የዐፄ ቴዎድሮስ የትውልድ ቦታና የቤተሰብ ታሪክ
አቻምየለህ ታምሩ
የኢትዮጵያ ዳግም ትንሳዔ አባት የሆኑት የዳግማዊ ዐፄ ቴዎድሮስ የልደት ቀን በታሪካቸው በምንኮራ ልጆቻቸው ብዙ ጊዜ ቢከበርም ንጉሡ መቼ ቀን እንደተወለዱ የሚያረጋግጥ በዘመናቸው የተመዘገበ ቀዳሚ የታሪክ ምንጭ እስካሁን ያለ አይመስለኝም።
ስለ ዳግማዊ ዐፄ ቴዎድሮስ ታሪክ የምናገኘው ቀዳሚ የታሪክ ምንጭ በአማርኛ የተጻፈው ታሪከ ነገሥታቸው ነው። የንጉሡ ዜና መዋዕል በሶስት ሰዎች ተጽፏል። አንደኛው በአለቃ ወልደ ማርያም ተጽፎ በሻርል ሞንዶን ቢዳይሌት ወደ ፈረንሳይኛ ቋንቋ የተተረጎመው ነው። ሁለተኛው በደብተራ ዘነብ ተጽፎ ኢኖ ሊትማን ያሳተመው ሲሆን ፕሮፌሰር ማርቲኖ ማርዮ ሞሬሮ ወደ ኢጣሊያ ቋንቋ ተርጉሞታል። ሶስተኛው ታሪከ ነገሥት ደግሞ ስማቸው በማይታወቅ ኢትዮጵያዊ ተጽፎ ካርሎ ኮንቲ ሮሲኒ በ1881 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ ወስዶት በ1951 ዓ.ም. በናፖሊ ከተማ በምስራቃዊ ቋንቋ ዩኒቨርሲቲ የአማርኛ አስተማሪ በነበረው በሉዊጂ ፉሴላ የታተመው ነው።
ስሙ ያልተገለጸውና ሶስተኛው የዐፄ ቴዎድሮስ ታሪከ ነገሥት ጸሐፊና ቀዳሚ የታሪክ ምንጭ እንደ አለቃ ወልደ ማርያምና ደብተራ ዘነብ ሁሉ ንጉሡ በሕይዎት እያሉ የሚያውቃቸውና የዐይን ምስክር የነበረው ሰው ነው። ለዚህ ማስረጃ የሚሆነው ጸሐፊው የዐፄ ቴዎድሮስን ታሪክ ሲጽፍ በጆሮ የሰማሁትን ቸል ብዬ ባይኔ ያየሁትን ያጤ ተክለ ጊዮርጊስንና ያጤ ዮሐንስን ታሪክ ብጽፍ አንድ ትቅል መጽሐፍ ያስፈልገኛል ብሎ ያሰፈረው የራሱ ቃል ነው። ከዚህ የጸሐፊው አገላለጽ ስም ያልተጠቀሰው የዐፄ ቴዎድሮስ ጸሐፌ ትዕዛዝ እስከ ዐፄ ዮሐንስ ዘመነ መንግሥት ድረስ በሕይዎት መኖሩን መናገር ይቻላል።
በዳግማዊ ዐፄ ቴዎድሮስ ዘመን ከተጻፉት ሶስቱ ታሪከ ነገሥቶች መካከል የንጉሡን የትውልድ ቦታና የእናትና የአባታቸውን ስም የመዘገበው ሶስተኛውና ስሙ ያልተጠቀሰው የዘመኑ የታሪክ ጸሐፊ ብቻ ነው። አለቃ ወልደ ማርያምና ደብተራ ዘነብ የጻፉት የዐፄ ቴዎድሮስ ታሪከ ነገሥት ስለ ንጉሡ የትውልድ ቦታ፣ እናትና አባት አይነግረንም።
ከዚህ በተጨማሪ ይህ ሶስተኛ የዐፄ ቴዎድሮስ ታሪከ ነገሥት ጸሐፊ አለቃ ወልደ ማርያምና ደብተራ ዘነብ በጻፉት የዳግማዊ ዐፄ ቴዎድሮስ ታሪከ ነገሥት ውስጥ ከጥቅሻ ባለፈ በስፋት ያላካተቱትን ዐፄ ቴዎድርስ ከእንግሊዝ ሠራዊት ጋር ያደረጉትን ጦርነት በሰፊው ይተርካል። የታሪክ ፍሰቱና ጭብጡም መቅደላ በእስር ላይ የቆዩትና እነሱን ለማስለቀስ ከውጭ የመጡት የናፒዬር ሠራዊት አባላት የነበሩ እንግሊዛውያን ከጦርነቱ በኋላ የሕይዎት ታሪካቸውን በመጽሐፍ መልክ ያሳተሙ የዐይን ምስክሮች ስለ መቅደላ ጦርነት ከተረኩት ጋር በእጅጉ ይስማማል።
