>

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን (ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም)

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም

ችግር ሁልጊዜ አንዳንድ መልካም ነገሮችን ይዞ ይመጣል፤ የዘመኑ ወረርሺኝም በእኔ አስተያየት ሁለት ጥሩ ነገሮችን አስከትሏል፤ አንዱና ዋናው ከጃንሆይ በኋላ ተሸሮ የነበረው እግዚአብሔርን መልሶ በቦታው ማስቀመጡና በየመገኛዎች የእግዚአብሔርን ስም ማንሣት ተለመደ፤ ይህ ትልቅ ንቃት ነው፤እግዚአብሔር ሁሌም በመንበሩ ላይ ነው፤ አይነቃነቅም፤ ሁለተኛው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ተረስታ ወደጓዳ ተደብቃ ነበር፤ ዛሬ ጉልበትዋ በሙሉ ባይሆንም ታየ፡፡


የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ዝናዋ አልተነገረም፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ያለበትን ውለታ ገና በትክክልና በዝርዝር የሚናገረው አላገኘም፤ እንደተዳፈነ ነው፤ ቤተ ክርስቲያኒቱን ተደግፈው የሚወጡ ሁሉ በሥልጣኑ ጣዕምና ሙቀት እዚያው ቀልጠው ይቀራሉ፤ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ለአሥር እውነተኛ ተማሪዎች የሊቅነት ማዕርግ የሚያሰጣቸው ነው፤ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የትምህርት ሚኒስቴር ነበረች፤ የበጎ አድራጎት ሚኒስቴር ነበረች፤ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ነበረች፤ የባህልና የቅርስ ጥበቃ ሚኒስቴር ነበረች … በዛሬው ጊዜ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የተማሩ ሰዎች አላጣችም፤ በጥቁርና በነጭ ልብስ የተሸሞነሞኑ ዓለማውያን ናቸው፤ እንደአቡነ ተክለ ሃይማኖት ያለው እንኳን ደፍሮ ጉልበተኖችን መጋፈጥ አልቻሉም፡፡

Filed in: Amharic