>
5:18 pm - Monday June 16, 8414

ሥርዓተ ሰሙነ ሕማማት፤ ሥርዓት ምንድን ነው?!?  (ዘመድኩን በቀለ)

ሥርዓተ ሰሙነ ሕማማት፤ ሥርዓት ምንድን ነው?!?

   ዘመድኩን በቀለ
ሰኞ
መርገመ በለስ የተፈጸመበት ሰኞ ይባላል፦ 
•••
በዚህ ዕለት ጌታችን ከቢታኒያ ሲወጣ ተራበ። ቅጠል ያለባትን በለስ ተመልክቶ ወደ በለሲቱ ቢቀርብ ከቅጠል በቀር ምንም ነገር ባለማግኘቱ “ከአሁን ጀምሮ ለዘላለም ምንም ካንቺ ፍሬ አይበላ” ማር ፲፩፥፲፬ በማለት ስለረገማት መርገመ በለስ የተፈጸመበት ሰኞ ይባላል።
ሰኞ
አንጽሖተ ቤተመቅደስም ይባላል፡- 
ጌታ ወደ ቤተመቅደስ ሄዶ በቤተመቅደሱ የሚሸጡትን እና የሚለውጡትን “ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች” ማቴ ፳፩፥፲፫ በማለት ከቤተመቅደስ ገርፎ አስወጥቷቸዋልና በዚህም ምክንያት አንጽሖተ ቤተ መቅደስ ይባላል።
•••
ወንድሞች ሆይ ከእኛ እንደተቀበለው ወግ ሳይሆን ያለ ሥርዓት ከሚሔድ ወንድም ትለዩ ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናዛችኋለን፡፡ …በእናንተ ዘንድ ያለ ሥርዓት አልሔድንምና፡፡ 2ኛተሰ.3፤6፡፡
•••
ሥርዓት የሥነ ፍጥረት ሕይወት ምሕዋር፣ መቆጣጠሪያ መሣሪያ ነው፡፡ የመዓልቱ በሌሊት፣ የሌሊቱ በመዓልት በመሠልጠን ሥርዓተ ዑደትን እንዳይጥስና የመዓልቱ በመዓልት የሌሊቱ በሌሊት እየተመላለሰ ዕለታዊ ግብሩን እንዲያከናውን ማንኛውንም ፍጡር ፈጣሪው በሥርዓት አሰማርቶታል፡፡ መዝ.105.19-24፡፡ በተለይ መንፈሳውያን ልኡካን መንፈሳዊውን ተልእኮ ያለ ሥርዓትና ያለ ሕግ ማካሔድ እንደማይችሉና እንደማይገባም ሐዋርያው አስተማረ፡፡ ያለ ሥርዓት ከሚሔድ ወንድም ተለዩ አለ፡፡
•••
ስለሆነም በሰሙነ ሕማማት የሚከናወኑ ሃይማኖታዊ እሴቶች ከዚህ ኃይለ ትምህርት የተገኙ መሆናቸውን እያሰብን በሰሙነ ሕማማት የሚከናወኑ የሕማማት ሥርዓቶችን ቀጥለን እንመለከታለን፡፡
ሰሙነ ሕማማት
•••
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከዕለተ ትንሣኤ በፊት ያለውን ሳምንት ሰሙነ ሕማማት በማለት ታከብረዋለች፡፡ የዚህ ስያሜ መነሻም የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መከራው፣ ሕማሙና ሞቱ የሚዘከርበት፣ ከአዳም እስከ ክርስቶስ የነበረው የዓመተ ፍዳ የዓመተ ኩነኔ ወቅትም የሚታሰብበት ስለሆነ ሰሙነ ሕማማት ተብሏል፡፡ የዚህ ጾም መነሻም በፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 15 ላይ ተደንግጓል፡፡ ጥንታዊ ቀዳማዊ መሆኑም ይታወቃል፡፡