ስሙ በማይታወቅ ኢትዮጵያዊ ስለተጻፈው የዐፄ ቴዎድሮስ ዜና መዋዕይ ይህንን ያህል ካልሁ በኋላ የዐፄ ቴዎድሮስን የትውልድ ቦታ እንዲሁም የእናትና የአባት ስም በዐፄ ቴዎድሮስ ዘመን ኖረው የዐይን ምስክር በመሆን ታሪኩን ለትውልድ ትተው ያለፉት እኒህ ብቸኛው ቀዳሚ የታሪክ ምንጭ በመጽሐፋቸው ስለ ዐፄ ቴዎድሮስ የጻፉትን ታሪክ ወደ ማቅረቡ ልሸጋገር። ስማቸው ያልተጠቀሰው የዐፄ ቴዎድሮስ ዜና መዋዕልና ስለ ንጉሡ የትውልድ ቦታ፣ የእናትና የአባት ስም ማስረጃ የሰጡን ብቸኛው የዐይን ምስክር የዐፄ ቴዎድሮስን ታሪክ ከንጉሡ ጋር ጎን ለጎን እየተጓዙ በመዘገቡበት ታሪክ ነገሥት ላይ ስለ ዐፄ ቴዎድሮስ የትውልድ ቦታና የእናትና የአባት እንዲህ ይላሉ፤
_________________
“ያጤ ቴዎድሮስ ትውልዳቸው። ያባታቸው አገር ቋራም ደምብያም ነው። ያባታቸው ስም ኃይሉ ወልደ ጊዮርጊስ ይባላሉ። [አባታቸው] የደጃች ክንፉ ወንድም ናቸው። የቋራ ባለ አባት ናቸው።
የእናታቸው ስምም ወይዘሮ አትጠገብ ይባላሉ። ከጎንደርም ከእንፍራዝም ከበጌምድርም ይወለዳሉ። ከነገሥታት ወገን ትውልድ አላቸው ይላሉ፤ ኃይሉ ወልደ ጊዮርጊስ ከደጃዝማች ማሩ ወይም ከወንድማቸው ከደጃች ክንፉ ተጣልተው ጎንደር ከገዳም አስደውለው ተቀምጠው ነበር። ከዚያ ወድያ ወይዘሮ አትጠገብን በጎንደር አገቡዋቸውና ዐፄ ቴዎድሮስን አረገዙ፤ ገና ተረግዘው ሳሉ አንድ መለኩሴ ለኃይሉ እንዲህ ብሎ ነገራቸው፤ ይህ ተረግዞ ያለ ወንድ ልጅ ነው፤ ታላቅ ንጉሥ ነው የሚሆነው፤ ነገር ግን ብዙ ሰውና ብዙ አብያተ ክርስቲያናት ያጠፋል፤ ብሎ ነገሯቸው ነበር። ይላሉ፡ ከዚህ በኋላ አጤ ቴዎድሮስ በጎንደር ተወለዱ።
ስማቸውም ካሳ ተባለ። የክርስትና ስማቸው ገብረ ኪዳን ነው። በጎንደርም አደጉ፡ ጥቂት ከፍ ታሉ ወድያ ወደ ደጃች ክንፉ ወደ አጎታቸው ሔዱ፤ ከርሳቸውም ሎሌ ሁነው ተቀመጡ”
______________
ስለ ዐፄ ቴዎድሮስ በዘመኑ ተመዝግቦ የምናገኘው የትውልድ ቦታና የእናትና የአባት ስም ይህ ስማቸው ያልተጻፈና በዐፄ ቴዎድሮስ ዘመን ኖረው የንጉሡን ታሪከ ነገሥት ከመዘገቡ የታሪክ ምስክር ብቻ ነው። በርግጥ ይህን የዐይን ምስክሩ የጻፉት የዐፄ ቴዎድሮስ ታሪክ በዘመኑ ኢትዮጵያን ከጎበኞት ተጓዦች መካከል፤
1ኛ. ጀርመናዊው Martin Theodor von Heuglin እ.ኤ.አ. በ1857 ዓ.ም. «Reisen in Nord-Ost-Afrika» በሚል ባሳተመው መጽሐፉ ገጽ 40 ላይ፤
2ኛ. ሌላኛው ጀርመናዊ Johann Ludwig Krapf እ.ኤ.አ. በ1860 ዓ.ም. «Travels, Researches and Missionary Labours During an Eighteen Years’ Residence in Eastern Africa» በሚል ባሳተመው የጉዞ ማስታወሻ ገጽ 457 ላይ፤
