>
5:13 pm - Thursday April 18, 6639

አለቃ ዘነብ - ፍልስፍናን እንደ ጨዋታ! (አሰፋ ሀይሉ)

አለቃ ዘነብ – ፍልስፍናን እንደ ጨዋታ!

አሰፋ ሀይሉ
 
* አለቃ ዘነብ “ጨዋታ ሥጋዊ ወ መንፈሣዊ” 
 
ፍልስፍና ምንድነው? ፍልስፍና የሰውን ልጅ የጭንቅላት አስተሳሰብ ተጠቅሞ ነገሮችን አንጥሮ የማወቂያ መንገድ ነው፡፡ ዓለምንና ሞላዋን፣ ሰውንና ተፈጥሮን፣ አዕምሮን፣ ሃሳብን፣ ሃሳብን ራሱን የምንፀንስበትንና የምናስብበትን አኳኋን፣ የነገሮችን ምንነት፣ እና ምንምነት፣ እና የመረዳታችንን ልክ፣ ውበትን፣ እውነትን፣ ሐሰትን፣ ክፉን እና መልካምን፣ ምግባርንና ህሊናን፣ ድርጊትንና ፍርድን፣ ጥቅምንና ጉዳትን፣ መኖርንና አለመኖርን፣ ስምምነትንና መቃረንን፣ መቀጠልንና መፎረሽን፣ በአጠቃላይ ሁሉንም የሰው ልጅ አዕምሮ ሊዘልቃቸው የሚችሉ ነገሮች ሁሉ ጠልቀን የምናይበት፣ የምናስብበት፣ የምንመረምርበትና የምንረዳበት የተራቀቀ አዕምሯዊ መንገድ ነው ፍልስፍና፡፡
ገና ከጅምሩ የሰው ልጅ ራሱንና አካባቢውን እንዲያውቅ ያደረገው ፍልስፍናዊ ጥያቄ ነው፡፡ ይሄ ለምን ሆነ? ያኛውስ ለምን እንዲያ ሆነ? ይሄኛው ከየት መጣ? የዚያኛውስ መነሻ? የዚህኛውስ መጨረሻ? ያንዱና የሌላው ግንኙነቱ ምንድነው? የዚህ ባህርይ ምንድነው? የዚያኛውስ? ሰውስ በምን መልኩ ነው የሚረዳቸው? ለምን?…. እያለ ይጠይቃል ፍልፍስና፡፡
እነዚያ ፍልስፍናዊ ጥያቄዎቹ ናቸው የሰውን ልጅ አዕምሮ አሠልጥነው ከሌሎች እንስሶች የለዩት፡፡ ሰውን ከሌሎች እንስሶች ብቻ ሳይሆን፣ አንዱን ሰው ከሌሎች ሰዎች የለዩትና የሚለዩትም እነዚሁ ፍልስፍናዊ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ፍልስፍና ባይኖር የሰው ልጅ በዚህች ዓለም ላይ በደመነፍስ የዕውር ድንብራቸውን ከሚርመሰመሱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ብልጥ ፍጡራን መካከል እንደ አንዱ ብቻ ሆኖ ይቀር ነበር!