በሕማማት የማይፈቀዱ
•••
በዚህ በሰሙነ ሕማማት ሳምንትም ቅደስት ቤተ ክርስቲያን ለየት ያለ የአገልግሎት ሥርዓት ሠርታለች:: ከጸሎተ ሐሙስ በቀር ቅዳሴ አይቀደስም፡ ይህ ብቻም አይደለም፡ የዘወትር የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልግሎት የሆነው ሥርዓተ ጥምቀተ፤ ክርስትና፣ ሥርዓተ ፍትሐት፣ ሥርዓተ ማኅሌት፣ ሥርዓተ ተክሊልና ሌሎችም የተለመዱ አገልግሎቶች አይካሔዱም፡፡
•••
በመስቀል መባረክ፣ ኑዛዜ መስጠትና መቀበል፣ እግዚአብሔር ይፍታህ ማለት የለም፡፡ በአጠቃላይ ከዓመት እስከ ዓመት በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አማካይነት ለምእመናን ይሰጡ የነበሩ መንፈሳውያት አገልግሎቶች አቁመው በሌላ ወቅታዊ ማለትም የጌታችንን ሕማሙን፤ መከራውን፤ መከሰሱን፤ መያዙን፤ ልብሱን መገፈፉን፤ በጲላጦስ ዐደባባይ መቆሙን፣ መስቀል ላይ መዋሉን፤ ሐሞት መጠጣቱን እና ሌሎችንም ለኀጢአተኛው የሰው ልጅ ሲባል የተከፈለውን ዕዳ በሚያስታውሱ አገልግሎቶች ይተካሉ፡፡
•••
እነዚህንም ሥርዓታዊና ምስጢራዊ የሰሙነ ሕማማት አገልግሎቶች እስከ ቀዳም ሥዑር ድረስ እንዴት እንደሚከናወኑ በአጭር በአጭሩ እንመለከታለን፡፡
ዕለተ ሰኑይ /ሰኞ/ በነግህ
•••
ከሁሉም በፊት የሰዓቱ ተረኛ አገልጋይ ቃጭል እየመታ ሦስት ጊዜ ቤተ ክርስቲያኑን ይዞራል: የሰባት ቀን ውዳሴ ማርያም፤ አንቀጸ ብርሃን፤ መዝሙረ ዳዊት በሙሉ ይጸለያል፤ በዕለቱ ተረኛ መምህር /መሪጌታ/ የዕለቱ ድጓ ይቃኛል፤ ድጓው ከዐራቱ ወንጌላት ምንባብ ጋር እንዲስማማ ሆኖ ነው የሚቃኘው ድጓውን እየተቀባበሉ እያዜሙ ይሰግዳሉ፡፡ የድጓው መሪ መምህር ሰኞ በቀኝ ከሆነ ማክሰኞ በግራ በኩል ባለው መምህር ይመራል እንዲህ እየተዘዋወረ ይሰነብታል ድጓው ሦስት ጊዜ ተመላልሶ ከተዘለቀ በኋላ፡-
ለከ ኀይል ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም
አማኑኤል አምላኪየ ለከ ኀይል ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም
ኦ እግዚእየ ኢየ ሱስ ክርስቶስ ለከ ኃይል ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም፣
