጎጃም ገበሬዎች የሞት ያህል ያስጨነቃቸውን የረሃብ አደጋ፣ የመኖር ህልውናቸው ያከተመ መሆኑ የተሰማቸውን ውስጣዊ ስሜት፣ እና ‹‹በዘመነ ወያኔ›› መሬታቸው የተወሰደባቸው ልጆቼን ምን ላብላቸው? በምን ላሳድጋቸው? እያሉ ብሶታቸውን በእንግርጉሮዎቻቸው ያሰማሉ፡፡ ተስፋ የቆረጠውም ከነጭራሹ በሮቹም እንደመሬቱ እንዳይወሰዱበት በመስጋት አምጡልኝ አርጄ ልብላቸው… በማለት የኢህአዴግ ካድሬዎችና የቀበሌ ተመራጮች ያደረሰቡትን ሰቆቃና በደል ለዘመዶቹ ያዋያል፡-
አልሞተ መስሎታል እሬሳው ታልወጣ
ያባቱን ባድማ ሲካፈሉት በእጣ፡፡
ተዘንድሮው እራብ የከርሞው ይብሳል
፣ሬቱ ተወስዶ ምኑ ይታረሳል?
ዘመነ ወያኔ፣ ዘመነ ኢህአዴግ
መሬቴ ተወስዶ ልጅ በምን ላሳድግ?
በሮቼን አምጡልኝ አርጄ ልብላቸው
ደሞ እንደ መሬቱ ሳይቆራርጧቸው፡፡
እላይ በተገለጹት የተለያዩ ችግሮች ምክንያት የጎጃም ገበሬዎች ከኢህአዴግ አባላት፣ የግብርና ባለሞያዎችና ኮሚቴዎች ጋር ከፍ ያለ ቅሬታ ውስጥ ይገባሉ፡፡ አፍ አውጥተው ለመናገርና ተቃውሟቸውን ፊት ለፊት ለማሰማት የሚሞክሩትም ከዚያው መሐል በወጡና በጥቅም በተያዙ የኢህአዴግ ታጣቂዎችና የኮር አባላት እየታደኑ ይታሰራሉ፡፡ ታዲያ እነዚያ የጎጃም ገበሬዎች በተወለዱበት መንደራቸው፣ ከአብሮ አደጎቻቸው ጋር በሰላም አብሮ መኖር ባለመቻላቸው ሥርዓቱ ያመጣባቸውን የእርስ በእርስ ግጭትና አዳኝ ታዳኝነት በምሬት አስተውለው ብሶታቸውንና ሮሮዋቸውን እንደሚከተለው ሲገልጹ ተደምጠዋል፡-
ምን ዓይነት ጣጣ ነው? ምን ዓይነት መከራ?
ሰው እንዴት አይኖርም ታብሮ አደጉ ጋራ?
የኛ ዳኞቻችን መሬታችን ናቸው፣ በሮቻችን ናቸው፣
አላስቀምጥ ያሉን ኮሚቴዎች ናቸው፡፡
ጥረት ባደረጉ እጅ ላለመስጠት
ጥረት ባደረጉ ብረት ላለመስጠት
ቃላቸው ተቀድቶ ገቡ ተውህኒ ቤት፡፡
ገበሬን አትንኩት! እዚያው ይቀመጥ
ጭቁኑን አትንኩት! እዚያው ይቀመጥ
ብዙ ጉድ ይወጣል ሲገለባበጥ፡፡
ይሄ ሁሉ ሲሆን፣ ገበሬው ባደገበት ቀዬ አርሶ መኖር ሲያቅተው፣ በሰላም በልቶ ጠጥቶ ማደር ሲያቅተው ልቡ እየሸፈተ ያስቸግረዋል፡፡ ምሬት ሂድ ሂድ እያለ ለስደት ይገፋዋል፡፡ እና ያን የውስጡን አውጥቶ እንዲህ እያለ በእንጉርጉሮው ይገልፀዋል፡-
አይተነው አይተነው፣ ታልሆነ ነገሩ
እኛም አውሬ እንሁን፣ እነሱም ያድኑ፡፡
እሄዳለሁ እንጅ ምነ አለመሄዴ?