ጥያቄ መጠየቅ ነውር አይደለም፣ ነውር ጥያቄ ካልጠየቅክ በቀር፡፡ የምትል አባባል አለች፡፡ ለፈላስፎች ግን ነውር ጥያቄ የለም፡፡ ለፈላስፋ ነውሩ ጥያቄ ሳያነሱ ዝም ብሎ መኖር ነው፡፡ ዓለማችን ታዲያ ብዙ ባለ ብርቱ ጥያቄ ፈላስፎችን አስተናግዳለች፡፡ ነገሮችን ሁሉ አበክረው የሚጠይቁ፣ እና ይበልጥ ለማወቅ የሚጓጉ፡፡ ከእነዚህ ጠያቂ ፈላስፎች መካከል ለዛሬው ላነሳቸው የወደድኩት ኢትዮጵያዊውን ቀደምት ፈላስፋ አለቃ ዘነብን ነው፡፡
አለቃ ዘነብ ከመቶ ሃምሳ አምስት ዓመታት በፊት (በ1857 ዓመተ ምህረት) የጻፉት ‹‹መጽሐፈ ጨዋታ ሥጋዊ ወ መንፈሳዊ›› በወቅቱ ከሰረፀው ወግአጥባቂነት የሚያይልበት ሀገራዊ ሐይማኖታዊ አስተሳሰብና ነገሮችን ጠልቆ የመጠየቅና ያለመጠየቅ ሁናቴ አንፃር ሲታይ እጅግ የሚያስደንቅ ማስተዋል የተገለፀበት ዓለምንና ሞላዋን (ሥጋዊውንም መንፈሳዊውንም ዓለም) በፍልስፍናዊ አቀራረብ በተለዩ መንገዶች የሚጠይቅና እነዚያን ለየት ያሉ አተያዮቹን በሚገርም ብቃት ያሰፈረ ድንቅ ኢትዮጵያዊ የፍልስፍና ሥራ ነው፡፡
በውጭው ዓለም በተለይ በአውሮፓ ጀርመን፣ ሆላንድና ፈረንሳይ ባሉ እንደነ ዴካርቴ፣ ስፒኖዛ፣ ካንት በመሳሰሉ ቀደምት ፈላስፎች ያሉበትን ማህበረሶችና ሥጋዊ-መንፈሳዊ ቀኖናዎች በፍልስፍናዊ መንገድ በመጠየቅ፣ በመተንተንና በማሄስ የታወቁ ናቸው፡፡ ሥራዎቻቸውንም ያሳትሙ የነበሩት ‹‹በነገሮች ምንነት ላይ የተደረጉ ጥያቄዎች›› ‹‹የተደረጉ የምርምር ጥያቄዎች›› ‹‹ኢንኳየሪስ›› በሚሉ ርዕሶች ነበረ፡፡ እነዚያን ድንቅ የተባሉ ጥያቄዎች ተከትለው የተነሱ የቀጣይ ትውልድ ሌሎች ፈላስፎች ደግሞ እነዚያ ጥያቄዎች ላይ ተመስርተው ፍልስፍናዎቻቸውን አዳብረውታል፡፡
አለቃ ዘነብም ከ150 ዓመታት በፊት ይህን የአውሮፓውያኑን አንቱ የተባሉ የፍልስፍና ሊቆች የመሰለ ሁሉን ነገር በጥያቄ መነፅር እያየ የሚፈትን አስተሳሰባቸውን ነው – ያውም በሚያምር የማዋዛት መንገድ ያቀረቡት፡፡ የቀልድ መፍጠር አቅማቸው እጅግ ምጡቅ ነው፡፡ ለዘብ ብለው ከነገሮች ተፈጥሮ ጀርባ ያለውን ልብ የማንለውን እውነታ ጣል በማድረግ ታላቅን ‹‹ሂዩመር›› በአዕምሯችን ይከስታሉ፡፡ እውነታውን ይገልጻሉ፡፡ እና ልክ እንደ ጥንቶቹ ግሪካውያን ፈላስፎች እነ አሪስቶፌነስ፣ ዩሪፒደስ፣ ዲሞክረስ፣… ወይም እንደነ አሪስቶትል፣ ሶክራተስ፣ ፕሌቶ – ኢትዮጵያዊው ፈላስፋ አለቃ ዘነብም – የተለያዩ የማያልቁ የፍልስፍና ጥያቄዎቻቸውን አንግበው ነው የሚራመዱት፡፡
አለቃ ዘነብ በጠያቂ ዓይኖቻቸው መነፅር ሁሉን ነገር አንጠርጥረው ያያሉ – ያዩትን ነገር እኛም እናየው ዘንድ ደግሞ – ከለመድነው አቅጣጫ ሳይሆን ካልሄድንበት አቅጣጫ ብቅ ብለው – ግልጽልጽ አድርገው ያሳዩናል! ይጠይቃሉ! ያዩትን ያሳያሉ! የነገሩን ባሕርይ ይፈላሰፉበታል፡፡ የነገሩን መነሻና መድረሻ አንስተው ይፈላሰፋሉ፡፡ ይሄሳሉ፡፡ በሰላ ጥያቄ ሾጥ ሳያደርጉት የሚያልፉት ምንም ነገር የለም! እና ሳሳ ካለች ፍልስፍናዊ አርጩሜያቸው በኋላ ምፀታዊ ፈገግታቸውን ያሳዩናል! ፈገግ በሉ እንጂ – ብለው እርሳቸው የፈገጉበትን ነገር አይተን እኛም እንድንደመምበት፣ ፈገግ እንድንሰኝበት ሃሳባቸውን ይጋብዙናል!
