>

የአዲሱ ኮሮና፣ COVID-19 በትንፋሸ አማካኝነት መተላለፉ ሳያንስ አሁን ደግሞ በአይነ ምድር ተከስቷል!!!   (ዶክተር ገበየሁ ተፈሪ)

የአዲሱ ኮሮና፣ COVID-19 በትንፋሸ አማካኝነት መተላለፉ ሳያንስ አሁን ደግሞ በአይነ ምድር ተከስቷል!!! 

 
በዶክተር ገበየሁ ተፈሪ


ይህ ግኝት አዲስ ነው፡፡ Gasteroentrology በተባለ መፅሔት ታትሞ ይወጣል፣ ግን ቀድሞ የደረሰኝን ላካፍል ብዬ ነው፡፡ ሁላችንም ማወቅ የሚገባን ነገር ነው፡፡ በተለይም አገር ቤት፡፡

ኮሮና (COVID-2019) መተላለፊያ መንገዶቹ ተደጋግመው ተተልፀዋል፡፡ መድገሙ ሰለማይከፋ

አንደኛ፡ በሳልና በማስነጠስ በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች የሚወጡት ለአይን የማይታዩ ጠብታዎች፣ ወደ ሌላ ሰው አፍ፣ አፍንጫ ሲዘልቁ፡፡ በነገራችን ላይ፣ ከዚህ በፊት በተደረገ ጥናት፣ ቫይረሱ በከፈተኛ መጠን የሚገኘው አፍንጫ ውስጥ ነው፡፡

ሁለተኛ፡፡ ሰዎች በሚያስሉበት ወይም በሚያስነጥሱበት ጊዜ፣ እነዚያ ቫይረሱን የተሸከሙ ጠብታዎች፣ ከሁለት ሜትር (ከስድሰት ጫማ) ርቀው አይሄዱም፡፡ ለዛ ነው ከስድስት ጫማ ወይም ሁለት ሜትር ርቀት ሁኑ የሚባለው፡፡ ነገር ግን ጠብታዎች ወደ ታቸ በመውረድ ያገኙት ቦታ ላይ ያርፋሉ፡፡ እንግዲህ ባለፈውም እንደጠቀስኩት፣ ቫይረሱ፣ ለዘጠኛ ቀናት ከሰውነት ውጭ ይቆያል ነው የሚባለው፡፡ ለምን ያህል ጊዜ መልሶ ሌላ ሰው የመያዝ ጉልበቱ ባይታወቅም፣ ቫይረሱ ያረፈበትን ቦታ በእጅ ከተነካ በኋላ፣ እጅ ሳይታጠቡ ወይም በአልኮል ሳይጠርጉ፣ አይንዎን፣ አፍንጫዎን፣ አፍዎን የሚነኩ ከሆነ፣ ቫይረሱን በቀጥታ ወደ ሰውነት ያስገባሉ፡፡ ለዚህ ነው፣ ታጠቡ፣ ታጠቡ፣ የሚለው ተደጋጋሚ መልክት የሚነገረው፡፡ መታጠብ ካልቻሉ፣ በ60ፐርስንት ወይም ከዛ በላይ በውስጡ አልኮል ባለው የእጅ መወልወያ፣ እጅዎን በደንብ፣ የመሻከር ስሜት እስኪሰማዎት ድረስ ይወልውሉ፡፡ ሳልዎን ይስብስቡ፣ እጅዎንም ይሰብስቡ፡፡

አሁን አዲሱ ነገር፣ ቫይረሱ በሌላ በየትኛው የሰውነት ክፍል ይራባል ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በሠገራ እንደሚወጣ ተገልጧል፡፡ ግን በዚህ በሠገራ የታየው ቫይረስ፣ አቅም ያለው፣ ሰው መልሶ መያዝ ይችላል ወይ የሚል ጥያቄ ነበረን፡፡ የግድ መታወቅ አለበት፡፡

የቻይና ሀኪሞች፣ በዚህ በኩል፣ በየወቅቱ፣ ለሌሎች ስለቫይረሱ የሚያካፍሉት ጥናት በጣም ወሳኝ ነው፡፡ አዲስ ቫይረስ ነው፣ አናውቀውም ገና፡፡