የኮሚቴን ደባ እያወቀው ሆዴ፡፡
የኮሚቴን ደባ ተማይ ተቀምጨ
የወያኔን ደባ ተማይ ተቀምጨ
የካድሬን ደባ ተማይ ተቀምጨ
ስደት መሄዴ ነው አገር አቋርጨ፡፡
ዓባይ ገመገሙ ታየኝ እዚያ ማዶ
የሚሻገርበት ወንድ ልጅ ተናዶ
መሬቱ ተወስዶ ቤቱ ሁኖ ባዶ፡፡
ሞፈሩን ቀንበሩን ክተቱት በጎታ
እናርስበታለን ቀን የወጣ ለታ፡፡
እነዚህ ገበሬዎች አንዳንዴ ሲያንጎራጉሩ የሚገኙት ግጥም ከመንደራቸውና ካካባቢያቸው አልፎ ስለ ሀገር ፖለቲካ የሚያጠነጥንበት ጊዜም አለ፡፡ ከደርግ ሶሻሊስታዊ መንግሥት ውድቀት በኋላ ኢትዮጵያን በዘርና በጎሳ የከፋፈለውና በገጠሩ የጎጃም ሕዝብ ላይ ብቻ ሳይሆን ባማራው ላይ እያደረሰ የነበረውን ዘር ላይ ያተኮረ ፖለቲካዊ ተፅዕኖ፣ እና በአማራው ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለውንም በደል በማንሳት የግፉ ሥርዓት ምሰሶ ናቸውና ተጠያቂ ናቸው የሚሏቸውንም እነማን እንሆኑ እየጠቆሙ በግጥሞቻቸው እንዲህ እያሉ ተቃውሟቸውን እስከመግለጥ ደርሰው ነበር፡-
 ሲከፋፋን ጊዜ ብናንጎራጉር
‹‹እነዚያ ነፍጠኞች›› እንባል ጀመር፡፡
ወይ አገሬ ጎጃም አጋሙ ግራሩ
ሁሉንም ቆረጡት ለማገር እያሉ፡፡
አማራን ‹‹ተኛ›› አለ ትግሬውን ‹‹ነግድ››
እንዲህ ነው ያገር ልጅ ስንፈቃቀድ?
እኛ መች ፈለግነው የትግራይን ጠጅ
እየበጠበጡ ያፋጁናል እንጅ፡፡
በአጠቃላይ እነዚህ በምሁራን ጥናት ከምሥራቅ ጎጃም የተሰባሰቡት የጎጃም ገበሬዎች የቃል ግጥሞች አስገራሚ ናቸው፡፡ በአንድ ሰው የህይወት ዘመን – ከአፄው ዘመን እስከ ደርግ ዘመን፣ ከደርግ እስከ ወያኔ-ኢህአዴግ ዘመን፣ እና ስለመጪውም ሁኔታ – ማኅበረሰቡ የተሰማውን ስሜትና ያሳለፈውን እውተኛ ኑሮና ህይወት፣ የደስታና የሀዘን፣ የመከራና የቁጭት ስሜት ግልጥልጥ አድርገው ያሳያሉ፡፡ ስለ ማኅበረሰብ ስናጠና ከነወጉና ልማዱ፣ ከነስነቃሉ፣ ከነ ቃላዊ ግጥሞቹ፣ ከነእንጉርጉሮዎቹ ካላጠናነው ምሉዕ ምስል እንደማናገኝ እነዚህ አስገራሚ ቃላዊ ግጥሞች ምስክሮች ናቸው፡፡
አንድ ቀን የሀገራችን ገበሬዎች ቀን ወጥቶላቸው ቃላዊ ቅርሶቻቸው በሚገባ ተጠንተው ማንነታችንንና ያሳለፍናቸውን ዘመናት በሚገባ እንድናውቅ እንዲህ በምሁራን ተጠንተው በታላቅ ክብር በታላላቅ የምርምር ማዕከላት ለትውልድ የሚቆዩበት ጊዜ ሩቅ እንዳይደለ – በተለይ በቅርብ ዓመታት በሀገራችን አንጋፋ የቋንቋና የሌሎችም ዘርፈ-ብዙ ሰብዓዊ መስኮች ልሂቃን የተደረጉ ብዙ ጥረቶችን ተመልክቶ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ ለምሳሌ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የ‹‹ፎክሎር›› (የማኅበረሰብ አፋዊ ኪነተቃሎች (ስነቃሎች)) የጥናት መስክ በማስተርስ ዲግሪ ደረጃ መከፈቱ ተሰምቷል፡፡ ይህ ወደምናስበው እርግጠኝነት የተደረገ አንድ ትልቅ እርምጃ ነው፡፡ ለወደፊቱ ብዙ ፍሬዎችን እንጠብቃለን፡፡ ለአሁኑ በዚህ ጥናት የተሳተፉ ሁሉንም ምሁራን ከልብ አመሰግኜ ተለየሁ፡፡
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!
ቸር እንሰንብት!
Filed in: Amharic