>
5:18 pm - Sunday June 15, 5788

በቀብርና በልደት በአል የተገኘ አንድ ሰው ብቻ ኮሮና አሠራጭቶ ያሰከተለው ችግር (ዶክተር ገበየሁ ተፈሪ)

በቀብርና በልደት በአል የተገኘ አንድ ሰው ብቻ ኮሮና አሠራጭቶ ያሰከተለው ችግር

 

(በዶክተር ገበየሁ ተፈሪ)

 

ለኮሮና ሥርጭት መገታት፣ የሰዎች እንቅሰቃሴ መገደብ መሆኑ አሌ የማይባል ነገር ነው፡፡ ከሁለት መንገዶች አንዱ የሆነው ይህ ሰዎች በየመኖሪያቸው ሰብሰብ ብለው እንዲሰነብቱ የሚሠጠው ምክርና፣ በመንግሥታቱም በኩል በአዋጅ መልክ የሚደረገው ነው፡፡ ሌላው ዋናው ነገር፣ ከዚህ ጋር በማያያዝ፣ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎችን በምርመራ አረጋግጦ ለይቶ ማስቀመጥ ነው፡፡ በዚህ ረገድ፣ ሥርጭቱን በማቀዝቀዝ የሚታወቁ፣ ይህ አሠራርም በተግባር የረዳቸው አገሮች አሉ፡፡ እነሱም፣ ቻይና፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ጃፓንና ሲንጋፖርን ይጨምራል፡፡
በየቤታችሁ ተሰብሰቡ ሲባል፣ ከዚህ ቁጥር በላይ አንድ ላይ አትሁኑ የሚባልም አብሮ የሚነገር ነገር አለ፡፡ ሲጀመር ከ50 ሰዎች በላይ ነበር፣ በኋላ ግን ይህ ቁጥር ወደ አስር ወረደ፡፡ ያም ሆኖ ቁጥሩ አስር የተባለበትን ምክንያት ያልተገነዘቡ ሰዎች፣ በርከት እያሉ መሰባሰባቸውን ቀጠሉ፡፡ ነገር ግን አስር የተባለበት ምክንያት፣ ድንገት የቤተሰብ አባላት ቁጥር አስር የሚሆንባቸው ቤተሰቦች ላለመነጣጠል ሲባል ነው እንጂ፣ ጭራሽ ሰው በቤቱ ከቤተሰቡ ውጭ ከሌላ ጋር ባይገናኝ ደስታውን ባልቻልነው የነበር፡፡
ይህንን ለማስረዳት፣ ማለትም ቁጥሩ ሳይሆን ከሌላ ሰው ጋር መገናኘቱ አደጋ እንደሚያሰከተል ለማሳየት፣ MMWR የተባለ የCDC ሳምንታዊ መፅሄት ያሰፈረውን ማጋራት የግድ ነው፡፡
ከዚህ በፊት አንደተገለጠው፣ አንድ ተላላፊ በሽታ በአንድ ሰው ላይ ሲከሰት፣ ከተያዘው ሰውየ በፊት ማን ሊያስይዘው እንደቻለ፣ ከዚያም የተያዘው ሰው ለማን ሊያሻግረው እንደቻለ፣ በተለይም በመንግሥት የጤና ቢሮዎች በኩል ክትትል ይደረጋል፡፡ Contact tracing ይባላል፡፡ ለኮሮና ብቻ አይደለም፣ ለሌችም ተላላፊ በሽታዎች ይደረጋል፤ የቆየ የተለመደ ሥራ ነው፡፡ አላማውም በሽታው ሳይዛመት የተያዙ ሰዎች ከሌሎች ጋር እንዳይገናኙ ማድረግ፣ ወይም ደግሞ አስፈላጊውን ህክምና በመሥጥት እንዲድኑና ለሌላ ሰው እንዳይሰተላልፉ ለማድረግ ነው፡፡