ኀይልየ ወጸወንየ ውእቱ እግዚእየ እስመ ኮንከኒ ረዳእየ እብል በአኮቴት
እየተባለ በቀኝ በኩል ስድስት፣ በግራ በኩል ስድስት ጊዜ እየተዜመ ይሰገዳል፡፡ በድምሩ 12 ጊዜ ማለት ነው በዚያው ልክ አቡነ ዘበሰማያት በዜማ /በንባብ/ ይደገማል፡፡ ከዚያ በመቀጠል፡-
ለአምላክ ይደሉ ክብር ወስብሐተ ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም
ለሥሉስ ይደሉ ክብር ወስብሐተ ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም
ለእዘዙ ይደሉ ክብር ወስብሐተ ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም
ለመንግሥቱ፣ ለሥልጣኑ፣ ለምኩ ናኑ፣ ለኢየሱስ፣ ለክርስቶስ፣ ለሕማሙ፣ /በዓርብ ለመስቀሉ/ ይደሉ]
እያሉ በቀኝ በግራ እየተቀባበሉ ይሰግዳሉ በመቀጠል የነግሁ ምንባብ መነበብ የጀምራል፡፡ በመጨረሻ ተአምረ ማርያምና ተአምረ ኢየሱስ ይነበባሉ፡፡ ከዚያ ከዳዊት መዝሙር ምስባክ ተሰብኮ የሰዓቱ ወንጌል ከተነበበ በኋላ ጸልዩ በእንተ ጽንዓ ዛቲ የተባለው ጸሎት በካህኑ ሲነበብ ምእመናንም አቤቱ ይቅር በለን እያሉ በመስገድ ይጸልያሉ፡፡ ከዚያም ሁለተኛው ሥርዓተ ስግደት ይጀመራል፡፡ ዜማው የሚጀመረው አሁንም በቀኝ በግራ በመቀባበል ነው፡፡ አንዱ ይመራል ሌላው ይቀበላል እንዲህ በማለት:-
ኪርያላይሶን /5 ጊዜ/ በመሪ በኩል
ኪርያላይሶን /2 ጊዜ/ ዕብኖዲ ናይን በተመሪ በኩል ኪርያላይሶን ታኦስ ናይን
ኪርያላይሶን ማስያስ ናይን
ኪርያላይሶን ኢየሱስ ናይን
ኪርያላይሶን ክርስቶስ ናይን
ኪርያላይሶን አማኑኤል ናይን
ኪርያላይሶን ትስቡጣ ናይን
እየተባለ በዚሁ መልኩ አንድ ጊዜ ከተዘለቀ በኋላ እንደገና ይደገማል፡፡ በመጨረሻም በግራ በቀኝ በማስተዛዘል አርባ አንድ ጊዜ እየተዜመ ይሰገዳል፡፡
•••
ከላይ የተጠቀሱት የጌታችን ኀቡዓት ስሞች ናቸው፡፡ ኪርያላይሶን ማለት አቤቱ ይቅር በለን ማለት ነው፡፡ በመቀጠል መልክአ ሕማማት በሊቃውንቱ ይዜማል ከዚያም ካህኑ ፍትሐት ዘወልድ፣ ጸሎተ ቡራኬ፣ ወዕቀቦሙ፣ ኦ ሥሉስ ቅዱስ፣ ኦ ማኅበራኒሁ ለክርስቶስ፣ ነዋ በግዑ የተሰኙ ምንባባትን እያፈራረቁ ያነባሉ፡፡ ካህኑም በጸሎታቸው ፍጻሜ 41 ኪርያላይሶን በሉ ብለው መልእክት ያስተላልፋሉ፡፡ ሕዝቡም መልእክቱን ተቀብሎ ይጸልያል፡፡ ዲያቆኑም ሑሩ በሰላም እግዚአብሔር የሀሉ ምስሌክሙ፤ ንዑ ወተጋብኡ ውስተ ቤተ ክርስቲያን በጊዜ ሠለስቱ ሰዓት ብሎ ያስናብታል፡፡
•••