በዚሁ ሁሉ ፈገግታቸው መሐል ግን – አለቃ ዘነብ – ወደ ቀልባቸው ይመለሱና ደግሞ – መንፈሳችንን ሳናቅበዘብዝ ለመልካሙ ህላዌ አዕምሯችንን እንድናስገዛ የአባት ምክር የመሰለ አስተያየታቸውን ጣል ማድረጋቸውን አይተዉም፡፡ ይግሙና ደግሞ ወደ ሌላ ፍልስፍናዊ እይታቸው ይሸጋገራሉ፡፡ የማይክማቸው ፈላስፋ ናቸው በእውነት!! አለቃ ዘነብ እነዚህን አስደማሚ ፍልስፍናዊ እይታቻቸውን ‹‹ጨዋታዎች›› ብለው ነው የጠሯቸው፡፡ ጨዋታ፡፡ የነፍስ ጨዋታ፡፡ የሥጋ ጨዋታ፡፡ ጨዋታ ሥጋዊ ወ መንፈሣዊ፡፡ ፍልስፍናን እንደ ጨዋታ!
አንድ ቦታ ላይ አለቃ ዘነብ የእንስሳትን ባህርይ ልብ ብለው ያስተውሉና፣ ከዚያ ተነስተው ከሰው ልጅ ባህርያት ጋር ያነፃፅሩትና መልሰው ይጠይቃሉ፡-
“እንስሶች ሁሉ የሚበሉት አንድ ሣር ነው፣ ምነው ፋንድያቸው ተለዋወጠ፡፡ ሰዎችም አባታቸው አንድ አዳም ሲሆን ምነው ዓይነታቸው በዛ፡፡… የዝንብ ብልሐቷ ምንድር ነው፣ ሌላው የሠራውን መብላት ነው፡፡ ሰነፎች ሰዎችም እንደዚሁ ሌላ ሰው የሠራውን መብላት ይወዳሉ፡፡… የውሻ ጅራቱ ወደላይ እንዲቆም፣ የሹመት ፈላጊም ልብ እንደዚያ ነው፡፡… ሰው ፍሪዳን አብልቶ ያሰባዋል፣ በመጨረሻውም ይበላዋል፡፡ ምነው ቢሉ አብልቶ መብላት ካልሆነም ገበያ ነው፡፡ ወርቅ ቢያብረቀርቅ ብር ያብለጨልጫል፣ ምነው እናንተ መናፍቃን ጥቂት ጥቂት ብልሐት አታዋጡምን፡፡… የእሳት ራት ዙራ ፈልጋ ከእሳት እንደምትገባ፣ ኃጥአንም ዲያብሎስን ዙረው ፈልገው ገሃነመ እሳት ይገባሉ፡፡… በሬ በቅልጥሙ ቅባቱን ይዞት ይኖራል፡፡ ገና ኋላ ለቁርበቱ ማልፊያ ይሆነኛል ብሎ ነውን፡፡ ያዳምም ልጆች እንደዚሁ ለተዝካራቸው ያኖራሉ፡፡ ምነው ዓይናቸው ሲያይ ለነዳይ ቢሰጡት ይኮነኑ ይሆን፡፡”
ከዚያ ትንሽ ወረድ ብለው ደግሞ እንዲህ ይላሉ፡-