በቺካጎ የደረሰውን፣ በክትትል ያገኙትን ውጤት ነው የማካፍላችሁ፡፡ ከጃንዋሪ አስከ ማርች 20 ድረስ ባለው ጊዜ፣ በተለያዩ የላብራቶሪ ተቋሞች ለኮቪድ-19 የተገኘባቸው ናሙናዎችን በማየት ከላይ የተጠቀሰው የንክኪ ምርመራ የግድ መጀመር ነበረበት፡፡ በበሽታው የተያዙት ሰዎች፣ ተፈልገው ከተገኙ በኋላ፣ ሥርአት ባለው መጠየቂያ ፎርም መሠረት ጥያቄ ይደረግላቸዋል፡፡
በዚህ ባደረጉት ክትትል፣ አንድ ግለሰብ ብቻ ያደረሰውን ጉዳት ይገልጣሉ፡፡
በፌብሩዋሪ 20፣ በሌላ ምክንያት የሞተ ሰው ቀብር ላይ፣ የቤተሰብ ቅርብ ጓደኛ የሆነ ሰው በቀብር ቦታው ይገኛል፡፡ ይህ ሰው በቅርቡ ከስቴቱ ውጭ ወጣ ብሎ የተመለሰና፣ በዚያን ጊዜ በጣም ቀላል የሆነ የሳል ስሜት ነበረው፡፡ ይህ ሰው፣ ቀብሩ ነገ ሊሆን ማምሻውን፣ ከሟቹ ቤተሰቦች ከሁለቱ ጋር በመሆን በቤታቸው እራት ይበላል፡፡ በእራቱ ላይ ለሶሰት ሰኣታት የቆየ ሲሆን፣ በነጋታው በቀብሩ ላይ ደግሞ ለሁለት ሰኣታት ከቤተሰቦች ጋር ይቆያል፡፡ ከዚህም ጋር የሟቹ ቤተሰቦች ከሆኑ ሰዎች ጋር ሀዘኑን ለመግለፅ መተቃቀፉን ገልጧል፡፡ ይህ ግለሰብ፣ ሌሎች ሰዎች ታመው መረጋገጡ ሲታወቅ፣ እሱም ምርመራ ተደርጎለት በኮቪድ-19 መያዙ ይታወቃል፡፡ ካለፈ በኋላ መሆኑ ነው፡፡
ሰውየው በቀብሩ ጊዜ፣ ሀዘኑን ለመግለፅ አብሯቸው ከነበሩ ሰዎች መሀከል፣ ሁለት ሰዎች፣ ከሰውየው ከተገናኙ በ2-4 ቀናት ባለው ጊዜ ውስጥ የበሽታ ስሜት ሰለነበራቸው፣ ምርመራ ተደርጎ በኮቪድ-19 መያዛቸው ይረጋገጣል፡፡ከሁለቱ አንደኛው በሽተኛ፣ ከተጋለጠ በ11ኛው ቀን በጠና ታሞ፣ ሆስፒታል ገብቶ፣ መተንፈሻ መሳሪያ ቢደረግለትም፣ ከተጋለጠ በአራት ሳምንት ህይወቱ ያልፋል፡፡ ሌላ ተጨማሪ ሶስተኛ ሰውም የበሽታ ስሜት ይታይበታል (በነገራችን ላይ የወንድ ፆታ ተጠቀምኩ እንጂ፣ ፆታቸው አይታወቅም) አነዚህ የተረፉት በተመላላሽ ህክምና ርዳታ ብቻ ቆየተው፣ ሁለቱም ሙሉ በሙሉ አገግመዋል፡፡
መጋለጡ ከተከሰተ በ11-14 ቀናት ባለው ውሥጥ፣ ከዋናው ሰውዬ ጋር በቀብሩ ጊዜ በጣም ቅርርብ የነበረ ሰው፣ ሆሰፒታል ገብቶ የሚረዳውን ሰው፣ ሆስፒታል ድረስ ገብቶ መጠየቅ፣ አቅፎ ደግፎ ለተወሰነ ጊዜ ርዳታ አድርጎ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ይህ ሰው፣ በዚያን ጊዜ ምንም አይነት የመከላከያ ልብስ አልበሰም፡፡ የታመመውን ሰው ከጠየቀና ከረዳ በኋላ በሶስተኛው ቀን፣ የኮቪድ በሽታ ስሜት ይሰማዋል፡፡ ይህ ሰው በቀብሩ ጊዜ የነበረ ቢሆንም፣ በጣም የተጋለጠው ታማሚውን በጠየቀበት ጊዜ መሆኑን ያስረዳል፡፡ ይህ በሀዘንና በቀብሩ ጊዜ ነው የሆነው፡፡ እንዳያችሁት ለአንድ ሰው ሕይወት መጥፋት ምክንያትም ሆኗል፡፡
