>
5:56 pm - Thursday February 2, 2023

ከዘጠኝ ሺ በላይ የአሜሪካ የጤና ባለሙያተኞቹ በኮቪድ መያዝና ያስከተለው ስጋት?!? (በዶክተር ገበየሁ ተፈሪ)

ከዘጠኝ ሺ በላይ የአሜሪካ የጤና ባለሙያተኞቹ በኮቪድ መያዝና ያስከተለው ስጋት?!?


በዶክተር ገበየሁ ተፈሪ


 የአሜሪካው የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል ባወጠው ዘገባ (MMWR Eearly release/vol.69) (April 14, 2020) እሰከ አፕሪል 9 ባለው ጊዜ ውስጥ፣ እንደምንከታተለው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡ በርግጥ አንዳንድ ስቴቶች፣ ሥርጭቱን ረገብ አድገውታል፡፡ ካሊፎረንያና፣ ዋሽንግተን፡፡ ኒው ዮርክ ቢሆን ግራፉ ወደላይ መሄዱን ትቶ ደልደል በማለት ወደ ታች የሚወርድ ይመሰላል፡፡ ያም ሆኖ በአንድ ቀን 750 ሰው ሞቶ አድሯል፡፡

በዚህ መሀል፣ ባልተለመደ ሁኔታ የጤና ባለሙያተኞች ከጠቅላለው ቁጥር ጠቀም ያለውን እየያዙ ነው፡፡ ከዚህም ከዚያም ግምት ነበር፡፡ አሁን ግን ማዕከሉ አሀዙን ስላወጣው፣ በርግጠኝነት መወያያት አንችላል፡፡ ከዚህ ቀደም በቫይረሱ የተያዙ የጤና ባለሙያተኞችን በቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ይዛ የነበረቸው ስፔይን ነበረች፡፡ ቁጥሩም፣ 5400 ነበር፣ ቻይናም ቢሆን ወደ 3300 ባለሙያተኞቿን አስመዝግባለች፡፡ በመሞት ግን የኢጣልያን የሚያህል የለም፡፡ ነርስና ዶክተሮች አንድ ላይ፣ መቶ የሚሞሉ በዚህ በሽታ ምክንያት ህይወታቸው አልፏል፡፡

በአፕሪል 14 የወጣው የሲዲሰ ዘገባ እንደሚያሳየው፣ በአሜሪካ ባጠቃላይ፣ 9282 የጤና ባለሙያተኞች በቫረሱ መያዛቸውን ነው፡፡ የነዚህ ሰዎች አማካይ ዕድሜ 42 አመት ነው፡፡ በአብዛኛው ሴቶች ናቸው፣ 73%፡፡ 

የጤና ባለሙያተኞች፣ ቫይረሱን የሚያገኙት በሶስት አቅጣጫ ነው፡፡ አንደኛ፣ እንደማንም የህብረተሰቡ አባል፣ ከህብረተሰቡ ሲሆን፣ ሁለተኛ፣ በሥራቸው ምክንያት ከህሙማኑም ነው፡፡ እዚህ ላይ በካሊፎርንያ ስቴት፣ አንድ በሽተኛ ብቻውን፣ 121 የጤና ባለሙያተኞችን ማስያዙ ይታወቃል፡፡ ሰውየው በትንፋሽ ዕጥረት ሲንገላታ ስለነበር፣ ሰውየውን ለመርዳት ያልተረባረበ አልነበረም፡፡ በዚያን ጊዜ፣ በአሜሪካ፣ ሰዎቹ፣ ቫይረሱ የለም እያሉ መድረክ ላይ በሚናገሩበት ጊዜ ነበር፡፡ ሶሰተኛው ደግሞ፣ ከሥራ ባልደረቦቻቸው በኩል ነው የሚመጣው፡፡

መረጃ ከተገኘላቸው ወይም ከሠጡት የጤና ባለሙያተኞች መሀከል፣ 780 (55%) የሆኑት የተጋለጡት በሥቸራቸው ምክንያት ከኮቪድ በሽተኛ ነው የሚሉት፡፡ ወደ 92% የሚሆኑት ቢያንስ ቢያንስ አንድ ምልክት ነበራቸው(ትኩሳት፣ ሳል፣ ወይም ትንፋሽ ማጠር)፡፡ 8% የሚሆኑት ደግሞ ምንም አይነት ስሜት አልነበራቸውም፡፡ አብዛኞቹ ማለትም 90% የሚሆኑት ወደ ሆስፒታል ባይገቡም፣ አሳዛኝ ሆኖ 27 የጤና ባለሙያተኞቹ ሞተዋል፡፡ ዝርዝሩ ሰፋ ያለ ሆኖ፣ የሞቱት ሰዎች ባህሪ ሲታይ፣ ልክ እንደሌላው ህብረተሰብ ሁሉ፣ በዕድሜ ገፋ ያሉ ነበሩ፡፡ ለማንኛውም ይህንን የሲዲሲ (CDC) ሠንጠረዥ ይመልከቱ፡፡

