>
2:06 pm - Monday January 30, 2023

አጼ ቴዎድሮስ እንዴት ከጎጃም ወደ ጎንደር ሔዱ!? ክርስቲያን ታደለ (ገብርዬ)

አጼ ቴዎድሮስ እንዴት ከጎጃም ወደ ጎንደር ሔዱ!?

ክርስቲያን ታደለ (ገብርዬ)
«የትግሬውን ንጉስ ሲንቁ ሲንቁ፣
የጅማውን ንጉስ ሲንቁ ሲንቁ፣
የከፋውን ንጉስ ሲንቁ ሲንቁ፣
ወንድ ያለራስዎ ገለውም አያውቁ!»
*****
አጤ ቴዎድሮስ የቋሪቱ ደቦል፥ የበልያው ነብር፥ የቋራው አንበሳ፥ የመቅደላው ጌታ ሚያዝያ 06/1860 ዓ.ም ሰማዕትነትን ተቀበሉ። ትናንት እንደይሁዳ አሳልፈው የሰጧቸው የባንዳ ውሉዶች ዛሬም ድረስ የአባቴን ታሪክ እየሰረዙ፣ እየደለዙና እየበረዙ የታገሉለትን፥ የሞቱለትን አማራዊ ማንነታቸውን እስከመካድ በመድረሳቸው ሰማእትነት የተቀበሉበትን ዕለት በማስታከክ መታወቅ ያለባቸውን ኃቆች ብቻ እጽፋለሁ።
የትውልድ ዘመንና ቦታ፦
ካሣ ኃይሉ ከአባታቸው ከልጅ ኃይሉ ጎሹና ከእናታቸው ወይዘሮ አትጠገብ አብተው መስከረም  10/1810 ጎጃም ቋሪት ውስጥ ተወለዱ። ወደ ቋራ የሄዱት ከ4 (አራት) ዓመታቸው በኋላ ነው። በጀግንነት የተወለዱት በ12 ዓመታቸው በቋራ ነው።
የአባታቸው የዘር ሀረግ፦
የካሣ አባት ልጅ ኃይሉ የደጅአዝማች ጎሹ ዘውዴ ልጅ ናቸው። ደጅአዝማች ጎሹ ዘውዴ በአፄ በእደ ማርያም ዘመነ መንግስት የጎጃም ንጉስ ከነበሩት አንበሳ ዳዊት የትውልድ ሀረጋቸው የሚመዘዝ ነው።  አንበሳ ዳዊት ወሰን ሰገድን ወለዱ፤ ወሰን ሰገድ ንግስትዘርአ ዮሐንስን፣ አምደ ብርሃንን፣ ኤፍራንና አዜብን ወለዱ፤ አዜብ አቤቶ ያእቆብን አግብታ ገራም ፋሲልን፣ አቤቶ ስግወ ቃልን፣ አቤቶ ተዝካረ ቃልንና ወለተ ማርያምን ስትወልድ፤ ኤፍራን ከአቤቶ ፊቅጦር መዝሙርን ወለደች። ፃህፈ ላህም መዝሙር ሰረገላን፣ ሰረገላ ዘስላሴን፣ ራስ ዘስላሴ ጣሜን [አሁንም ድረስ ደጋ ዳሞት በስማቸው የሚጠራ ቦታ አለ! ]፣ ደጅ አዝማች ጣሜ አኖራን [ኖረህ እየተባሉም ይጠራሉ! ]፣ ድጅ አዝማች አኖራ ወልደ አበቢብን፣ ደጅ አዝማች ወልደ አቢብ ወልደጊዮርጊስን፣ ጌታ መንበረን፣ ጌታ መንበረ ፊታውራሪ ጌታ ተብለው ቋራን ሲገዙ ሸነን፤ ሸነን ግራዝማች እሸቴን፣ እሸቴ ራስ ወልደ ልዑልን፣ ራስ ወልደ ልዑል እሸቴን [አባታቸውን ለመዘከር ለልጃቸው ያወጡለት ነው! ]፣ ራስ እሸቴ ዘውዴን፣ ደጅ አዝማች ዘውዴ ደጅ አዝማች ጎሹን፤ ደጅ አዝማች ጎሹ የካሣን አባት ልጅ ኃይሉን ወለዱ። የካሣ አባት ልጅ ኃይሉ እናቱ ወ/ሮ ውባየሁ ሲባሉ ውባየሁም ሰከላ ዘገዛ ማርያም / ጉደራ ባሕር አካባቢ የነበሩት የባላንባራስ እንቁ ፀሐይ ልጅ ናቸው። ወ/ሮ ውባየሁ ከልጅ ኃይሉ ሌላ ከደጅ አዝማች ጎሹ ደጅ አዝማች ተሰማን፣ ደጅ አዝማች ብሩን፣ ደጅ አዝማች እሌሚቱን፣ ደጅ አዝማች ንጉሴን [ደጅ አዝማች ንጉሴ ደጅ አዝማች ደስታን፣ ደጅ አዝማች ደስታ ሙሉነሽን፣ ሙሉነሽ ከግራ አዝማች ፀጋዬ ታደለን፣ ታደለ ክርስቲያንን]፣ ደጅ አዝማች ማሩን፣ ልጅ ይማምን እና አራት ሴቶችን ወልደዋል።