ከቀብሩ ከሶስት ቀናት በኋላ፣ ይህ ዋናው ሰው፣ አሁንም ቀለል ያለ የጉንፋን ስሜት እየተሰማው፣ የልደት በአል ለማክበር ወደ ሰዎች ቤት ጎራ ይላል፡፡ ይህ የልደት በአል ሌሎች ዘጠኝ የቤተሰብ አባላት የተገኙበት ቤት ውስጥ የተከበረ ነው፡፡ በበአሉ፣ ከዋናው ሰውዬ ጋር ቅርበት ያለው ግንኙነት ነበረ፡፡ ዋናው ሰውዬ ሰው ማቀፍ የሚወድ መሰለኝ፤ በዚህ ልደትም ሌሎችን አቅፎ፣ ሶስት ሰአታት በፈጀ በአል ምግብ አብሮ በልቷል፡፡
ከልደት በአሉ ከሶሰት እስከ ሰባት ቀናት ባለው ጊዜ ውስጥ፣ በልደት በአሉ ላይ ከነበሩ ሰዎች መሀከል፣ ሰባት ሰዎች የኮቪድ-19 በሽታ ይታይባቸዋል፣ ከነዚህ መሀከል ሶሰቱ በላቦራቶሪ የተረጋገጠ ነው፡፡ አስታውሱ፣ ይህ ክትትል ሁኔታው ከተከሰተ በኋላ የተደረገ ነው፡፡ በዚያን ጊዜ፣ ምርመራ ሙሉ በሙሉ ሰላልነበር፣ የተለያዩ መስፈርቶችን በመጠቀም ሰዎችን በኮቪድ-19 ተይዘዋል ማለት ይቻላል፡፡ በልደቱ ከነበሩት መሀከል ሁለት ሰዎች ብቻ ከአስራ ቀናት በኋላ ምንም አይነት የበሽታ ስሜት አልታየባቸውም፡፡ ከታመሙት መሀከል ግን ሁለት ሰዎች ወደ ሆስፐታል ገብተዋል፡፡ ሁለቱም በጠና ታመው፣ የመተንፈሻ ርዳታ ቢደረግላቸውም፣ ሁለቱም ህይወታቸው ያልፋል፡፡ ሌሎች ከተረፉት መሀከል፣ የበሸታ ሰሜት ተሰምቷቸው፣ ምርመራ ሲደረግ በኮቪድ-19 መያዛቸው ይረጋገጣል፡፡
በልደት በአሉ ተገኝቶ የታመመውን ሰው፣ ሌሎች ሁለት በልደት በአሉ ላይ ያልነበሩ ሰዎች፣ ምንም መከላከያ ሳይለብሱ፣ ሰውየውን ሲረዱ የነበሩም፣ ታማሚውን በረዱ በሶሰተኛው ቀን፣ አዲስ ሳል እንደጀመራቸው ተዘግቧል፡፡ እነዚህ በልደቱ በአል ያልተኙት፣ በበሽታው የተያዙት፣ በልደት በአሉ ተገኝቶ ከታመመው ሰው ነው፡፡ ይህ ማለት ሌላ ደረጃ መተላለፍ ማለት ነው፡፡ ያም ከመጀመሪያው ከዋናው ሰው ጋር ምንም አይነት ግንኙነት ሳይኖራቸው ነው፡፡
እንግዲህ ሌላው ተጨማሪ ነገር፣ በልደት በአሉ ላይ ከነበሩ ሶስቱ፣ የበሽታ ስሜት ከተሰማቸው ከስድስት ቀናት በኋላ ወደ ቤተክርሰቲያን ይሄዳሉ፡፡ በቤተክርስቲያኑ የነበረ፣ ከነዚህ ሶሰት ሰዎች ጋር በቅርበት የተገናኘ ሰው የበሽታ ሰሜት ይታይበትና ሲመረመር በኮቪድ-19 መያዙ ይረጋገጣል፡፡ ይህ ሰው የጤና ባለሙያተኛ ነው፡፡ ከሶስቱ ሰዎች ጋር፣ በአንድ መደዳ በመቀመጥ ዘጠና ደቂቃ በቆየ ጊዜ ጠጋ ብሎ ወሬ ሲያወራቸው የነበረና፣ የምፅዋት ሙዳዩን ሲቀባበል የነበረ ነው፡፡
ስለሰዎቹ የሚታወቀው ወይም የተገለጠ ነገር ቢኖር፣ ዕድሜያቸው ከ5 እስከ 86 አመት መሀከል ያሉ ሲሆን፡፡ ሶሰቱም ከዚህ ንክኪ ጋር በተያያዘ የሞቱት ሰዎች፣ ዕደሜያቸው ከ60 አመታት በላይ ነበር፡፡
እንግዲህ በዚህ በተጠናከረ መረጃ ያያናቸው ብዙ ነገሮች አሉ