3ኛ. እንግሊዛዊው Henry Aaron Stern እ.ኤ.አ. በ1862 ዓ.ም. “Wanderings Among the Falashas in Abyssinia, Together with a Description of the Country and Its Various Inhabitants” በሚል ባሳተመው የሕይዎት ታሪክ ገጽ 63 ላይ እና
4ኛ. ፈረንሳዊው ተጓዥ እ.ኤ.አ. በ1865 ዓ.ም. Guillaume Lejean “ Théodore II et le nouvel empire d’Abyssinie” በሚል ባሳተመው መጽሐፍ ገጽ 19 ላይ ከሰፈረው የዐፄ ቴዎድሮስ ታሪክ ጋር ይስማማል።
ባጭሩ ስለ ዐፄ ቴዎድሮስ የትውልድ ቦታና የእናትና የአባት ስም በዘመኑ ተጽፎ የምናገኘው ቀደም ብዬ የጠቀስሁት ያባታቸው አገር ቋራና ደምብያ፤ ያባታቸው ስም ኃይሉ ወልደ ጊዮርጊስ፤ የእናታቸው ስም ወይዘሮ አትጠገብ በወንድ ወሰን የተባሉ ከጎንደርም ከእንፍራዝም ከበጌምድርም የሚወለዱ ወይዘሮ መሆናቸው ብቻ ነው። ከዚህ ውጭ ያለው የዐፄ ቴዎድሮስ የትልውድ ቦታና የእናትና የአባት ስም ተረት ተረት ነው።
ስለ ዐፄ ቴዎድሮስ የትውልድ ቦታና የእናትና የአባት ስም ተረት ፈጥረው “የጥንቷ የኢትዮጵያ ትንሣኤ ታሪክ” የሚል ርዕስ በሰጡት ድሪቶ ባደረቱት ልብ ለወድ ትውልድ ያሳሳቱት ራሳቸው «መሪራስ» በማለት ይጠሩ የነበሩት አማን በላይ ናቸው። አማን በላይ ያለአንዳች የታሪክ ማስረጃ ከአምእሯቸው አንቅተው የፈጠሩት የዐፄ ቴዎድሮስ ታሪክ በቀዳሚ የታሪክ ምንጭና በራሳቸው በዐፄ ቴውድሮስ ዜና መዋዕል የሚደገፍ ስላልሆነ እንደ ታሪክ ምንጭ የሚቀርብ አይደለም።
ፍቅሬ ቶሎሳ «የኦሮሞ እና የአማራ እውነተኛ የዘር ምንጭ” በሚል ርዕስ የጻፉት መጽሐፍ ከሚነቀፍባቸው ድክመቶች አንዱ የአማን በላይን በነጠረ ማስረጃ ሊደገፉ የማይችሉ ተረቶችን እንደ ታሪክ ማቅረቡ ነው። በመሆኑም አማን በላይ ስለ ዐፄ ቴዎሮስ የትውልድ ቦታና የእናትና የአባት ስም ከአእምሯቸው አንቅተው ያለ አንዳች ማስረጃ የፈጠሩት ድሪቶ ተቀዶ ሊጣል እንጂ እንደ ታሪክ ምንጭ ሊጠቀስ አይገባውም።
ጽሑፌን የምቋቸው ከእውነትና ከታሪክ የተቀዳውን ከያኒውን ስለ ዐፄ ቴዎድሮስና ጎንደር የተቀኘውን ግጥም በመጋበዝ ነው. . .
ጎንደር ጎንደር፣
የቴዎድሮስ አገር፣
የአንዲት ኢትዮጵያ ዋልታና ማገር፤
ከታች የታተመው ዶሴ ቀደም ሲል ያቀረብሁት የዐፄ ቴዎድሮስ ታሪክ የተመዘገበበት የዐፄ ቴዎድሮስን የትውልድ ቦታና የእናትና የአባት ስም የሚጠቅሰው ብቸኛው የዘመን ምስክርና ታሪከ ነገሥት ጸሐፉ ስለ ዐፄ ቴዎድሮስ የትውልድ ቦታ፣ የእናትና የአባት ስም የጻፉት ነው።