“አቀፈ፣ አዘለ ማለት ምንድር ነው፣ ስሙና አጠራሩ በየራሱ ቢሆን ነው እንጂ፣ ሁሉም ተሸከመ ማለት ነው፡፡ … ሰይጣን፣ ጋኔን፣ ዛር፣ ማለት ምንድር ነው፣ ስሙ መለዋወጡ እንጂ ሁሉም አንድ ጋኔን ነው፡፡”
አለቃ ዘነብ ስለ መርፌ የተናገሯትን ሳይ አስገርመውኛል፡፡ መርፌ የያዘችው ክር እና የምትበሳው ጨርቅ ክር ኋላ ዞረው በስፌት ባንድ ሊገጥሙ ዝም ብላ ያንንም ይሄንንም መውጋቷ ምን መሆኗ ነው? እያሉ ነው በትዝብት ለዛ የሚሄሱት አለቃ፡-
“መርፌ ሸማን የሚወጋው ምን እጠቀም ብሎ ነው፣ በኋላው እንጂ ፈትል ተከትሎታል፣ እነዚያ እንዲጠቃቀሙ አያውቅምን፣ እንደዚህ ያለ ሞኝ የፊቱን እንጂ የኋላውን የማያይ፣ ይልቁንስ የርሱን ቀዳዳ በጠቀመ፡፡”
ደግሞ ተክልንና ተፈጥሮን አስተውለው የሚከተለውን አነፃፅረው እናገኛቸዋለን፡-
“ማሽላን ወፎች እራስ እራሱን ሲሉት አይቶ፣ ባቄላ ፍሬውን በጎኑ አዝሎ ክንፉን አልብሶ ይኖራል፡፡ ውሃ ወርዶ ወርዶ ባይመቸው ኩሬ ይሆናል፡፡ ብልህ ሰው በጨነቀው ጊዜ ሞኝ ይሆናል፡፡… ሱፍ አበባውን አሳምሮ እሾሁን አጥሮ ይኖራል፡፡ ምነው ቢሉ የአዳም ልጆች ጎምጂዎች ናቸውና ዘለው እንዳይዙት ነው፡፡ አሁን ቢጮህ አጣጥና ግራር ባልረዱዋቸውምን፡፡ እረ ገና እነዚህ ፍሬ ቢሶች፣ ተገትረው የቀሩትን፣ ምን ጣም አላቸው ብለው ነው እሾሃቸውን ማብዛታቸው፡፡… ሥጋ ፍራቱን እጅግ አበዛው፣ ከታረደ በኋላ ምን ያንቀጠቅጠዋል፡፡ ምንስ ያንበደብደዋል፡፡”
በፍልስፍና ‹‹ዱዋሊዝም›› የሚሰኘውን የነገሮችን ሁለትዮሽ የሚያስተነትነው እሳቤ፣ አለቃ ዘነብ ደግሞ በቀላሉ እንዲህ በማለት ያስቀምጡታል፡-
“እግዚአብሔር በጥበብ ሁሉን ሁለት ሁለት አድርጎ ፈጠረ፡፡ አስተውል፣ ሰማይንና ምድርን፣ ፀሐይንና ጨረቃን፣ በጋንና ክረምትን፣ ቀንንና ሌሊትን፣ ሰውንና መላእክትን፣ አዳምንና ሔዋንን፣ ጽድቅንና ኩነኔን፣ ይህችን ዓለምና የወዲያኛይቱን ዓለም፡፡”