የእናታቸው የዘር ሀረግ፦
የካሣ እናት ወ/ሮ አትጠገብ ከዳግማዊ ዮሐንስ ልጅ አቤቶ ልዑል ልጅ ከአብተው የተወለዱ ናቸው። ወ/ሮ አትጠገብ አምባ ጊዮርጊስ ኮሶጌ በሚባል ቦታ ከእናታቸው ወ/ሮ ወለተ ተክሌ እና ከአባታቸወወ አብተው ልዑል ዮሐንስ ተወለዱ። ዳግማዊ ዮሐንስ የአፄ በካፋ [ብከፋ] ወንድም ናቸው።
የአትጠገብ እናት ወለተ ተክሌ የዘጌው አለቃ ኃይለማርያም ንብሉ ልጅ ሲሆኑ እናታቸውም አልጣሽ ይባላሉ። አለቃ ኃይሉ (ኃይለማርያም) የደንቢያ ርእሰመኳንንት ደጅ አዝማች ማሩ ኃይለማርያም አባት ናቸው። ወ/ሮ ወለተ ተክሌ የቋራው ደጅ አዝማች ክንፉ  ኃይሉ ወልደጊዮርጊስን (የካሳ አጎት የአትጠገብ ወንድም) የወለዱት የአትጠገብን አባት አብተውን ፈተው ያገቧቸው የአማራ ሳይንቱ ደጅ አዝማች አንድነዋ ከራስ ጉግሳ ጋር በነበረ ጦርነት ከሞቱባቸው በኋላ ነው።
በአጭሩ ካሣ በእናታቸውም በአባታቸውም የአማራ ነጋሲ ውሉድ ናቸው። በሁለቱም በኩል ነጋሲነታቸውን ለማረጋገጥም እሁድ የካቲት 05፣ 1847 ዓ. ም ደረስጌ ማርያም ላይ ሲነግሱ ስመ መንግስታቸውን «ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ እጓለ አንበሳ» አሰኝተዋል፤ በአፄ በእደ ማርያም ዘመነ መንግሥት በጎጃም ከነገሱት ንጉስ አንበሳ ዳዊት ሥር መመዘዛቸውን ሲያስረግጡ! በኋላም ለሚያጉረመርሙ ስዎች በፃፉት ደብዳቤ «በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ [አሐዱ] አምላክ ንጽህፍ [ለወልደ ነገስት] ለእጓለ አንበሳ ዳዊት አፄ ቴዎድሮስ ዘ ምስረፀ እምብሄረ አማራ» የሚል ግልፅ መልእክት አስፍረዋል።  በነገሬ ላይ የአጤ ቴዎድሮስ ቀኝ እጅ ገብረሕይወት ጎሹ (ገብርዬ) የደጅአዝማች ጎሹ ዘውዴ ልጅ ሲሆኑ የአጤ ቴዎድሮስ አጎት ናቸው።
እውነታው ይኼ ሆኖ ሳለ ለአገሩና ሕዝቡ እንደክርስቶስ ራሱን አሳልፎ የሰጠውን የእኛውን ካሣ ስለምን ማንነቱንና ታሪኩን ለመሰረዝ፣ ለመደለዝና ለመበረዝ ውሉደ ባንዳዎች ታተሩ?
***
አጤ ቴዎድሮስ እንዳሁኑ ዘመን ያለውን መንደር ነጋሲነት በማስወገድ የተባበረ ሕዝብና በእውቀትና ጥበብ ጠንካራ ኢትዮጵያን ለመገንባት ሲታትሩ ርእያቸውን የሚረዳ አጋዥ በዘመናቸው ባለመኖሩ ኅልማቸውን አርግዘው ሚያዝያ 06፣ 1860 ዓ. ም ሰማእትነትን ተቀበሉ።
ቁልፍ መልእክት፦
ከኅልውና አደጋ የሚያወጣን የአጤ ቴዎድሮስ መንገድ ነው!
መውጫ
ደግነትህን እንጂ ቁጣህን ባንወርሰው፣
አገሩን አልፎ ሂያጅ በየጁ ቆረሰው።
«ታላቅ ነበርን፥ ታላቅም እንሆናለን! »
Filed in: Amharic