አሁን የተመለከትነው ሥርዓት ሰኞ በነግህ /በጥዋት/ የሚከናወነውን ነው፡፡ በ3፣ በ6፣ በ9፣ በ11 ሰዓት የሚከናወነው ሥርዓትም አሁን በተመለከትነው መሠረት ነው፡፡ የሚለያዩት ምንባባቱ ብቻ ናቸው፡፡ የሰሙነ ሕማማት ዜማም ከሰኞ እስከ ረቡዕ ግእዝ፣ ሐሙስ አራራይ፣ ዓርብና ቅዳሜ እዝል ነው፡፡ አሁን በተመለከትነው መሠረት ሰኞ፣ ማክሰኞ፣ ረቡዕ ከምንባባቸው በቀር ከላይ በተመለከትነው አኳኀን ሥርዓታቸው ይፈጸማል፡፡
አሁን ደግሞ የምንመለከተው ሥርዓተ ጸሎተ ሐሙስን ነው፡፡
ጸሎተ ሐሙስ
•••
በብሉይ ኪዳን የቂጣ በዓል የሚለውን ትርጉም ከመስጠቱ በተጨማሪ ጌታችን ምስጢረ ቁርባንን ከምስጢረ ጸሎት ጋር አዋሕዶ የገለጠበት ዕለት ስለሆነ ታላቅ የምስጢር ቀን ነው፡፡ በዚህ ዕለት ስግደቱ፣ ጸሎቱ፣ ምንባባቱ እንደተለመደው ይከናወናሉ ለየት ያለው ሥርዓት መንበሩ /ታቦት/ ጥቁር ልብስ ይለብሳል ጸሎተ ዕጣን ይጸለያል ቤተ ክርስቲያኑ በማዕጠንት ይታጠናል፡፡
•••
በዘጠኝ ሰዓት ዲያቆኑ ሁለት ኰስኰስቶችን ውኃ ሞልቶ ያቀርባል አንዱ ለእግር፣ አንዱ ለእጅ መታጠቢያ፡፡ ጸሎተ አኮቴት የተባለ የጸሎት ዐይነት ተጸልዮ ወንጌል ተነቦ ውኃው በካህኑ /በሊቀ ጳጳሱ/ እጅ ተባርኮ የሕጽበተ እግር ሥርዓት ከካህናት እስከ ምእመናን ከወንዶች እስከ ሴቶች በካህኑ አስተናጋጅነት ይከናወናል፡፡ ሥርዓተ ኅጽበቱ የሚከናወነውም በውኃ ብቻ ሳይሆን የወይራና የወይን ቅጠልንም ለሥርዓቱ ማስፈጸሚያነት እንጠቀምባቸዋለን፡፡
•••
ምስጢሩም የሚከተለውን ይመስላል፡፡
ወይራ ጸኑዕ ነው ክርስቶስ ጽኑ መከራ መቀበሉን ከማስረዳቱ በተጨማሪ እኛም /የሚያጥበውና የሚታጠበው ክርስቲያን/ መከራ ለመቀበል ዝግጁ ነን ለማለት ነው፡፡ የወይኑ ቅጠል በወይን የተመሰለ ደሙን አፍስሶ ለምእመናን የሕይወት መጠጥ ይሆናቸው ዘንድ መስጠቱን ለማዘከር ነው፡፡ ማቴ 26.26 ይህም ሥርዓት ጌታችን የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠብ ያሳየውን የተግባር ትምህርት ለምእመናን ለማሳየት ነው ዮሐ. 13፤14፡፡ በቀኝና በግራ የቆሙ ሊቃውንትም ሐዋርያቲሁ ከበበ እግረ አርዳኢሁ ሐፀበ እያሉ ይዘምራሉ፡፡
ይህ ሥርዓት ከተጠናቀቀ በኋላ ሥርዓተ ቅዳሴው ተከናውኖ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ምእመናን ይቀበላሉ፡፡
የጸሎተ ሐሙስ ቅዳሴ
•••