አለቃ ዘነብ መጽሐፈ ጨዋታ ሥጋዊውን ለብቻ፡፡ መጽሐፈ ጨዋታ መንፈሳዊውን ደግሞ ለብቻ፣ መጽሐፈ ጨዋታ ወንጌላዊንም ለብቻ አድርገው ነው ጽሕፈታቸውን ያዋቀሩት፡፡ እና የመጽሐፈ ጨዋታ መንፈሳዊን ‹‹ሀ›› ብለው የሚጀምሩት መጽሐፍ ለሰው ልጅ እንደምን ያለ እንደሆነ በመግለጽ ነው፣ እንዲህ በማለት፡-
“ቅቤ ለመጽሐፍ ዘመዱ አይደለም፡፡ መጽሐፍ ግን ለሰው ቅቤ ነው፡፡ አትክልት ሆኖ ካላፈራ፣ ሰው ሆኖ እግዚአብሔርን ካልፈራ፣ መቆረጥ አይቀርለትም፡፡ ኮትኳችና አራሚ የሌለው አትክልት አይረባም፣ ንጉሥና መምሕር የሌላትም አገር እንደዚህ ናት፡፡.. ከረጢት መሰፋቱ ለወርቅ መያዣ ነው፣ የሰው ልብም መፈጠሩ ክፉና በጎ ለማወቅ ነው፡፡… እግዚአብሔር አብ ጣት ነው፡፡ እግዚአብሔር ወልድ ብዕር ነው፡፡ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ቀለም ነው፡፡ ሰማይና ምድር ወረቀት ናቸው፡፡ ፊደሉም ፍጥረት ነው፡፡ እግዚአብሔር አብም በቃሉ ሰማይና ምድርን ፈጠረ፡፡ ያለባቸውንም ፍጥረት ሁሉ ፈጠረ፡፡ በመንፈሱም አጸናቸው፡፡.. የወጥ ማጣፈጫው ምንድር ነው፣ ጨውና ቅመም ቅቤም ነው፡፡ የሰውም ማጣፈጫው ሃይማኖትና ፍቅር ነው፡፡”
አለቃ ዘነብ በተለያዩ ቦታዎች ላይ – ስለ ብርሃንና ጨለማ፣ ስለ ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብት የተለያዩ ምሳሌዎችን እየሰጡ ይጠይቃሉ፣ ይመረምራሉ፣ እና ሲያሻቸውም ያሄሳሉ፡፡ አለቃ ዘነብን እነዚህ የጨለማና የብርሃን ጠባያት ሳያስገርሟቸውና በብርቱ ሳያመራምሯቸው አልቀሩም፡፡ የሚገርመው ነገር – በምዕራቡም ዓለም አለቃ ዘነብ ጽሑፋቸውን በጻፉባቸው ዓመታት – ሳይንቲስቱ፣ ሰዉ፣ አርቲስቱ፣ ጠቢባኑ ሁሉ – በብርሃንና በጨለማ ባህርያት ምርምር ፍቅር ላይ የወደቀበት ዘመን ነበረ፡፡ በሁለት ዓለሞች በተመሳሳይ ወቅት ያረበበ – ደስ የሚል የብርሃን ፍቅር ሆነብኝ! (የብርሃን ፍቅር! ያለው ማን ነበር? መንግሥቱ ለማ?)