ለዚህ የቫይረሱ በሠገራ መገኘት፣ ከላይ በተጠቀሰው መሄት ሊወጣ የተባውን ጥናት ላካፍላችሁ፡፡

ከዛ በፊት ግን፣ ሰለ ቫይረሱ የትኛውን የሰውነት ክፍል ለምን እንደሚያጠቃ ልግለፅ፡፡ ቫይረሶች ወደ ሰው ሰውነት ሲዘልቁ፣ ለይተው የሚያጠቋቸው ሴሎች ወይም የሰውነት ክፍሎች አሉ፡፡ እንግዲህ ሴሎችም ሆነ የተለያዩ የሰውነት ክፍሎች፣ በላያቸው ላይ የሚያሳዩዋቸው ሞሎኪሎች ነገሮች አሉ፡፡ ይህ ቫይረስ የሚያጠቃቸው የሰውነት ክፍሎች፣ ወይም ሴሎች፣ በላያቸው ላይ ACE 2, የተባለ ሞሎኪል የሚያሳዩትን ነው፡፡ እንግዲህ የመተንፈሻ የአካል ክፍሎች፣ ሴሎች ይህን ACE 2 የተባለ ሞሎኪል ሰለሚያሳዩ በቀላሉ እንዚህ ሴሎች በማወቅ፣ ይህንን ሞሎኪል በመጠቀም ወደ ሴሎቹ ይገባል ማለት ነው፡፡ አንደመታወቂያ ካርድ ወይም ኮድ በሉት፡፡

ታዲያ ከሳንባና ከመተንፈሻ መሰመሮች ውጭ፣ ያንን ሞሎኪል በብዛት የያዙ ሌሎች የሰውነት ክፍሎች አሉ፡፡ እነሱም ከጨጓራ ጀምሮ ፣ አንጀትን በመጨመር ነው፡፡ ለዚህ ነው እንግዲህ ይህ አዲሱ ቫይረስ፣ ከጨጓራ ጀምሮ አንጀትን በመውረር የሚከሰተው፡፡ አሁን ሚስጥሩ የገባችሁ ይመስለኛል፡፡ በኮረናው ቫይረስ የተያዙ ሰዎችም አንዳንዶቹ ትውከትና ተቅማት እንዳላቸው ይታወቃል፡፡

ወደ ጥናቱ አንሄድ፤ ይህ ቫይረስ አዲስ አንደመሆኑ፣ ሀኪሞቹ፣ ምርምራ ሲያደርጉ፣ ከጉሮሮ፣ አፍንጫ ጀምሮ፣ ደም ምርመራ፣ ሠገራና ሽንት ምርመራም እያደረጉ ነው የከረሙት፡፡ ኢንዶሰኮፒ የሚባል ነገር ተጠቅመውም ጨጓራና አንጀትን ማየትና ናሙና መሰብሰብ ችለዋል፡፡

እንደተጠቀሰው በሠገራ ወይም በእይነ ምድር ቫይረሱ SARS-Co-V2 (ትክክለኛ መጠሪያው ነው) ሰለታየ፡፡ ተጨማሪ ምርምራ ለማድረግ በሆስፒታል እየታከሙ ያሉ ህሙማን ላይ በ71 በሠገራቸው ላይ የ SARS-Co-V2 ምርመራ ማድረግ ወሰኑ፡፡ በአንድ በሽተኛ ላይ ግን፣ ከጨጓራውና ከአንጀቱና ከፊንጢጣው፣ ናሙና ወሰዱ (በኢንዶሰኮፒ ውስጥ በመዝለቅ)፡፡ ከተወሰደው ናሙና፣ ቫይረሱ መኖሩን የሚያረጋግጡ ምርመራዎችም ተደረጉ፡፡

በዚህ ጥናት በአውሮፓ አቆጣጠር ከየካቲት 1-14፣ 2020፣ በ SARS-Co-V2 ተይዘው ሆስፒታል ሲረዱ ከነበሩት ከ73 ሰዎች መሀል፣ በ39 (25 ወንዶችና 14 ሴቶች) በሠገራቸው ላይ የSARS-Co-V2 ይገኝባቸዋል፡፡ እነዚህ በጥናቱ የተካተቱ ሰዎች፣ ዕድሜያቸው ከ10 ወራት እስከ 78 አመታት ድረስ ነው፡፡ ቫይረሱ በሠገራው የተገኘበት የጊዜ መጠን ከአንድ ቀን አስከ 12 ቀናት ድረስ ነበር፡፤ አሳሳቢው የሚከተለው ነው፡፡ ሰዎቹ በአፍና በአፍንጫ በኩል በሚደረገው ምርመራ ቫይረሱ አለመኖሩ ወይም መጥራቱ ቢረጋገጥም፣ በሠገራቸው ላይ ግን ቫይረሱ ይገኝ ወይም ይታያል፡፡ ያ በኢንዶስከፒ ምርምራ የተደረገለት ሰው፣ በሠገራው ብቻ ሳይሆን፣ ከጨጓራው፣ ከአንጀቱና ከፊንጢጣው በተደረገው የናሙና ምርመራ ቫይረሱ መኖሩን አረጋገጡ፡፡ አጥኘዎቹ የሚሉት በሠገራ የሚወጣው ቫይረስ፣ አቅም ያለው፣ መልሶ ሌላ ሰው መያዝ የሚችል ነው፡፡