ከቤተሰብ ውጭ በሚደረግ ግንኙነት ቫየረሱን ለማዛመት አንድ ሰው ይበቃል፡፡ ከአስር በላይ አትሰበሰቡ ለቤተሰብ ነው እንጂ ከማያወቁት ሰው ወይም የቤተሰብ አባል ካልሆነ ሰው ጋር አይደለም፡፡ የሰማሁት በአንዳንድ ቦታ፣ ቁጥራቸው ቀነስ ሳላለ፣ ጓደኛሞች በቡድን በቡድን እየሆኑ የበረንዳ ቡና እንደሚጠጡ ነው፡፡ ከዚህ መማር ይገባቸዋል፡
ሁለተኛ፣ የህመም ስሜት ከተሰማችሁ አትውጡ የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ ለሌላ ሰው ታሻግራላችሁ ነው፡፡
ሶሰተኛ፤ በዚህ ዘገባ እንደተረዳነው፤ ምንም እንኳን ሌሎች ጤነኛ ቢመሰሉ ወይም በቀላሉ በሽታውን ቢወጡ፣ ይህ ቫይረስ ወደሚገለው ሰው መድረሱ አይቀርም፡፡ በዚህ በአንድ ሰው ምክንያት፣ ተገድቦ ካልተያዘ በስተቀር ሶስት ሰዎች ህይወታቸው አልፏል፣ ሌሎችም ሊጨመሩ ይችላሉ፡፡ ዋናው ሰውዬ ምን አይነት ስሜት ሊሰማው አንደሚችል እግዚአብሔር ነው የሚያወቀው፡፡
አራተኛ፤ ርቀት ጠብቁ ለሚለው ምክር ይህ መረጃ ማረጋገጫ ነው፡፡ ሰውየው በሀዘኑም በደስታውም ጊዜ ሰው ማቀፍ ይወዳል፡፡ ምናልባትም ራቅ ያሉት ይሆናሉ ከመያዝ ያመለጡት
አምስተኛ፡ ሰው ሲታመም፣ ገለል በል የሚባለው ለሌላ የቤተሰብ አባል እንዳያስተላልፍ ነው፡፡ የታመመውን የሚረዱ ሰዎችም በቂ ጥንቃቄ ማድረግ የሚኖርባቸው ለዚህ ነው፡፡ መከላከያ መልበስ፣ እጅ መታጠብ፡፡ የታመመው ሰው ከክፍሉ ሲወጣ አፍና አፍንጫውን በማስክ መሸፈን አንዱ ትልቁ ነገር ነው፡፡
ስድሰተኛ፡ ይህ ነገር ገለል እሰከሚል ድረስ፣ ክርስትና ይሁን፣ ልደት፣ ሀዘንም ቢሆን ከቤተሰብ አባላት ውጭ የሚያገናኝ ነገር ከማዘጋጀት መቆጠብ ነው፡፡ የቤተሰብ አባል ሲባል፣ በቤት ውስጥ አብሮ የሚኖረውን ለማለት አንጂ፣ ከቤቱ ውጭ የሚኖሩ ወንደም ሆነ እህት እንደ ሌላ ሰው ነው የሚቆጠሩት፡፡ ነገሩ ከባድ ይመስላል፣ ምክሩ ግን አትገናኙ ነው፡፡ እናንተም ወደ ሰው ቤት አትሂዱ፣ ሰውም ወደቤታችሁ አይምጣ ማለት ነው፡፡
ከዚህ በኋላ፣ አስር ሰው ነው፣ የለም ስድሰት ሰው ነው የሚባለው ቁጥር እንደማያዋጣ መገንዘብ ነው፡፡ ከዚህ ላይ የምጨምረው ነገር፡፡ የበሽታ ስሜት ያላቸው ሰዎች፣ ለሌሎች ቢያዝኑና ራሳቸው በየቤታቸው ሰብሰብ እንዲሉ የመመፃን ያህል ነው የምጠይቀው፡፡ እዚህ ላይ ግን ለቫይረሱ መሠራጨት ትልቅ አስተዋፅኦ እያደረጉ ያሉት፣ የበሽታ ስሜት የሌለባቸው ግን በቫይረሱ ተይዘው ቫይሱን የሚስተላልፈ ሰዎች መኖራቸው የተረጋገጠ ሰለሆነ፣ ከዚህ ሁሉ ሰብሰብ ማለቱ ነው የሚያዋጣው፡፡
.
___
ይህንን መሰል ትምህርታዊ ፅሁፎችን ማንበብ ከፈለጋቸሁ የዶክተር ገበየሁ ተፈሪን www.goshhealth.org ድረ ገፅ እንድትጎበኙ ነው የምጋብዛችሁ።

 

ምንጭ:- ወሰን ሰገድ ገብረሚካኤል 

Filed in: Amharic