እና አለቃ ዘነብ እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ሆነው ስለ ብርሃንና ጨለማ ከሚመራመሩባቸው ዓመታት ብዙም ሳይርቁ ነው የአውሮፓ ተመራማሪዎች እነ ሃምፍሬይ ዴቪ በወቅቱ ዓለምን ጉድ ያሰኙ የኤሌክትሪክ ባትሪ መቅረዞችን የሰሩት፣ ኋላ እነ ኤዲሰን የአምፑል ብርሃንን ሲያገኙ፣ እነ ቴስላ የማግኔት ብርሃንን ሲመራመሩ የአውሮፓ ደራሲዎችና ሰዓሊዎች ሁሉ ሥራዎቻቸው ባጠቃላይ ተቀይረው በብርሃንና በጥላ ብቻ የሚገለጡ እስከመሆን ደርሰው ነበረ፡፡ አለቃ ዘነብም እንደዚያ በሚመስል የብርሃን መደመም ነው እየደጋገሙ ስለ ጨረቃና ፀሐይ፣ ስለ ጨለማና ብርሃን የሚመረምሩት፡፡ ምን ነበረበት አለቃ ዘነብ ፈላስፋ ብቻ ሳይሆን ፈላስፋ ሳይንቲስት ቢሆኑ? ወይ ፈላስፋም ሆነው፣ ሳይንቲስት ትውልድ ቢከተላቸው? – እያልኩ፡፡
አለቃ ዘነብ ከብዙ ስለ ጨረቃና ጸሐይ ብርሃን ከሚመሰጡባቸው ቦታዎች በአንደኛው ላይ እንዲህ ይላሉ፡-
“ብርሃን ከፀሐይ ጋር ምን ያለማምጠዋል፣ እርሱ አስቀድሞ ተፈጥሮ የለምን፡፡ ነገር ግን ልደምስስህ እያለው ሆዱን ያከፋዋል እንጂ ዘመድ ናቸው፡፡.. ብርሃን ለእኛ ዘመዳችን ነው፡፡ ከፀሐይ ቀድሞ ስናየው ደስ ይለናልና፡፡ ነገር ግን አንድ ክፋት አለበት፡፡ ጨለማ ሲመጣ ትቶን ይሸሻል፡፡ በዚህ ዓለም ከቶ አንድ አንድ ክዳት ያለው አይታጣም፡፡ በጨለማ ጊዜ ጨረቃና ከዋክብት ባይኖሩ ጅብ በበላን ነበር፡፡ … ፀሐይ ምንም ዘመኗ ብዙ ሆኖ ለቆላ ኮምጣጣ ብትሆን፣ ለደጋ ግን በተሀ ናት፡፡ ቆላ ምን ባደረገ ኮመጠጠችበት ይሆን፡፡ ቢርቃት ቢሸሻት፡፡ ደጋማ ሁል ጊዜ ቀርቦ ይለማመጣታል፡፡ እረ ገና አወትር በረዶ ሲፈላበት እያየች ዝም ትለው የለችምን አይደለም፡፡ ስታኮርፈው ጊዜ ነው እንጂ፣ ባታኮርፈውስ አንድ ጊዜ ወጥታ ታቀልጥለት ነበር፡፡ ጨረቃና ከዋክብትስ መሞቅ የለ ሁል ጊዜ መቀዝቀዝ ምንድር ነው፡፡ ሰማይ የለም ይሆን ተሰብስበው ፀሐይን የማይዘርፏት መንጋ ፈሪ በሰማይ ተሰብስቦ፡፡ ደመናም የታዘዘው ዝናም ሊያዘንም ታዘዘ እንጂ እንዲያው በድንገት እየመጣ የሚያፍነን ምን ባልነው ነው፡፡ ነፋስስ እኛን ለመግደል ነው የታዘዘ፡፡ አሁን ግንብ ሠርተን መውጫ መተንፈሻ ባሳጣነው፡፡”
አለቃ ዘነብ በብርሃንና ጨለማ፣ በዳመናና ንፋሳት ብቻ ላይ አያቆሙም፡፡ እንደ ጥንታውያኑ የግሪክ ፈላስፎች ስለ ውሃና እሳትም የሚሉት፣ የሚጠይቁት፣ የሚጫወቱት ብዙ አላቸው፡፡ ከብዙው መሐል ወደ መጨረሻ ላይ ስለ ውሃና እሳት ባህርያት ያሰፈሯት አስደምማኛለች፡፡ እንዲህ ይላሉ አለቃ ዘነብ፡-