ሀሳቡ ምንድን ነው‹ ጥንቃቄ ስናደረግ፣ ሁሉንም ነገር ማድረግ ሊኖርብን ነው፡፡ በሠገራ የሚወጡ ቫይረሶች ሆነ ባክቴሪያ፣ ባልተፀዳዳ ሰው አማከኝነት፣ ምግብና መጠጥ ከተነካካ፣ በሽታው ወደ ሌላ ሰው መዛመቱ ነው፡፡ እን ሄፓታይትሰ ኤ የመሰሉ ቫይረሶች በዚህ መንገድ እንደሚተላለፉ አናውቃለን፡፡ ከባክቴሪየ ደግሚ፣ ኮሌራ፣ ታይፎይደ ፊቨርን ጨምሮ ሌሎችም፡፡ ከጥገኛ ፓራሳይቶቸ፣ አሜባ፣ ጃርዲያ የመሳሰሉትም ይተላለፋሉ፡፡ ይህ አዲሱ ጎበዝም አንግዲህ ይኸው በሠገራ የመተላለፍ ችሎታውን አስመስክሯል፡፡

ይህ የሚያመጣው ነገር፣ አሁን ያለን አሠራር ላይ፣ የግድ ለውጥ ማድረግ ሊኖርብን ነው፡፡ ነገሩ፣ አንድ ሰው በ SARS-Co-V2 መያዙ ከተረጋገጠ በኋላ፣ ለአሥራ አራት ቀናት፣ ተገልሎ እንዲቆይ ይደረጋል፡፡ ሰለታመመ አሁን quarantine ሳይሆን  isolation ነው፡፡ ታዲያ ከቫይረሱ ነጸ መሆኑን ለማረጋገጥ፣ አሁን ያለው ፕሮቶኮል፣ የሚመራው፣ ታማሚው፣ ከአስራ አራት ቀናት በኋላ፣ በ24 ሰኣታት ልየኑት፣ ሁለት ምርመራ አድርጎ በሁለቱም ምርመራ ቫይረሱ ካልተገኘ ነው ነጻ የሚሆነው፡፡ ምርመረው ደግሞ ከመተንፈሻ አካሎች በኩል ነው፡፡ ነገር ግን፣ በዚህ ጥናት አንዳያችሁት፣ በሽተኞቹ፣ በመተንፈሻ አካላቸው በኩል ቫይረሱ ቢጠራም፣ በሠገራቸው ዘግይት ብሎ መገኘት ቀጥሏል፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ ከ20% በላይ በሆኑ ሰዎች ታይቷል፡፡ ሰለዚህ አጥኝዎች የሚሉት ደግሞ፣ ሰውየው ጠርቷል ለማለት፣ የሠገራ ምርመራ ይጨመርበት ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ግን፣ በተለይም በሆስፒታል የሚገኙ የዚህ ቫይረስ ህሙማን፣ ቫይረሱ እንዳይዛመት በሚደረገው ጥንቃቂ ሠገራ ውስጥ መገኘቱን በመገንዘብ፣ ጥንቃቄው ሰፋ እንዲል ነው፡፡

ወደ ሀገራችን ስንመለስ፣ ቸግሩን ራሳችሁ የምትገነዘቡት ይመስለኛል፡፡ ለዚህ ነው፣ የንፁህ ውሀ አቅርቦትና፣ የመፃዳጃ ቤቶች መኖር፣ ከምንም ጊዜ በላይ ቅድሚያ ሊሠጣቸው የሚገባ ነገሮች የሚሆኑት፡፡ አሁንም፣ በተለይ አሁን በሚደረገው የቫይረሱን መዛመት ሊገድቡ ይችላሉ ተብለው ከሚወሰዱ እርምጃዎች ጋር አብሮ እንዲታሰብበት፡፡ ህዝቡ ቢሆን ይህንን ነገር የኔ ብሎ መተባበር አለበት፡፡ ንፅህና መጉደል ያንድ ሰው ችግር አይደለም፡፡ ዞሮ ዞሮ፣ ነገሩ ያላቸው ሰዎች ቤት መድረሱ አይቀርም፡፡ የሚገርመው ነገር፣ ካስተዋላችሁ፣ ይህ አዲሱ ቫይረስ እያጠቃ ያለው፣ አላቸው የሚባሉ ሰዎችን ነው፡፡ ለምን ለሥራም ይሁን ለመዝናናት ከአገር አገር የሚዞሩትን ነው፡፡