ቅዳሴው የሚከናወነው በተመጠነ ድምፅ ነው፡፡ ደወሉ የጸናጽል ድምጽ ሲሆን በቀስታ ስለሚጮህ ነው፡፡ የድምጽ ማጉያ አይጠቀሙም፡፡ ምክንያቱም ዲያቆኑና ካህኑ ዜማውን በቀስታ የሚሉት ይሁዳ በምስጢር ጌታችንን ማስያዙን ለመጠቆም ሲሆን በሌላ በኩል የዘመነ ብሉይ ጸሎት ዋጋው ምድራዊ እንደነበር ለማስታወስ ነው፡፡ በመቀጠል ክቡር ይእቲ፣ ዕጣነ ሞገር ዝማሬ የተባሉ የድጓ ክፍሎች ተዘምረው አገልግሎቱ ይጠናቀቃል፡፡ ሕዝቡም ያለ ኑዛዜና ቡራኬ ይሰናበታሉ፡፡
ዕለተ ዓርብ ነግህ
•••
ዕለተ ዓርብ የአዳምን ነጻነት ለመመለስ የአዳምን ዕዳ በደል አምላካችን የተሸከመበት ዕለት የኀዘን ዕለት የድኅነት ዕለትም ነው፡፡ በዚሁ ዕለት ሁሉም ነገር እንደተለመደው ይከናወናል:: መሪው እዝል ይመራል ሕዝቡ ይከተላል አራቱ ወንጌላት ይነበባሉ፡፡ በየመሀሉ ወጸቢሖ ተማከሩ ሊቃነ ካህናት፤ ሲነጋም ሊቃነ ከህናት ተማከሩ የሚለው ዜማ በመሪ በተመሪ በሕዝብ ተሰጥዎ ይከናወናል፡፡ ምንባቡም ስግደቱም ድጓውም እንደ አለፈው ይቀጥላል፡፡
በሦስት ሰዓት
•••
ሥዕለ ስቅለቱ መስቀሉ ወንጌሉ መብራቱ ጽንሐሑ በመቅደሱ በር ላይ ይዘጋጃል ዲያቆኑ በቃለ ማኅዘኒ በሚያሳዝን ቃል ግፍኦሙ እግዚኦ ለእለ ይገፍኡኒ ይላል፡፡ ካህናቱም ምእመናኑም በዜማ እየተቀበሉ ይሰግዳሉ፡፡ ምስባክ ተሰብኮ አራቱ ወንጌላት ይነበባሉ፡፡ በየመሀሉ የሰዓቱ ድጓ ይቃኛል፡፡
ስድስት ሰዓት
•••
የዕለቱ መሪ እዝል ይመራል፡፡ ሦስቱ ካህናት ጽንሐሑን ይዘው ከርቤ እያጠኑ ዲያቆናት መብራት እያበሩ ለመስቀልከ ንስግድ እያሉ ያዜማሉ ምእመናን ዜማውን እየተቀበሉ ይሰግዳሉ፡ ከዚያም ዲያቆኑ ቀነውኒ እደውየ ወእገርየ የሚለውን ምስባክ ሰብኮ አራቱ ወንጌላት ይነበባሉ በየመሀሉ ድጓው ይዜማል፡፡
•••
ከዚህ ቀጥሎ ምእመናን ይቀመጣሉ ሦስቱ ካህናት ጥቁር ልብስ ለብሰው በሚያሳዝን ዜማ አምንስቲቲ ሙኪርያ አንቲ ፋሲልያሱ ፤ጌታዬ ሆይ ስለ እኔ ሞትህ ወዮ እኔ ልሙትልህ እያሉ ሦስት ጊዜ ያዜማሉ፡፡ ሕዝቡ ይቀበላል በዚያው አያይዘው ተዘከረነ እግዚኦ በውስተ መንግሥትከ እያሉ በዜማ ይጸልያሉ ሕዝቡ ይቆማል ሥርዓተ ስግደቱም ይከናወናል፡፡
በዘጠኝ ሰዓት
•••
ሌላው እንደተለመደው ሆኖ ኦ ዘጥዕመ ሞተ በሥጋ ሦስት ጊዜ ካህናቱ በዜማ ይሉታል ምእመናንም ይቀበላሉ፡፡ ምስባክ ተሰብኮ አራቱ ወንጌላት ይነበባሉ ስግደት እንደተለመደው ነው፡፡ በሦስት ሰዓት፣ በስድስት ሰዓት፣ በዘጠኝ ሰዓት፣ ወንጌላቱ ተነበው እንዳለቁ ለምእመናን ትምህርተ ወንጌል ይሰጣል፡፡ ይህ ግን እንደ ቋሚ ሥርዓት ሳይሆን እንደ ሁኔታው አመቺነት ነው፡፡
አሥራ አንድ ሰዓት
•••