“ወሀን አንተ ባሪያ ብለው እጅግ ከፋው፣ እንግዴህስ ይወቀው፣ ከቶም አህያ ነው፡፡ የሁሉን እድፍና ጉድፍ ተጭኖ የሚሄድ፡፡ ነገር ግን ልግመኛ ነው፡፡ ዓይኑ ሲያይ ቢጭኑበት፣ መርፌ እንኳን ቢሆን ያሰጥመዋል፡፡ በመርከብ አድርጎ ሳያይ ቢጭኑበት ግን፣ ፩ ሚሊዮን የሚሆን መድፍም አይከብደው ያንሳፍፈዋል፡፡ ይህም ተንኮሉና ልግሙ አቅጥኖት ይኖራል፡፡ ሀብቱም ወደታች ከመፍሰስ በቀር ወደላይ መውጣት የለውም፡፡ ፍጥረት ሁሉ በጉንጩ እንደያዘው አያውቅምን፡፡ ወሃ በክረምት በክረምት ዘመዳችንን ይወስዳል፣ በበጋ ደግሞ ጥሩ ነው ብለን ከሆዳችን ስናገባው የሰውነታችንን ልክ ይመረምርና ይኮራል፡፡ እንግዲያውስ ጠጅ በጥባጭ አይደለምን፣ ወሃውን ጌሾና ጠዶ ይቆራኙት፡፡ እሳትም ብረትን ሠርቶ ጋግሮ ቀቅሎ አብስሎ ሲያበላ ደግ ያደርጋል፡፡ ሲቀርቡት ግን ይፈጃል፣ ለእኛም አይገዛ፡፡ ስለዚህ እንዳይሞት፣ እንዳይድን አድርገን ብናኖረው ይሻላል፡፡”
የአለቃ ዘነብ ዘመንን ያስቆጠረ ‹‹ሰኪዩላር ኤንድ ስፒሪቹዋል ኢንኳየሪስ›› – “ጨዋታ ሥጋዊ ወ መንፈሣዊ” የሚያነሳሳቸው ሃሳቦችና ጥያቄዎች፣ ነገሮችን የሚመለከትባቸው መንገዶች፣ የተገለጠበት የአስተውሎት አቅም፣ እና ሁሉን ነገር በተጠየቃዊ መንገድ የሚያሄሰው፣ እና ሌሎቹም አስደናቂ ፈገግታን የሚያጭሩ ንፅፅሮሾቹና የሚያሳያቸው እውነቶች – እያንዳንዳቸው ቢጠኑ – ከብዙ የዘመናችን ፍልስፍናዊ አተያዮች አንፃር ብዙ ብዙ ነገሮችን የዳሰሱ ሆነው እንደምናገኛቸው ጥርጥር የለውም፡፡
ከምንም በላይ ፍፁም ኢትዮጵያዊ በሆነ የራስ አተያይ፣ ለዛና አቀራረብ እንደ ኢትዮጵያዊው ቀደምት ፈላስፋ እንደ ዘረያዕቆብ ሁሉ – እኚህም መንፈሳዊ አባት፣ የፍልስፍና ሊቅና ሲበዛ ተጫዋች የሆኑ ጠያቂ ኢትዮጵያዊ – የዚህችን ሀገር ፍልስፍና አጥንቶ – ኢትዮጵያዊ ፍልስፍናን ለዓለም የሚያበረክት ትውልድ በሚመጣ ጊዜ – ትልቅና ድንቅ ኢትዮጵያዊ ኦሪጂናል የፍልስፍና ሥጦታ ሆኖ እንደሚገኝ፣ እና እንደሚያገለግል ታላቅ እምነት አለኝ፡፡ ለታላቁ ተጫዋች ሊቅ – ለአለቃ ዘነብ – ምስጋና በሰማዩ ቤታቸው ይድረስልን!
አለቃ ዘነብ “ጨዋታ ሥጋዊ ወ መንፈሣዊ” ጽሕፈታቸውን ሲጨርሱ የተጠቀሟትን የመጨረሻ ዐረፍተ ነገር ጠቅሼ – በዚሁ እሰናበታለሁ፡-
“ምስጋና ይሁን ለአብ፣ ለወልድ፣ ለመንፈስ ቅዱስ አንድ አምላክ፣ ቀድሞ የነበረ፣ አሁንም ያለ፣ ኋላም የሚኖር፣ አስጀምሮ ላስጨረሰን፣ ክብር ይግባው ለዘለዓለም፣ አሜን፡፡”
Filed in: Amharic