ድሮ ድሮ፣ ተላላፊ በሽታዎች ይከበሩ ነበር፡፡ አሁን ግን ተረሥተው፣ እንደዚህ ብቅ ሲሉ አለምን ያሸብራሉ፡፡ ሰለዚህ ሳልና መፀዳዳትን የመሠሉ ነገሮች አንደ ባህል መያዝ አለባቸው፡፡ የከተማና ውበት መለኪያው የፎቅ ብዛት መሆን የለበትም፡፡ በነገራችን ላይ ያውሮፓ ውብ ከተሞች፣ በፕላን የተሠሩትና ግፊቱም የመጣው በተላላፊ በሸታዎች ምክንያት ነው፡፡ አውሮፓን ያልረገጠ ወረረሽን በሽታ አልነበረም፡፡ ያን ጊዜ፣ ሽንት ቤትም አያውቁም፣ በፖፖ በመሰኮት ሲደፉ ነበሩ፡፡ ትምህርት ወሰዱና አደጉ፡፡

ሌላው እንዲህ አይነት ወረረሽኝ ሲከሰት፣ ያንድን አካባቢ ግጥም አድርጎ መዝጋትና የዛ አካባቢ ሰው እንዳይወጣ ማገድ፣ አሁን ቻይኖቹ የተጠቀሙበት ዋነኛ ነገር ነው፡፡ ልብ በሉ አዲስ እንዳይመስላችሁ፡፡ የቀደምት የኛ ሰዎች፣ አንድ አካባቢ ተስቦ ከገባ፣ በር በሩን በመያዝ የዛ አካባቢ ሰው ከሌላ ጋር እንዳይደባለቅ እየጠበቁና እየከለከሉ ነው የተረፉት፡፡

በዐፄ ቴዎድሮስ ጊዜ፣ ቆራጣ የሚባል ቦታ ሠፍረው እያል፣ የኮሌራ ወረርሽኝ ገብቶ ብዙ ሰው ወታደር ፈጀ፡፡ ያን ጊዜ ኮሌራውን ነፍጠኛ ፈንግል ነበር የሚሉት፡፡ ታዲያ ንጉሡ ያደረጉት፣ የታመመውንና ያልታመመውን ለይተው በማስፈር፣ አንዱ ካንዱ እንዳይገናኝ አድርገው ነው ሠራዊታቸውን ያተረፉት፡፡

ይሀ አይነት ነገር ድንገት ቢደረግ፣ አትደንግጡ፣ ይልቁንስ፣ መንግሥት ከማድረጉ በፊት፣ ሁሉም ሰው በእንቅስቃሴው ቆጠብ ብሎ የቫይረሱን መዛመት በየአካባቢው ቢቀንስ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ለዚህ ነገር በተለይ ፈንጠር ያሉ ትንንሽ ከተሞች፣ በደንብ መቆጣጠር የሚችሉት ነገር፡፡ ለማንኛውም የአገሪቱ መሪዎች የሚሉትን ስሙ፡፡ ከቻይና ብዙ መማር ተችሏል፡፡ የአገሪቱን አቅም ማወቅም ጥሩ ነው፡፡ ኢጣልያ ካለቻለችው፣ ይኸው አሜሪካ ሽብር በሽብር ከሆኑ፣ ረጋ ብሎ ማሰብና መደረግ ያለበትን እንደህብረተሰብ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ መሸበር አያስፈልግም፣ መስገበገብም ጥሩ አይደለም፡፡ በደንብ ሰለ በሽታው ማወቅ፣ ማን በጣም ሊጎዳ እንደሚችል መገንዘብና መደረግ የሚገባውን ማድረግ ነው፡፡

በሁሉም የመጣ ነገር ነው፡፡ እውነት ለህዝብ የሚቆረቆር ድረጅት፣ አሁን ነው መታየት ያለበት፡፡

 

(ዋቢ)
Evidence for gastrointestinal infection of SARS-CoV-2
Fei Xiao, Meiwen Tang, Xiaobin Zheng, Ye Liu, Xiaofeng Li, Hong Shan

Filed in: Amharic