ካህናት በአራቱ መዕዘን ቁመው አራት መቶ እግዚኦታ ያደርሳሉ፤ ዕለቱን የሚመለከቱ መዝሙራት ተመርጠው ይነበባሉ፡፡ ንሴብሖ እየተባለ ቤተ መቅደሱን በመዞር በከበሮ በጽናጽል በሕማሙ ያዳነን እግዚአብሔር ይመሰገናል፡፡ ዑደት የሚደረገው ሥነ ስቅለቱን በመያዝ ነው፡፡
•••
ምእመናን በሰሙነ ሕማማት የሠሩትን ኃጢአት እየተናዘዙ በካህናት አባቶች ንስሐ ይቀበላሉ፤ በወይራ ቅጠልም ቸብ ቸብ ይደረጋሉ የመከራው ተሳታፊዎች መሆናቸውን ለመግለጥ ነው፡፡ ወይራ ጽኑዕ ነው የተቀበልከው መከራም ጽኑዕ ነው እኛም ይህን መከራ ለመቀበል ዝግጁ ነን ለማለት ነው፡፡ በታዘዙት መሠረትም ሰግደታቸውን ያጠናቅቃሉ፡፡
•••
ከዚያ በኋላ በካህኑ ኑዛዜ ምእመናን ወደ የቤታቸው ይሰናበታሉ፡፡ መስቀል መሳለም አሁንም የለም የቻለ ከሐሙስ ጀምሮ አሊያም ከዓርብ ማታ ጀምሮ እስከ ዕለተ ትንሣኤው ድረስ ያከፍላል /ይጾማል/ የተጀመረውም በዕለተ ስቅለቱ በሐዋርያትና በእመቤታችን እንደሆነ አበው ያሰተምራሉ፡፡
ቀዳም ሥዑር
•••
የማትጾመዋ ቅዳሜ ስለምትጾም ስዑር /የተሻረች/ ተብላለች በዓል መሻርን አይመለከትም፡፡ ቀዳም ሥዑር በጾም ምክንያት የተሻረችው ቀዳሚት ሰንበት ሌሊት ሥርዓቱ የሚጀመረው በመኀልየ ሰሎሞን ምንባብ ነው፡፡ ማኀሌቱም እዝሉ እየተቃኘ፣ እየተመለጠነ፣ እየተዘመመ እየተመረገደ እየተጸፉ ያድራል ጥዋት አቡን መዋሥዕት ውዳሴ ማርያም ዜማ ተደርሶ ወለመልአከ ሕይወትሰ ሰቀልዎ በሚለው ሰላም ይጠናቀቃል፡፡ ገብረ ሰላም በመስቀሉ እየተባለ እየተዘመረ ቀጤማውም ቤተ መቅደሱን ዞሮ በካህኑ ተባርኮ ለምእመናን ይታደላል፡፡
•••
የቀጤማው አመጣጥና ምስጢርም ከአባታችን ከኖኅ ታሪክ ጋር የተያያዘ ነው ምድር በማየ አይኅ /በጥፋት ውኃ/ በጠፋችበት ወቅት የኖኅ ታማኝ መልእክተኛ ርግብ የውኃውን መጉደል ያበሰረችው ቀጤማ ይዛ በመግባት ነው፡፡ ዛሬም ለሐዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች የኃጢአት ውኃ ጐደለ፣ የኃጢአት ውኃ ጠፋ በክርሰቶስ ሞትና ትንሣኤ ነጻነት ተሰበከ ታወጀ በማለት ካህናት ቄጠማ ይዘው ምእመናንን ያበሥሩበታል፡፡ በአጠቃላይ ሥርዓተ ሕማሙን፤ ሰሙነ ሕማማት ብለው የተለየ ሥርዓት አውጥተው አባቶቻችን ተግተው ያቆዩልንን ሥርዓተ መላእክት ልንጠብቀውም ልንጠቀምበት ይገባል፡፡
ምንጭ፡- ስምዐ ተዋሕዶ፤ ልዩ እትም፤ ከሚያዝያ 1-5 ቀን 2004 ዓም
•••
ሻሎም !   ሰላም !  
ሚየዝያ 5/2012 ዓም
ከራየን ወንዝ ማዶ።
Filed in: Amharic