 መልክቱ ግልጽ ነው፡፡ ያ ለመቶ ሀያ አንድ የጤና ባለሙያተኞች መያዝ ምክንያት የሆነው ሰው፣ የታመመበት ጊዜ፣ በሽታው አለ የለም እየተባለ በሚሞገትበት ጊዜ መሆኑን ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡ መልክቱ ለኢትዮጵያ ጤና ባለሙያተኞች ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ፣ እነዚህን የጤና ባለሙያተኞች መጋለጥ ሕይወት ማለፍ ምክንያት በደንብ ማጤንና የሚቀነስበት መንገድ መፈለግ ነው፡፡ ለእንደዚህ አይነት ተላላፊ በሽታ ሙሉ ትጥቅ አድርጎ መሥራት የተለመደ ነገር ነበር፣ አሁን ለምን እንግዳ እንደሆነ አይገባንም፡፡ በብዙ መንግሥታት አይን፣ ይህ የጠቅላላ ሀገሪቱን ህዝብ ጤንነት የሚንከባከብ፣ ባብዛኛው ድሙፁን ሳያሰማ ግዴታ የሚወጣውን ሠራተኛና ሥራን እንደ እንጀራ ልጅ መቆጠሩ ቢቆም መልካም ነው፡፡ የሚበቃ በጀትም መመደብ አለበት፡፡ አንባቢ ጤና ባለሙየተኛ ካልሆነ፣ የሲንጋፖር ሰዎች እንዳደረጉት ሁሉ፣ የጤና ባለሙያተኞችን በተገኙበት ማማስገን ተገቢ ነው፡፡ በአሜሪካ የአንድ ነዳጅ ኩባንያ፣ በጋሎን 50 ሳንቲም ቅናሽ በማድረግ ጤና ባለሙያተኞችን ለማመስግን የወሰደውን ርምጃ በምስጋና ተቀብለነዋል፡፡

ለዚህ ሁሉ መፈጠር ሥርጭቱ እንዲባባስ የሚያደርጉ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ ነገና ከነገ ወዲያ ተጠያቂ ናቸው፡፡ ህዝብ ባይጠይቅም የህሊና ወቀሳ እየቆየ ነው የሚመጣው፡፡

ዛሬ መግለጫ ስመለከት የኒው ዮርክ አስተዳዳሪው፣ ምርር ያላቸው ይመስላሉ፡፡ ሁሉም ሰው ማስክ ያድርግ በተለይ ከሌላ ሰው ጋር በሚገናኝበት ቦታዎች በሙሉ አሉ፡፡ ድንጋጌም አድርገውታል፡፡ ከንግግራቸው መሀል፣ መልክታቸው፣ ማስክ ሳታደርግ አትጠጋኝ፣ እኔን በቫይረስ የማያስያዝ መብት የለህም አሉ፡፡ (You have no right to infect me) ተመስገን፡፡  

እንግዲህ አጋላጩ ደንታ ከሌለው፣ ተጋላጩ መወራጨት አለበት፡፡ ይህን ስል ግን በምክርና በማስተማር ነው፡፡ ግፋ ቢልም፣ እነግዴየለሾችን አጠገባችን አትድረሱ ማለት ነው፡፡ ይሉኝታ ምን ያደርጋል፡፡ በይሉኝታ ብቻ፣ በሌላ የህብረተሰቡ ቁስል የደረሰውንና የሚደርሰውን አደጋ አይተናል፡፡ ይበቃል፡፡

ከዚህ ጋር አያይዤም የማቀርበው፣ ከዚሁ ከሲዲሲ ከቀረበው ሪፖርት፣ በአሜሪካ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎችን የዕደሜ ክፍፍል ነው፡፡ ልጆችንም ጨምሮ አይያዙም አይደለም፣ ይያዛሉ፣ መጠኑ ቢለያይም፣ ወይም ደግሞ የህመም ደረጃው ቢለያይም፡፡ ዋናው ጉዳቱ ቫይረሱን እንደምንም አድርገው ሊሞቱ ወደሚችሉ ሰዎች ማድረሳቸው ሰለሆነ፡፡ ተከተቱ ብለናል፡፡

 

Filed in: Amharic